ለታማኝነት የተዛባ አመለካከት ያለው ዓለም
ለታማኝነት የተዛባ አመለካከት ያለው ዓለም
በቴል አቪቭ እስራኤል በአንድ ሞቃታማ የዓርብ ምሽት አንድ ወጣት ዳንስ ቤት ለመግባት ይጠብቁ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ተቀላቀለ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማ።
አጥፍቶ ጠፊዎች ከሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች መካከል ይህ አንዱ ብቻ ሲሆን ወጣቱ የራሱንና የሌሎች 19 ወጣቶችን ሕይወት አሰቃቂ በሆነ መንገድ ቀጥፏል። አንድ ሐኪም “አካባቢው በተቆራረጡ የሰው አካላት ተሞላ። አደጋው የደረሰባቸው በሙሉ ለጋ ወጣቶች ናቸው። እንደዚህ ያለ ዘግናኝ ሁኔታ በሕይወቴ ሙሉ አይቼ አላውቅም” በማለት ለዜና ዘጋቢዎች ተናግረዋል።
ተርስታን ብሬዊን ዘ ላንሴት በተባለው መጽሐፍ ላይ “እንደ ታማኝነት . . . ያሉ በብዙዎች ዘንድ ከፍ ተደርገው የሚታዩ ባሕርያት ጦርነት እንዲቆሰቆስና የተጀመረውም ጦርነት እንዳያቆም ዕንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት ጽፏል። አዎን፣ የሰው ልጅ ታሪክ ሕዝበ ክርስትና ከተካፈለችበት ከመስቀል ጦርነት አንስቶ በናዚ ጀርመን እስከተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ድረስ በታማኝነት ስም እንደ ጎርፍ በፈሰሰ ደም ተጨማልቋል።
ታማኝ አለመሆን የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
ጭፍን ታማኝነት አጥፊ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ታማኝ ሳይሆኑ መቅረትም አንድን ኅብረተሰብ እንዲፈረካከስ ሊያደርግ ይችላል። ታማኝ መሆን ማለት ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ ዓላማ መቆም ማለት ሲሆን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥም ላለመክዳት የሙጥኝ ብሎ የመቆምን መንፈስ ያስተላልፋል። ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለውን የታማኝነት ባሕርይ እንደሚያደንቁ ቢናገሩም ታማኝነት በጣም መሠረታዊ በሆነው በቤተሰብ ክልል ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመጥፋቱ ምክንያት ኅብረተሰብ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። የግል ፍላጎትን የማርካት ምኞት፣ የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈጥረው ውጥረትና በትዳር ውስጥ በፆታ ታማኝ ሆኖ አለመገኘት የፍቺ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል። እንዲሁም በቴል አቪቭ በደረሰው ፍንዳታ ላይ እንደታየው ብዙውን ጊዜ የችግሩ ሰለባዎች ንጹሐን ወጣቶች ናቸው።
“ፍቺ፣ ተለያይቶ መኖርና በነጠላ ወላጅ መተዳደር በቤተሰብ ውስጥ አለመረጋጋትን የሚያስከትል ሲሆን ይህም ብዙውን ጊዜ ልጆች ትምህርታቸውን በሚገባ እንዳይከታተሉ እንቅፋት ይፈጥራል” በማለት አንድ ሪፖርት ዘግቧል። በነጠላ እናት የሚተዳደሩ ወንዶች ልጆች ትምህርታቸውን የማቋረጥ፣ ሕይወታቸውን የማጥፋትና ወንጀል የመፈጸም ዕድላቸው በጣም ከፍ ያለ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ልጆች ወላጆቻቸው ይፋታሉ። በተጨማሪም በዚችው አገር በትዳር ውስጥ ከተወለዱት ልጆች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 18 ዓመት ከመድረሱ በፊት ወላጆቻቸው ይፋታሉ። አኃዞች እንደሚያሳዩት በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የበርካታ ወጣቶች የወደፊት ዕጣም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ታማኝነትን ማሳየት በጣም ከባድ ነውን?
በኅብረተሰቡ ውስጥ እየታየ ያለው የታማኝነት መጓደል ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደግ ሰው የለምና አንተው ድረስልኝ! ከሰዎችም መካከል አንድ ታማኝ አይገኝም” በማለት የተናገራቸው ቃላት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳሉ ያሳያል። (መዝሙር 12:1 አ.መ.ት ) ታማኝነት ይህን ያህል የጠፋው ለምንድን ነው? ሮጀር ሮሴንበላት የተባሉ አንድ ሰው በታይም መጽሔት ላይ እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ታማኝነት ከፍ ተደርጎ የሚታይ ባሕርይ ቢሆንም እንኳ ፍርሃት፣ በራስ የመተማመን ስሜት ማጣት፣ ለግል ጥቅም መሯሯጥና ደካማ የሆኑ የሰው ዘሮች ይህን ባሕርይ እንዲያሳዩ መጠባበቅ ታማኝነት እንዲጠፋ አድርገዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ጊዜ በሚመለከት “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ . . . ቅድስና [“ታማኝነት፣” NW ] የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው” በማለት በግልጽ ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ታማኝ መሆን ወይም ታማኝ ሳይሆኑ መቅረት በአንድ ሰው አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ከመረመርን በኋላ ‘ታማኝ መሆን ያለብኝ ለማን ነው’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ተመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከላይ ያለው ፎቶ:- © AFP/CORBIS