በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጽናት ላይ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ጨምሩ

በጽናት ላይ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ጨምሩ

በጽናት ላይ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ጨምሩ

“በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ የማደርን ባሕርይ፣” NW ] ጨምሩ።”​2 ጴጥሮስ 1:​5, 6

1, 2. (ሀ) አንድ ሕፃን ምን ዓይነት እድገት እንዲያደርግ ይጠበቅበታል? (ለ) መንፈሳዊ እድገት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

 እድገት ለአንድ ልጅ ወሳኝ ነገር ቢሆንም አካላዊ እድገት ብቻውን በቂ አይደለም። ልጁ በአእምሮና በስሜትም መብሰል ይኖርበታል። ውሎ አድሮ የልጅነት ባሕርይውን እየተወ የጎለመሰ ወንድ ወይም የጎለመሰች ሴት ወደመሆን ይደርሳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፣ እንደ ልጅም አስብ ነበር፣ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጒልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህንን ማመልከቱ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​11

2 እነዚህ የጳውሎስ ቃላት መንፈሳዊ እድገትን በተመለከተ ከፍተኛ መልእክት ይዘዋል። ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ሕፃንነት ‘በማስተዋል ችሎታቸው የጎለመሱ’ ወደ መሆን ማደግ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:​20 NW ) “የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ” ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ ‘በትምህርት ነፋስ ሁሉ የሚፍገመገሙና ወዲያና ወዲህ የሚንሳፈፉ ሕፃናት’ አይሆኑም።​—⁠ኤፌሶን 4:​13, 14

3, 4. (ሀ) በመንፈሳዊ እንድንጎለምስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) የትኞቹን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይገባናል? እያንዳንዱ ባሕርይ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

3 በመንፈሳዊ የጎለመስን መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አካላዊ እድገት በአብዛኛው በራሱ የሚመጣ ሲሆን መንፈሳዊ እድገት ግን የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በመጀመሪያ የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ከዚያም የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። (ዕብራውያን 5:​14፤ 2 ጴጥሮስ 1:​2, 3) ይህም በአጸፋው አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድናንጸባርቅ ያስችለናል። እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል አብሮ እንደሚያድግ ሁሉ አምላካዊ ባሕርያትም አንድ ላይ እያደጉና እየዳበሩ የሚሄዱ ናቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን፣ በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣” NW ]፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።”​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​5-7

4 ጴጥሮስ የዘረዘራቸው ባሕርያት በሙሉ እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው አንዱም ቢሆን ችላ ሊባል አይገባውም። አክሎም “እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:​8) በመጽናት ላይ ለአምላክ የማደር ባሕርይ መጨመር አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

የጽናት አስፈላጊነት

5. መጽናት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

5 ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ከጽናት ጋር አያይዘው ጠቅሰውታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​11) መጽናት ማለት ችግርን ተቋቁሞ ባሉበት መርጋት ማለት ብቻ ሳይሆን መከራ፣ መሰናክል፣ ፈተና ወይም ስደት በሚያጋጥምበት ጊዜ ተስፋ ሳይቆርጡ ትዕግሥት፣ ድፍረትና ታማኝነት ማሳየትን የሚጨምር ነው። ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ ያደርን ሆነን’ መኖር ስለምንፈልግ ስደት እንደሚያጋጥመን እንጠብቃለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12 NW ) ይሖዋን እንደምንወድ ማሳየትና ለመዳን አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን ማዳበር የምንፈልግ ከሆነ መጽናት ይኖርብናል። (ሮሜ 5:​3-5፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​7, 8፤ ያዕቆብ 1:​3, 4, 12) ካልጸናን የዘላለም ሕይወት አናገኝም።​—⁠ሮሜ 2:​6, 7፤ ዕብራውያን 10:​36

6. እስከ መጨረሻው መጽናት ምን ማድረግን ይጨምራል?

