አረጀሁ፣ ዕድሜም ጠገብኩ
የሕይወት ታሪክ
አረጀሁ፣ ዕድሜም ጠገብኩ
ሙርኤል ስሚዝ እንደተናገረችው
የፊት ለፊቱ በር በኃይል ተንኳኳ። የጠዋቱን ጊዜ በስብከቱ ሥራ ካሳለፍኩ በኋላ ለምሳ ገና ወደ ቤት መመለሴ ነበር። እንደ ልማዴ ለሻይ የሚሆን ውኃ ከጣድኩ በኋላ ለግማሽ ሰዓት ያህል አረፍ ለማለት እየተዘጋጀሁ ነበር። በሩ አለማቋረጥ መንኳኳቱን ቀጠለ። በሩን ለመክፈት እየሄድኩ ሳለ በዚህ ሰዓት የመጣው ማን ነው ብዬ አሰብኩ። ወዲያው ለጥያቄዬ መልስ አገኘሁ። በሬ ላይ ቆመው የነበሩት ሁለት ሰዎች የፖሊስ መኮንኖች እንደሆኑና የመጡትም በወቅቱ በእገዳ ሥር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳትሙት ጽሑፍ በቤቴ መኖሩን ለመፈተሽ እንደሆነ ገለጹልኝ።
የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በአውስትራሊያ የታገደው ለምን ነበር? እኔስ የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት እንዴት ነው? ነገሩ የጀመረው በ1910 የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ በሰጠችኝ አንድ ስጦታ ነበር።
ቤተሰባችን ከኖርዝ ሲድኒ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በክሮውዝ ኔስት በአንድ የእንጨት ቤት ውስጥ ይኖር ነበር። አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ እናቴ በራችን ደጃፍ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ስታወራ አገኘኋት። ሙሉ ልብስ ለብሶ በመጻሕፍት የታጨቀ ቦርሳ የያዘውን የዚህን እንግዳ ሰው ማንነት ለማወቅ ጓጉቼ ነበር። ይቅርታ ጠየቅኩኝና ወደ ቤት ገባሁ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን እናቴ ጠራችኝ። “ይህ ሰው ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩ አንዳንድ ጥሩ መጻሕፍት ይዟል። በቅርቡ ልደትሽን ማክበርሽ ስለማይቀር አዲስ ቀሚስ ቢገዛልሽ ይሻልሻል ወይስ እነዚህ መጻሕፍት? የትኛውን ትመርጫለሽ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“እማዬ፣ መጽሐፎቹ ይሻሉኛል” አልኳት።
ስለዚህ ገና በአሥር ዓመቴ በቻርልስ ቴዝ ራስል ከተዘጋጁት የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉ መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ጥራዞች አገኘሁ። መጽሐፎቹን ለመረዳት ከባድ ሊሆንብኝ ስለሚችል እናቴ እንድትረዳኝ ሰውዬው ነገራት። እናቴም ልትረዳኝ ፈቃደኛ መሆንዋን ገለጸችለት። የሚያሳዝነው ግን ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እናታችን ሞተች። እኔን ወንድሜንና እህቴን የማሳደጉ ሥራ በአባታችን ላይ ወደቀ፤ እኔም ተጨማሪ ኃላፊነቶች መቀበል ነበረብኝ። ይህ ደግሞ ከአቅሜ በላይ ሆኖ ታየኝ። ይባስ ብሎ ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ገጠመኝ ከፊታችን ይጠብቀን ነበር።
በ1914 የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተጀመረና ከአንድ ዓመት በኋላ አባታችን ተገደለ። ወላጅ አልባ ስለሆንን ወንድሜና እህቴ ከዘመዶቻችን ጋር እንዲኖሩ ሲላኩ እኔ ደግሞ በካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት እንድገባ ተደረገ። አንዳንድ ጊዜ በብቸኝነት ስሜት እዋጥ ነበር። ቢሆንም ለሙዚቃ በተለይም ለፒያኖ የነበረኝን ፍቅር የምወጣበት አጋጣሚ በማግኘቴ ደስተኛ ነበርኩ። በዚህ ሁኔታ ዓመታት አለፉ፤ እኔም ከነበርኩበት ትምህርት ቤት ተመረቅኩ። በ1919 ሮይ ስሚዝ የተባለ የሙዚቃ መሣሪያዎች ነጋዴ አገባሁ። በ1920 አንድ ልጅ ወለድንና እንደገና በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ተጠመድኩ። እነዚያ መጽሐፎችስ የት ደረሱ?
