በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት ተገዙ

ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት ተገዙ

ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት ተገዙ

“እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው።”—ኢሳይያስ 33:22

1. የጥንቱ እስራኤል ከሌሎች ብሔራት የተለየ ምን ነገር ነበረው?

 በ1513 ከዘአበ የእስራኤል ብሔር ተወለደ። በዚህ ጊዜ ብሔሩ ዋና ከተማም ሆነ አገር እንዲሁም ሰብዓዊ ንጉሥ አልነበረውም። ቀደም ሲል ዜጎቹ በባርነት ቀንበር ሥር ነበሩ። ይሁን እንጂ ይህን አዲስ ብሔር ልዩ የሚያደርገው አንድ ሌላም ገጽታ አለ። ይሖዋ አምላክ በዓይን የማይታይ ፈራጃቸው፣ ሕግ ሰጪያቸውና ንጉሣቸው ነበር። (ዘጸአት 19:​5, 6፤ ኢሳይያስ 33:​22) እንዲህ የመሰለ ሁኔታ ያለው ሌላ ብሔር አልነበረም!

2. የእስራኤል ብሔር የተደራጀበት መንገድ ምን ጥያቄ ይነሳል? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

2 ይሖዋ የሥርዓትና የሰላም አምላክ እንደመሆኑ መጠን በእርሱ አገዛዝ ሥር የሚገኝ የትኛውም ብሔር በሚገባ የተደራጀ እንደሚሆን እንጠብቃለን። (1 ቆሮንቶስ 14:​33) ይህ ሁኔታ በእስራኤል እውነት ሆኖ ተገኝቷል። ሆኖም በምድር ላይ የሚገኝ አንድ ድርጅት በዓይን በማይታይ አምላክ ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ይህን ጥንታዊ ብሔር እንዴት እንደመራው ብንመረምርና በተለይ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት የመገዛትን አስፈላጊነት እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ ለማስተዋል ብንሞክር እንጠቀማለን።

የጥንቱ እስራኤል አመራር ያገኘበት መንገድ

3. ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት ምን ተግባራዊ ዝግጅቶች አድርጎ ነበር?

3 ይሖዋ በዓይን የማይታይ የእስራኤል ንጉሥ ቢሆንም እንኳ እርሱን ወክለው የሚያስተዳድሩ ታማኝ ወንዶችን ሾሞ ነበር። አስተማሪና ዳኛ ሆነው ሕዝቡን የሚያገለግሉ አለቆች፣ የቤተሰብ አባቶችና ሽማግሌዎች ተሹመው ነበር። (ዘጸአት 18:​25, 26፤ ዘዳግም 1:​15) ይሁን እንጂ እነዚህ ኃላፊነት የተጣለባቸው ወንዶች ያለ መለኮታዊ መመሪያ ማስተዋልና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ፍርድ መስጠት ይችላሉ ብለን ማሰብ የለብንም። ፍጹማን አልነበሩም፤ እንዲሁም የእምነት ጓደኞቻቸውን ልብ ማንበብ አይችሉም። ይሁንና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው እነዚህ ፈራጆች ምክር የሚሰጡት በይሖዋ ሕግ ላይ ተመርተው ስለሆነ የእምነት ጓደኞቻቸውን መጥቀም ይችላሉ።​—⁠ዘዳግም 19:​15፤ መዝሙር 119:​97-100

4. ታማኝ የእስራኤል ፈራጆች የትኞቹን ዝንባሌዎች እንዲያስወግዱ ይጠበቅባቸው ነበር? ለምንስ?

4 ፈራጅ ለመሆን ሕጉን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የሚበልጥ ብቃት ማሟላት ይጠይቃል። ሽማግሌዎቹ ፍጹማን ስላልነበሩ እንደ ራስ ወዳድነት፣ አድልዎና ስስት የመሰሉ የፍርድ አሰጣጥን ሊያጣምሙ የሚችሉ ግብረ ገብነት የጎደላቸውን ዝንባሌዎች ለማስወገድ ንቁ መሆን ነበረባቸው። ሙሴ “በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፤ ታላቁን እንደምትሰሙ፣ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፤ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ” ብሏቸዋል። አዎን፣ የእስራኤል ፈራጆች የሚፈርዱት ለአምላክ ነበር። ይህ ምንኛ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መብት ነው!​—⁠ዘዳግም 1:​16, 17፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

5. ይሖዋ ፈራጆች ከመሾሙ በተጨማሪ ሕዝቡን ለመንከባከብ ያደረጋቸው ሌሎች ዝግጅቶች ምንድን ናቸው?

