በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእውነት ይመላለሳሉ

በእውነት ይመላለሳሉ

በእውነት ይመላለሳሉ

“ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።”​—⁠3 ዮሐንስ 4

1. ‘የእውነት ወንጌል’ ያተኮረው በምን ላይ ነው?

 ይሖዋ የሚቀበለው “በመንፈስና በእውነት” የሚያመልኩትን ሰዎች ብቻ ነው። (ዮሐንስ 4:​24) እነዚህ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች በሙሉ በመቀበል ለእውነት እንደሚታዘዙ ያሳያሉ። ይህ ‘የወንጌል እውነት’ በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ በሚያስተዳድረው መንግሥት አማካኝነት በሚረጋገጠው የይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ያተኮረ ነው። (ገላትያ 2:​14) አምላክ ሐሰትን ለመረጡት ሰዎች ‘የስሕተት አሠራር ይልክባቸዋል።’ መዳን ለማግኘት ግን በምሥራቹ ማመንና በእውነት ውስጥ መመላለስ ያስፈልጋል።​—⁠2 ተሰሎንቄ 2:​9-12፤ ኤፌሶን 1:​13, 14

2. ሐዋርያው ዮሐንስ የሚደሰትበት ምን ምክንያት ነበረው? ከጋይዮስ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስላል?

2 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የሚካፈሉ ሰዎች ‘ለእውነት አብረው የሚሠሩ’ ናቸው። እነርሱም ልክ እንደ ሐዋርያው ዮሐንስና እንደ ወዳጁ ጋይዮስ እውነትን አጥብቀው በመያዝ በዚያው መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ። ዮሐንስ ጋይዮስን በማሰብ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል። (3 ዮሐንስ 3-8) ለጋይዮስ እውነትን የነገረው ዮሐንስ ባይሆንም ይህ በዕድሜ የገፋና በመንፈሳዊ የጎለመሰ ሐዋርያ ለእርሱ ከነበረው አባታዊ ፍቅር የተነሳ ወጣቱን ጋይዮስ እንደ መንፈሳዊ ልጁ ሊቆጥረው ችሏል።

እውነት እና የክርስትና አምልኮ

3. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ዓላማ ምን ነበር? ጥቅማቸውስ?

3 የጥንት ክርስቲያኖች እውነትን ለመማር አብዛኛውን ጊዜ በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። (ሮሜ 16:​3-5) በስብሰባዎች አማካኝነት ማበረታቻ ከማግኘታቸውም በላይ እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ይነቃቃሉ። (ዕብራውያን 10:​24, 25) ተርቱሊያን (ከ155 ገደማ–220 እዘአ) ትንሽ ቆየት ብሎ ስለነበሩት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ሲጽፍ “የአምላክን መጽሐፎች ለማንበብ እንሰበሰባለን። . . . በዚህ ቅዱስ ቃል አማካኝነት እምነታችንን እንገነባለን፣ ተስፋችንን እናለመልማለን፣ ትምክህታችንን እናጠናክራለን” ብሏል።​—⁠አፖሎጂ ምዕራፍ 39

4. መዝሙሮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ምን ድርሻ ነበራቸው?

4 የጥንት ክርስቲያኖች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መዝሙር መዘመር የተለመደ ነገር እንደሚሆን እሙን ነው። (ኤፌሶን 5:​19፤ ቆላስይስ 3:​16) በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረው ሴልሰስ የተባለ ሐያሲ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የሚዘምሯቸው “ማራኪ መዝሙሮች ውስጡን ይረብሹት” እንደነበረ ፕሮፌሰር ሄንሪ ቻድዊክ ጽፈዋል። ቻድዊክ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ክርስቲያኖች ማዳመጥ የሚኖርባቸው ምን ዓይነት ሙዚቃ እንደሆነ የጻፈ የመጀመሪያው ክርስቲያን ጸሐፊ የእስክንድርያው ክሌመንት ነው። ሙዚቃዎቹ የፆታን ስሜት ለሚያነሳሳ ዳንስ እንደሚመቹ ሆነው የሚዘጋጁ መሆን እንደማይገባቸው መመሪያ ሰጥቷል።” (ዚ ኧርሊ ቸርች ገጽ 274-5) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አንድ ላይ በሚሰበሰቡበት ጊዜ መዝሙር ይዘምሩ እንደነበር ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች በአብዛኞቹ ስብሰባዎቻቸው ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱና አምላክንና መንግሥቱን የሚያወድሱ ብርቱ መልእክት ያላቸው መዝሙሮች ይዘምራሉ።

5. (ሀ) የጥንቶቹ የክርስቲያን ጉባኤዎች መንፈሳዊ መመሪያ የሚያገኙት እንዴት ነበር? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 23:​8, 9 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነው?

