በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማመዛዘን ችሎታ ሊጠብቅህ የሚችለው እንዴት ነው?

የማመዛዘን ችሎታ ሊጠብቅህ የሚችለው እንዴት ነው?

የማመዛዘን ችሎታ ሊጠብቅህ የሚችለው እንዴት ነው?

በጣም ኃይለኛ የሆነ የባሕር ማዕበል ከሩቅ ሆኖ ለሚመለከተው እጅግ የሚማርክ ትዕይንት ቢሆንም ለመርከበኞች ግን አደጋ እየመጣ እንዳለ የሚጠቁም ምልክት ነው። እንዲህ ያለው ኃይለኛ ማዕበል ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው ይችላል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የአምላክ አገልጋዮችም እንደ ማዕበል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚሄዱ ከባድ ተጽዕኖዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። በክርስቲያኖች ላይ እንደ ማዕበል ያሉ ተደራራቢ መከራዎችና ፈተናዎች እንደሚደርሱ አስተውለህ ይሆናል። መንፈሳዊ የመርከብ መሰበር እንዳይደርስብህ እነዚህን ፈተናዎች በቆራጥነት ለማሸነፍ እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ለዚህ በዋነኛነት የሚረዳህ የማመዛዘን ችሎታ ነው። ለመሆኑ የማመዛዘን ችሎታ ምንድን ነው? እንዴትስ ማዳበር ይቻላል?

“የማመዛዘን ችሎታ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል መዚማህ ሲሆን “እቅድ መንደፍ” የሚል ትርጉም ካለው መሠረታዊ ቃል የመጣ ነው። (ምሳሌ 1:4 NW ) በመሆኑም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መዚማህ የሚለውን ቃል “ጥንቃቄ” ወይም “አርቆ ማስተዋል” ብለው ተርጉመውታል። ጄመይሰን፣ ፎሴት እና ብራውን የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን መዚማህ የሚለውን ቃል “ከክፉ ለመሸሽና መልካም ነገርን ለማግኘት የሚረዳን ጠንቃቃነት” በማለት ገልጸውታል። ይህም ድርጊቶቻችን ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የሚያስከትሉትን ውጤት ግምት ውስጥ ማስገባትን ያመለክታል። የማመዛዘን ችሎታ ካለን በተለይ ከባድ ውሳኔዎችን ከመወሰናችን በፊት ቆም ብለን ያሉንን አማራጮች በጥንቃቄ እናስባለን።

የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው የወደፊቱንም ሆነ አሁን ያለበትን ሁኔታ የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ከመወሰኑ አስቀድሞ ሊያጋጥሙት የሚችሉትን አደጋዎች ወይም ወጥመዶች በጥንቃቄ ያጤናል። ሊያጋጥሙት የሚችሉትን አደጋዎች ለይቶ ካወቀ በኋላ አካባቢውንና ከሰዎች ጋር ያለውን ቅርርብ ግምት ውስጥ በማስገባት ከእነዚህ አደጋዎች ማምለጥ የሚችልበትን መላ ይፈጥራል። እንዲህ በማድረግ መልካም ውጤት፣ አልፎ ተርፎም የአምላክን በረከት ማግኘት የሚያስችለውን አቅጣጫ ይቀይሳል። እስቲ ይህ ምክር ተግባራዊ የሚሆንባቸውን አንዳንድ አቅጣጫዎች እንመልከት።

ከጾታ ብልግና ወጥመድ ሽሽ

በነፋስ እየተገፋ የሚመጣ ኃይለኛ የባሕር ሞገድ የአንድ ጀልባን የፊት ለፊት ክፍል የሚመታበት ጊዜ ይኖራል። መርከበኞቹ የጀልባቸውን አፍንጫ ሞገዱ ወደሚመጣበት አቅጣጫ አዙረው ማዕበሉን ፊት ለፊት ካልተጋፈጡት በስተቀር ጀልባዋ ልትገለበጥ ትችላለች።

እኛም በዚህ በጾታ ስሜት ባበደ ዓለም ውስጥ ስንኖር ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያጋጥመናል። ወሲባዊ ምስሎችና ጽሑፎች በየዕለቱ ይጎርፉብናል። ተፈጥሮአዊ በሆነው የጾታ ስሜታችን ላይ ምንም አሉታዊ ተጽዕኖ አያሳድሩም ልንል አንችልም። አደገኛ በሆኑት ሁኔታዎች በቀላሉ ከመወሰድ ይልቅ የማመዛዘን ችሎታችንን በመጠቀም ፈተናውን በቆራጥነት ማሸነፍ ይኖርብናል።