5 ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመንከባከብ ሌሎች ዝግጅቶችም አድርጎ ነበር። ተስፋይቱ ምድር ገና ከመግባታቸው በፊት ለእውነተኛው አምልኮ ማዕከል የሚሆን የመገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። በተጨማሪም ሕጉን የሚያስተምር፣ የእንስሳ መሥዋዕት የሚያቀርብና በየጠዋቱና በየማታው ዕጣን የሚያሳርግ የክህነት ሥርዓት አቋቁሞላቸው ነበር። አምላክ የእስራኤል ሊቀ ካህን እንዲሆን የሙሴን ታላቅ ወንድም አሮንን፣ በሥራው እንዲያግዙት ደግሞ ወንዶች ልጆቹን ሾመ።​—⁠ዘጸአት 28:​1፤ ዘኁልቁ 3:​10፤ 2 ዜና መዋዕል 13:​10, 11

6, 7. (ሀ) ካህናት በሆኑትና ባልሆኑት ሌዋውያን መካከል የነበረው የሥራ ዝምድና ምንድን ነው? (ለ) ሌዋውያኑ ከነበራቸው የተለያየ የሥራ ምድብ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ቆላስይስ 3:​23)

6 በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ከባድ ኃላፊነት ከመሆኑም በላይ ከሕዝቡ ብዛት አንጻር የካህናቱ ቁጥር ጥቂት ነበር። በመሆኑም ሌሎች የሌዊ ነገድ አባላት አሮንና ልጆቹን እንዲረዷቸው ዝግጅት ተደረገ። ይሖዋ ሙሴን “ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ” አለው።​—⁠ዘኁልቁ 3:​9, 39

7 ሌዋውያኑ በሚገባ የተደራጁ ነበሩ። ጌድሶናውያን፣ ቀዓታውያንና ሜራራውያን በሚባሉ ሦስት ወገኖች የተከፈሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የምድብ ሥራ ነበራቸው። (ዘኁልቁ 3:​14-17, 23-37) አንዳንዶቹ የሥራ ምድቦች ከሌሎቹ ይበልጥ አስፈላጊ መስለው ሊታዩ ቢችሉም ሁሉም የግድ አስፈላጊ ናቸው። ቀዓታውያን የሚያከናውኑት ሥራ ቅዱስ ከሆነው የቃል ኪዳኑ ታቦትና ከመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ጋር ያገናኛቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቀዓታዊም ሆነ አልሆነ እያንዳንዱ ሌዋዊ ግሩም መብቶች ነበሩት። (ዘኁልቁ 1:​51, 53) የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶቹ መብታቸውን ሳያደንቁ ቀሩ። ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት ከመገዛት ይልቅ ባገኙት መብት ሳይረኩ ቀሩ። ለኩራት፣ ለሥልጣን ጥማትና ለምቀኝነት ተሸነፉ። ከእነዚህ መካከል ቆሬ የተባለ አንድ ሌዋዊ ሰው ይገኝበት ነበር።

“ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን?”

8. (ሀ) ቆሬ ማን ነበር? (ለ) ቆሬ ካህናቱን በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመልከት እንዲጀምር ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?

