“ምሳሌ ትቼላችኋለሁ”
“ምሳሌ ትቼላችኋለሁ”
‘ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ ነበር።’—ዕብራውያን 5:12
1. አንድ ክርስቲያን ዕብራውያን 5:12ን ማንበቡ ስለ ራሱ ብቃት እንዲያስብ የሚያደርገው ለምንድን ነው?
በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውንና ጭብጡ የተመሠረተበትን ይህን ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ ‘እኔስ ብሆን እንዴት ነኝ?’ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ይሆናል። ከሆነ ሁኔታው የሚያሳስበው አንተን ብቻ አይደለም። የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን አስተማሪዎች መሆን እንዳለብን እናውቃለን። (ማቴዎስ 28:19, 20) በተጨማሪም ጥሩ የማስተማር ችሎታ የግድ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ውስጥ እንደምንገኝ እንረዳለን። እንዲሁም የምናስተምረው ትምህርት ለሰዎች የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን! (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እንግዲያው እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው:- ‘አስተማሪ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት አሟላለሁን? እንዴት ማሻሻል እችላለሁ?’
2, 3. (ሀ) አንድ መምህር ለጥሩ አስተማሪነት መሠረቱ ምን እንደሆነ የገለጹት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ አስተማሪነትን በሚመለከት ምን ምሳሌ ትቶልናል?
2 ሆኖም ሁኔታው ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። አስተማሪነት ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ሙያ እንደሆነ አድርገን የምናስብ ከሆነ ምንም መሻሻል ማድረግ እንደማንችል ስለሚሰማን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ይሁን እንጂ ለጥሩ አስተማሪነት መሠረቱ አንድ ዓይነት ጥበብ ሳይሆን ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። ጥሩ ልምድ ያላቸው አንድ መምህር አስተማሪነትን በሚመለከት ባወጡት አንድ መጽሐፍ ላይ ምን እንዳሉ ተመልከት:- “ጥሩ የማስተማር ችሎታ አንድ የተወሰነ ጥበብ ወይም ስልት፣ ዘዴ ወይም እቅድ የመከተል ጉዳይ አይደለም። . . . ጥሩ አስተማሪነት በአንደኛ ደረጃ ፍቅር የማሳየት ጉዳይ ነው።” እኚህ ሰው ይህን የተናገሩት የቀለም ትምህርት አስተማሪነትን በተመለከተ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም እርሳቸው የጠቀሱት ይህ ነጥብ በክርስቲያንነታችን ለምናከናውነው የማስተማር ሥራ ይበልጥ ሊሠራ ይችላል። እንዴት?
3 በአስተማሪነት ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌያችን ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:15 አ.መ.ት ) ይህንን ሲናገር ትሕትና በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መጥቀሱ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ ወደ ምድር የመጣበትን ዋነኛውን ሥራ እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። ሥራው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ማስተማር ነበር። (ሉቃስ 4:43) ከዚህ አንጻር የኢየሱስን አገልግሎት በአንድ ቃል ጠቅለል አድርገህ ግለጸው ብትባል የትኛውን ቃል ትጠቀማለህ? “ፍቅር” እንደምትል እሙን ነው። (ቆላስይስ 1:15፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ለይሖዋ ያለው ፍቅር ተወዳዳሪ የለውም። (ዮሐንስ 14:31) ሆኖም ኢየሱስ አስተማሪ እንደመሆኑ በሌሎች ሁለት መንገዶችም ፍቅር አሳይቷል። ለሚያስተምረው እውነት እንዲሁም ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር ነበረው። ኢየሱስ በእነዚህ ሁለት አቅጣጫዎች ፍቅርን በማሳየት የተወልንን ምሳሌ በጥልቅ እንመርምር።
ለመለኮታዊ እውነት የጸና ፍቅር ነበረው
4. ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለሚሰጠው ትምህርት ፍቅር ያዳበረው እንዴት ነበር?