ለምሳሌ ያህል ክርስቲያን ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን ለጾታ ስሜት ማርኪያ ብቻ እንደተፈጠሩ አድርገው ከሚቆጥሩ ወንዶች ጋር አብረው ይውሉ ይሆናል። እነዚህ የሥራ ባልደረቦች በንግግራቸው መሃል ጸያፍ ቀልዶችንና የብልግና ወሬዎችን ጣል ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህን ዓይነቱ ሁኔታ በአንድ ክርስቲያን አእምሮ ውስጥ ቀስ በቀስ የብልግና ሐሳቦች እንዲሰርጹ ሊያደርግ ይችላል።

አንዲት ክርስቲያን ሴትም ተቀጥራ በምትሠራበት ቦታ ችግሮች ሊያጋጥሟት ይችላሉ። የምትሠራው የእሷ ዓይነት የሥነ ምግባር አቋም ከሌላቸው ወንዶችና ሴቶች ጋር ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አንድ የሥራ ባልደረባዋ ከእሷ ጋር መቀራረብ ይፈልግ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ አሳቢና ሃይማኖታዊ አመለካከቷንም የሚያከብር ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። ዘወትር የሚያሳያት አሳቢነትና አብረው ተቀራርበው መሥራታቸው እሷም ከእሱ ጋር ይበልጥ የመቀራረብ ፍላጎት እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲገጥሙን የማመዛዘን ችሎታ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስከትሉት መንፈሳዊ አደጋ እንዲታየን የሚያደርግ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተገቢውን እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይችላል። (ምሳሌ 3:21-23) ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታችን የተነሳ የሥነ ምግባር አቋማችን ከእነርሱ የተለየ መሆኑን ለሥራ ባልደረባዎቻችን በግልጽ መናገር ሊኖርብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ይህን አባባላችንን ይበልጥ ማጠናከር እንችላለን። በተጨማሪም ከአንዳንድ የሥራ ባልደረባዎቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ገደብ ማበጀት ያስፈልገን ይሆናል።

ይሁን እንጂ ወደ ሥነ ምግባር ውድቀት የሚመሩ ተጽዕኖዎች የሚያጋጥሙት በሥራ ቦታ ብቻ አይደለም። አንድ ባልና ሚስት አንድነታቸውን የሚያናጉ ችግሮች እንዲኖሩ ከፈቀዱ እነዚህ ተጽዕኖዎች በትዳር ውስጥም ሊያጋጥሙ ይችላሉ። አንድ ተጓዥ አገልጋይ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ትዳር የሚፈርሰው እንዲያው በድንገት አይደለም። ባልና ሚስቱ እርስ በእርስ የሚያወሩበት ወይም አብረው ሆነው የሚያሳልፉት ጊዜ በመቀነሱ ቀስ በቀስ እየተራራቁ ይሄዳሉ። በትዳራቸው መሃል ያለውን ክፍተት ለመሸፈን ሲሉ ቁሳዊ ሀብት ማሳደድ ይጀምራሉ። እርስ በእርስ የአድናቆት መግለጫ ስለማይለዋወጡ ሌላ ተቃራኒ ፆታ በሚሰጣቸው አትኩሮት በቀላሉ ሊማረኩ ይችላሉ።”

ይህ ተሞክሮ ያለው አገልጋይ አክሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ባልና ሚስት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ነገር ተፈጥሮ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ በየጊዜው ቁጭ ብለው መወያየት ይኖርባቸዋል። አብረው የሚያጠኑበት፣ የሚጸልዩበትና በአገልግሎት የሚሳተፉበት ፕሮግራም ማውጣት አለባቸው። ወላጆችና ልጆች ሊያደርጉት እንደሚገባው እነርሱም ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድም ሲሄዱ፣ ሲተኙም ሆነ ሲነሱ’ እርስ በእርስ የሐሳብ ልውውጥ ቢያደርጉ በእጅጉ ይጠቀማሉ።”​—⁠ዘዳግም 6:7-9

የሌሎች ክርስቲያኖችን ድክመት መቻል

የማመዛዘን ችሎታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ እንድናሸንፍ ከመርዳቱም ባሻገር ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የሚነሱ ችግሮችንም እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል። ማዕበል ከጀልባዋ ኋላ የሚመጣበትም ጊዜ ይኖራል። ይህ ሞገድ ጀልባዋን ከኋላ በኩል አንስቶ ወደ ጎን ሊያዞራት ይችላል። የጀልባዋ የጎን ክፍል በማዕበሉ ስለሚመታ ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል።

