‘የአምላክ ታላቅ ሥራ’ ለተግባር ያነሳሳል
‘የአምላክ ታላቅ ሥራ’ ለተግባር ያነሳሳል
“የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”—ሥራ 2:11
1, 2. በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ምን አስገራሚ ነገር ተከናወነ?
በ33 እዘአ የጸደይ ወቅት መገባደጃ አንድ ቀን ጠዋት ኢየሩሳሌም በሚገኝ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ ወንዶችና ሴቶች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ . . . በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።”—ሥራ 2:2-4, 15
2 ብዙ ሕዝብ ወደ ቤቱ መጥቶ ተሰበሰበ። ከእነዚህም መካከል የጰንጠቆስጤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ በሌላ አገር የተወለዱ ‘በጸሎት ይተጉ የነበሩ’ አይሁድ ይገኙበታል። ሰዎቹ ደቀ መዛሙርቱ በእነሱ ቋንቋ “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” ሲናገሩ በመስማታቸው በጣም ተገረሙ። ሁሉም የገሊላ ሰዎች ሆነው ሳሉ በተለያየ ቋንቋ ሊናገሩ የቻሉት እንዴት ነው?—ሥራ 2:5-8, 11
3. ሐዋርያው ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ምን ንግግር አቀረበ?
3 ከእነዚህ የገሊላ ሰዎች መካከል አንዱ ጴጥሮስ ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ በክፉዎች እጅ መገደሉን ገለጸ። ይሁን እንጂ አምላክ ልጁን ከሞት አስነሣው። ከዚያም ጴጥሮስንና በዚያ የተገኙ ደቀ መዛሙርትን ጨምሮ ኢየሱስ ለብዙዎቹ ታየ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ገና አሥር ቀን መሆኑ ነው። በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ያፈሰሰው እርሱ ነው። ይህ ክንውን የጰንጠቆስጤን በዓል ለማክበር ለመጡት ሰዎች ትርጉም ይኖረው ይሆን? አዎን፣ አለው። የኢየሱስ ሞት የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙና በእሱ ላይ እምነት ካሳደሩ “የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ” እንዲቀበሉ በር ይከፍትላቸዋል። (ሥራ 2:22-24, 32, 33, 38) ታዲያ በቦታው የተገኙት ሰዎች ለሰሙት ‘ለእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ’ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? እንዲሁም ይህ ዘገባ ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎታችንን እንድንገመግም የሚረዳን እንዴት ነው?
ለተግባር ተንቀሳቀሱ!
4. በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ፍጻሜውን ያገኘው የትኛው የኢዩኤል ትንቢት ነው?
4 በኢየሩሳሌም ተገኝተው መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት ደቀ መዛሙርት በዚያን ዕለት ጠዋት በዓሉን ለማክበር ከተሰበሰቡት ሰዎች አንስተው የመዳንን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል ጊዜ አላጠፉም ነበር። የስብከት እንቅስቃሴያቸው የባቱኤል ልጅ ኢዩኤል ከስምንት መቶ ዘመናት በፊት የመዘገበው አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስችሏል:- “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፣ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ።”—ኢዩኤል 1:1፤ 2:28, 29, 31፤ ሥራ 2:17, 18, 20
5. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ትንቢት የተናገሩት በምን መንገድ ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
5 እንዲህ ሲባል ታዲያ አምላክ እንደ ዳዊት፣ ኢዩኤልና ዲቦራ የመሳሰሉ ወንዶችና ሴቶች ነቢያትን አስነስቶ ወደፊት የሚከናወኑ ነገሮችን እንዲተነብዩ ያደርጋል ማለት ነው? አይደለም። ክርስቲያን ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዲሁም ባሪያዎች’ ትንቢት ይናገራሉ ሲባል ይሖዋ እስካሁን ድረስ ያደረጋቸውንና ወደፊትም የሚያደርጋቸውን ‘ታላላቅ ሥራዎች’ እንዲያውጁ በእሱ መንፈስ ይንቀሳቀሳሉ ማለት ነው። በዚህም መንገድ የልዑል ቃል አቀባይ ሆነው ያገለግላሉ። a ሆኖም የሕዝቡ ምላሽ ምን ነበር?—ዕብራውያን 1:1, 2
6. የጴጥሮስን ንግግር ካዳመጡ በኋላ አብዛኞቹ ሰዎች ምን ለማድረግ ተነሳስተዋል?