4 አንድ አስተማሪ ለሚያስተምረው ትምህርት ያለው አመለካከት በማስተማር ሙያው ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። አስተማሪው ለሚያስተምረው ትምህርት ግድ የለሽ ከሆነ ይህ ስሜት ወደ ተማሪዎቹም መጋባቱ የማይቀር ነው። ኢየሱስ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ላስተማረው ውድ እውነት ግድ የለሽነት ተሰምቶት አያውቅም። ኢየሱስ ለትምህርቱ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ሲሆን እንዲህ ያለውን ፍቅር ያዳበረው ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው። የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ባሳለፋቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት በጉጉት የሚከታተል ተማሪ ነበር። ኢሳይያስ 50:4, 5 እንዲህ በማለት ሁኔታውን በትክክል አስቀምጦታል:- “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል። ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፣ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም።”
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ምን ልዩ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? ይህስ በእሱ ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል? (ለ) በአምላክ ቃል አጠቃቀም ረገድ በኢየሱስ እና በሰይጣን መካከል ምን ልዩነት አለ?
5 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም በልጅነት ዕድሜው ለመለኮታዊ ጥበብ የነበረው ፍቅር አልቀነሰም። (ሉቃስ 2:52) ከዚያም በተጠመቀበት ወቅት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሁኔታ አጋጠመው። ሉቃስ 3:21 “ሰማይ ተከፈተ” በማለት ስለ ሁኔታው ይናገራል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወስ ችሎ እንደነበር መረዳት ይቻላል። ከዚያ በኋላ በምድረ በዳ ለ40 ቀናት ጾመ። በዚህ ወቅት ሰማይ ሳለ ከይሖዋ ባገኘው የተለያየ ትምህርት ላይ ማሰላሰሉ ይህ ነው የማይባል ደስታ አስገኝቶለት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ለአምላክ እውነት ያለው ፍቅር ተፈተነ።
6 ኢየሱስ ደክሞትና ርቦት በነበረበት ወቅት ሰይጣን ሊፈትነው ፈለገ። በእነዚህ ሁለት የአምላክ ልጆች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ሰፊ ነው! ሁለቱም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ይጥቀሱ እንጂ ለቃሉ ያላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለያየ ነበር። ሰይጣን የስስት ጥቅሙን ለማራመድ ሲል የአምላክን ቃል አክብሮት በጎደለው ሁኔታ እያጣመመ ይጠቅስ ነበር። በእርግጥም፣ ይህ ዐመፀኛ ለመለኮታዊ እውነት ከፍተኛ ንቀት ነበረው። በሌላ በኩል ኢየሱስ ለሚሰጠው መልስ ሁሉ የአምላክን ቃል በትክክል ይጠቀም ስለነበር ለቅዱሳን ጽሑፎች ፍቅር እንዳለው በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ይህ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ከመስፈሩ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በሕይወት የነበረ ቢሆንም ለቃሉ ጥልቅ አክብሮት አሳይቷል። ከሰማያዊ አባቱ የተሰጡ ውድ እውነቶች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር! ኢየሱስ ከይሖዋ የተሰጡት እነዚህ ቃላት ከመብል እንደሚበልጡበት ለሰይጣን ነግሮታል። (ማቴዎስ 4:1-11) አዎን፣ ኢየሱስ ይሖዋ ላስተማረው እውነት ልባዊ ፍቅር ነበረው። ይሁን እንጂ በማስተማር ሥራው ላይ ይህን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ለሚያስተምረው እውነት ፍቅር ነበረው
7. ኢየሱስ የራሱን ትምህርት ከማስተማር የተቆጠበው ለምን ነበር?
7 ኢየሱስ ለሚያስተምረው ትምህርት ያለው ፍቅር ምንጊዜም በግልጽ ይታይ ነበር። የሆነ ሆኖ ይህ ነው የማይባል እውቀትና ጥበብ ስለነበረው በቀላሉ የራሱን አመለካከት ወደማስተማር ሊያዘነብል ይችል ነበር። (ቆላስይስ 2:3) ይሁን እንጂ የሚያስተምረው ትምህርት በሙሉ የመነጨው ከሰማያዊው አባቱ እንጂ ከራሱ እንዳልሆነ ለአድማጮቹ ደግሞ ደጋግሞ ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዮሐንስ 7:16፤ 8:28፤ 12:49፤ 14:10) መለኮታዊውን እውነት እጅግ ከመውደዱ የተነሳ የራሱን አስተሳሰብ ለማስተማር አስቦ አያውቅም።
8. ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት በአምላክ ቃል በመጠቀም ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነበር?