አንድ ጎረቤቴ መንፈሳዊ እውነትን አካፈለችኝ
በነዚያ ዓመታት ሁሉ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሐፎቹ” በሄድኩበት አይለዩኝም ነበር። አንብቤያቸው ባላውቅም እንኳ የያዙት መልእክት ጠቃሚ እንደሆነ አውቅ ነበር። በ1920ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አካባቢ አንድ ቀን ሊል ቢምሶን የተባለች ጎረቤታችን ልትጠይቀን ቤታችን መጣች። ሳሎን ገባንና ቁጭ ብለን ሻይ እየጠጣን መጫወት ጀመርን።
በድንገት “እነዚህ መጽሐፎች አሉሽ!” ስትል በመደነቅ ተናገረች።
“የትኞቹ መጽሐፎች?” ግራ በመጋባት ጠየቅኳት።
መጽሐፍ መደርደሪያው ላይ የሚገኙትን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉትን መጻሕፍት ጠቆመችኝ። ሊል የዚያኑ ቀን መጽሐፎቹን ተዋሰችኝና ቤቷ ወስዳ በጉጉት አነበበቻቸው። ባነበበችው ነገር እንደተደሰተች ከሁኔታዋ በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ሊል በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ተጨማሪ መጻሕፍት አገኘች። ከዚህም በላይ ያገኘችውን እውቀት በሙሉ ታካፍለን ነበር። ካገኘቻቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እኛም ይህ መጽሐፍ ደረሰን። ጊዜ ወስጄ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ማንበብ ስጀምር የክርስቲያናዊ ሕይወቴ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተከፈተ። በመጨረሻም የነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን ሊመልሳቸው ያልቻላቸው መሠረታዊ ለሆኑ ጥያቄዎቼ መልስ አገኘሁ።
ደስ የሚለው ደግሞ ሮይም ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልዩ ትኩረት ሰጠና ሁለታችንም ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆንን። ሮይ ከዚህ ቀደም ፍሪሜሰንስ ተብሎ የሚጠራው ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ነበር። አሁን ቤተሰባችን በሙሉ በእውነተኛው አምልኮ አንድ ስለሆነ አንድ ወንድም በሳምንት ሁለት ጊዜ መላውን ቤተሰባችንን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረን ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መሰብሰብ ስንጀምር በይበልጥ ተበረታታን። በሲድኒ ስብሰባው የሚካሄደው ኑታውን ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የኪራይ አዳራሽ ውስጥ ነበር። በወቅቱ በመላው አገሪቱ የነበሩት የምሥክሮቹ ቁጥር ከ400 የሚያንስ ስለነበር አብዛኞቹ ወንድሞች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረባቸው።
የእኛ ቤተሰብ በስብሰባ ላይ ለመገኘት ዘወትር የሲድኒን ወደብ ማቋረጥ ነበረበት። የሲድኒ ድልድይ በ1932 ከመሠራቱ በፊት ወደቡን ማቋረጥ የሚቻለው በመኪና ማሻገሪያ ጀልባ ብቻ ነበር። ጉዞው ጊዜያችንንና ገንዘባችንን የሚጨርስ ቢሆንም ይሖዋ ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግቦች አንዱም እንዳያመልጠን ጥረት እናደርግ ነበር። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊፈነዳ ተቃርቦ ስለነበርና ይህም በቤተሰባችን ላይ የገለልተኝነትን ጥያቄ በቀጥታ የሚያስነሳ በመሆኑ በእውነት ውስጥ ስር ሰደን ለመቆም ያደረግነው ጥረት በእጅጉ ክሶናል።
የፈተናና የበረከት ወቅት