6 በዚያ የተገኘው ሕዝብ የጴጥሮስን ንግግር ካዳመጠ በኋላ አብዛኞቹ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስተዋል። “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ።” (ሥራ 2:41) ሰዎቹ በትውልድ አይሁዳዊና ወደ ይሁዲ እምነት የተቀየሩ በመሆናቸው የቅዱሳን ጽሑፎች መሠረታዊ እውቀት ነበራቸው። ይህ እውቀታቸው የጴጥሮስን ንግግር ካዳመጡ በኋላ ካዳበሩት እምነት ጋር ተዳምሮ “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲጠመቁ መሠረት ሆኗቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ከተጠመቁ በኋላ ‘በሐዋርያት ትምህርት ይተጉ ነበር።’ የተቀበሉትን አዲስ እምነት ለሌሎች ማካፈል ጀምረውም ነበር። በእርግጥም “በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ . . . እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው።” ከዚህ የምሥክርነት እንቅስቃሴ የተነሳ “ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።” (ሥራ 2:42, 46, 47) እነዚህ አዳዲስ አማኞች በሚኖሩባቸው በርካታ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ጉባኤዎች ተቋቋሙ። በተወሰነ መጠን እንዲህ ያለው እድገት ሊገኝ የቻለው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ‘ወንጌሉን’ በቅንዓት ለመስበክ ባደረጉት ጥረት እንደሆነ የታወቀ ነው።—ቆላስይስ 1:23
የአምላክ ቃል ይሠራል
7. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት እንዲመጡ የሚስባቸው ምንድን ነው? (ለ) በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአካባቢያችን ተጨማሪ እድገት ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁም ምን ነገር አለ? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
7 በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን ፍላጎት ስላላቸው ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? እነሱም ቢሆኑ የአምላክን ቃል በጥንቃቄ ማጥናት ያስፈልጋቸዋል። ቃሉን ሲያጠኑ ይሖዋ አምላክ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን ይገነዘባሉ። (ዘጸአት 34:6፤ ሥራ 13:48) ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥና በደሙ ከኃጢአት ሁሉ እንዲያነጻቸው በመላክ ይሖዋ ስላደረገው ደግነት የተሞላበት ዝግጅት ይማራሉ። (1 ዮሐንስ 1:7) አምላክ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ” ዓላማው እንደሆነ ሲያውቁ በአመስጋኝነት ይሞላሉ። (ሥራ 24:15) የእነዚህ ‘ታላላቅ ሥራዎች’ ምንጭ ለሆነው አካል ፍቅር ስለሚያድርባቸው እነዚህን አስደናቂ እውነቶች ለመስበክ ይነሳሳሉ። ከዚያም ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የአምላክ አገልጋዮች ከሆኑ በኋላ ‘በእግዚአብሔር እውቀት እያደጉ’ መሄዳቸውን ይቀጥላሉ። b—ቆላስይስ 1:12፤ 2 ቆሮንቶስ 5:14
8-10. (ሀ) የአንዲት ክርስቲያን ሴት ተሞክሮ የአምላክ ቃል ‘የሚሠራ’ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ይሖዋና ከአገልጋዮቹ ጋር ስላለው ግንኙነት ከዚህ ተሞክሮ ምን ትማራለህ? (ዘጸአት 4:12)
8 የአምላክ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የሚያገኙት እውቀት እንዲሁ የጭንቅላት እውቀት አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ልባቸውን ይነካል፣ አስተሳሰባቸውን ይለውጣል እንዲሁም የሕይወታቸው ክፍል ሆኖ ይኖራል። (ዕብራውያን 4:12) ከሚል የምትባል አንዲትን ሴት እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ከሚል ሥራዋ አረጋውያንን መንከባከብ ነበር። እንክብካቤ ከምታደርግላቸው አረጋውያን መካከል ማርታ የሚባሉ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ይገኙበታል። እኚህ ሴት ከባድ የአእምሮ በሽታ ስላለባቸው የማያቋርጥ ክትትል ያስፈልጋቸው ነበር። ምግብ እንዲበሉና አልፎ ተርፎም የጎረሱትን እንዲውጡ የሚያስታውሳቸው ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቀጥሎ እንደምናየው ከአእምሯቸው ያልጠፋ አንድ ነገር ነበር።