8 ኢየሱስ ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ገና እንደጀመረ አንድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ተስፋ የተደረገበት መሲህ መሆኑን መጀመሪያ ለአምላክ ሕዝቦች ያሳወቀበትን መንገድ እስቲ ተመልከት። መሲህ መሆኑን ያሳወቀው እንዲሁ በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን በማወጅና ሰዎች እንዲያምኑ ለማድረግ ሲል የተለያዩ አስደናቂ ተአምራትን በመፈጸም አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማንበብ አዘውትረው ወደሚሰበሰቡበት ወደ ምኩራብ ሄዶ በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ድምፁን ከፍ አድርጎ ካነበበ በኋላ ይህ ትንቢታዊ እውነት በእርሱ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ተናገረ። (ሉቃስ 4:16-22) የፈጸማቸው በርካታ ተአምራት የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች ነበሩ። ያም ሆኖ ለሚያስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ድጋፍ አድርጎ የሚጠቅሰው የአምላክን ቃል ነበር።
9. ኢየሱስ ከፈሪሳውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ለአምላክ ቃል ታማኝ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቀናቃኞቹ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት ይከራከሩት በነበረበት ጊዜ ምንም እንኳን በቀላሉ አፋቸውን ማስያዝ ይችል የነበረ ቢሆንም እንደዚያ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ቃል እየጠቀሰ የሚያነሱትን መከራከሪያ ነጥብ ውድቅ ያደርግባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በእርሻ መካከል ሲያልፉ ጥቂት የስንዴ እሸት ዘለላዎችን አሽተው በበሉ ጊዜ ፈሪሳውያን የሰንበትን ሕግ ጥሰዋል ብለው ሰንዝረውት የነበረውን ክስ አስታውስ። ኢየሱስ “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፣ እርሱ ያደረገውን . . . አላነበባችሁምን?” በማለት መልስ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 12:1-5) እነዚያ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰዎች በ1 ሳሙኤል 21:1-6 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ታሪክ አንብበውት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ታሪኩ የያዘውን በጣም አስፈላጊ ትምህርት አላስተዋሉም ነበር። ኢየሱስ ግን ታሪኩን በማንበብ ብቻ ሳይወሰን ምን ማለት እንደሆነ በደንብ አስቦበትና መልእክቱ ገብቶት ነበር። ይሖዋ በዚያ ታሪክ አማካኝነት ለሰጠው መሠረታዊ ሥርዓት ኢየሱስ ፍቅር አድሮበታል። ስለሆነም ይህንን ታሪክና ከሙሴ ሕግ ውስጥ ሌሎች ምሳሌዎችን በመጠቀም ሕጉ ሚዛናዊ እንደሆነ አስረድቷቸዋል። እንዲሁም፣ ኢየሱስ ለአምላክ ቃል የነበረው ታማኝ ፍቅር ሃይማኖታዊ መሪዎች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ቃሉን ሲያጣምሙ ወይም ሕጉን በሰዎች ወግ ሲተበትቡ እያየ በዝምታ እንዳያልፍ አስገድዶታል።
10. ኢየሱስ የትምህርቱን ይዘት በሚመለከት የተነገሩ የትኞቹን ትንቢቶች ፈጽሟል?