5 በጥንቶቹ የክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ የበላይ ተመልካቾች እውነትን ሲያስተምሩ የጉባኤ አገልጋዮች ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ይረዱ ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:​1) በአምላክ ቃልና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የአስተዳደር አካል መንፈሳዊ መመሪያዎችን ይሰጥ ነበር። (ሥራ 15:​6, 23-31) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ በማለት አዝዟቸዋል:- “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ።” በዚህ ምክንያት የጥንት ክርስቲያኖች በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች ተጠርተው አያውቁም። (ማቴዎስ 23:​8, 9) የጥንት ክርስቲያኖችንና የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያመሳስሏቸው እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ናቸው።

እውነትን በመስበካቸው ስደት ደርሶባቸዋል

6, 7. እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሰብኩት የሰላም መልእክት ቢሆንም ምን ይደርስባቸው ነበር?

6 የጥንት ክርስቲያኖች ይሰብኩ የነበረው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የሰላም መልእክት ቢሆንም እነርሱም እንደ ኢየሱስ ስደት ደርሶባቸዋል። (ዮሐንስ 15:​20፤ 17:​14) ታሪክ ጸሐፊው ጆን ኤል ፎን ሞስሃይም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን “በመንግሥት ደህንነት ላይ ስጋት የመፍጠር ሐሳቡም ፍላጎቱም የሌላቸውና ሌላውን ሰው የማይጎዱ ሰላማዊ ሰዎች” በማለት ጠርቷቸዋል። ዶክተር ሞስሃይም “ሮማውያን ክርስቲያኖችን የጠሉበት ምክንያት የክርስቲያኖቹ አምልኮ ያልተወሳሰበና ሌሎች ሕዝቦች ቅዱስ አድርገው ከሚመለከቷቸው የአምልኮ ሥርዓቶች የተለየ በመሆኑ ነው” በማለት ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- ‘መሥዋዕት አያቀርቡም፣ ቤተ መቅደስም ሆነ ሃይማኖታዊ ምስል አልነበራቸውም። ይህ ደግሞ አንድ ሃይማኖት እነዚህን የአምልኮ ሥርዓቶች ካላሟላ ሃይማኖት አይባልም የሚል ጭፍን አመለካከት በነበረው በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። በዚህ ምክንያት አምላክ የለሾች ተደርገው ይታዩ ነበር። በሮማውያን ሕግ መሠረት ደግሞ አምላክ የለሾች የኅብረተሰብ ጠንቅ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር።’

7 የጣዖት ቅርፃ ቅርፆችን መተዳደሪያቸው ያደረጉ ቀሳውስት፣ የእጅ ባለ ሙያዎችና ሌሎች ሰዎች ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ በማይሳተፉት ክርስቲያኖች ላይ እንዲነሳባቸው ይቀሰቅሱ ነበር። (ሥራ 19:​23-40፤ 1 ቆሮንቶስ 10:​14) ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ችግር ወይም መጥፎ አጋጣሚ ምክንያት ተደርገው የሚጠቀሱት ክርስቲያኖች ናቸው። የታይበር ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፉ ቢሞላ፣ የናይል ወንዝ ቢጎድልና ማሳውን ማጠጣት ባይችል፣ ዝናብ ቢጠፋ ወይም የምድር መናወጥ ቢከሰት፣ የምግብ እጦት ቢያጋጥም፣ ወረርሽኝ ቢነሳ ወዲያውኑ የሚመጣላቸው ሐሳብ ‘እነዚህን ክርስቲያኖች ለአንበሳ መስጠት አለብን’ የሚል ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ምንም ቢመጣ ‘ራሳቸውን ከጣዖት ይጠብቃሉ።’”​—⁠1 ዮሐንስ 5:​21

እውነት እና ሃይማኖታዊ በዓላት

8. በእውነት የሚመላለሱ ሰዎች የገናን በዓል የማያከብሩት ለምንድን ነው?