8 ቆሬ የሌዊ ነገድም ሆነ የቀዓታውያን ወገኖች አለቃ አልነበረም። (ዘኁልቁ 3:​30, 32) ይሁን እንጂ በእስራኤል ውስጥ የተከበረ አለቃ ነበር። የቆሬ የሥራ ምድብ ከአሮንና ከልጆቹ ጋር በቅርብ ሳያገናኘው አልቀረም። (ዘኁልቁ 4:​18, 19) ቆሬ አሮንና ልጆቹ የሚሠሩትን ስህተት ሲመለከት እንዲህ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል:- ‘እነዚህ ሰዎች እንደ እኔው ፍጹማን አይደሉም። ታዲያ ለምንድን ነው የምገዛላቸው! በቅርቡ አሮን የወርቅ ጥጃ ሠርቶ፣ ሕዝቡም ይህን ጥጃ በማምለክ የጣዖት አምልኮ ፈጽሞ ነበር። አሁን ደግሞ የሙሴ ወንድም ስለሆነ ብቻ ሊቀ ካህናት ሆኖ ያገለግላል! እንዴት ያለ አድልዎ ነው! የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ ቢሆኑስ? ለተሰጣቸው የአገልግሎት መብት ከፍተኛ ንቀት በማሳየታቸው ምክንያት ይሖዋ ቀስፏቸዋል!’ a (ዘጸአት 32:​1-5፤ ዘሌዋውያን 10:​1, 2) የቆሬ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን የክህነት አገልግሎቱን በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመልከት እንደጀመረ ግልጽ ነው። ይህም በመጀመሪያ በሙሴና በአሮን ከዚያም በይሖዋ ላይ እንዲያምፅ አደረገው።​—⁠1 ሳሙኤል 15:​23፤ ያዕቆብ 1:​14, 15

9, 10. ቆሬና በዓመፁ የተባበሩት ሰዎች በሙሴ ላይ ምን ክስ ሰነዘሩ? ምን ነገር ማስታወስ ነበረባቸው?

9 ቆሬ ተደማጭነት የነበረው ሰው በመሆኑ ግብረ አበሮችን ለማሰባሰብ አልተቸገረም። ዳታንንና አቤሮንን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ከነበሩት አለቆች መካከል 250 የሚሆኑ ደጋፊዎችን አገኘ። በአንድነት በሙሴና በአሮን ፊት ቀርበው “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” አሏቸው።​—⁠ዘኁልቊ 16:​1-3

10 እነዚህ ዓመፀኞች መለስ ብለው ቢያስቡ ኖሮ የሙሴን ሥልጣን ከመጋፋት በታቀቡ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በፊት አሮንና ማርያም ተመሳሳይ ስህተት ፈጽመዋል። የቆሬ ዓይነት አስተሳሰብ አዳብረው ነበር! ዘኁልቁ 12:​1, 2 እንደሚነግረን “በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” በማለት ጥያቄ አነሱ። ይህን ሲናገሩ ይሖዋ ይሰማቸው ነበር። ይሖዋ መሪ እንዲሆን የሚመርጠው ማንን እንደሆነ ለማሳወቅ ሙሴ፣ አሮንና ማርያም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ እንዲቆሙ አዘዛቸው። ከዚያም ይሖዋ በግልጽ እንዲህ አላቸው:- “በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፣ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፣ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።” ከዚያም ይሖዋ ማርያምን ለተወሰነ ጊዜ በለምጽ መታት።​—⁠ዘኁልቁ 12:​4-7, 10

11. ቆሬ ለቆሰቆሰው ዓመፅ ሙሴ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

11 ቆሬና ተባባሪዎቹ ይህን ታሪክ የሚያውቁ መሆን አለበት። እንዲያምፁ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። እንዲህም ሆኖ ሙሴ በትዕግሥት ሊረዳቸው ሙከራ አድርጎ ነበር። ላገኙት መብት አመስጋኝ እንዲሆኑ በማሳሰብ “የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፣ . . . ወደ እርሱ[ም] ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን?” አላቸው። በእርግጥም ያገኙት የአገልግሎት መብት ‘ይበቃቸው’ ነበር! ሌዋውያኑ ከፍተኛ መብት ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ የበለጠ ምን ይፈልጋሉ? ሙሴ “ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን?” በማለት የልባቸውን ምኞት አጋለጠ። b (ዘኁልቁ 12:​3፤ 16:​9, 10) ይሁንና በመለኮታዊ ሥልጣን ላይ ለተነሳው ለዚህ ዓመፅ ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ?

የእስራኤል ፈራጅ ጣልቃ ገባ

12. እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የነበራቸው መልካም ዝምድና ተጠብቆ እንዲቆይ ከፈለጉ ምን ማድረግ ነበረባቸው?

12 ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤል በሰጠ ጊዜ ትእዛዙን የሚጠብቁ ከሆነ ‘የተቀደሰ ሕዝብ’ እንደሚሆኑና ብሔሩ የይሖዋን ዝግጅት እስከተቀበለ ድረስ በቅድስና ሊኖሩ እንደሚችሉ ነግሯቸው ነበር። (ዘጸአት 19:​5, 6) እንዲህ ያለው ሆን ተብሎ የተደረገ ዓመፅ በተቀሰቀሰበት ወቅት የእስራኤል ፈራጅና ሕግ ሰጪ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ! ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው:- “ነገ አንተ፣ ወገንህም ሁሉ፣ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤ ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፣ ዕጣንም አድርጉባቸው፣ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፣ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ።”​—⁠ዘኁልቊ 16:16, 17

13. (ሀ) ዓመፀኞቹ በይሖዋ ፊት ዕጣን ለማቅረብ መሞከራቸው እንደ ድፍረት የሚቆጠረው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ ምን እርምጃ ወሰደ?

13 በአምላክ ሕግ መሠረት ዕጣን እንዲያጥኑ የተፈቀደላቸው ካህናቱ ብቻ ነበሩ። ካህን ላልሆነ አንድ ሌዋዊ በይሖዋ ፊት ዕጣን ማቅረብ የሚለው ሐሳብ እነዚህን ዓመፀኞች ሊያስደነግጥና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። (ዘጸአት 30:​7፤ ዘኁልቁ 4:​16) ቆሬና ግብረ አበሮቹ ግን እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አልነበሩም! በማግስቱ ቆሬ “ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ [በሙሴና በአሮን] ላይ ሰበሰበ።” ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው:- ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።” ሆኖም ሙሴና አሮን የሕዝቡን ሕይወት ለመታደግ ይሖዋን ተማጸኑ፤ እርሱም እርምጃ ከመውሰድ ተመለሰ። ቆሬንና ግብረ አበሮቹን ግን “እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።”​—⁠ዘኁልቁ 16:​19-22, 35 c

14. ይሖዋ በእስራኤል ጉባኤ ላይ ጥብቅ እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ የተመለከቱ እስራኤላውያን ከሁኔታው አለመማራቸው ደግሞ በጣም የሚያስገርም ነው። “በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ:- እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ።” እስራኤላውያኑ የሴረኞቹ ግብረ አበሮች ሆነው ነበር! በመጨረሻ የይሖዋ ትዕግሥት አለቀ። ከዚህ በኋላ ሙሴም ሆነ አሮን ወይም የትኛውም ሌላ ሰው ሕዝቡን ሊያማልድ አይችልም። ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ መቅሠፍት አወረደ። “በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።”​—⁠ዘኁልቁ 16:​41-49

15. (ሀ) እስራኤላውያን የሙሴንና የአሮንን አመራር ምንም ሳያቅማሙ እንዲቀበሉ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምርሃል?

15 በጉዳዩ ላይ በጥሞና ቢያስቡ ኖሮ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ለሞት ባልተዳረጉ ነበር። ራሳቸውን እንዲህ እያሉ መጠየቅ ይችሉ ነበር:- ‘በሕይወታቸው ቆርጠው ፈርዖን ፊት የቀረቡት እነማን ናቸው? እስራኤላውያን ነፃ እንዲወጡ የጠየቁት እነማን ናቸው? እስራኤላውያን ነፃ ከወጡ በኋላ ከአምላክ መልአክ ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ወደ ኮሬብ ተራራ እንዲወጣ የተፈቀደለት ማን ነው?’ በእርግጥም ሙሴና አሮን ያስመዘገቡት አስደናቂ ታሪክ ለይሖዋ ታማኝ እንደነበሩና ለሕዝቡ ፍቅር እንደነበራቸው ያረጋግጣል። (ዘጸአት 10:​28፤ 19:​24፤ 24:​12-15) ይሖዋ ዓመፀኞችን በመግደል የሚያገኘው ደስታ የለም። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ከዓመፅ ድርጊታቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምክንያት ይሖዋ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል። (ሕዝቅኤል 33:​11) ይህ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ከፍተኛ ትርጉም አለው። እንዴት?

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚጠቀምበትን የመገናኛ መስመር ለይቶ ማወቅ

16. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል መሆኑን እንዲቀበሉ የሚያደርግ ምን ማስረጃ ነበራቸው? (ለ) ይሖዋ የሌዋውያንን የክህነት አገልግሎት በምን ተካው? ለምንስ?