10 ኢየሱስ ለሚያስተምረው እውነት ፍቅር ስለነበረው ትምህርቱ አሰልቺና ሙዝዝ ያለ አልነበረም። መሲሁ “መልካም ቃልን” እንደሚናገርና ‘ከከንፈሮቹ ጸጋ እንደሚፈስ’ አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር። (መዝሙር 45:2፤ ዘፍጥረት 49:21) ኢየሱስ በጣም የሚወደውን እውነት በሚያስተምርበት ጊዜ ‘ጸጋ የተሞላባቸው ቃላት’ እየተናገረ መልእክቱን ሕያውና ግልጽ አድርጎ በማቅረብ ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል። (ሉቃስ 4:22) አድናቆቱና ለትምህርቱ ያለው ጥልቅ ስሜት በፊቱና በዓይኑ ላይ በግልጽ ይነበብ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። እርሱ ሲያስተምር ማዳመጥ ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነበር! ስለተማርነው ነገር ለሌሎች በምንናገርበት ጊዜ ልንከተለው የሚገባን እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
11. ኢየሱስ ግሩም የማስተማር ችሎታ ቢኖረውም ኩራት ያልተሰማው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ መለኮታዊውን እውነት የመረዳት ግሩም ችሎታውና ስሜቱን ጥሩ አድርጎ በቃላት የመግለጽ ተሰጥኦው እንዲታበይ አድርጎት ይሆን? ሰብዓዊ አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ ይታይባቸዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አምላካዊ ፍርሃት እንዳለው የሚያሳይ ጥበብ እንደነበረው አትዘንጋ። ‘ጥበብ የምትገኘው በትሑታን ዘንድ ነው።’ (ምሳሌ 11:2) በመሆኑም ኢየሱስ ያለው ጥበብ ለትዕቢት ቦታ አይሰጥም። ኢየሱስ እንዳይኮራ ወይም እንዳይታበይ ያደረገው ሌላም ነገር አለ።
ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር ነበረው
12. ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲፈሩት እንደማይፈልግ ያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ለሰዎች ያለው ጥልቅ ፍቅር በትምህርቱ ላይ በግልጽ ይንጸባረቅ ነበር። ትምህርቶቹ ኩራት እንደሚያጠቃቸው የሰው ልጆች ሌሎች እንዲሸማቀቁ የሚያደርጉ አልነበሩም። (መክብብ 8:9) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የፈጸመውን አንድ ተአምር ከተመለከተ በኋላ እጅግ ከማድነቁ የተነሳ በኢየሱስ ጉልበት ላይ ወደቀ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ ለእርሱ የሚያርበደብድ ፍርሃት እንዲሰማቸው ፍላጎቱ አልነበረም። ኢየሱስ ጴጥሮስን በደግነት “አትፍራ” ካለው በኋላ ወደፊት ስለሚያከናውነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ አስደሳች ሥራ ነገረው። (ሉቃስ 5:8-10) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ አምላክ ባገኟቸው ውድ እውነቶች ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው እንጂ አስተማሪያቸውን ፈርተው እንዲያገለግሉ አይፈልግም።
13, 14. ኢየሱስ ለሰዎች አዘኔታ ያሳየባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
13 በተጨማሪም ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ያለው ፍቅር ለእነርሱ በሚሰማው የርኅራኄ ስሜት በግልጽ ይታይ ነበር። “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው ያዝንላቸውና እነርሱን ለመርዳት እርምጃ ይወስድ ነበር።
14 ኢየሱስ በሌላ ወቅት ያሳየውን የርኅራኄ ስሜት ተመልከት። ደም ይፈስሳት የነበረች አንዲት ሴት በሰዎች መካከል ተሹለክልካ መጥታ የልብሱን ዘርፍ በነካች ጊዜ በተአምራዊ መንገድ ተፈወሰች። ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደወጣ ይሰማው እንጂ የተፈወሰው ማን እንደሆነ አላወቀም ነበር። የነካችው ማን እንደሆነች ጠየቀ። ለምን? ማንነቷን የጠየቀው እርሷ እንደፈራችው ሕጉን ወይም የጻፎችንና የፈሪሳውያንን ደንብ ጥሰሻል ብሎ ለመውቀስ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ” ብሎ አሰናበታት። (ማርቆስ 5:25-34) ምን ያህል እንዳዘነላት ከእነዚህ ቃላት መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ “ተፈወሽ” ብቻ ብሎ ከመሸኘት ይልቅ “በሰላም ሂጂ ከስቃይሽም ተፈወሽ” እንዳላት ልብ ማለት ይገባል። ማርቆስ እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀመው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም በአብዛኛው ሰዎችን “ለማሰቃየት” የሚሠራበትን የግርፊያ ዓይነት የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ሕመምዋ ከባድ አካላዊና ስሜታዊ ስቃይ እንዳስከተለባት ተረድቶ ከልብ አዝኖላታል።