የ1930ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ለእኔና ለቤተሰቤ አስደሳች ወቅት ነበሩ። በ1930 ተጠመቅኩና በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አስደሳች ስም በተቀበልንበት የማይረሳ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ሮይ እና እኔ በሁሉም የስብከቱ እንቅስቃሴዎችና ድርጅቱ በሚያስተባብራቸው ዘመቻዎች በመሳተፍ ከዚህ ስም ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ጥረት እናደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ1932 የሲድኒ ወደብ ድልድይ ሲከፈት ለማየት ለመጡት ሰዎች ቡክሌት በማሰራጨቱ ልዩ ዘመቻ ላይ ተካፍለናል። በተለይ ልዩ ትኩረት እንሰጠው የነበረው እንቅስቃሴ ድምፅ ማጉያ በተገጠመላቸው መኪናዎች በመጠቀም መስበክ ሲሆን እኛም በመኪናችን ላይ የድምፅ መሣሪያ የማስገጠም አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የወንድም ራዘርፎርድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች በሲድኒ አውራ ጎዳናዎች ላይ አሰምተናል።
ይሁን እንጂ ሁኔታዎች እየተለወጡና ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆኑ መጡ። በ1932 በደረሰው ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት አውስትራሊያ ክፉኛ ተመታች። በመሆኑም እኔና ሮይ ኑሯችንን ቀላል ለማድረግ ወሰንን። ይህንን ውሳኔያችንን ተግባራዊ ያደረግንበት አንዱ መንገድ መኖሪያችንን በጉባኤው አቅራቢያ በማድረግ ሲሆን ይህም የመጓጓዣ ወጪያችንን በእጅጉ ቀንሶልናል። ዓለም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሽብር ስትዋጥ ግን የኑሮው ውድነት ከነጭራሹ ተረሳ።
የይሖዋ ምሥክሮች የዓለም ክፍል አለመሆንን በተመለከተ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በመከተላቸው በዓለም ዙሪያ የስደት ዒላማ የሆኑ ሲሆን በአውስትራሊያም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። በጦርነት ስሜት ያበዱ አንዳንዶች ኮሚኒስቶች እያሉ ይጠሩን ጀመር። እነዚህ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች በአውስትራሊያ የነበሯቸውን አራት የሬዲዮ ጣቢያዎች ለጃፓን ሠራዊት መልእክት ለማቀበል እየተጠቀሙበት ነው የሚል የሐሰት ክስ አቅርበው ነበር።
ለወታደራዊ አገልግሎት መጥሪያ የደረሳቸው ወጣት ወንድሞች አቋማቸውን እንዲያላሉ ተጽዕኖ ይደረግባቸው ነበር። ሦስቱም ወንዶች ልጆቻችን ለእምነታቸው እንደቆሙና ገለልተኝነታቸውን እንደጠበቁ አፌን ሞልቼ መናገር በመቻሌ ያስደስተኛል። ትልቁ ልጃችን ሪቻርድ የ18 ወር እስራት ተፈረደበት። ሁለተኛው ልጃችን ኬቨን ግን በሕሊናው ምክንያት እንደማይዋጋ ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ከግዳጅ ነፃ ሆነ። የሚያሳዝነው ግን የመጨረሻው ልጃችን ስቱዋርት የገለልተኝነትን ጉዳይ በሚመለከት የመከላከያ ሐሳብ ለማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ በደረሰበት የሞተር ብስክሌት አደጋ ሕይወቱ አለፈ። ይህ አደጋ ከባድ ሐዘን ላይ ጥሎን ነበር። ሆኖም ትኩረታችንን በመንግሥቱና ይሖዋ በሰጠን የትንሣኤ ተስፋ ላይ ማድረጋችን በጽናት እንድንወጣው ረድቶናል።
ትልቁን ምሥጢር ሳያገኙ ቀሩ
በአውስትራሊያ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በጥር ወር 1941 ታገደ። ሆኖም እኔና ሮይ ልክ እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሰዎች ይልቅ አምላክን በመታዘዝ ሁለት ዓመት ተኩል ለሚያክል ጊዜ ሥራችንን በድብቅ ማከናወን ቀጠልን። በዚህ ወቅት ነበር በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው ሁለት የሲቪል ልብስ የለበሱ ፖሊሶች በሬን ያንኳኩት። ከዚያስ ምን ሆነ?
ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋበዝኳቸው። ከገቡ በኋላ “ቤቱን መፈተሽ ከመጀመራችሁ በፊት ሻዬን ጠጥቼ እንድጨርስ ትፈቅዱልኛላችሁ?” ስል ጠየቅኋቸው። የሚያስገርመው በጥያቄዬ ተስማሙ። ወደ ጓዳ ገባሁና ወደ ይሖዋ በመጸለይ ለመረጋጋት ሞከርኩ። ስመለስ አንዱ ፖሊስ የጥናት ክፍላችን ውስጥ ገባና በአገልግሎት ቦርሳዬ ውስጥ የነበረውን ጽሑፍና መጽሐፍ ቅዱሴን ጨምሮ የመጠበቂያ ግንብ ምልክት ያለባቸውን ሁሉንም ጽሑፎች ወሰደ።
ከዚያም “በካርቶን አድርጋችሁ የደበቃችኋቸው ሌሎች ጽሑፎች የሏችሁም?” ሲል ጠየቀኝ። “በዚህ ጎዳና መጨረሻ ላይ በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ በየሳምንቱ እንደምትሰበሰቡና ብዙ ጽሑፎችን ወደዚያ እንደምትወስዱ መረጃ ደርሶናል።”
“አልተሳሳትክም። ጽሑፎቹ ግን አሁን በዚያ የሉም” በማለት መለስኩለት።
“አዎን፣ ጽሑፎቹ እዚያ እንደሌሉ እናውቃለን፣ ወይዘሮ ስሚዝ። ጽሑፎቹ በአውራጃው ውስጥ በተለያዩ ሰዎች ቤት ውስጥ እንደሚቀመጡም እናውቃለን” አለኝ።
በልጆቻችን የመኝታ ክፍል ውስጥ ፍሪደም ኦር ሮማኒዝም የተሰኘውን ቡክሌት የያዙ አምስት ካርቶኖች አገኙ።
“ጋራዡ ውስጥ የደበቃችሁት ሌላ ጽሑፍ የለም?” በማለት ጠየቀኝ።
“ምንም የለም” አልኩት።
ከዚያም ምግብ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ቁም ሳጥን ከፍቶ ሲበረብር የጉባኤው ሪፖርት የሚሞላባቸው ባዶ ቅጾችን አገኘ። እነዚህን ከወሰደ በኋላ ጋራዡንም ካልፈተሽኩኝ አለ።
“በዚህ በኩል ኑ” ብዬ እየመራሁ ወሰድኳቸው።
ጋራዡን ከፈተሹ በኋላ ሄዱ።
ፖሊሶቹ አምስቱን ካርቶኖች ማግኘታቸውን እንደ ትልቅ ነገር ቆጥረውት ነበር! ይሁን እንጂ ዋናውን ነገር ሳያገኙ ነው የሄዱት። በወቅቱ እንደ ጉባኤ ጸሐፊ ሆኜ አገለግል ስለነበር የጉባኤ አስፋፊዎች ስም ዝርዝርና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎች በቤት ውስጥ አስቀምጬ ነበር። ወንድሞች ምስጋና ይግባቸውና ቤታችን እንደሚፈተሽ አስቀድመው ነግረውን ስለነበር እነዚህን ሰነዶች በጥንቃቄ ደብቄያቸው ነበር። በፖስታ ውስጥ አድርጌ ሻይ፣ ስኳርና ዱቄት በማስቀምጥባቸው የቆርቆሮ ጣሳዎች ሥር ከተትኳቸው። የተወሰነውን ደግሞ ጋራዡ አጠገብ በነበረው የእርግብ ቤት ውስጥ ደብቀናቸው ነበር። ስለዚህ ፖሊሶቹ በዋነኛነት የሚፈልጉትን መረጃ የተቀመጠበትን ቦታ አልፈው ሄዱ።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር
በ1947 ትላልቆቹ ልጆቻችን የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው መኖር ጀምረው ነበር። ስለዚህ ሮይና እኔ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዳንጀምር የሚያግደን ምንም ነገር እንደሌለ ተሰማን። በደቡብ አውስትራሊያ የአገልግሎት መስክ ተጨማሪ ሰዎች ያስፈልጉ ስለነበር ቤታችንን ሸጥንና “መጠበቂያ ግንብ” የሚል ትርጉም ያለውን ምጽጳ ብለን የሰየምናትን ተጎታች ቤት ገዛን። ይህ ዓይነቱ አኗኗር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች እንድንሰብክ አስችሎናል። አብዛኛውን ጊዜ የምናገለግለው ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ የገጠር ክልሎች ውስጥ ነበር። ስለዚህ ወቅት ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ። ቤቨርሊይ የተባለች አንዲት ወጣት ሴትን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። ለጥምቀት ከመድረሷ በፊት አካባቢውን ለቅቃ ሄደች። ከዓመታት በኋላ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንዲት እህት ወደ እኔ መጥታ ቤቨርሊይ እንደሆነች ስትነግረኝ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ገምቱ። እነዚያን ሁሉ ዓመታት ከባሏና ከልጆችዋ ጋር ሆና ይሖዋን እያገለገለች እንደነበር ማወቄ በጣም አስደሰተኝ!
በ1979 በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። በትምህርት ቤቱ ላይ ጎላ ብለው ከቀረቡት ትምህርቶች መካከል አንዱ በአቅኚነት አገልግሎት ለመጽናት ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር። ይህን እውነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሕይወቴ በጥናት በስብሰባዎችና በአገልግሎት የተሞላ ነበር። በዘወትር አቅኚነት ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት የማገልገል ልዩ መብት በማግኘቴ እንደ ትልቅ ክብር አድርጌ እቆጥረዋለሁ።
የጤና ችግሮችን መቋቋም
የመጨረሻዎቹ የሕይወት ዘመኖቼ ለየት ያሉ ፈተናዎች ያየሁባቸው ዓመታት ነበሩ። በ1962 ግላውኮማ የተባለ የዓይን በሽታ እንዳለብኝ በምርመራ ተረጋገጠ። በወቅቱ ለዚህ በሽታ የነበረው ሕክምና መጠነኛ ስለነበር
የማየት ችሎታዬ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ሄደ። የሮይም ጤንነት እንዲሁ እየተዳከመ ሄደና በ1983 በአንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ግማሽ አካሉ ሽባ ሆነ እንዲሁም አንደበቱ ተዘጋ። በ1986 በሞት ተለየኝ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሁሉ ከጎኔ ሳይለይ ድጋፍ ይሰጠኝ ስለነበር እሱን ማጣት በጣም አጉድሎኛል።እነዚህ እንቅፋቶች እያሉም መንፈሳዊ ፕሮግራሜን ሳላዛንፍ ለመቀጠል ጥረት አደረግሁ። ለምንኖርበት ከፊል ገጠራማ ለሆነ አካባቢ ለመስክ አገልግሎት የሚመች አንድ ጠንካራ መኪና ገዛሁና ሴት ልጄ ጆይሲ በምታደርግልኝ እርዳታ በአቅኚነት አገልግሎት ቀጠልኩ። የዓይን ሕመሜ እያደር እየተባባሰ ሄደና አንደኛው ዓይኔ ጨርሶ ማየት ተሳነው። ሐኪሞች ሰው ሠራሽ ዓይን አደረጉልኝ። ከዚህም በኋላ ግን አጉሊ መነፅር በመጠቀም በቀረችኝ አንድ ዓይን በትላልቅ ፊደላት የታተሙ ጽሑፎችን በማንበብ በቀን ከሦስት እስከ አምስት ሰዓት አጠና ነበር።
ለጥናት ፕሮግራሜ ምንጊዜም ትልቅ ቦታ እሰጥ ነበር። በመሆኑም አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ የግል ጥናት ሳደርግ ድንገት ምንም ነገር ማየት ሲያቅተኝ ምንኛ እንደ ደነገጥኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። የሆነ ሰው መብራቱን እንዳጠፋብኝ ያህል ነበር። አሁን ምንም ነገር ማየት አልችልም። ታዲያ በግል ጥናቴ የቀጠልኩት እንዴት ነው? ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የመስማት ችግር ያለብኝ ቢሆንም የቴፕ ክሮችን በመጠቀምና ቤተሰቤ በሚሰጠኝ ፍቅራዊ እርዳታ አማካኝነት በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኜ ለመቀጠል ችያለሁ።
