ጽድቅን በመዝራት የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት እጨዱ
ጽድቅን በመዝራት የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት እጨዱ
“ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሚሆን መከራ ያገኘዋል፤ ዋስትና ለመስጠት እጅ የማይመታ ግን ምንም አይደርስበትም።” (ምሳሌ 11:15 አ.መ.ት ) ይህ እጥር ምጥን ያለ ምሳሌ ስለምንወስደው እርምጃ ጠንቃቆች እንድንሆን ያሳስበናል። ለማያስተማምን ሰው ዋስ መሆን ችግር ላይ የሚጥል ሲሆን እጅ ከመምታት (በጥንት እስራኤል እጅ መምታት አንድን ስምምነት በፊርማ እንደማጽደቅ ይቆጠራል) መታቀብ ግን ዕዳ ውስጥ ከመግባት ያድናል።
በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው ይህ ሐሳብ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ከሚለው መሠረታዊ እውነት ጋር የሚስማማ ነው። (ገላትያ 6:7) ነቢዩ ሆሴዕም “በጽድቅ ዝሩ፣ እንደ ምሕረቱም [“ፍቅራዊ ደግነቱም፣” NW ] መጠን እጨዱ” ብሏል። (ሆሴዕ 10:12) አዎን፣ ነገሮችን አምላክ በሚፈልገው መንገድ በማከናወን ጽድቅን ብትዘሩ ፍቅራዊ ደግነትን ታጭዳላችሁ። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት በተደጋጋሚ በመናገር ድርጊታችን፣ አነጋገራችንና ባሕርያችን ቀና እንዲሆን አሳስቦናል። ጥበብ የተሞላባቸውን እነዚህን ቃላት በጥንቃቄ መመርመራችን ጽድቅን እንድንዘራ ያስችለናል።—ምሳሌ 11:15-31
‘ሞገስን’ በመዝራት “ክብርን” ማጨድ
ጠቢቡ ንጉሥ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፣ ሀኬተኞችም [“ጉልበተኛ ሰዎች፣” አ.መ.ት ] ሀብትን ያገኛሉ።” (ምሳሌ 11:16) ይህ ጥቅስ ሞገስ ያላት ሴት የምታገኘውን ዘላቂ ክብር ጉልበተኛ ሰዎች ከሚያገኙት ጊዜያዊ ሀብት ጋር ያነጻጽራል።
አንድ ሰው የሚያስከብር ሞገስ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? ሰሎሞን “መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። . . . ለአንገትህም ሞገስ [ይሆናል]” በማለት መክሯል። (ምሳሌ 3:21, 22) መዝሙራዊውም ‘ሞገስ በንጉሥ ከንፈሮች እንደሚፈስስ’ ተናግሯል። (መዝሙር 45:1, 2) ጥበብ፣ ማስተዋልና አንደበትን በአግባቡ መጠቀም ለአንድ ሰው ክብርንና ሞገስን እንደሚጨምርለት የታወቀ ነው። ይህ አባባል አስተዋይ ለሆነች ሴትም እንደሚሠራ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ ሰነፍ የነበረው የናባል ሚስት አቢግያ ምሳሌ ትሆናለች። “የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፣ መልክዋም የተዋበ” ነበረ። ንጉሥ ዳዊትም አስተዋይ በመሆኗ አመስግኗታል።—1 ሳሙኤል 25:3, 33
ለአምላክ ያደረች እውነተኛ ሞገስ ያላት ሴት ክብር ማግኘቷ አይቀርም። በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ከማትረፏም በላይ ያገባች ከሆነች ደግሞ በባልዋ ዘንድ ትከበራለች፤ ለቤተሰቧም መኩሪያ ትሆናለች። የምታገኘው ምሳሌ 22:1) በአምላክም ዘንድ ዘላቂ ስም ታተርፋለች።
ክብርም ዘለቄታ ያለው ይሆናል። “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፣ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።” (‘የጉልበተኛ’ እጣ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። (ምሳሌ 11:16 አ.መ.ት ) ጉልበተኛ ሰው ከክፉዎችና የይሖዋን አምላኪዎች ከሚቃወሙ ሰዎች ጋር ተፈርጆአል። (ኢዮብ 6:23፤ 27:13) እንደዚህ ያለው ሰው ‘እግዚአብሔርን በፊቱ አላደረገውም።’ (መዝሙር 54:3) ንጹሐንን በመጨቆንና በመዝረፍ ‘ብርን እንደ አፈር ይከምራል።’ (ኢዮብ 27:16) ሆኖም አንድ ቀን በተኛበት ይቀራል፤ ዓይኑን ይከፍታል፣ እርሱም የለም። (ኢዮብ 27:19) ሀብቱም ሆነ ያገኘው ስኬት ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል።—ሉቃስ 12:16-21