15, 16. ኢየሱስ የሌሎች ሰዎችን በጎ ጎን ይመለከት እንደነበረ የሚያሳዩት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
15 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የሰዎችን በጎ ጎን በመመልከት ለሰዎች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያ እስከመሆን የደረሰውን ናትናኤልን ባገኘው ጊዜ የተከሰተውን ተመልከት። “ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ:- ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።” ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የናትናኤልን ልብ ተመልክቶ ስለ እርሱ ብዙ ነገር ተረድቶ ነበር። ናትናኤል ፍጹም እንዳልነበረ የታወቀ ነው። እንደማንኛችንም ሁሉ እርሱም ጉድለቶች ነበሩበት። እንዲያውም መጀመሪያ ስለ ኢየሱስ ሲነገረው “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” በማለት የተሰማውን በግልጽ ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 1:45-51) ይሁን እንጂ ናትናኤል ሌሎች ብዙ ባሕርያት ቢኖሩትም ኢየሱስ ያተኮረው ይህ ሰው ባለው ጥሩ ጎን ማለትም በቅንነቱ ላይ ነበር።
16 በተመሳሳይም ከአሕዛብ ወገን እንደሆነ የሚገመት አንድ ሮማዊ የጦር መኮንን በሕመም የሚሰቃይ አገልጋዩን እንዲፈውስለት ሲጠይቀው ኢየሱስ ይህ ወታደር መጥፎ ጎኖች እንዳሉት ያውቅ ነበር። በዚያን ዘመን አንድ የጦር መኮንን በብዙ የጭካኔ ድርጊቶች፣ በደም መፋሰስ እንዲሁም በሐሰት አምልኮ ሥርዓቶች ይካፈል እንደነበረ ይገመታል። ሆኖም ኢየሱስ ያተኮረው ሰውዬው ባለው ጥሩ ጎን ይኸውም ባሳየው ከፍተኛ እምነት ላይ ነበር። (ማቴዎስ 8:5-13) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከጎኑ የተሰቀለውን ወንጀለኛ ባነጋገረበት ወቅት ሰውዬውን ከዚያ ቀደም ስለሠራው ወንጀል አልወቀሰውም። ከዚህ ይልቅ በፊቱ ስለሚጠብቀው ተስፋ በመንገር አበረታቶታል። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ የሌሎችን ደካማ ጎን አንስቶ መተቸት ተስፋ ከማስቆረጥ ሌላ ምንም ፋይዳ እንደማይኖረው ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ የሌሎችን በጎ ጎን መመልከቱ ብዙ ሰዎች ከበፊቱ የተሻለ እንዲያደርጉ ረድቷቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
ሰዎችን ለማገልገል ያሳየው ፈቃደኛነት
17, 18. ኢየሱስ ወደ ምድር ተልኮ በመጣበት ወቅት ሌሎችን ለማገልገል የፈቃደኝነት መንፈስ ያሳየው እንዴት ነበር?
17 ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር እንደነበረው የሚያሳየው ሌላው ጉልህ ማስረጃ እነርሱን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኑ ነው። የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የሰው ልጆችን ይወድድ ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) የይሖዋ “ቃል” ወይም ቃል አቀባይ እንደመሆኑ መጠን ከሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት መሥርቶ መሆን አለበት። (ዮሐንስ 1:1) ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን በቀጥታ ለማስተማር ሲል በሰማይ የነበረውን ከፍተኛ ቦታ በመተው “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵስዩስ 2:7፤ 2 ቆሮንቶስ 8:9) እዚህ ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ኢየሱስ ሌሎች እንዲያገለግሉት የሚጠብቅ ሰው አልነበረም። እንዲያውም “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ከተናገራቸው ከእነዚህ ቃላት ጋር ሙሉ በሙሉ በሚስማማ መንገድ ኖሯል።
