አጉል እምነት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራልን?
አጉል እምነት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራልን?
አጉል እምነቶች በመላው ዓለም ተስፋፍተው ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ እንደ ባህላዊ ቅርስ ስለሚታዩ ከፍ ያለ ግምት ይሰጣቸዋል። ወይም ደግሞ ለሕይወት ጣዕም የሚጨምሩ ተራ ነገሮች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በምዕራቡ ዓለም አጉል እምነቶች እምብዛም ትኩረት አይሰጣቸውም። በሌላው የዓለም ክፍል ግን ለምሳሌ በአፍሪካ፣ አጉል እምነቶች በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
አብዛኛው የአፍሪካ ባህል በአጉል እምነቶች ላይ የተመሠረተ ነው። አፍሪካ ውስጥ በሚዘጋጁ ፊልሞች፣ የራዲዮ ፕሮግራሞችና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ባብዛኛው እንደ አስማት፣ የቀድሞ አባቶች አምልኮና ክታብ ያሉ ከአጉል እምነትና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዙ ነገሮች ጎላ ብለው ሲንጸባረቁ ይታያል። አጉል እምነቶች በሰዎች ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ የሚያሳድሩት ለምንድን ነው? ምንጫቸውስ ከየት ነው?
አጉል እምነት ከምን ሊመነጭ ይችላል?
አብዛኞቹ አጉል እምነቶች የሙታንን መናፍስት ወይም ማንኛውንም ዓይነት መንፈስ ከመፍራት የሚመነጩ ናቸው። እነዚህ መናፍስት አንዳንድ ያልተለመዱ ዓይነት ክስተቶች እንዲፈጸሙ በማድረግ ሕያዋንን ለማስፈራራት፣ ለማስጠንቀቅ ወይም ለመባረክ እንደሚሞክሩ ተደርጎ ይታመናል።
አጉል እምነት ከፈውስና ከሕክምና ጋርም የቅርብ ቁርኝት አለው። በታዳጊ አገሮች ለሚኖሩት ለአብዛኞቹ ሰዎች ዘመናዊ ሕክምና በጣም ውድ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ አይገኝም። በመሆኑም ብዙዎች ፈውስ ማግኘት ወይም አንዳንድ የመከላከያ እርምጃዎች መውሰድ ሲፈልጉ ሲወርድ ሲዋረድ ወደ መጣው ልማድ፣ ወደ መናፍስታዊ ድርጊት ወይም ወደ አጉል እምነት ዞር ይላሉ። ደግሞም ከአንድ የሕክምና ዶክተር ጋር ከመነጋገር ይልቅ የራሳቸውን ቋንቋ ከሚናገርና ባህላቸውን በደንብ ከሚያውቅ ጠንቋይ ጋር መነጋገሩ ይቀላቸዋል። በዚህ መንገድ አጉል እምነቶች እየተስፋፉ ይሄዳሉ።
በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ወጎች ሕመም ወይም አደጋ እንዲያው በአጋጣሚ የሚከሰት ሳይሆን በመንፈሳዊው ዓለም ያሉ ኃይሎች የሚያመጡት ነገር እንደሆነ ይናገራሉ። ጠንቋዮች አንድ ሰው ሲታመም ወይም አደጋ ሲያጋጥመው አንድ የሞተ ዘመዱ በሆነ ምክንያት ቅር ስለተሰኘ ነው ይሉ ይሆናል። መናፍስት ጠሪዎች ደግሞ በሌላ ተቀናቃኝ ጠንቋይ አማካኝነት ድግምት ስለተደገመበት እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል።
አጉል እምነቶች በዓለም ዙሪያ የተለያየ መልክ ያላቸው ሲሆን የሚነገረውም ነገር እንደየአካባቢው አፈ ታሪክ እና ገጠመኝ የተለያየ ነው። ሆኖም በማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ያለው ሰው ወይም መንፈስ ጉዳት እንዳያደርስ የሚፈልገውን ሁሉ ማሟላት ይገባል የሚለው አስተሳሰብ የሁሉም የጋራ እምነት ነው።
አጉል እምነቶች ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ናቸውን?