እስከ መጨረሻው መጽናት
በአሁኑ ወቅት ዕድሜዬ ከመቶ ዓመት በላይ በመሆኑና ጤናዬም እያሽቆለቆለ በመሄዱ እንደ ድሮው ቀልጠፍጠፍ ማለት አልችልም። አንዳንዴ ነገሮች ሁሉ ግራ ያጋቡኛል። ምንም ነገር ማየት ስለማልችል መንገዴን ስቼ የምጠፋበትም ጊዜ አለ። ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቢኖሩኝ ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም በዚህ ጤንነቴ እንደ በፊቱ ጥናቶች ማግኘት አይቻለኝም። መጀመሪያ ላይ ይህ ሁኔታ ጭንቀት ውስጥ ከቶኝ ነበር። የአቅም ገደብ እንዳለብኝ አምኖ መቀበልንና አቅሜ የፈቀደውን በመሥራት መርካትን መማር አስፈልጎኝ ነበር። ይህ ደግሞ ቀላል አልነበረም። ቢሆንም በየወሩ ስለ ታላቁ አምላካችን ስለ ይሖዋ በመናገር ያሳለፍኩትን ሰዓት ሪፖርት ማድረግ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ነርሶች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች ሰዎች ወደ ቤቴ ሲመጡ አጋጣሚውን ተጠቅሜ በጥበብ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አነጋግራቸዋለሁ።
ካገኘኋቸው በረከቶች ሁሉ ትልቅ እርካታ የሚሰጠኝ ቤተሰቤ እስከ አራት ትውልድ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት ሲያመልክ መመልከቴ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አቅኚ ሆነው ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት አካባቢ በመሄድ፣ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ወይም በቤቴል ያገለግላሉ። እርግጥ ነው በኔ ዕድሜ እንደሚገኙት እንደ አብዛኞቹ ሰዎች እኔም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በቶሎ ይመጣል ብዬ አስቤ ነበር። ይሁን እንጂ በአገልግሎት ባሳለፍኳቸው ሰባት አሥርተ ዓመታት የተመለከትኩት ጭማሪ ምንኛ ታላቅ ነው! ይህን በመሰለ ታላቅ ሥራ ተሳትፎ በማድረጌ ከፍተኛ እርካታ ይሰማኛል።
ሊንከባከቡኝ የሚመጡት ነርሶች እስካሁን በሕይወት እንድቆይ ያደረገኝ እምነቴ መሆን እንዳለበት ይነግሩኛል። እኔም በሐሳባቸው እስማማለሁ። በይሖዋ አገልግሎት በቅንዓት መሳተፍ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ያስገኛል። ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት አረጀሁ፣ ዕድሜም ጠገብኩ ብዬ በእውነት መናገር እችላለሁ።—1 ዜና መዋዕል 29:28
(እህት ሙርኤል ስሚዝ ይህ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እያለ ሚያዝያ 1, 2002 አርፋለች። አንድ መቶ ሁለት ዓመት ሊሞላት የቀራት አንድ ወር ብቻ ነበር። በእርግጥም ታማኝ በመሆንና ጽናት በማሳየት ረገድ ትልቅ ምሳሌ ነች።)
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁና በ19 ዓመቴ ከባለቤቴ ከሮይ ጋር በተዋወቅሁበት ወቅት
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መኪናችንና ምጽጳ ብለን ስም ያወጣንለት ተጎታች ቤት
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሮይ ጋር በ1971