በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው?

ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው?

ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው?

‘አገራችን . . . ትክክልም ሆነች አልሆነች፣ አገራችን እስከሆነች ድረስ ለአገራችን ታማኝ መሆን አለብን።’​—⁠ስቴቨን ዲካቱር፣ የዩ ኤስ የባሕር ኃይል መኮንን፣ 1779-1820

ብዙ ሰዎች ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ታማኝ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የስቴቨን ዲካቱርንን አነጋገር ትንሽ ለወጥ በማድረግ ‘ሃይማኖቴ ትክክልም ሆነ አልሆነ፣ ሃይማኖቴ እስከሆነ ድረስ ለሃይማኖቴ ታማኝ መሆን አለብኝ’ ሲሉ ይደመጣሉ።

በአንድ አገር ውስጥ ወይም በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ስለተወለድን ብቻ ለአገራችን ወይም ለሃይማኖታችን ታማኝ ሆነን መገኘት እንዳለብን ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ታማኝነት ከፍ ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ መንገድ መወሰን አይኖርበትም። ታማኝነት በትውልድ ቦታ መወሰን የለበትም ብሎ መናገር ግን ድፍረት የሚጠይቅና አልፎ ተርፎም ችግር ላይ የሚጥል ነው።

በታማኝነት ላይ የተነሳ ጥያቄ

በዛምቢያ ያደገች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ከልጅነቴ ጀምሮ ሃይማኖተኛ ነበርኩ። ወላጆቼ በቤተሰባችን የጸሎት ክፍል ውስጥ በየዕለቱ እንድጸልይ፣ ሃይማኖታዊ በዓላትን እንዳከብርና ወደ ቤተ መቅደስ ዘወትር እንድሄድ እያበረታቱ አሳድገውኛል። ባሕላችን፣ የምንኖርበት ኅብረተሰብና ቤተሰቤ ከሃይማኖትና ከአምልኮ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።”

ሆኖም ይህች ሴት ወደ ሃያዎቹ ዕድሜ እየተቃረበች ስትመጣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ከዚያ ብዙም ሳትቆይ ሃይማኖቷን መለወጥ እንዳለባት ወሰነች። ይህ ዓይነቱ እርምጃ እንደ ክህደት የሚቆጠር ነውን?

ዝላትኮ ያደገው በቦስኒያ ሲሆን አገሪቱን ባመሰው ጦርነት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ተካፍሏል። እርሱም እንዲሁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በዚህም የተነሳ በማንም ላይ እጁን እንደማያነሳ ገለጸ። ይህ አቋሙ አገሩን እንደካደ ያስቆጥረዋልን?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ እንደየሰዉ አመለካከት ይለያያል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴት እንዲህ ብላለች:- “እኔ በምኖርበት አካባቢ ሃይማኖትን መለወጥ አሳፋሪ ድርጊት እንደመፈጸም ተደርጎ የሚታይ ሲሆን ቤተሰብንና ኅብረተሰቡን እንደ መካድ ተደርጎ ይቆጠራል።” በተመሳሳይም የዝላትኮ የቀድሞ ባልደረቦች ከእነርሱ ጋር ሆኖ ለመዋጋት ፈቃደኛ የማይሆንን ሰው የሚቆጥሩት ከዳተኛ እንደሆነ አድርገው ነው። ሆኖም ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴትም ሆነች ዝላትኮ እንዲህ ያለውን እርምጃ የወሰዱት ከምንም በላይ ለአምላክ ታማኝ መሆን ስላለባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እዚህ ላይ አምላክ ለእርሱ ታማኝ ለመሆን የሚፈልጉትን ሰዎች የሚመለከታቸው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል።

እውነተኛ ታማኝነት የፍቅር መግለጫ ነው

ንጉሥ ዳዊት “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን . . . ታሳያለህ” በማለት ስለ ይሖዋ አምላክ ተናግሯል። (2 ሳሙኤል 22:26 አ.መ.ት ) እዚህ ላይ “ታማኝ መሆን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የአንድ ነገር ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ከዚያ ነገር ጋር ራሱን በፍቅር ሙጭጭ በማለት ደግነት ማሳየት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። አንዲት እናት ለሚጠባ ልጅዋ ከፍተኛ ስሜት እንደሚኖራት ሁሉ ይሖዋም ለእርሱ ታማኝ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር በፍቅር ይጣበቃል። ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል ለነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹ “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 49:15) ከምንም ነገር በላይ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን የሚፈልጉ የአምላክን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።

ለይሖዋ የምናሳየው ታማኝነት በፍቅር ላይ መመሥረት አለበት። እንዲህ ዓይነቱ የታማኝነት ባሕርይ አንድ ሰው ይሖዋ የሚወድደውን እንዲወድድና ይሖዋ የሚጠላቸውን ክፉ ነገሮች እንዲጠላ ያነሳሳዋል። (መዝሙር 97:10) የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው ለአምላክ ታማኝ መሆኑ በሌሎች ላይ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም ይጠብቀዋል። (1 ዮሐንስ 4:8) ስለዚህ አንድ ሰው ለአምላክ ካለው ታማኝነት በመነሳት ሃይማኖቱን ቢለውጥ ቤተሰቡን ጠልቷቸዋል ማለት አይደለም።