6 ጅምራችን ምንም ያህል ጥሩ ቢሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር መጽናታችን ነው። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​13) አዎን፣ እስከ ሕይወታችን ፍጻሜም ይሁን እስከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ መጽናት ይኖርብናል። ምንጊዜም ለአምላክ ጽኑ አቋም ይዘን መገኘት ይገባናል። ይሁን እንጂ በጽናታችን ላይ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ካልታከለበት ይሖዋን ማስደሰትና የዘላለም ሕይወት ማግኘት አንችልም። ታዲያ ለአምላክ ያደሩ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ለአምላክ ያደሩ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

7. ለአምላክ ያደሩ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ምንስ እንድናደርግ ይገፋፋናል?

7 ለአምላክ ያደሩ መሆን ሲባል ለይሖዋ አምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ታማኝ በመሆን እርሱን ማክበር፣ ማምለክና ማገልገል ማለት ነው። ከይሖዋ ጋር ባለን ግንኙነት ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በሥራ ለማሳየት ስለ እርሱና ስለ መንገዶቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልገናል። አምላክን በግል ማወቅና ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ይገባናል። እንዲህ ማድረጋችን እርሱን ከልብ እንድንወደውና ይህንንም በድርጊታችንና በአኗኗራችን እንድንገልጽ ይገፋፋናል። በተቻለን መጠን ይሖዋን የመምሰል ማለትም መንገዶቹን የመኮረጅና ባሕሪውን የማንጸባረቅ ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። (ኤፌሶን 5:​1) እርግጥ ነው፣ ለአምላክ የማደር ባሕርይ በድርጊቶቻችን ሁሉ አምላክን ለማስደሰት እንድንጣጣር ይገፋፋናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​31

8. ለአምላክ የማደር ባሕርይ እና እርሱን ብቻ ማምለክ ምን ግንኙነት አላቸው?

8 ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በትክክል ለማንጸባረቅ ልባችን ሳይከፋፈል ይሖዋን ብቻ ማምለክ ይኖርብናል። ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን እርሱን ብቻ እንድናመልክ የመጠየቅ መብት አለው። (ዘዳግም 4:​24፤ ኢሳይያስ 42:​8) ሆኖም ይሖዋ እንድናመልከው አያስገድደንም። በፈቃደኝነት ለእርሱ ያደርን እንድንሆን ይፈልጋል። ሥነ ምግባራዊም ሆነ አካላዊ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ፣ ያለምንም ገደብ ራሳችንን ለእርሱ እንድንወስንና ከውሳኔያችን ጋር ተስማምተን እንድንኖር የሚገፋፋን በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው።

ከአምላክ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና አጎልብቱ

9, 10. ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ማጎልበትና ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በጥምቀት ካሳየን በኋላም ቢሆን ከእርሱ ጋር በግል የመሠረትነው ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ለማድረግና ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ያለን ፍላጎት ቃሉን ዘወትር እንድናጠናና እንድናሰላስል ይገፋፋናል። የአምላክ መንፈስ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲሠራ በፈቀድን መጠን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ከእርሱ ጋር የመሠረትነው ዝምድና በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ይይዛል። ይሖዋን የቅርብ ወዳጃችን አድርገን በማየት በማንኛውም ጊዜ እርሱን ለማስደሰት እንፈልጋለን። (1 ዮሐንስ 5:​3) ከአምላክ ጋር አስደሳች ዝምድና በመመሥረታችን ምክንያት የምናገኘው ደስታ እየጨመረ ከመሄዱም በላይ ስለ ፍቅራዊ መመሪያውና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ስለሚሰጠን እርማት አመስጋኞች ነን።​—⁠ዘዳግም 8:​5