8 በእውነት የሚመላለሱ ሰዎች ‘ብርሃን ከጨለማ ጋር ምንም ኅብረት’ እንደሌለው ስለሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በዓላትን አያከብሩም። (2 ቆሮንቶስ 6:​14-18) ለምሳሌ ያህል ታኅሣሥ 25 ወይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 ቀን የሚከበረውን የገና በዓል አያከብሩም። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም” ይላል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና በ1956 እትሙ “በገና በዓል ላይ ለሚንጸባረቁት ለአብዛኛዎቹ የፈንጠዝያ ልማዶች መሠረት የሆነው በታኅሣሥ አጋማሽ ላይ ይከበር የነበረው ሳተርናሊያ የተባለው የሮማውያን በዓል ነው” በማለት ዘግቧል። የማክሊንቶክ እና ስትሮንግስ ሳይክሎፒዲያ “አምላክ የገና በዓል እንዲከበር አላዘዘም ወይም መከበር እንዳለበት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰ ነገር የለም” ይላል። እንዲሁም ዴይሊ ላይፍ ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ የተባለው መጽሐፍ “መንጋዎች . . . ክረምቱን የሚያሳልፉት በጉሮኗቸው ውስጥ ሆነው ነበር። እረኞች መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ ማደራቸውን ከሚናገረው የወንጌል ዘገባ አንጻር ሲታይ የገና በዓል [በአውሮፓ] ቅዝቃዜ በሚበረታባቸው ወራት መከበሩ ራሱ ቀኑ ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ ያስገነዝባል።”​—⁠ሉቃስ 2:​8-11

9. ጥንትም ሆነ ዛሬ የይሖዋ አገልጋዮች በዓለ ትንሣኤን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

9 በዓለ ትንሣኤ የሚከበረው የክርስቶስን ትንሣኤ ለማስታወስ ነው ቢባልም ተአማኒነት ያላቸው የጽሑፍ ማስረጃዎች ግን በዓሉ ከሐሰት አምልኮ የመነጨ መሆኑን ይመሠክራሉ። ዘ ዌስትሚንስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል በዓለ ትንሣኤ “ጥንት በአንግሎ ሳክሶኖች ኢስትሬ [ወይም ኦስትሬ] ትባል የነበረችው የቲውቶናውያን የብርሃንና የፀደይ አምላክ የምትከበርበት የፀደይ በዓል ነበር” ይላል። ያም ሆነ ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ በ11ኛው እትሙ ላይ “አዲስ ኪዳን ውስጥ በዓለ ትንሣኤ እንደተከበረ የሚያሳይ ማስረጃ አይገኝም” በማለት ይገልጻል። የትንሣኤን በዓል የጥንት ክርስቲያኖችም አክብረው አያውቁም፤ ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮችም አያከብሩትም።

10. ኢየሱስ ያቋቋመው በዓል ምንድን ነው? ይህንን በዓል በሥርዓቱ የሚያከብሩትስ እነማን ናቸው?

10 ኢየሱስ ተከታዮቹ ልደቱንም ሆነ ትንሣኤውን እንዲያከብሩለት አላዘዘም። ከዚህ ይልቅ መሥዋዕታዊ ሞቱን የሚያስቡበት በዓል አቋቋመላቸው። (ሮሜ 5:​8) ደቀ መዛሙርቱ እንዲያከብሩት ያዘዘው በዓል ይህ ብቻ ነው። (ሉቃስ 22:​19, 20) ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮችም የጌታ እራት እየተባለ የሚጠራውን ይህን ዓመታዊ በዓል ያከብራሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:​20-26

በምድር ዙሪያ እየተሰበከ ያለው እውነት

11, 12. ጥንትም ሆነ ዛሬ በእውነት የሚመላለሱ ሰዎች የስብከቱን እንቅስቃሴ የደገፉት እንዴት ነው?

11 እውነትን የሚያውቁ ሰዎች ጊዜአቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን ለምሥራቹ የስብከት ሥራ ማዋላቸውን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። (ማርቆስ 13:​10) የጥንት ክርስቲያኖች ያከናውኑት የነበረው የስብከት እንቅስቃሴ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 8:​12፤ 9:​7) ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የገንዘብ መሰብሰቢያ ዕቃ የነበረ ቢሆንም ሃይማኖት ትርፍ ማስገቢያ ንግድ ይመስል የመግቢያ ዋጋ በማስከፈል ገንዘብ አይሰበሰብም ነበር። እያንዳንዱ ግለሰብ በወር አንድ ጊዜ ወይም በቻለ ጊዜ በመሰብሰቢያው ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይጥላል። ይህን መዋጮ የሚያደርገው በፈቃደኝነትና እንደአቅሙ እንጂ በግዳጅ አይደለም።”​—⁠አፖሎጂ ምዕራፍ 39

12 በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮችም በተጨማሪ ፍላጎት ያላቸው አድናቂ ሰዎች ይህን ሥራ በገንዘብ መደገፉን እንደ መብት ይቆጥሩታል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችንና የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያመሳስላቸው ሌላው ነገር ይህ ነው።

እውነት እና የግል ሕይወታቸው

13. የይሖዋ ምሥክሮች ጴጥሮስ አኗኗርን በሚመለከት የሰጠውን የትኛውን ምክር ይከተላሉ?