16 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የማይታይ ፈራጅ፣ ሕግ አውጪና ንጉሥ የሆነለት አንድ አዲስ “ብሔር” አለ። (ማቴዎስ 21:​43) ይህ “ብሔር” ሕልውናውን ያገኘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ሲሆን በዚያን ጊዜ በሙሴ ዘመን የነበረው መገናኛ ድንኳን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ውብ ቤተ መቅደስ ተተክቶ ነበር። በዚያም የሌዋውያን ክህነት ገና በሥራ ላይ ነበር። (ሉቃስ 1:​5, 8, 9) ይሁን እንጂ በ29 እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህን ሆኖ የተሾመበት መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ተቋቋመ። (ዕብራውያን 9:​9, 11) መለኮታዊ ሥልጣንን በተመለከተ አሁንም ጥያቄ ተነሳ። ይሖዋ ይህን አዲስ “ብሔር” እንዲመራ የሚሾመው ማንን ነው? ኢየሱስ ለአምላክ ታማኝ መሆኑን በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። ሰዎችን ያፈቅር ነበር። በርካታ አስደናቂ ተአምራትም ፈጽሟል። ይሁን እንጂ አንገተ ደንዳና እንደነበሩት አባቶቻቸው ሁሉ አብዛኞቹ ሌዋውያን ኢየሱስን ሳይቀበሉ ቀሩ። (ማቴዎስ 26:​63-68፤ ሥራ 4:​5, 6, 18፤ 5:​17) በመጨረሻም ይሖዋ የሌዋውያንን የክህነት አገልግሎት ፍጹም ልዩ በሆነ በንጉሥ ካህናት ተካው። ይህ የንጉሥ ካህናት እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል።

17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የንጉሥ ካህናት የሆነው የትኛው ቡድን ነው? (ለ) ይሖዋ በንጉሥ ካህናት ቡድን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜ የዚህ የንጉሥ ካህናት አባላት እነማን ናቸው? ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በመጀመሪያው ደብዳቤ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ጴጥሮስ በመንፈስ ለተቀቡት የክርስቶስ አካል አባላት “እናንተ . . . ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ከዚህ ጥቅስ ለመረዳት እንደሚቻለው የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉት ቅቡዓን በቡድን ደረጃ “የንጉሥ ካህናት” አባላት ሲሆኑ ጴጥሮስ “ቅዱስ ሕዝብ” በማለትም ጠርቷቸዋል። ይሖዋ ሕዝቡን ለማስተማርና መንፈሳዊ መመሪያ ለመስጠት የመገናኛ መስመር ሆነው ያገለግላሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​45-47

18. በጉባኤ ሽማግሌዎችና በንጉሥ ካህናቱ መካከል ምን ዝምድና አለ?

18 በምድር ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሽማግሌዎች እነዚህን የንጉሥ ካህናት ወክለው ይሠራሉ። እነዚህ ወንዶች በመንፈስ የተቀቡም ሆኑ አልሆኑ ልናከብራቸውና በሙሉ ልብ ልንደግፋቸው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሽማግሌ ሆነው እንዲያገለግሉ በቅዱስ መንፈሱ ስለሾማቸው ነው። (ዕብራውያን 13:​7, 17) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

19. ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት እንዴት ነው?

19 እነዚህ ሽማግሌዎች በአምላክ መንፈስ አማካኝነት በተዘጋጀው በአምላክ ቃል ላይ የተዘረዘሩትን ብቃቶች ያሟላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1-7፤ ቲቶ 1:​5-9) በመሆኑም በመንፈስ ቅዱስ ተሹመዋል ሊባል ይችላል። (ሥራ 20:​28) ሽማግሌዎቹ የአምላክን ቃል ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን አለባቸው። ሽማግሌዎቹ ለሹመት እንዳበቃቸው እንደ ታላቁ ፈራጅ ማንኛውንም ዓይነት የፍርድ መድሎ መጥላት አለባቸው።​—⁠ዘዳግም 10:​17, 18

20. በትጋት የሚሠሩ ሽማግሌዎችን እንድታደንቅ የሚያደርግህ ምንድን ነው?

