ማንበብና መጻፍ በመቻላቸው እጅግ ተደስተዋል!
ማንበብና መጻፍ በመቻላቸው እጅግ ተደስተዋል!
በአንዳንድ የሰሎሞን ደሴቶች ውስጥ ከሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 80 በመቶ የሚያህሉት ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር። ይህም በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፏቸው ውስን እንዲሆንና የመንግሥቱን እውነት ለሌሎች ማስተማር በጣም ፈታኝ እንዲሆንባቸው አድርጓል። በሕይወታቸው ውስጥ አንድም ጊዜ ጽፈው የማያውቁ አዋቂ ሰዎች ማንበብና መጻፍ መማር ይችሉ ይሆን?
በመላው የሰሎሞን ደሴቶች በሚገኙት በሁሉም ጉባኤዎች ማለት ይቻላል፣ ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር በመጠቀም መሠረተ ትምህርት ተሰጠ። የሚከተሉት ተሞክሮዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ፕሮግራም በመጠቀም ችሎታቸውን እንዳሻሻሉ ያሳያሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ማንበብ መቻላቸው ስለ እምነታቸው የተሻለ ምስክርነት ለመስጠት አስችሏቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:15
ከመቶ በላይ አስፋፊዎች ባሉት ጉባኤ እንድታገለግል የተመደበች አንዲት ሚስዮናዊ እህት በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት በሚደረገው ሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የራሳቸው ቅጂ ያላቸው ጥቂቶች እንደሆኑና ሐሳብ የሚሰጡት ደግሞ ከዚያም ያነሱ እንደሆኑ አስተዋለች። ይህ የሆነው ማንበብ ስለማይችሉ ነበር። ጉባኤው ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ትምህርት ቤት እንዳቋቋመ በማስታወቂያ ሲነገር ይህቺ ሚስዮናዊ እህት አስተማሪ ለመሆን በደስታ ራስዋን አቀረበች። መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ ጥቂት ነበሩ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ከ40 የሚበልጡ የተለያየ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች በትምህርት ቤቱ መካፈል ጀመሩ።
ምን ውጤት ተገኘ? ሚስዮናዊቷ እህት እንዲህ ትላለች:- “ማንበብና መጻፍ ማስተማር ከጀመርን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለሚስዮናውያኑ ቤተሰብ ምግብ ለመግዛት ጠዋት በአሥራ ሁለት ሰዓት ገበያ ወጣሁ። እዚያም ከተማሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ፣ በጣም ትናንሾቹም ጭምር ኮኮናትና አትክልት ሲሸጡ አገኘኋቸው። እንደዚህ የሚያደርጉት
ለምን ነበር? ለትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጋቸውን እስክሪብቶና ማስታወሻ ደብተር ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ማግኘት ስለፈለጉ ነበር። በትምህርት ቤቱ መካፈላቸው የራሳቸው የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ እንዲኖራቸውም አበረታቷቸዋል።” አክላም እንዲህ ትላለች:- “አሁን በጉባኤ መጠበቂያ ግንብ ሲጠና ወጣቶችና አረጋውያን እኩል ተሳትፎ ስለሚያደርጉ ጥናቱ ሕያው ሆኗል።” በትምህርት ቤቱ ከተካፈሉት መካከል አራቱ ለሕዝብ በመመስከሩ ሥራ መሳተፍ ይችሉ እንደሆነ ሲጠይቁ ሚስዮናዊቷ እህት በጣም ተደሰተች። ለምን እንደዚህ ማድረግ እንደፈለጉ ሲናገሩ “ከአሁን በኋላ አንፈራም” ብለዋል።ተማሪዎቹ በዚህ ትምህርት ቤት በመካፈላቸው ማንበብና መጻፍ ብቻ ሳይሆን ሌላም ጥቅም አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለበርካታ ዓመታት ጉባኤውን የምታስቸግር አማኝ ያልሆነች የአንድ ወንድም ሚስት ነበረች። በትንሽ በትልቁ ስለምትበሳጭ በሰዎች ላይ ድንጋይ እስከ መወርወር አልፎ ተርፎም ሌሎች ሴቶችን በዱላ እስከ መደብደብ ትደርስ ነበር። አልፎ አልፎ ከባልዋ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝም በጣም ስለምትቀና ሌሎች ሴቶችን አየህ ብላ እንዳትወቅሰው ሲል ባልዋ ጥቁር የፀሐይ መነጽር ያደርግ ነበር።
ትምህርት ቤቱ ማስተማር ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይህቺ ሴት “እኔም መማር እችላለሁ?” ስትል በረጋ መንፈስ ትጠይቃለች። መልሱ ትችያለሽ የሚል ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ከትምህርት ቤቱም ሆነ ከጉባኤ ስብሰባዎች ቀርታ አታውቅም። ተግታ በመማርና በማጥናት አስደናቂ ለውጥ ያደረገች ሲሆን በዚህም በጣም ተደሰተች። ቀጣዩ ጥያቄዋ “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እችላለሁ?” የሚል ነበር። ባልዋ በደስታ ያስጠናት ጀመር፤ አሁን በማንበብና በመጻፍ ችሎታዋም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትዋ እድገት እያደረገች ነው።
በሕይወቱ ሙሉ ጽፎ ለማያውቅ የ50 ዓመት ሰው እርሳስ ይዞ ፊደል መጻፍ ትልቅ ፈተና ነው። አንዳንዶች መማር እንደጀመሩ አካባቢ እርሳሱን በጣም ስለሚጫኑት ጣቶቻቸው ውኃ ቋጥረው ነበር። አንዳንድ ተማሪዎች እርሳሱን ይዘው በትክክል ለመጻፍ ለሳምንታት ሲታገሉ ከቆዩ በኋላ ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ “ያላንዳች ችግር መጻፍ ቻልኩ!” ሲሉ በደስታ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ እድገት እያደረጉ ሲሄዱ መመልከቱ አስተማሪዎቹንም ያስደስታቸዋል። ከመምህራኑ አንዷ እንዲህ ብላለች:- “ማስተማር በጣም ያስደስታል፤ ተማሪዎቹም ይሖዋ ላደረገላቸው ለዚህ ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት በትምህርቱ መጨረሻ ላይ በጭብጨባ ይገልጻሉ።”
አሁን ማንበብና መጻፍ የቻሉት እነዚህ ምሥክሮች ከሚስዮናውያኑ ጎን ተሰልፈው በተሻለ ሁኔታ ይሖዋን ማወደስ በመቻላቸው በእጅጉ ተደስተዋል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ይህ ዝግጅት ስለተደረገላቸው ተደስተዋል