13 በእውነት የተመላለሱት የጥንት ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል የሰጠውን ምክር ታዝዘዋል:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 2:​12) የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን ምክር በጥብቅ ይከተላሉ።

14. ክርስቲያኖች የብልግና መዝናኛዎችን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

14 ክህደት ሰርጎ ከገባ በኋላም እንኳን ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ድርጊቶች ተቆጥበዋል። የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ደብሊው ዲ ኪለን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን በየከተማው የነበረው ቲያትር ቤት የሰዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ዘማዊ የነበሩት ተዋንያን የሚጫወቱት ቲያትር በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን ነውረኛ ፍላጎት ማርካት ችሎ ነበር። . . . እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ እንዲህ ላለው ቲያትር ጥላቻ ነበራቸው። . . . በቲያትሩ ላይ ይቀርቡ የነበሩትን ወራዳ ትዕይንቶች ይጸየፉ ነበር። በቲያትሩ ውስጥ ለአረማውያን ወንድና ሴት አማልክት የሚሰጠው ከፍ ያለ ቦታም ከሃይማኖታዊ እምነታቸው ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነበር።” (ዚ ኤንሸንት ቸርች ገጽ 318-​19) ዛሬ ያሉት የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ አስጸያፊ ከሆኑና ብልግና ከሞላባቸው መዝናኛዎች ይርቃሉ።​—⁠ኤፌሶን 5:​3-5

እውነት እና ‘የበላይ ባለ ሥልጣኖች’

15, 16. ‘በበላይ ያሉት ባለ ሥልጣናት’ እነማን ናቸው? በእውነት ውስጥ የሚመላለሱ ሰዎች ለእነርሱ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

15 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መልካም ምግባር ያላቸው ሰዎች ቢሆኑም አብዛኞቹ የሮማ ንጉሠ ነገሥታት ስለ እነርሱ የተሳሳተ ግምት ነበራቸው። ታሪክ ጸሐፊው ኢ ጂ ሃርዲ ንጉሠ ነገሥታቱ ክርስቲያኖችን “የተጨበጠ ነገር የሌላቸው ስሜታዊ ሰዎች” አድርገው በመመልከት ይንቋቸው እንደነበር ተናግሯል። የቢታንያው አገረ ገዥ ትንሹ ፕሊኒ እና ንጉሠ ነገሥት ትራጃን የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች እንደሚጠቁሙት በጥቅሉ ሲታይ የገዥው መደብ የክርስትናን ምንነት በትክክል አልተገነዘበም ነበር። ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖችስ ለመንግሥት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

16 የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ ‘በበላይ ላሉት የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች’ በአንጻራዊ ሁኔታ ይገዛሉ። (ሮሜ 13:​1-7) ሰዎች ከእነርሱ የሚፈልጉት ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ግን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል አቋም ይይዛሉ። (ሥራ 5:​29) አፍተር ጂሰስ —⁠ዘ ትራያምፍ ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ክርስቲያኖች በንጉሠ ነገሥታዊ አምልኮ አይሳተፉ እንጂ ዓመፅ ቆስቋሾች አልነበሩም። እንዲሁም ሃይማኖታቸው ከሌሎች ለየት ያለና ከአረማዊ አምልኮ አንጻር ሲታይ አንዳንድ ጊዜ ቅር የሚያሰኝ ቢሆንም በመንግሥት ላይ አንዳችም ስጋት የሚፈጥር አልነበረም።”

17. (ሀ) የጥንት ክርስቲያኖች የየትኛው መንግሥት ደጋፊዎች ነበሩ? (ለ) የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ኢሳይያስ 2:​4ን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