9 አንድ ቀን ከሚል ባጋጠማት ችግር የተነሳ ተጨንቃ ስታለቅስ እኚህ ሴት አዩዋት። ከሚልን አቅፈዋት ከእርሳቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ሐሳብ አቀረቡላት። በዚያ ሁኔታ ላይ እያሉ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ይችላሉ? አዎን፣ ይችላሉ! ማርታ ብዙ ነገር የረሱ ቢሆንም ታላቁን አምላካቸውን እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማሯቸውን ውድ እውነቶች አልዘነጉም። ከሚል እያንዳንዱን አንቀጽ፣ የተጠቀሱትን ጥቅሶች፣ ከታች የሰፈረውን ጥያቄ እንድታነብብና ከዚያም መልሱን እንድትሰጥ በማድረግ ጥናቱን ይመሩ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ በዚህ መልኩ እያጠኑ የቀጠሉ ሲሆን ማርታ የአቅም ገደብ ያሉባቸው ቢሆንም እንኳ ከሚል በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እያደገች ሄደች። ማርታ፣ ከሚል አምላክን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር መሰብሰብ እንዳለባት ተገነዘቡ። ከሚል ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ስትገኝ ሥርዓታማ የሆነ ልብስና ጫማ እንዲኖራት በማሰብ ለስብሰባ የሚሆናትን ቀሚስና ጫማ ሰጧት።
10 ከሚል የማርታ ፍቅራዊ አሳቢነት፣ ምሳሌና ጽኑ እምነት ልቧን ነካው። ማርታ በርካታ ነገሮችን የረሱ ቢሆንም እንኳ ከቅዱሳን ጽሑፎች የተማሯቸውን ነገሮች ግን አልረሱም፤ በዚህም የተነሳ ማርታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሯት ትምህርት በጣም አስፈላጊ መሆን አለበት ብላ አሰበች። ከጊዜ በኋላ ከሚል የሥራ ቦታዋን ቀይራ ወደ ሌላ ተቋም ከመሄዷ በፊት እርምጃ መውሰድ እንዳለባት ተገነዘበች። አስጠኚዋ የሰጧትን ቀሚስና ጫማ አድርጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄደችና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኗት ጠየቀች። ከሚል ጥሩ እድገት አደረገችና ተጠመቀች።
የይሖዋን መሥፈርቶች ለማክበር መነሳሳት
11. በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ከመካፈል በተጨማሪ የመንግሥቱ መልእክት ለተግባር እንዳነሳሳን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 በዛሬው ጊዜ እንደ ማርታና ከሚል ያሉ በዓለም ዙሪያ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ የሚሰብኩ ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እነርሱም ‘በእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ’ በጥልቅ ተነክተዋል። የይሖዋን ስም የመሸከምና መንፈሱን የማግኘት ልዩ መብት በማግኘታቸው አመስጋኞች ናቸው። ከዚህም የተነሳ ‘እንደሚገባ በመመላለስ ይሖዋን በነገር ሁሉ ደስ ለማሰኘትና’ መሥፈርቶቹን በመላ ሕይወታቸው ተግባራዊ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። ይህም በአለባበስና በአበጣጠር የአምላክን መሥፈርቶች ማክበርን ይጨምራል።—ቆላስይስ 1:12፤ ቲቶ 2:9, 10
12. አለባበስንና አበጣጠርን በተመለከተ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 ላይ ምን ቀጥተኛ ምክር እናገኛለን
12 አዎን፣ ይሖዋ አለባበሳችንንና አበጣጠራችንን በተመለከተ መመሪያ የሚሆን ደንብ አውጥቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ አምላክ ያወጣቸውን አንዳንድ ብቃቶች ዘርዝሯል። “ሴቶች በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ ይልበሱ እንጂ በሹሩባ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉ እንደሚገባ በመልካም ተግባር ይዋቡ።” c ከዚህ ጥቅስ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 አ.መ.ት
13. (ሀ) ‘ተገቢ የሆነ ልብስ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) የይሖዋን መመሪያዎች መከተል አስቸጋሪ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
13 የጳውሎስ ቃላት ክርስቲያኖች ‘ተገቢ የሆነ ልብስ መልበስ’ እንዳለባቸው ያሳያሉ። ልብሳቸው የተዝረከረከ፣ የቆሸሸ ወይም ቅጥ ያጣ መሆን የለበትም። ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ጨምሮ ማንኛውም ሰው የሚለብሰውን ልብስ በሥርዓት፣ በንጽሕናና በሚያስከብር ሁኔታ በመያዝ እነዚህን ለመታዘዝ አስቸጋሪ ያልሆኑ መመሪያዎች መከተል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ አገር የሚኖሩ ምሥክሮች በየዓመቱ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥቅጥቅ ባለ ጫካ በርካታ ኪሎ ሜትሮች በእግር ከተጓዙ በኋላ ለብዙ ሰዓት በታንኳ ይሄዳሉ። በጉዟቸው ወቅት ከመካከላቸው ወንዝ ውስጥ የሚወድቅ ወይም ልብሱ በእሾህ የሚቦጨቅበት ሰው አይታጣም። በዚህም የተነሳ ተጓዦቹ የአውራጃ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ ሲመጡ በአብዛኛው ተጎሳቁለው ነው የሚደርሱት። በመሆኑም በስብሰባው ወቅት የሚለብሷቸውን ልብሶች ቁልፍ ለመትከል፣ የተበላሹ ዚፖችን ለመጠገንና አጥቦ ለመተኮስ ጊዜ ይመድባሉ። ከይሖዋ ማዕድ እንዲመገቡ የቀረበላቸውን ግብዣ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ከመሆኑም በላይ በአግባቡ ለብሰው መገኘት ይፈልጋሉ።
14. (ሀ) “በጨዋነትና ራስን በመግዛት” መልበስ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) አለባበሳችን ‘እግዚአብሔርን እናመልካለን ለሚሉ ሰዎች’ የተገባ እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን?