10 ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ውድ ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ የማያቋርጥ ጥረት ካላደረግን በስተቀር ሊዳከም ይችላል። የመሠረትነው ዝምድና ቢዳከም ጥፋቱ የእኛ እንጂ የአምላክ አይሆንም፤ ምክንያቱም እርሱ “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሥራ 17:​27) ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (1 ዮሐንስ 5:​14, 15) እንግዲያው ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው የግል ዝምድና እንዲጠናከር ጥረት ማድረግ ይገባናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንድናዳብርና ጠብቀን እንድንኖር የተለያዩ ዝግጅቶች በማድረግ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይረዳናል። (ያዕቆብ 4:​8) በእነዚህ ፍቅራዊ ዝግጅቶች በሚገባ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሁኑ

11. ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

11 ለአምላክ ያለን ጥልቅ ፍቅር ለእርሱ ያደርን መሆናችንን በተግባር እንድናሳይ ይገፋፋናል። ጳወሎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” በማለት የሰጠው ምክር ከዚህ ጋር ይስማማል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15) ይህን ለማድረግ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ የመገኘትና በመስክ አገልግሎት የመሳተፍ ጥሩ ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። በተጨማሪም ‘ሳናቋርጥ በመጸለይ’ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:​17) እነዚህ ሁሉ ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በተግባር የምናሳይባቸው መንገዶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱን ቸል ብንል መንፈሳዊ ሕመም ሊያስከትልብንና በሰይጣን ጥቃት በቀላሉ እንድንሸነፍ ሊያደርገን ይችላል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​8

12. የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

12 በተጨማሪም በመንፈሳዊ ጠንካራና ንቁ መሆናችን የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ፈተናዎች እንድንቋቋም ይረዳናል። በጣም ከባድ የሆኑ ፈተናዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ከቤተሰብ አባሎቻችን፣ ከዘመዶቻችን ወይም ከጎረቤቶቻችን ግዴለሽነት፣ ተቃውሞና ስደት በሚያጋጥመን ጊዜ መቋቋም ሊከብደን ይችላል። በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድንጥስ በዘዴ ግፊት ይደረግብን ይሆናል። ተስፋ መቁረጥ፣ ሕመምና የመንፈስ ጭንቀት አካላችንን ሊያዳክም ብሎም የእምነት ፈተናዎችን የመቋቋም ኃይል ሊያሳጣን ይችላል። ሆኖም ‘የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየተጠባበቅንና እያስቸኰልን በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል [“ለአምላክ ያደርንም በመሆን፣” NW ]’ የምንጸና ከሆነ ማንኛውንም ፈተና በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 3:​11, 12) እንዲሁም አምላክ እንደሚባርከን በመተማመን ደስተኞች ሆነን መቀጠል እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 10:​22

13. ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማሳየታችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይገባናል?

13 ሰይጣን ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን የጥቃቱ ዒላማ ቢያደርጋቸውም መፍራት አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ “የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን . . . ያውቃል።” (2 ጴጥሮስ 2:​9) ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ለመጽናትና መዳንን ለማግኘት ‘ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፣ . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል [“ለአምላክ ያደሩ በመሆንም፣” NW ] መኖር’ ይገባናል። (ቲቶ 2:​12) ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ከሥጋ ምኞት ጋር የተያያዘ ማንኛውም ድክመትና ድርጊት ለአምላክ ያደርን ሰዎች ሆነን ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት ቀስ በቀስ እንዳያዳክምብንና ይህን ባሕርይ ጨርሶ እንዳያጠፋብን መጠንቀቅ ይገባናል። በዚህ ረገድ እንቅፋት ሊፈጥሩብን ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን።