ለአምላክ ታማኝ መሆን ለበጎ ነገር ይገፋፋል

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴት የወሰደችውን እርምጃ በተመለከተ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ አማካኝነት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ ተገነዘብኩ፤ ከእርሱም ጋር የግል ዝምድና መሠረትኩ። ይሖዋ ቀደም ሲል አመልካቸው ከነበሩት አማልክት ፍጹም የተለየ አምላክ ነው። ፍቅሩን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ኃይሉን ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምባቸዋል። ይሖዋ እርሱን ብቻ እንድናመልከው ስለሚፈልግ ሌሎችን አማልክት መተው ነበረብኝ።

“ወላጆቼ በዚህ በወሰድኩት እርምጃ በጣም እንዳዘኑብኝና እንዳሳፈርኳቸው በተደጋጋሚ ይነግሩኝ ነበር። ወላጆቼ ውሳኔዬን እንዲቀበሉልኝ እፈልግ ስለነበር እነርሱን ማሳዘኔ በጣም ከበደኝ። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለኝ እውቀት ይበልጥ እያደገ ሲመጣ ያለኝ ምርጫ አንድ ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ጀርባዬን ለይሖዋ መስጠት አልቻልኩም።

“ከሃይማኖታዊ ልማድ ይልቅ ለይሖዋ ታማኝ መሆኔ ቤተሰቦቼን እንደካድኳቸው የሚያሳይ አይደለም። ስሜታቸውን እንደምረዳላቸው በቃልም ሆነ በድርጊት ልገልጽላቸው እሞክራለሁ። ለይሖዋ ታማኝ ሳልሆን ብቀር ግን ወላጆቼ እርሱን ለማወቅ የሚያስችላቸው አጋጣሚ ላያገኙ ይችላሉ፤ ከዚህ የከፋ ክህደት ደግሞ የለም።”

በተመሳሳይም፣ አንድ ሰው ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ሲል ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ቢሆንና በሌሎች ላይ ቃታ ለመሳብ እምቢ ቢል ከሐዲ አያሰኘውም። ዝላትኮ የወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በስመ ክርስትና እምነት ውስጥ ያደግሁ ብሆንም ክርስቲያን ያልሆነች ሚስት አገባሁ። ጦርነቱ በተጀመረ ጊዜ ድጋፍ እንድሰጥ ከሁለቱም ጎራዎች ጥያቄ ቀረበልኝ። የግድ ከአንዱ ጎራ ተሰልፌ መዋጋት ነበረብኝ። ለሦስት ዓመት ተኩል በጦርነቱ ተካፈልኩ። በመጨረሻ እኔና ባለቤቴ ጠፍተን ክሮኤሽያ ገባን። እዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘን።

“ከሁሉ ይበልጥ ታማኝነታችንን ልናሳይ የሚገባን ለይሖዋ እንደሆነና እርሱም የሰዎች ዘር ወይም ሃይማኖት ምንም ይሁን ምን ጎረቤቶቻችንን እንድንወድ እንደሚፈልግብን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ተገነዘብን። አሁን ባለቤቴና እኔ በይሖዋ አምልኮ የተባበርን ሲሆን ከጎረቤቶቼ ጋር እየተዋጋሁ ለአምላክ ታማኝ መሆን እንደማልችል ተምሬአለሁ።”

በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ታማኝነት

ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ታማኝነትን ከሚጠይቅ ከምንም ነገር በላይ ለእርሱ ታማኝ መሆን ይኖርብናል። (ራእይ 4:​10, 11) ይሁን እንጂ ለአምላክ የምናሳየው ታማኝነት ጭፍንና ጥፋት የሚያደርስ እንዳይሆን በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ . . . ቅድስና [“ታማኝነት፣” NW ] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌሶን 4:23, 24፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህን ቃላት በመንፈስ ተገፋፍቶ የጻፈው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ይህ ሰው በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ስላደገ ብቻ ለዚያ ሃይማኖት ታማኝ መሆን እንደሌለበት ለመናገር የሚያስችል ድፍረት ነበረው። ያደረገው ምርምር ለውጥ እንዲያሳዩ ረድቶታል።

ሳውል በጊዜያችን እንዳሉት ብዙ ሰዎች ታማኝነት ማሳየት ያለብኝ ለማን ነው የሚል ጥያቄ ገጥሞት ነበር። ሳውል ያደገው የአካባቢን ልማድ በጥብቅ በሚከተል ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ለተወለደበትም ሃይማኖት ታማኝ ነበር። ለእምነቱ የነበረው ታማኝነት ከእርሱ የተለየ አመለካከት የነበራቸውን ሰዎች እያደነ አካላዊ ጥቃት እንኳን ሳይቀር እስከመፈጸም አድርሶታል። ሳውል በእያንዳንዱ ቤት እየገባ ክርስቲያኖችን በማደንና በማስቀጣት ከዚያም በላይ እንዲገደሉ በማድረግ ሥራው ይታወቅ ነበር።​—⁠ሥራ 22:3-5፤ ፊልጵስዩስ 3:4-6