ከምሳሌ 11:16 ምንኛ ግሩም ትምህርት እናገኛለን! የእስራኤል ንጉሥ ሞገስን ያገኘ ሰውም ሆነ ጉልበተኛ የሚያጭዱትን ፍሬ አጠር ባለ መንገድ በመግለጽ ጽድቅን እንድንዘራ ያሳስበናል።
‘ደግነት’ በረከት ያስገኛል
ሰሎሞን በሰዎች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት ተጨማሪ ትምህርት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ቸር [“ደግ፣” አ.መ.ት ] ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል።” (ምሳሌ 11:17) አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “የምሳሌው ዋና ፍሬ ነገር አንድ ሰው ለሌሎች የሚያሳየው ጥሩም ይሁን መጥፎ ባሕርይ በራሱ ላይ ያልታሰበ ውጤት ያስከትላል።” ሊዛ የተባለች አንዲት ወጣት የገጠማትን ሁኔታ ተመልከት። a ጥሩ ሰው ብትሆንም ሁልጊዜ ቀጠሮ አታከብርም። ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ቀጠሮ በምትይዝበት ጊዜ 30 ደቂቃ አንዳንዴም ከዚያ በላይ አርፍዳ የመድረስ ልማድ አላት። ሊዛ ‘ለራስዋ መልካም እያደረገች’ አይደለም። ሌሎች ውድ ጊዜያቸውን ላለማባከን ብለው ከእርስዋ ጋር ቀጠሮ መያዝ ቢያቆሙ ማዘንዋ ተገቢ ነው?
ከራሱ ፍጽምናን የሚጠብቅ ሰውም ራሱን ይጎዳል። ሁልጊዜ የማይደረስባቸው ግቦች ላይ ለመድረስ ስለሚፍጨረጨር በራሱ ላይ ድካምና ብስጭትን ያመጣል። በሌላ በኩል ግን ልንደርስባቸው የምንችላቸውን ግቦች ብናወጣ ለራሳችን መልካም እናደርጋለን። ምናልባት አንዳንድ ሐሳቦችን ለመረዳት ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ጊዜ ይወስድብን ይሆናል። ወይም ደግሞ ሕመም ወይም የዕድሜ መግፋት አቅማችንን ገድቦብን ይሆናል። እንግዲያው ፈጣን መንፈሳዊ ዕድገት ማድረግ ባለመቻላችን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የአቅም ገደቦቻችንን ግምት ውስጥ ያስገባ አመለካከት ይኑረን። አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ለመሥራት ‘ስንተጋ’ ደስተኞች እንሆናለን።—2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ ፊልጵስዩስ 4:5 NW
ጠቢቡ ንጉሥ ጻድቅ ሰው ራሱን ሲጠቅም ጨካኝ ሰው ግን ራሱን የሚጎዳው እንዴት እንደሆነ የበለጠ ሲያብራራ እንዲህ ይላል:- “የኀጥእ ሰው ሞያ ሐሰተኛ ነው፤ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው። በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው። ልበ ጠማሞች በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፤ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው። ክፉ ሰው እጅ በእጅ ሳይቀጣ አይቀርም፤ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል።”—ምሳሌ 11:18-21
እነዚህ ጥቅሶች ጽድቅን በመዝራት የሚገኘውን በረከት እጨዱ የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ ያጎላሉ። ክፉ የሆነ ሰው ምንም ሳይደክም በማታለል ወይም በቁማር አንድ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት ይሞክራል። በዚህ መንገድ የሚገኘው ጥቅም የሐሰት ስለሚሆን ብስጭት ያስከትልበታል። ጥሮ ግሮ የሚሠራ ሰው ግን የሚያገኘው ገቢ የታመነ በመሆኑ ምንም አይፈራም። ነቀፋ የሌለበት ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስለሚያገኝ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖረዋል። ክፉ ሰውስ ምን ይደርስበታል? ክፉዎች አብረው ቢዶልቱም ከቅጣት አያመልጡም። (ምሳሌ 2:21, 22) ይህ ጽድቅን እንድንዘራ የሚያበረታታ እንዴት ያለ ግሩም ማሳሰቢያ ነው!