20 ሥልጣናቸውን ከመጋፋት ይልቅ በትጋት የሚሠሩ ሽማግሌዎቻችንን ከልብ እናደንቃለን! አብዛኞቹ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ መሆናቸው በእነርሱ ላይ ትምክህት እንድንጥል ያነሳሳናል። ለጉባኤ ስብሰባዎች በታማኝነት ይዘጋጃሉ፣ ስብሰባዎቹንም ይመራሉ፤ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ አብረውን ይሰብካሉ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይሰጡናል። (ማቴዎስ 24:​14፤ ዕብራውያን 10:​23, 25፤ 1 ጴጥሮስ 5:​2) ስንታመም ይጠይቁናል፣ ስንተክዝ ያጽናኑናል። ራሳቸውን ሳይቆጥቡ መንግሥቱን በታማኝነት ይደግፋሉ። ይሖዋ መንፈሱን ይሰጣቸዋል፤ በእርሱ ዘንድም ተቀባይነት አላቸው።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

21. ሽማግሌዎች መዘንጋት የሌለባቸው ጉዳይ ምንድን ነው? ለምንስ?

21 እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ፍጹማን አይደሉም። የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ስለሚገነዘቡ መንጋውን ማለትም የአምላክን ‘ማኅበር’ በኃይል እንዳይገዙ ይጠነቀቃሉ። ከዚህ ይልቅ ‘ለወንድሞቻቸው ደስታ አብረዋቸው የሚሠሩ እንደሆኑ’ አድርገው ያስባሉ። (1 ጴጥሮስ 5:​3፤ 2 ቆሮንቶስ 1:​24) ሥራቸውን በትጋት የሚያከናውኑ ትሑት ሽማግሌዎች ይሖዋን ይወድዳሉ፤ እንዲሁም በይበልጥ እሱን እየመሰሉ በሄዱ መጠን ጉባኤውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቅሙ ይገነዘባሉ። ይህን በማስታወስ እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ትዕግሥት የመሰሉትን ባሕርያት በማፍራት አምላክን ለመምሰል የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋሉ።

22. የቆሬን ታሪክ መመርመርህ በሚታየው የይሖዋ ድርጅት ላይ ያለህን እምነት ያጠናከረልህ እንዴት ነው?

22 የማይታይ ገዣችንን ይሖዋን፣ ሊቀ ካህናችንን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ አስተማሪዎቻችንን ቅቡዓን የንጉሥ ካህናትን እንዲሁም መካሪዎቻችንን ታማኝ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን! በሰዎች የሚመራ ድርጅት ፍጽምና ሊኖረው ባይችልም ለመለኮታዊ ሥልጣን በደስታ ከሚገዙ ታማኝ የእምነት አጋሮቻችን ጋር አምላክን ማገልገል መቻላችን ያስደስተናል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሌሎቹ የአሮን ልጆች፣ አልዓዛርና ኢታምር ምሳሌ የሚሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ።​—⁠ዘሌዋውያን 10:​6

b ከቆሬ ጋር ያሴሩት ዳታንና አቤሮን ከሮቤል ነገድ ነበሩ። የክህነትን ቦታ ለማግኘት አልተመኙ ይሆናል። ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የነበራቸው ምኞት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሳይፈጸም በመቅረቱ ምክንያት እነርሱም የሙሴን አመራር ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል።​—⁠ዘኁልቁ 16:​12-14

c በፓትርያርኮች ዘመን እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ ሚስቱንና ልጆቹን ወክሎ በአምላክ ፊት ከመቅረቡም በላይ እነሱን ወክሎ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። (ዘፍጥረት 8:​20፤ 46:​1፤ ኢዮብ 1:​5) ይሁን እንጂ ሕጉ ከተሰጠ በኋላ ይሖዋ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉና መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የአሮንን ቤተሰብ ወንዶች ልጆች ሾመ። እነዚህ 250 የሚሆኑ ዓመፀኞች ከዚህ የአሠራር ለውጥ ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች አለመሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል።

ምን ትምህርት አግኝተናል?

• ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመንከባከብ ምን ፍቅራዊ ዝግጅቶች አድርጎ ነበር?

• ቆሬ በሙሴና በአሮን ላይ እንዲያምፅ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት ያልነበረው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ ከወሰደው እርምጃ ምን ትምህርት እናገኛለን?

• በዛሬው ጊዜ የተቋቋመውን የይሖዋን ዝግጅት እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ቤት ውስጥ የሚሰጥህን ማንኛውንም አገልግሎት እንደ መብት አድርገህ ትቆጥረዋለህ?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉባኤ ሽማግሌዎች የንጉሥ ካህናቱን ይወክላሉ