17 አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ‘አምላክ የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ’ በተስፋ ይጠባበቁ እንደነበር ሁሉ የጥንት ክርስቲያኖችም የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች ነበሩ። (ዕብራውያን 11:​8-10) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ጌታቸው ሁሉ ‘የዓለም ክፍል’ አልነበሩም። (ዮሐንስ 17:​14-16) በሰዎች መካከል ጦርነትና ግጭት በሚነሳበት ጊዜ ሰላምን ይከተላሉ። እነርሱ ‘ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ’ ያደረጉ ሰዎች ናቸው። (ኢሳይያስ 2:​4) የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስተማሪ የሆኑት ጄፍሪ ኤፍ ነቶል ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች አቋም ከጥንቱ ጋር ያለውን ተመሳሳይነት በማስተዋል እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ሐቁን መቀበል ሊከብደን ቢችልም የጥንት ክርስቲያኖች ለጦርነት የነበራቸው አመለካከት ራሳቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ብለው የሚጠሩ ሰዎች ካላቸው አቋም ጋር በጣም የሚመሳሰል ነው።”

18. የትኛውም መንግሥት ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮችን መፍራት የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

18 የጥንት ክርስቲያኖች ‘ለበላይ ባለ ሥልጣናት’ የሚገዙና ገለልተኞች ስለነበሩ ለየትኛውም የፖለቲካ ወገን ስጋት የሚፈጥሩ አልነበሩም። የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ ናቸው። አንድ የሰሜን አሜሪካ ጋዜጠኛ “አንድ ሰው ጭፍንና ተጠራጣሪ ካልሆነ በስተቀር የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛውም ፖለቲካዊ መስተዳድር ላይ ስጋት ይፈጥራሉ ብሎ አያስብም። ከአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን እንደሚጠበቀው ዓመፅ ለማነሳሳት የማይዳዳቸውና ሰላም ወዳዶች ናቸው” በማለት ዘግቧል። በቂ ግንዛቤ ያላቸው ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰጉ እንዳልሆኑ ያውቃሉ።

19. ግብር መክፈልን በሚመለከት ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖችና ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ለማለት ይቻላል?

19 የጥንት ክርስቲያኖች ‘ለበላይ ባለ ሥልጣናት’ አክብሮት ያሳዩበት አንደኛው መንገድ የሚፈለግባቸውን ግብር በመክፈል ነው። ሰማዕቱ ጀስቲን ለሮማው ንጉሠ ነገሥት አንቶኒነስ ፓየስ (ከ138-161 እዘአ) በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ያለባቸውን ግብር “ከሰው ሁሉ ቀድመው” እንደሚከፍሉ አስረድቷል። (ፈርስት አፖሎጂ ምዕራፍ 17) ክርስቲያኖች ያለባቸውን ግብር በትጋት ይከፍሉ ስለነበር ተርቱልያን ለሮማ ገዥዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀረጥ ሰብሳቢዎቻቸው “ክርስቲያኖችን ሊያመሰግኗቸው ይገባል” በማለት ተናግሯል። (አፖሎጂ ምዕራፍ 42) ክርስቲያኖች የፓክስ ሮማና ወይም የሮማ ሰላም ተጠቃሚዎች እንደነበሩ አያጠራጥርም። ይህ ሰላም ሕግና ሥርዓት የተከበረበት የተረጋጋ አገዛዝ፣ ጥሩ ጥሩ መንገዶችንና በመጠኑም ቢሆን በባሕር ላይ ያለ ስጋት መጓዝ የሚቻልበት ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ውለታ እንደተደረገላቸው በመቁጠር “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” የሚለውን የኢየሱስ ማሳሰቢያ ታዝዘዋል። (ማርቆስ 12:​17) በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦችም ይህንን ምክር ተከትለው የሚፈልግባቸውን ግብር በሐቀኝነት በመክፈላቸው የሌሎችን አድናቆት አትርፈዋል።​—⁠ዕብራውያን 13:​18

እውነት​—⁠የአንድነት ማሰሪያ

20, 21. ሰላማዊ ወንድማማችነትን በሚመለከት ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ሆነ በዛሬው ጊዜ ስላሉት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ለማለት ይቻላል?