ጥበበኞች ያላቸው እውነተኛ ውበት
በመቀጠል ሰሎሞን “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፣ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 11:22) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በአፍንጫ ላይ ጌጥ ማድረግ የተለመደ ነበር። በአንዲት ሴት አፍንጫ ላይ የሚደረግ ጌጥ በቀላሉ ይታያል። እንዲህ ያለው የሚያምር ጌጥ በአንድ አሳማ አፍንጫ ላይ እንደማይሰካ የታወቀ ነው። “ጥበብ” የጎደለው ቆንጆ ሰውም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ወንድም ይሁን ሴት ጌጡ አያምርበትም። እንዲያውም አለቦታው የገባና የማይስብ ይሆናል።
እውነት ነው፣ ስለ መልካችን መጨነቅ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ስለ መልካችን ወይም ስለ ቁመናችን ከልክ በላይ መጨነቅ ይኖርብናልን? መልካችንን ልንለውጠው አንችልም። ከዚህም በላይ አካላዊ ውበት ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አይደለም። የምንወዳቸውና የምናደንቃቸው አብዛኞቹ ሰዎች ቆንጆ የሚባሉ አለመሆናቸው እውነት አይደለም? አካላዊ ውበት ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ አይደለም። የበለጠ ዋጋ ያለው ውስጣዊ ውበት ሲሆን ይህም ዘላቂ የሆኑ አምላካዊ ባሕርያትን በማዳበር የሚገኝ ነው። እንግዲያው ጥበበኞች በመሆን እነዚህን ባሕርያት እንኮትኩት።
“ለጋስ ይበለጽጋል”
ንጉሥ ሰሎሞን “የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፤ የኀጥአን ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው” በማለት ተናግሯል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “ያለውን የሚበትን ሰው አለ፣ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፣ ይደኸያልም” ብሏል።—ምሳሌ 11:23, 24
የአምላክን ቃል እውቀት በትጋት ስንበትን ወይም ለሌሎች ስናካፍል የእኛም እውቀት “ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም” የበለጠ ይጨምራል። (ኤፌሶን 3:18) በሌላ በኩል ደግሞ እውቀቱን የማይጠቀምበት ሰው ያለውንም ሊያጣ ይችላል። አዎን፣ “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፣ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።”—2 ቆሮንቶስ 9:6
ንጉሡ እንዲህ በማለት ቀጥሎ ይናገራል:- “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል።” (ምሳሌ 11:25 አ.መ.ት ) ጊዜያችንንና ሀብታችንን በልግስና ለእውነተኛው አምልኮ ስናውል ይሖዋ ይደሰትብናል። (ዕብራውያን 13:15, 16) ‘የሰማይን መስኮት ይከፍትልናል፣ በረከትንም አትረፍርፎ ያፈስስልናል።’ (ሚልክያስ 3:10) ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ያገኙትን መንፈሳዊ ብልጽግና ተመልከት!