14 ጳውሎስ አለባበሳችን ‘ጨዋነትና ራስን መግዛት’ ሊንጸባረቅበት እንደሚገባም ጠቅሷል። ይህም ማለት አለባበሳችን ለታይታ የሚደረግ፣ ቅጥ ያጣ፣ ለወሲብ የሚጋብዝ፣ ዕርቃንን የሚያሳይ ወይም ዘመን አመጣሽ መሆን የለበትም። በተጨማሪም አለባበሳችን ‘አምላክን ለሚያመልኩ’ ሰዎች የሚገባ መሆን አለበት። ይህ ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፤ አይደለም እንዴ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በሥርዓት እንለብሳለን በሌሎች ጊዜያት ግን እንዳሻን እንሆናለን ማለት አይደለም። በቀን ውስጥ የ24 ሰዓት ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆናችን አለባበሳችን ምንጊዜም የሚያስከብር መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት የምንለብሳቸው ልብሶች ከሥራችን ባሕርይ ጋር የሚጣጣሙ መሆን አለባቸው። እንደዚያም ሆኖ አለባበሳችን ጨዋነት የሚንጸባረቅበትና የሚያስከብር መሆን አለበት። አለባበሳችን የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን የሚያንጸባርቅ ከሆነ በአለባበሳችን አፍረን መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ከመስጠት ወደኋላ አንልም።—1 ጴጥሮስ 3:15
‘ዓለምን አትውደዱ’
15, 16. (ሀ) በአለባበስና በአበጣጠር ረገድ ዓለምን ከመምሰል መራቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ዮሐንስ 5:19) (ለ) በአለባበስና በአበጣጠር ረገድ ፋሽን ከመከተል እንድንርቅ የሚያደርገን ተጨባጭ ምክንያት ምንድን ነው?
15 በ1 ዮሐንስ 2:15, 16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ምክር በአለባበስና በጠጉር አበጣጠር ምርጫችን ረገድም ተጨማሪ መመሪያ ይሰጣል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”
16 ይህ ምክር ምንኛ ወቅታዊ ነው! የእኩዮች ተጽዕኖ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ባየለበት በዚህ ዘመን ዓለም የአለባበስና የአበጣጠር ምርጫችንን እንዲወስንልን መፍቀድ አይኖርብንም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የልብስና የአበጣጠር ፋሽኖች ሥርዓት እያጡ መጥተዋል። ሌላው ቀርቶ በንግዱ ዓለም የተሰማሩ ሰዎችና ባለሙያዎች የሚለብሱት የልብስ ዓይነት ለክርስቲያኖች ተገቢ የሆነውን አለባበስ ለመወሰን ሁልጊዜ አስተማማኝ መሥፈርት ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። ይህም አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት መኖርና ‘ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር ማስመስገን’ ከፈለግን ‘ይህን ዓለም ላለመምሰል’ ምንጊዜም ንቁ እንድንሆን የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያት ነው።—ሮሜ 12:2፤ ቲቶ 2:10
17. (ሀ) ልብስ ስንገዛ ወይም ስንመርጥ የትኞቹን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል? (ለ) የቤተሰብ ራሶች የቤተሰቡን አባላት አለባበስ በትኩረት መከታተል ያለባቸው ለምንድን ነው?