ለአምላክ ያደርን ሰዎች እንዳንሆን እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች

14. ፍቅረ ነዋይ ወጥመድ ቢሆንብን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

14 ፍቅረ ነዋይ ለብዙዎች ወጥመድ ነው። ‘ለአምላክ ያደሩ መሆን ቁሳዊ ጥቅም ማትረፊያ’ እንደሆነ አድርገን በማሰብ ራሳችንን ልናታልልና የእምነት ባልንጀሮቻችንን መጠቀሚያ ለማድረግ ልንሞክር እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:​5) የተበደርነውን የመክፈል አቅም እንደሌለን እያወቅን አንድን ሃብታም ክርስቲያን ገንዘብ እንዲያበድረን መጎትጎት ምንም ችግር እንደሌለው አድርገን እናስብ ይሆናል። (መዝሙር 37:​21) ሆኖም ‘ለአሁንና ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ አለው’ የተባለው ለአምላክ የማደር ባሕርይ እንጂ ቁሳዊ ነገሮች ማካበት አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ‘ወደ ዓለም ምንም አላመጣንም፤ አንዳችም መውሰድ አይቻለንም።’ ስለሆነም ‘ኑሮዬ ይበቃኛል በማለት ለአምላክ የማደርን ባሕርይ’ እንኮትኩት። “ምግብና ልብስ ከኖረን” እርሱ ይበቃናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​6-11

15. ተድላ ማሳደድ ለአምላክ የማደር ባሕርያችንን እንዳያጠፋብን ምን ማድረግ እንችላለን?

15 ተድላን ማሳደድ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ሊያጠፋብን ይችላል። በዚህ ረገድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያስፈልገን ይሆን? ስፖርትና መዝናኛ የተወሰነ ጥቅም እንደሚኖረው አይካድም። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የሚገኘው ጥቅም ከዘላለም ሕይወት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። (1 ዮሐንስ 2:​25) ዛሬ ብዙ ሰዎች ‘ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ፤ የአምልኮት መልክ ያላቸው ኃይሉን ግን የካዱ’ በመሆናቸው እንደነዚህ ካሉ ግለሰቦች መራቅ ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​4, 5) ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ለማሳየት የሚተጉ ሰዎች “እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ” ይሰበስባሉ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​19

16. አንዳንዶች አምላክ ያወጣቸውን የጽድቅ ብቃቶች እንዳያሟሉ እንቅፋት የሚሆኑባቸው የትኞቹ የኃጢአት ምኞቶች ናቸው? እነዚህን ምኞቶች ማሸነፍ የምንችለውስ እንዴት ነው?

16 የአልኮል መጠጥና የአደገኛ ዕፆች ሱሰኛነት፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም የኃጢአት ምኞቶች ለአምላክ የማደር ባሕርያችንን ሊያጠፉብን ይችላሉ። በእነዚህ ወጥመዶች መሸነፍ አምላክ የሚፈልግብንን የጽድቅ ብቃቶች እንዳናሟላ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1) ጳውሎስ እንኳን ፍጹም ካልሆነው ሥጋው ጋር የማያቋርጥ ትግል ማድረግ ነበረበት። (ሮሜ 7:​21-25) መጥፎ ምኞቶችን ጨርሶ ለማስወገድ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ “በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው” በማለት ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:​5) ብልቶቻችንን ለመግደል ማለትም እነዚህን የኃጢአት ድርጊቶች ላለመፈጸም ቁርጥ አቋም መውሰድ ይኖርብናል። የአምላክን እርዳታ ለማግኘት የምናቀርበው ልባዊ ጸሎት በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ጽድቅንና ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንድንኮተኩት ያስችለናል።

17. ለተግሣጽ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

17 ተስፋ መቁረጥ ጽናታችንን ሊያዳክምብንና ለአምላክ የማደር ባሕርያችን ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ተስፋ የቆረጡባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘኁልቊ 11:​11-15፤ ዕዝራ 4:​4፤ ዮናስ 4:​3) በተለይ ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ያደረብን ሰዎች ስላስቀየሙን ወይም በተሰጠን እርማት ወይም ተግሣጽ ምክንያት ተከፍተን ከሆነ ውጤቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እርማትና ተግሣጽ አምላክ እንደሚያስብልንና እንደሚወደን የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች ናቸው። (ዕብራውያን 12:​5-7, 10, 11) ተግሣጽ በጽድቅ ጎዳና ለምናደርገው ጉዞ ማሰልጠኛ እንደሆነ እንጂ ቅጣት ብቻ ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም። ትሁቶች ከሆንን “የተግሣጽ ዘለፋ የሕይወት መንገድ” መሆኑን በመገንዘብ የሚሰጠንን ምክር በጸጋ እንቀበላለን። (ምሳሌ 6:​23) ይህ ደግሞ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በመከተል አስፈላጊውን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ይረዳናል።

18. ቅሬታ በሚፈጠርበት ጊዜ ምን የማድረግ ግዴታ አለብን?

