በአጉል እምነት የተተበተበ ሕይወት
በአጉል እምነት የተተበተበ ሕይወት
ከቤትህ ስትወጣ ከአንድ ሰው ጋር ትጋጫለህ ወይም መንገድ ላይ እንቅፋት ይመታሃል። አንዲት ወፍ ምሽት ላይ ለየት ያለ ድምፅ ታሰማለች። በተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ሕልም ታያለህ። ለብዙ ሰዎች እነዚህ ነገሮች ተራና ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ክስተቶች ናቸው። በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ግን እንደ ምልክት፣ ገድን የሚያመለክት ነገር ወይም ከመንፈሳዊው ዓለም የተላከ መልእክት አድርገው ይወስዱታል። ከታየው ምልክትና ለምልክቱ ከተሰጠው ትርጉም በመነሳት ወይ መልካም ዕድል አሊያም መቅሠፍት እንደሚመጣ ይታሰባል።
እርግጥ ነው በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎችም አጉል እምነቶች አሏቸው። በቻይናና በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ሪፑብሊኮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለበርካታ ዓመታት አምላክ የለሽ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ቢኖሩም ከአጉል እምነት አልተላቀቁም። በምዕራቡ ዓለምም ብዙዎች በኮከብ ቆጠራ ያምናሉ፣ 13ኛው ቀን ዓርብ ላይ ሲውል መጥፎ ነገር እንደሚገጥማቸው አድርገው ያስባሉ እንዲሁም ከጥቁር ድመቶች ይሸሻሉ። በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የሚኖሩ አንዳንዶች ደግሞ በዚያ አካባቢ በየጊዜው የሚታየው ለየት ያለ ብርሃን (aurora borealis) ጦርነትና ቸነፈር እንደሚመጣ የሚያመለክት መጥፎ ገድ እንደሆነ ያምናሉ። በሕንድ ሞቃታማ በሆኑ ቀኖች ሰውነታቸውን ለማቀዝቀዝ የጾታ ግንኙነት ማድረግ እንዳለባቸው የሚያምኑ የከባድ መኪና ሾፌሮች ኤድስን በማዛመት ላይ ይገኛሉ። በጃፓን የምድር ውስጥ መተላለፊያ መንገድ የሚሠሩ ሰዎች መንገዱ ተሠርቶ ከማለቁ በፊት ሴት ከገባች መጥፎ ዕድል እንደሚያመጣ ያምናሉ። አጉል እምነት በስፖርቱ ዓለም ውስጥም ተስፋፍቶ ይገኛል። እንዲያውም አንድ የመረብ ኳስ ተጫዋች ቡድኑ በተከታታይ ሊያሸንፍ የቻለው ነጭ ካልሲ ከማድረግ ይልቅ ጥቁር ካልሲ በማድረጉ እንደሆነ ይናገራል። ሁሉንም እንዘርዝር ብንል ማብቂያ አይኖረውም።
አንተስ? ምናልባት ልትገልጸው የማትችለው በውስጥህ የሚሰማህ ፍርሃት ይኖር ይሆን? ‘አሳማኝ ማስረጃ በሌለው ነገር ታምናለህ ወይም ልማድ አድርገህ ትከተላለህ?’ አጉል እምነት የሚባለው ይህ ነው። በመሆኑም ለጥያቄው የምትሰጠው መልስ አጉል እምነት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆንና አለመሆኑን ያሳያል።
በሚያደርጋቸው ውሳኔዎችና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ አጉል እምነት ተጽዕኖ እንዲያሳድር የሚፈቅድ ሰው ለራሱም ግልጽ ባልሆነለት ነገር እየተመራ እንዳለ ማወቅ አለበት። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ይሆናልን? በጥልቀት ለማናውቀውና ምናልባትም ጉዳት ሊያስከትል ለሚችል ተጽዕኖ ራሳችንን ማጋለጥ አለብን? አጉል እምነት ምንም ጉዳት የሌለው ተራ ነገር ነው ወይስ ጎጂ ልማድ?