18 ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ሰዎች በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለማገልገል ራሱን ምንም ሳይቆጥብ በትሕትና አቅርቧል። በተቻለው መጠን ብዙ ሰዎችን አግኝቶ ለማነጋገር ሲል በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር የስብከት ጉዞ በማድረግ ተስፋይቱ ምድርን በእግሩ አዳርሷል ማለት ይቻላል። ኢየሱስ ኩራተኛ ከነበሩት ፈሪሳውያንና ጻፎች በተቃራኒ ትሑትና ሌሎች በቀላሉ የሚቀርቡት ሰው ነበር። ሹማምንት፣ ወታደሮች፣ ሕግ አዋቂዎች፣ ሴቶች፣ ልጆች፣ ድሆች፣ በሽተኞች ሌላው ቀርቶ ኅብረተሰቡ የሚያገልላቸው ሰዎች እንኳን ያለ ፍርሃት ደስ እያላቸው ይቀርቡት ነበር። ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም ልክ እንደ እኛው የሚደክመውና የሚርበው ሰው ነበር። ድካም በተሰማው ወይም ለእረፍትም ሆነ ለጸሎት የሚያመች ጸጥ ያለ ሰዓት ባስፈለገው ጊዜም እንኳን ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም አስቀድሟል።—ማርቆስ 1:35-39
19. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በትሕትና፣ በትዕግሥትና በደግነት በመያዝ ረገድ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ የራሱን ደቀ መዛሙርት ለማገልገል ከዚህ የማይተናነስ ፈቃደኝነት አሳይቷል። ይህን ያደረገው በደግነትና በትዕግሥት በማስተማር ነበር። በጣም አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ትምህርቶችን ለመረዳት በሚቸገሩበት ጊዜ ተስፋ አይቆርጥባቸውም፣ አይቆጣቸውም ወይም አይነቅፋቸውም ነበር። ነጥቡን ለማስረዳት ሌላ ዘዴ ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዛሙርቱ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል ሽኩቻ ምን ያህል ጊዜ ተጣልተው እንደነበር አስታውስ። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት እስከነበረው ምሽት ድረስ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም አንዳቸው ለሌላው ትሕትና ማሳየት እንዳለባቸው ደግሞ ደጋግሞ አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ በሌሎች የተለያዩ መንገዶች ምሳሌ እንደሆነው ሁሉ ትሕትና በማሳየት ረገድም ‘ምሳሌ ትቼላችኋለሁ’ ማለቱ የተገባው ነው።—ዮሐንስ 13:5-15፤ ማቴዎስ 20:25፤ ማርቆስ 9:34-37
20. ኢየሱስን ከፈሪሳውያን የተለየ የሚያደርገው የትኛው የማስተማሪያ ዘዴ ነው? ዘዴው ውጤታማ የሆነውስ ለምንድን ነው?
20 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተናግሮ ብቻ ዞር እንዳላለ ከዚህ ይልቅ ‘ምሳሌ እንደተወላቸው’ ልብ ማለት ይገባል። እርሱ ራሱ አርአያ በመሆን አስተምሯቸዋል። ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት እነርሱ እንዲሠሩ ያዘዛቸውን ነገር መሥራት የእርሱን ክብር እንደሚቀንስበት አድርጎ አላሰበም። በዚህ ባሕርያቸው የሚታወቁት ፈሪሳውያን ነበሩ። ኢየሱስ “እየተናገሩ አያደርጉትም” በማለት ስለ እነርሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:3) ኢየሱስ ያስተማረውን እርሱ ራሱ ተግባራዊ በማድረግ ከተማሪዎቹ ምን እንደሚጠበቅባቸው በትሕትና አሳይቷቸዋል። ስለሆነም ተከታዮቹ ከፍቅረ ነዋይ የራቀ ቀላል ሕይወት እንዲመሩ ሲያሳስባቸው ይህን ትምህርት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ግር አላላቸውም። “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” በማለት የተናገረውን ቃል በአኗኗሩ ማየት ችለዋል። (ማቴዎስ 8:20) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምሳሌ በመተው በትሕትና አገልግሏቸዋል።
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 ኢየሱስ እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም! ለሚያስተምረው ትምህርትና ለሚያስተምራቸው ሰዎች የነበረው ፍቅር ሲያስተምር ለተመለከቱትና ለሰሙት ልበ ቅን ሰዎች በሙሉ በግልጽ የሚታይ ነበር። እርሱ የተወልንን ምሳሌ ለምናጠና በዚህ ዘመን ለምንኖር ሰዎችም የዚያኑ ያህል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የክርስቶስን ፍጹም ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ጥያቄ ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ለጥሩ አስተማሪነት መሠረቱ ምንድን ነው? ምሳሌ የሚሆነንስ ማን ነው?
• ኢየሱስ ለሚያስተምረው ትምህርት ፍቅር እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
• ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
• ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ሰዎች በትሕትና ለማገልገል የፈቃደኝነት መንፈስ እንዳለው የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?