ብዙ ቤተሰቦች መንታ ልጆች ሲወለዱላቸው ይደሰታሉ። በአጉል እምነት የሚመራ ሰው ግን ይህ ልዩ ትርጉም እንዳለው አድርጎ ሊያስብ ይችላል። በምዕራብ አፍሪካ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች መንትዮች ሲወለዱ አማልክት እንደተወለዱ አድርገው ስለሚያስቡ
መንትዮቹን ያመልኳቸዋል። ከመንትዮቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ቢሞቱ መንትዮቹን የሚወክሉ ትናንሽ ሐውልቶች ይሠሩና ቤተሰቡ ለእነዚህ ጣዖቶች ምግብ ያቀርባል። በሌላ ቦታ ደግሞ የመንትዮች መወለድ እንደ እርግማን ስለሚቆጠር አንዳንድ ወላጆች ቢያንስ ከመንትዮቹ አንዱን ይገድሉታል። ለምን? ምክንያቱም ሁለቱም በሕይወት ከኖሩ አንድ ቀን ወላጆቻቸውን ይገድላሉ ብለው ያምናሉ።እንደነዚህ የመሳሰሉ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ምንም እንኳን አንዳንድ አጉል እምነቶች ማራኪ ወይም ምንም ጉዳት የሌላቸው ቢመስሉም አንዳንዶቹ ግን አደገኛ ብሎም ሞት የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ምንም ጉዳት የሌለው ክስተት መጥፎ ትርጉም ስለተሰጠው ብቻ ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊመራ ይችላል።
አዎን፣ ሐቁ እንደሚያሳየው አጉል እምነት ራሱን የቻለ ሃይማኖት ነው ሊባል ይችላል። አጉል እምነት የሚያስከትላቸውን አደገኛ ሁኔታዎች ስንመለከት እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ተገቢ ይሆናል:- በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች የሚጠቅሙት ማንን ነው?
ከአጉል እምነቶች በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች
ሰይጣን እና ክፉ መናፍስት ስለመኖራቸው አሳማኝ ማስረጃ ቢኖርም ዛሬ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ይህንን ሐቅ መቀበል አይፈልጉም። ሆኖም በጦርነት ወቅት አደገኛ ጠላት መኖሩን ለመቀበል አሻፈረኝ ማለት ወደ ጥፋት ከመምራት ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ከሰው በላይ ኃይል ካላቸው መንፈሳዊ ፍጡራን ጋር በምናደርገው ውጊያም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘መጋደላችን ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው’ ሲል ጽፏል።—ኤፌሶን 6:12
እኛ ልናያቸው ባንችልም ክፉ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ የማይታይ መንፈሳዊ አካል በእባብ ተጠቅሞ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን በአምላክ ላይ እንድታምፅ ተጽዕኖ ያደረገባት መሆኑን ይገልጻል። (ዘፍጥረት 3:1-5) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን መንፈሳዊ አካል “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው . . . እርሱም የቀደመው እባብ” በማለት ይጠራዋል። (ራእይ 12:9) ይህ መንፈሳዊ አካል ማለትም ሰይጣን ሌሎች መላእክትም በአምላክ ላይ እንዲያምፁ አደረገ። (ይሁዳ 6) እነዚህ ክፉ መላእክትም የአምላክ ጠላቶች ወይም አጋንንት ሆኑ።
ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን ከአጋንንት አላቅቀዋል። (ማርቆስ 1:34፤ ሥራ 16:18) ሙታን ‘አንዳች ስለማያውቁ’ እነዚህ መናፍስት የሞቱ የቀድሞ አባቶች አይደሉም። (መክብብ 9:5) ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ያሳሳታቸው ዓመፀኛ መላእክት ናቸው። ከእነሱ ጋር ግንኙነት መፍጠር ወይም እነሱ ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ እጅ መስጠት አደገኛ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ልክ እንደ መሪያቸው እንደ ሰይጣን ዲያብሎስ እነርሱም ሊውጡን ይፈልጋሉ። (1 ጴጥሮስ 5:8) ግባቸው የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ ከሆነው የአምላክ መንግሥት እኛን ማራቅ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱን ይነግረናል:- “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” (2 ቆሮንቶስ 11:14) ሰይጣን የተሻለ ሕይወት እንደሚሰጠን በማሳመን ሊያታልለን ይፈልጋል። በመሆኑም በክፉ መናፍስት ጣልቃ ገብነት አንዳንድ ጊዜያዊ ጥቅሞች ማግኘት የሚቻል ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ አይችሉም። (2 ጴጥሮስ 2:4) ለማንም የዘላለም ሕይወት መስጠት የማይችሉ ከመሆኑም በላይ በቅርቡ ይጠፋሉ። (ሮሜ 16:20) የዘላለም ሕይወትና እውነተኛ ደስታ ሊሰጠንና ከክፉ መናፍስታዊ ኃይሎች ሊጠብቀን የሚችለው ፈጣሪያችን ብቻ ነው።—ያዕቆብ 4:7
አምላክ መናፍስታዊ ድርጊቶችን በመፈጸም እርዳታ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያወግዘዋል። (ዘዳግም 18:10-12፤ 2 ነገሥት 21:6) ይህንን ማድረግ አምላክን ከካዱ ጠላቶች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል። በኮከብ ቆጠራ መጠቀም፣ አዋቂ መጠየቅ ወይም በማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት መካፈል በሕይወትህ ውስጥ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ክፉ መናፍስት ተጽእኖ እንዲያሳድሩ መፍቀድ ማለት ነው። ይህም ከእነርሱ ጋር በመተባበር በአምላክ ላይ ከማመፅ ተለይቶ አይታይም።
ከክፉ መናፍስት ጥበቃ ማግኘት ይቻላልን?
በኒጀር የሚኖረው አዴ a ‘ብዙ ጠላቶች ስለነበሩት’ በሱቁ ውስጥ ክታብ ያንጠለጥል ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከሆነ ሰው ጋር ተገናኘና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። የሙሉ ጊዜ አገልጋዩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” የሚለውን የመዝሙር 34:7 ጥቅስ በማንበብ እውነተኛ ጥበቃ ማግኘት የሚቻለው ከይሖዋ ብቻ መሆኑን ገለጸለት። አዴም “ይሖዋ በእርግጥ ጥበቃ ሊያደርግልኝ የሚችል ከሆነ ክታቡን እጥለዋለሁ” ሲል ወሰነ። ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ብዙ ዓመታት ያለፉ ሲሆን አዴ አሁን የጉባኤ ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው። ከጠላቶቹ መካከል አንዳቸውም ጉዳት አላደረሱበትም።
አጉል እምነቶችን ተከተልንም አልተከተልን ሁላችንም ያልተጠበቁ ክስተቶች እንደሚያጋጥሙን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መክብብ 9:11 NW ) ሆኖም ይሖዋ በምንም ዓይነት በክፉ አይፈትነንም። (ያዕቆብ 1:13) የሰው ልጅ ከአዳም የወረሰው ኃጢአት አለፍጽምናና ሞት አምጥቶበታል። (ሮሜ 5:12) በዚህ የተነሳ ሁሉም ሰው በየጊዜው ይታመማል ወይም አሳዛኝ ውጤት የሚያስከትሉ ስሕተቶች ይፈጽማል። በመሆኑም ሁሉንም ሕመም ወይም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥመንን ችግር በሙሉ ከክፉ መናፍስታዊ ድርጊት ጋር ማያያዙ ስሕተት ይሆናል። እንደዚህ ዓይነቱ እምነት በሆነ መንገድ መናፍስቱን ለማስደሰት እንድንጥር ሊያደርገን ይችላል። b ስንታመም ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት መሞከር እንጂ “ሐሰተኛ የሐሰትም አባት” ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ምክር መጠየቅ አይገባንም። (ዮሐንስ 8:44) መረጃዎች እንደሚያሳዩት አጉል እምነት በተስፋፋባቸው አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በሌሎች አገሮች ከሚኖሩት የበለጠ ረጅም ዕድሜም ሆነ የተሻለ ሕይወት አይኖራቸውም። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አጉል እምነት በጤና ረገድ የሚያስገኘው ጥቅም የለም።
አምላክ ከማንኛውም ክፉ መንፈስ የበለጠ ኃይል ያለው ከመሆኑም በላይ ደህንነታችን ያሳስበዋል። “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል።” (1 ጴጥሮስ 3:12) ጥበቃና ጥበብ ለማግኘት ወደ እሱ ጸልይ። (ምሳሌ 15:29፤ 18:10) ቅዱስ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት አድርግ። ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ከሁሉ የላቀ ጥበቃ ነው። መጥፎ ነገሮች የሚደርሱት ለምን እንደሆነና ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል።
አምላክን ማወቅ የሚያስገኘው ጥቅም
እውነተኛ ጥበቃ ለማግኘት ቁልፉ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ሲሆን ይህ የአጉል እምነት ተቃራኒ ነው። በቤኒን የሚኖረው የዣን ታሪክ ይህንን ያሳያል። በዣን ቤተሰብ ውስጥ አጉል እምነቶች ስር ሰድደው ነበር። በአጉል እምነት ላይ በተመሠረተው የአካባቢው ወግ መሠረት ወንድ ልጅ የወለደች አራስ ሴት ለዘጠኝ ቀናት ያህል ለየት ባለ ሁኔታ በተሠራ ጎጆ ውስጥ መቆየት አለባት። የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ ደግሞ በጎጆው ውስጥ ለሰባት ቀናት ትቆያለች።
በ1975 የዣን ሚስት ማርክ የተባለውን ልጃቸውን ወለደች። ዣንና ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት አግኝተው ስለነበር ከክፉ መናፍስት ጋር ግንኙነት ያለው ምንም ነገር ማድረግ አልፈለጉም። ታዲያ በፍርሃትና በተጽዕኖ ተሸንፈው እናትየው በተለየ ጎጆ ውስጥ እንድትቆይ ያደርጉ ይሆን? በፍጹም እንደዚያ አላደረጉም።—ሮሜ 6:16፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14, 15
የዣን ቤተሰብ ይህን ባለማድረጉ መጥፎ ነገር አጋጥሞት ይሆን? ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ብዙ ዓመታት ያለፉ ሲሆን ማርክ በአሁኑ ጊዜ በአካባቢያቸው ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ነው። ቤተሰቡ አጉል እምነት ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርና መንፈሳዊ ደህንነታቸውን አደጋ ላይ እንዲጥለው ባለመፍቀዳቸው ደስተኞች ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 10:21, 22
እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአጉል እምነቶች ርቀው ፈጣሪያቸው ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጡትን መንፈሳዊ ብርሃን መቀበል አለባቸው። በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን እያደረጉ እንዳሉ ማወቃቸው እውነተኛ የአእምሮ ሰላም ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ዮሐንስ 8:32
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