20 የጥንት ክርስቲያኖች በእውነት በመመላለሳቸው ሰላም በሰፈነበት ወንድማማችነት ተሳስረው ነበር። ዛሬ ያሉትም የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሁ ናቸው። (ሥራ 10:​34, 35) ዘ ሞስኮ ታይምስ በተባለ ጋዜጣ ላይ የታተመ አንድ ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “[የይሖዋ ምሥክሮች] በቀላሉ የሚቀረቡ፣ የሚወደድ ባሕርይ ያላቸው፣ ደጎችና የዋሆች እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የማያሳድሩ ሰዎች መሆናቸው የታወቀ ነው። . . . በመካከላቸው ጉበኞች፣ ሰካራሞች ወይም የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች አይገኙም። ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ ነው። በሚያደርጉትና በሚናገሩት ነገር ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመመራት ይጥራሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉት ሰዎች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ለመመላለስ ጥቂት እንኳ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ በጭካኔ የተሞላችው ዓለማችን ከአሁኑ ፈጽሞ የተለየ ሁኔታ ይኖራት ነበር።”

21 ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኧርሊ ክርስቺያኒቲ እንደገለጸው “የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ በፊት ባላንጣዎች የነበሩት አይሁዳውያንና አሕዛብ አንድ ሆነው በሰላም የሚኖሩበት አዲስ ኅብረተሰብ ነበር።” የይሖዋ ምሥክሮችም ሰላም ወዳድ በሆነ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ታቅፈዋል። በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የዓለም ኅብረተሰብ መሥርተዋል። (ኤፌሶን 2:​11-18፤ 1 ጴጥሮስ 5:​9፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13) በደቡብ አፍሪካ ርዕሰ ከተማ በፕሪቶሪያ የሚገኙ የትርኢት ማሳያ ስፍራዎች የጥበቃ ዋና ኃላፊ ለአውራጃ ስብሰባ ወደ እነዚህ ሥፍራዎች ስለመጡ የተለያየ ዘር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “አንዱ ለሌላው አክብሮት አለው፤ እርስ በርስ የሚነጋገሩትም ቅንነት ባለው መንገድ ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ያሳያችሁት ጠባይ በመካከላችሁ ያሉትን ሰዎች ግሩም ሥነ ምግባር ያስመሠከረና ሁላችሁም እንደ አንድ ደስተኛ ቤተሰብ ሆናችሁ እንደምትኖሩ የሚያረጋግጥ ነው።”

እውነትን በማስተማራቸው ተባርከዋል

22. ክርስቲያኖች እውነትን ለሌሎች በማሳወቃቸው ምን ውጤት እየተገኘ ነው?

22 ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች በአኗኗራቸውና በስብከት ሥራቸው አማካኝነት ‘እውነት እንዲታወቅ’ አድርገዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:​2) የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ነገር እያደረጉና ለአሕዛብ ሁሉ እውነትን እያስተማሩ ነው ቢባል አትስማማም? በዓለም ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ እየተቀበሉና ወደ ‘ይሖዋ ቤት ተራራ’ እየጎረፉ ነው። (ኢሳይያስ 2:​2, 3) በየዓመቱ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት ይጠመቃሉ። ከዚህ የተነሣ ብዙ አዳዲስ ጉባኤዎች እየተቋቋሙ ነው።

23. እውነትን ለአሕዛብ ሁሉ በማስተማር ላይ ላሉት ሰዎች ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?

23 የይሖዋ አገልጋዮች የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ቢሆኑም በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነዋል። እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። (ዮሐንስ 13:​35) ‘አምላክ በእርግጥ በመካከላቸው እንዳለ’ አይሰማህም? (1 ቆሮንቶስ 14:​25) አንተስ ለአሕዛብ ሁሉ እውነትን እያስተማሩ ካሉት ሰዎች ጎን ተሰልፈሃል? ከሆነ ለእውነት ያለህ አድናቆት እያደገ እንዲሄድና በእውነት መንገድ ለዘላለም መጓዝህን እንድትቀጥል እንመኝልሃለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በአምልኮ ሥርዓት ረገድ በጥንት ክርስቲያኖች እና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ምን ተመሳሳይነት ይታያል?

• በእውነት የሚመላለሱ ሰዎች የሚያከብሩት ብቸኛው በዓል የትኛው ነው?

• ‘የበላይ ባለ ሥልጣናት’ የተባሉት እነማን ናቸው? ክርስቲያኖችስ ለእነርሱ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

• እውነት የአንድነት ማሠሪያ የሆነው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጥንትም ሆነ ዛሬ በእውነት ለሚመላለሱ ሰዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ኖረዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ተከታዮቹ የመሥዋዕታዊ ሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ አዝዟቸዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ‘የበላይ ባለ ሥልጣናትን’ ያከብራሉ