ሆኖም ሳውል ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሲያገኝ ወዳጆቹ እንደ እብደት አድርገው የቆጠሩትን አንድ እርምጃ ወሰደ። ሃይማኖቱን ለወጠ። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ሳውል ከሃይማኖታዊ ወግ ይልቅ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን መረጠ። ሳውል በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ለአምላክ ታማኝ መሆኑ በፊት የነበረውን የአጥፊነትና የአክራሪነት ባሕርይ እርግፍ አድርጎ በመተው ቻይ፣ አፍቃሪና ሌሎችን የሚያንጽ ሰው እንዲሆን አስችሎታል።

ታማኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

አምላክ ትክክል ነው ብሎ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ታማኝ መሆናችን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ በ1999 አውስትራሊያ ከሚገኘው የቤተሰብ ጥናት ተቋም የወጣ አንድ ዘገባ እንዳመለከተው ዘለቄታ ያለውና እርካታ የሚገኝበት ጋብቻ ለመመሥረት ከሚያስችሉት መሠረታዊ ነገሮች መካከል “መተማመንና ታማኝነት . . . [እንዲሁም] ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ማሳየት” እንደሚገኙበት ተናግሯል። ይኸው ጥናት እንዳረጋገጠው “ጽኑና እርካታ የሚገኝበት ትዳር” ወንዶችና ሴቶች ይበልጥ ደስተኞች፣ ጤነኞችና ረዥም ዕድሜ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። ጠንካራ የሆነ ጋብቻ ልጆች ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ ያስችላል።

ዋስትና በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ ታማኝነት በመስጠም ላይ የሚገኝን ዋናተኛ ለማዳን ከአንድ ሕይወት አድን ጀልባ ላይ ከሚወረወር ገመድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። “ዋናተኛው” ገመዱን ሳይዝ ከቀረ በማዕበሉና በነፋሱ ይንገላታል። የያዘው ገመድ በመስጠም ላይ ከሚገኝ መርከብ ጋር የታሠረ ከሆነ ደግሞ ገመዱን ምንም ያህል ሙጭጭ አድርጎ ቢይዝ ዋጋ አይኖረውም። ይህ ሳውል ቀደም ሲል ይከተለው ከነበረው የጥፋት ጎዳና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሁን እንጂ ከሕይወት አድን ጀልባ ላይ የተወረወረው ገመድ ዋናተኛው ሳይናወጥ ከችግሩ እንዲወጣ እንደሚረዳው ሁሉ በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ለይሖዋ ታማኝ መሆን በእምነት ሳንናወጥ ወደ መዳን እንድንደርስ ይረዳናል።​—⁠ኤፌሶን 4:13-15

ይሖዋ በታማኝነት ከጎኑ ለሚቆሙ ሰዎች የሚከተለውን ቃል ገብቶላቸዋል:- “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥላቸውም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።” (መዝሙር 37:28 አ.መ.ት ) ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የተገኙ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። እዚያም ከሐዘንና ከህመም ተላቅቀው በሃይማኖትና በፖለቲካ ሳይከፋፈሉ በደስታ ለዘላለም ይኖራሉ።​—⁠ራእይ 7:9, 14፤ ራእይ 21:3, 4

አሁንም እንኳ ሳይቀር በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ሊገኝ የሚችለው ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ብቻ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው እውነት መሠረት ስለ ታማኝነት ያለህን አመለካከት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለምን አትመረምርም? መጽሐፍ ቅዱስ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ይናገራል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 13:5

ስለ እምነታችን ትክክለኛነትና ለእምነታችን ታማኝ ስለምንሆንበት ምክንያት ጥያቄ ማንሳት ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ስለሚረዳን ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይሆንም። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴት እንዲህ በማለት የተሰማትን ስሜት ተናግራለች:- “ለይሖዋና እርሱ ላወጣቸው መሥፈርቶቸ ታማኝ መሆን ከቤተሰባችን ጋር ሚዛናዊ ግንኙነት እንዲኖረንና የተሻልን የኅብረተሰቡ አባላት እንድንሆን እንደሚረዳን ተገንዝቤአለሁ። የሚገጥመን ፈተና ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን እርሱም ለእኛ ታማኝ ይሆናል።” ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ እንደሚስማሙ ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳውል ትክክለኛ እውቀት ማግኘቱ አቋሙን በማስተካከል ለአምላክ ታማኝ እንዲሆን ረድቶታል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተጠቅመህ ታማኝ መሆን የሚኖርብህ ለማን እንደሆነ ለምን አትመረምርም?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ በስተግራ፣ ቸርችል:- U.S. National Archives photo; ከላይ በስተቀኝ፣ ጆሴፍ ጎብል:- Library of Congress