b በመስከረም 1, 1999 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “እንድንታመም የሚያደርገን ዲያብሎስ ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በመላው ዓለም የሚገኙ አንዳንድ አጉል እምነቶች
• በጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ባለ ሩዝ ላይ ቾፕ ስቲክ (የሩቅ ምሥራቅ ሹካ) ቀጥ ብሎ ከተሰካ አንድ ሰው እንደሚሞት ይታሰባል
• በፀሐይ ብርሃን ጉጉት ማየት መጥፎ ዕድል ያመጣል
• በአንድ ሥነ ሥርዓት የተለኮሰ ሻማ በድንገት ከጠፋ በአቅራቢያው ክፉ መናፍስት አሉ ማለት ነው
• አንድ ሰው ቤት ውስጥ ዣንጥላ አምልጦት ከወደቀ ቤቱ ውስጥ ግድያ እንደሚፈጸም ያመለክታል
• ባርኔጣ አልጋ ላይ ማስቀመጥ መጥፎ ዕድል ያመጣል
• የደወል ድምፅ አጋንንትን ያባርራል
• አንድ ሰው በልደት ኬኩ ላይ የበሩትን ሻማዎች ሁሉ በአንድ ትንፋሽ ማጥፋት ከቻለ ምኞቱ ይፈጸምለታል
• መጥረጊያ ከአልጋ ግርጌ ከተቀመጠ መጥረጊያው ላይ ያሉት ክፉ መናፍስት አልጋው ላይ ይደግሙበታል
• መንገድ ላይ ጥቁር ድመት ካቋረጠችህ መጥፎ ዕድል ያጋጥምሃል
• ሹካ አምልጦህ ከወደቀ እንግዳ ይመጣል ማለት ነው
• የዝሆን ስዕል ከበሩ ፊት ለፊት ቢሰቀል መልካም ዕድል ያመጣል
• ደጃፉ ላይ የፈረስ ጫማ ያንጠለጠለ ሰው ዕድሉ የተቃና ይሆናል
• ሐረግ ቤት ላይ ሲያድግ ከክፉ መንፈስ ይጠብቃል
• በመሰላል ሥር ያለፈ ሰው መጥፎ ነገር ይገጥመዋል
• አንድ ሰው መስታወት ከተሰበረበት ለሰባት ዓመታት ያህል ዕድሉ አይቃናለትም
• በርበሬ ከተደፋብህ ከልብ ወዳጅህ ጋር ትጣላለህ ማለት ነው
• ጨው ሲደፋ ትንሽ ተቆንጥሮ በግራ ትከሻ በኩል ካልተበተነ በቀር መጥፎ ዕድል ያመጣል
• የሚወዛወዝ ወንበር እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ባዶውን ከተተወ አጋንንት እንዲቀመጡበት ይጋብዛል
• ጫማን ወደ ታች ደፍቶ ማስቀመጥ መጥፎ ዕድል ያመጣል
• አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ እንድትወጣ መስኮቶቹ መከፈት አለባቸው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አጉል እምነት ከሚያሳድረው ተጽእኖ ነጻ መውጣት
የይሖዋ ምሥክሮች በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ በአንድ አካባቢ እየሰበኩ ነበር። ምሥክሮቹ አንድ ቤት አንኳኩተው በሩ ሲከፈት ከላይ እስከ ታች የሳንጎማ (የጠንቋይ) ልብስ የለበሰች ሴት ታጋጥማቸዋለች። ትተዋት ሊሄዱ ቢፈልጉም ሴትየዋ መልእክታቸውን እንዲነግሯት ወተወተቻቸው። ከምሥክሮቹ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ምን እንደሚል ለማሳየት ዘዳግም 18:10-12ን አነበበላት። ጠንቋይዋም መልእክቱን ተቀብላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። ጥንቆላ የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ድርጊት መሆኑን የሚያሳምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ካገኘች ይህንን ሥራ እንደምታቆም ተናገረች።
በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ ካጠናች በኋላ ከጥንቆላ ጋር የተያያዙ ዕቃዎቿን ሁሉ አቃጠለችና በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች። ከዚህም በላይ ምንም እንኳን ከባሏ ጋር ለ17 ዓመት ያህል ተለያይተው የነበረ ቢሆንም ጋብቻቸውን ሕጋዊ አደረገች። አሁን ሁለቱም ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ጠንቋይዋ” በመናፍስታዊ ድርጊት አማካኝነት የአንድን ሕመምተኛ ችግር ለማወቅ አጥንት ትወረውራለች
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እውነተኛ ጥበቃና ደስታ ያስገኛል