እኛም በተመሳሳይ ካልተጠበቀ አቅጣጫ ለሚመጣ አደጋ ልንጋለጥ እንችላለን። ታማኝ ከሆኑ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ‘አንድ ሆነን’ ይሖዋን እናገለግላለን። (ሶፎንያስ 3:9) ከእነዚህ አንዱ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ባሕርይ ቢያሳይ በጣም ልንቀየምና ከልብ ልናዝን እንችላለን። የማመዛዘን ችሎታ ሚዛናችንን እንዳንስትና ከመጠን በላይ እንዳንጎዳ ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?

‘የማይበድል ሰው እንደሌለ’ አስታውስ። (1 ነገሥት 8:46) ስለዚህ አንድ ወንድም ሊያስቀይመን ወይም ሊያበሳጨን የሚችል ነገር ቢያደርግ ሊያስገርመን አይገባም። ይህን ከተገነዘብን ራሳችንን ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አስቀድመን ማዘጋጀትና ሁኔታው ሲያጋጥም ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርብን ማሰላሰል እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያን ወንድሞቹ ንቀትን በሚያሳይና ስሜቱን ሊጎዳ በሚችል መንገድ ስለ እርሱ በተናገሩ ጊዜ ያደረገው ነገር ምን ነበር? መንፈሳዊ ሚዛኑን ከመሳት ይልቅ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት እንደሚበልጥ አሰበ። (2 ቆሮንቶስ 10:10-18) ይህን ዓይነቱን አመለካከት መያዝ ሌሎች ሲያስቀይሙን በችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ሊጠብቀን ይችላል።

ይህ ሁኔታ የእግራችንን ጣት እንቅፋት ሲመታን ከሚሰማን ስሜት ጋር በመጠኑም ቢሆን ይመሳሰላል። እንቅፋት ሲመታን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ምን እንደምናደርግ ይጠፋናል። ሆኖም ሕመሙ በረድ ሲልልን በትክክል ማሰብና መንቀሳቀስ እንጀምራለን። በተመሳሳይም ሰዎች ደግነት የጎደለው ነገር ሲናገሩን ወይም ሲያደርጉብን ወዲያውኑ አጸፋውን ለመመለስ መቸኮል አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ቆም ብለን በችኮላ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ የሚያስከትለውን ውጤት እናስብ።

ለበርካታ ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለው ማልከም ሰዎች ሲያስቀይሙት ምን እንደሚያደርግ እንዲህ በማለት ገልጿል። “የመጀመሪያው እርምጃዬ ቀደም ሲል በአእምሮዬ የያዝኳቸውን ጥያቄዎች ራሴን መጠየቅ ነው። በዚህ ወንድም የተበሳጨሁት ባሕርያችን ስላልተጣጣመ ነው? የተናገረኝ ነገር ያን ያህል የሚጎዳ ነው? ያለብኝ የወባ በሽታ በቀላሉ እንድበሳጭ እያደረገኝ ይሆን? ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ለተፈጠረው ሁኔታ ያለኝ አመለካከት ይለወጥ ይሆን?” ማልከም አብዛኛውን ጊዜ የተፈጠረው አለመግባባት እዚህ ግባ የማይባልና በቸልታ ሊታለፍ የሚቻል ሆኖ አግኝቶታል። a

ማልከም አክሎ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ሁኔታውን ለማስተካከል የቱንም ያህል ጥረት ባደርግ ወንድም ቅር እንደተሰኘ ሊቀጥል ይችላል። በዚህ ላለመረበሽ እሞክራለሁ። የምችለውን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ አመለካከቴን አስተካክላለሁ። ጉዳዩን ወዲያው መፍትሔ ላገኝለት እንደሚገባ ችግር ሳይሆን በጊዜ ሂደት ሊፈታ እንደሚችል አድርጌ እተወዋለሁ። በመንፈሳዊ እንዲጎዳኝ ወይም ከይሖዋም ሆነ ከወንድሞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንዲያበላሽብኝ አልፈቅድም።”

እኛም አንድ ግለሰብ የሚያሳየው ተገቢ ያልሆነ ባሕርይ ከመጠን በላይ እንዲረብሸን መፍቀድ አይኖርብንም። በየጉባኤው ተወዳጅና ታማኝ የሆኑ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በክርስቲያናዊው ጎዳና ከእነርሱ ጋር ‘አብሮ’ መጓዝ የሚያስደስት ነው። (ፊልጵስዩስ 1:27) ሰማያዊው አባታችን የሚያደርግልንን ፍቅራዊ ድጋፍ ማስታወሳችንም ጉዳዩን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድናየው ይረዳናል።​—⁠መዝሙር 23:1-3፤ ምሳሌ 5:1, 2፤ 8:12