18 አለመግባባትና ግጭት ለአምላክ ያደርን እንዳንሆን እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። በአንዳንዶች ላይ ጭንቀት ሊፈጥሩ ወይም ራሳቸውን ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዲያገልሉ ማድረግን የመሰለ ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጓቸው ይሆናል። (ምሳሌ 18:​1) ሆኖም በሌሎች ላይ ቂም መያዝ ወይም የጥላቻ ስሜት ማሳደር ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ሊያበላሽብን እንደሚችል ማስታወስ አለብን። (ዘሌዋውያን 19:​18) “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው” እንደማይችል የታወቀ ነው። (1 ዮሐንስ 4:​20) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ከሌሎች ጋር የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ፈጣን እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። አድማጮቹን እንዲህ አላቸው:- “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:​23, 24) ይቅርታ መጠየቅ በጎጂ ቃላት ወይም ድርጊት የተፈጠረው ቁስል እንዲሽር ይረዳል። ይቅርታ የምንጠይቅና ጥፋታችንን አምነን የምንቀበል ከሆነ የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት እንደገና ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት እንችላለን። ኢየሱስ አለመግባባትን መፍታት የሚቻልበት ሌላም ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 18:​15-17) አለመግባባቶችን ለመፍታት ያደረግነው ጥረት ስኬታማ ሲሆን ምንኛ እንደሰታለን!​—⁠ሮሜ 12:​18፤ ኤፌሶን 4:​26, 27

የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

19. የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ፈተና ማጋጠሙ የማይቀር ነገር ነው። ሆኖም ፈተናው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ለምናደርገው ሩጫ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። ይሖዋ ከፈተና ሊያወጣን እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። ‘ሸክምን ሁሉ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት’ በምንሮጥበት ጊዜ ‘የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን’ እንመልከት። (ዕብራውያን 12:​1-3) የኢየሱስን ምሳሌ መመርመራችን እንዲሁም በቃልና በድርጊት እርሱን ለመኮረጅ መጣጣራችን ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንድናዳብርና ይህን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ እንድናንጸባርቅ ይረዳናል።

20. መጽናትና ለአምላክ የማደር ባሕርይ በማሳየት ምን በረከቶች ማግኘት ይቻላል?

20 ጽናትና ለአምላክ ያደሩ መሆን አስተማማኝ ደኅንነት እንድናገኝ የሚረዱን ጎን ለጎን የሚሄዱ ባሕርያት ናቸው። እነዚህን ውድ ባሕርያት በማንጸባረቅ በታማኝነት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችንን መቀጠል እንችላለን። ከጸናንና ለአምላክ ያደርን ከሆንን ይሖዋ ስለሚንከባከበንና ስለሚባርከን ፈተና ቢያጋጥመን እንኳን ደስታ አናጣም። (ያዕቆብ 5:​11) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ራሱ “በመታገሣችሁም [“በመጽናታችሁ፣” NW ] ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።​—⁠ሉቃስ 21:​19

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መጽናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ለአምላክ ያደሩ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? እንዴትስ ማሳየት ይቻላል?

• ከአምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረትና ወዳጅነቱን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• ለአምላክ የማደር ባሕርያችንን ሊያጠፉብን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ልናስወግዳቸው እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ የማደር ባሕርይ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ የማደር ባሕሪህ እንዳይጠፋ ተጠንቀቅ