17 አንድ ዓይነት ልብስ ከመግዛታችሁ በፊት ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ጥበብ ነው:- ‘ይህን የልብስ ፋሽን የወደድኩት ለምንድን ነው? አንድ የማደንቀው ታዋቂ ሰው የሚለብሰው የፋሽን ዓይነት ይሆን? ዱርዬዎች ወይም የዓመፀኝነት መንፈስ የሚያስፋፉ ቡድኖች የሚለዩበት አለባበስ ነው?’ በተጨማሪም ልብሱን አገላብጠን ማየት ይኖርብናል። ቀሚስ ከሆነ ርዝመቱ እንዴት ነው? ስፌቱስ? ልብሱ ልከኛ፣ ተስማሚና የሚያስከብር ነው ወይስ የሰውነት ቅርጽ የሚያሳይ፣ ለወሲብ የሚጋብዝና ቅጥ ያጣ ነው? ‘ይህን ልብስ ብለብስ ሌሎች ይሰናከሉ ይሆን?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 6:3, 4) ይህ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና” ስለሚል ነው። (ሮሜ 15:3) ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶች የቤተሰቡን አባላት አለባበስና አበጣጠር ሊከታተሉ ይገባል። የቤተሰብ ራሶች ለሚያመልኩት ታላቅ አምላክ ካላቸው አክብሮት የተነሳ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥብቅና ፍቅራዊ ምክር ከመስጠት ወደኋላ ማለት የለባቸውም።—ያዕቆብ 3:13
18. ለአለባበሳችንና ለአበጣጠራችን ትኩረት እንድንሰጥ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
18 የምንሰብከው መልእክት የክብርና የቅድስና ምሳሌ ከሆነው ከይሖዋ የመነጨ ነው። (ኢሳይያስ 6:3) መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ተወደዱ ልጆች” ይሖዋን እንድንመስል ያሳስበናል። (ኤፌሶን 5:1) አለባበሳችንና አበጣጠራችን ሰማያዊ አባታችንን ሊያስከብር ወይም ሊያስነቅፍ ይችላል። ሆኖም ፍላጎታችን የእሱን ልብ ማስደሰት መሆን ይኖርበታል!—ምሳሌ 27:11
19. “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” ለሌሎች ማሳወቅ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?
19 እስከ አሁን ስለተማርከው ‘ስለ እግዚአብሔር ታላቅ ሥራ’ ምን ይሰማሃል? በእርግጥም፣ እውነትን በማወቃችን ምንኛ ተባርከናል! በፈሰሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ስለምናምን የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል። (ሥራ 2:38) ከዚህም የተነሳ ሳንሸማቀቅ በአምላክ ፊት የመናገር ነፃነት አለን። ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች ሞትን አንፈራም። ከዚህ ይልቅ ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት’ እንደሚመጣ ኢየሱስ የተናገረው ማረጋገጫ አለን። (ዮሐንስ 5:28, 29) ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለእኛ በመግለጥ ደግነት አሳይቶናል። ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱሱን አፍስሶልናል። ስለዚህ ለእነዚህ ሁሉ መልካም ስጦታዎቹ ያለን አመስጋኝነት ከፍ ያሉትን መሥፈርቶቹን እንድናከብርና ‘ታላቅ ሥራውን’ ለሌሎች በማወጅ እርሱን በቅንዓት እንድናወድስ ሊገፋፋን ይገባል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሙሴና አሮን ሕዝቡን ወክለው ፈርዖንን እንዲያነጋግሩ ይሖዋ በሾማቸው ጊዜ ሙሴን “እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል” ብሎት ነበር። (ዘጸአት 7:1፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አሮን ነቢይ ሆኖ ያገለገለው ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን በመተንበይ ሳይሆን የሙሴ ቃል አቀባይ በመሆን ነው።
b መጋቢት 28, 2002 በዋለው ዓመታዊው የጌታ እራት በዓል ላይ ከተገኙት በጣም ብዙ ተሰብሳቢዎች መካከል ይሖዋን ማገልገል ያልጀመሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ከልባቸው ተነሳስተው በቅርቡ የምሥራቹ አስፋፊዎች እንዲሆኑ ጸሎታችን ነው።
c ምንም እንኳ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ለክርስቲያን ሴቶች ቢሆንም መመሪያው ለክርስቲያን ወንዶችና ወጣቶች ይሠራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በዓሉን ለማክበር የተሰበሰቡት ሰዎች የሰሙት “ታላቅ ሥራ” ምንድን ነው? ምንስ ምላሽ ሰጡ?
• አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚሆነው እንዴት ነው? ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገርን ያካትታል?
• ለአለባበሳችንና ለአበጣጠራችን ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• አንድ ልብስ ወይም ፋሽን ሥርዓታማ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ልናስብባቸው የሚገቡ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ጴጥሮስ በግልጽ ተናግሯል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አለባበስህና አበጣጠርህ የምታመልከውን አምላክ የሚያስከብር ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ወላጆች የቤተሰብ አባሎቻቸውን አለባበስና የጠጉር አያያዝ ሊከታተሉ ይገባል