ሰሎሞን በጻድቅና በክፉ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “እህልን የሚያስቀር ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፤ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው።” (ምሳሌ 11:26) ዕቃዎች ርካሽ በሚሆኑበት ጊዜ በብዛት ገዝቶ ማስቀመጥና ዋጋቸው ሲያሻቅብ አውጥቶ መሸጥ ትርፍ ያስገኝ ይሆናል። ትርፍ ለማጋበስ ብሎ መቆጠብ ጥቅም ሊያስገኝ ቢችልም እንደዚህ የሚያደርግ ሰው ራስ ወዳድ በመሆኑ ሰዎች ይጠሉታል። በሌላ በኩል ግን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ብዙ ትርፍ ለማግኘት የማይስገበገብ ሰው በሌሎች ዘንድ አክብሮትን ያተርፋል።
የእስራኤል ንጉሥ መልካም ወይም ጽድቅ የሆነውን ምሳሌ 11:27, 28
መፈለጋችንን እንድንቀጥል ሲያበረታታን እንዲህ ብሏል:- “መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፤ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል። በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል፤ ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ።”—ጻድቅ ነፍሳትን ይማርካል
ሰሎሞን የሞኝነት ድርጊት እንዴት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በምሳሌ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል።” (ምሳሌ 11:29ሀ) አካን መጥፎ ተግባር መፈጸሙ በራሱ ላይ መከራ አምጥቶበታል፤ እሱና ቤተሰቡ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። (ኢያሱ ምዕራፍ 7) ዛሬም አንድ የክርስቲያን ቤተሰብ ራስና ቤተሰቡ ለውገዳ የሚያደርስ ኃጢአት ሊሠሩ ይችላሉ። የቤተሰቡ ራስ የአምላክን ትእዛዛት ባለማክበሩና በቤተሰቡ ውስጥ ኃጢአት ሲፈጸም ዝም ብሎ በመመልከቱ በቤተሰቡ ላይ መከራ ሊያመጣ ይችላል። እሱና ምናልባትም ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ንስሐ የማይገቡ ከሆነ ደግሞ ከክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) ይህ ሰው ምን ያተረፈው ነገር አለ? ነፋስን ከመውረስ የተሻለ ምንም ያገኘው ነገር የለም።
ጥቅሱ በመቀጠል “ሰነፍም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 11:29ለ) ሰነፍ ሰው ጥበብ ስለሚጎድለው ከበድ ያለ ኃላፊነት አይሰጠውም። ከዚህም በላይ የተደራጀ አለመሆኑ በሆነ መንገድ የሌላ ሰው ተገዢ እንዲሆን ያደርገዋል። እንደዚህ ያለው ጥበብ የጎደለው ሰው “ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል።” በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አስተዋዮችና ጥበበኞች መሆናችን ጠቃሚ ነው።
ጠቢቡ ንጉሥ “የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፣ ነፍሶችንም የሚሰበስብ [“የሚማርክ፣” አ.መ.ት ] እርሱ ጠቢብ ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 11:30) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ጻድቅ ሰው በንግግሩና በድርጊቱ ለሌሎች መንፈሳዊ እረፍት ያስገኛል። ይሖዋን በማገልገል አምላክ የሚሰጠውን ሕይወት እንዲያገኙ ያበረታታቸዋል።
‘ኃጢአተኞች የባሰ ፍዳ ይቀበላሉ’
እስካሁን የተመለከትናቸው ምሳሌዎች ጽድቅን እንድንዘራ አሳማኝ በሆነ መንገድ ያሳስቡናል። “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ሰሎሞን በሌላ መንገድ ሲገልጸው እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፣ ይልቁንስ ኀጥእና ዓመፀኛ እንዴት ይሆናሉ!” —ምሳሌ 11:31
ጻድቅ ሰው ትክክል የሆነውን ለማድረግ ቢጥርም አልፎ አልፎ ስሕተት መሥራቱ አይቀርም። (መክብብ 7:20) ለሠራው ስሕተት ተግሳጽ ሲሰጠው ‘ፍዳውን ይቀበላል።’ ሆነ ብሎ በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስና ወደ ጽድቅ ለመመለስ ምንም ጥረት የማያደርግ ክፉ ሰውስ ምን ያጋጥመዋል? የባሰ ቅጣት ወይም ‘ፍዳ’ መቀበል አይኖርበትምን? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 4:18) እንግዲያው ሁልጊዜ ጽድቅን ለመዝራት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስምዋ ተለውጧል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቢግያ “ሞገስ” ያላት መሆኗ “ክብር” አስገኝቶላታል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘የኀጥእ ሰው ሞያ ሐሰተኛ ነው፤ ጻድቅ ግን የታመነ ዋጋ አለው’
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በበረከት በመዝራት በበረከት እጨዱ’