በዓለም ያሉትን ነገሮች አለመውደድ

የማመዛዘን ችሎታ አንድ ሌላ ስውር ተጽዕኖም እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል። ማዕበሉ የጀልባዋን የጎን ክፍል የሚመታበት ወቅትም አለ። ኃይለኛ ያልሆነ ማዕበል ጀልባዋን ከጎን በኩል እየገፋ ቀስ በቀስ አቅጣጫዋን ሊያስቀይራት ይችላል። ይሁን እንጂ ማዕበሉ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ጀልባዋን ሊገለብጣት ይችላል።

በተመሳሳይ እኛም ይህ ክፉ ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ሁሉ የመደሰት ፍላጎት በሚያሳድረው ግፊት ከተሸነፍን በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረው እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር መንፈሳዊ አቅጣጫችንን እንድንስት ሊያደርገን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 4:10) ካልተጠነቀቅን ዓለምን መውደድ ቀስ በቀስ ከክርስቲያናዊ ሕይወት እንድንወጣ ሊያደርገን ይችላል። (1 ዮሐንስ 2:15) የማመዛዘን ችሎታ በዚህ ረገድ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን አደጋዎች እንድናመዛዝን ይረዳናል። ዓለም እኛን ለማባበል የማይጠቀምበት ዘዴ የለም። ሁሉም ሰው ሊከተለው እንደሚገባው ተደርጎ የሚታሰበውን ቱጃሮች፣ ታዋቂነትን ያተረፉና “ተሳክቶላቸዋል” የሚባሉት ሰዎች የሚያራምዱትን የይታይልኝ መንፈስ የተንጸባረቀበት የአኗኗር ዘይቤ ያበረታታል። (1 ዮሐንስ 2:16) በሁሉም ሰዎች በተለይም በእኩዮቻችንና በጎረቤቶቻችን ዘንድ በቀላሉ አድናቆትና ተቀባይነት ማትረፍ እንደምንችል እንዲሰማን ያደርጋል። የማመዛዘን ችሎታ ‘ከቶ እንደማይተወን’ ከይሖዋ ቃል ስለተገባልን ‘ራሳችንን ከፍቅረ ንዋይ መጠበቅ’ ያለውን ጠቀሜታ እንድናስታውስ በማድረግ ይህንን ፕሮፓጋንዳ እንድንቋቋም ይረዳናል።​—⁠ዕብራውያን 13:5 አ.መ.ት 

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታ ‘ከእውነት ስተው’ የወጡትን እንዳንከተል ያደርገናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:18) እንወዳቸውና እምነት እንጥልባቸው የነበሩ ሰዎችን መቃወም በጣም ይከብዳል። (1 ቆሮንቶስ 15:12, 32-34) ቢሆንም ከክርስቲያናዊ የሕይወት መንገድ ዘወር ያሉ ሰዎች የሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ትንሽም እንኳን ቢሆን መንፈሳዊ እድገታችንን ሊያቀጭጭብን አልፎ ተርፎም አደጋ ውስጥ ሊከተን ይችላል። ከትክክለኛው የጉዞ መስመር ትንሽ ዝንፍ ባለች ጀልባ ልንመሰል እንችላለን። ጀልባዋ ብዙ በተጓዘች መጠን ከትክክለኛው አቅጣጫ ይበልጥ እየራቀች ልትሄድ ትችላለች።​—⁠ዕብራውያን 3:12

የማመዛዘን ችሎታ በመንፈሳዊ በምን ሁኔታ ላይ እንደምንገኝና ወዴት እያመራን እንደሆነ እንድናውቅ ያስችለናል። ምናልባት በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንገነዘብ ይሆናል። (ዕብራውያን 6:11, 12) አንድ ወጣት ምሥክር የማመዛዘን ችሎታውን ተጠቅሞ መንፈሳዊ ግቦችን መከታተል የቻለው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። “ጋዜጠኛ የመሆን አጋጣሚ ነበረኝ። ጋዜጠኝነት የምወደው ሥራ ቢሆንም ‘ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስታወስኩ። (1 ዮሐንስ 2:17) አኗኗሬ ክርስቲያናዊ እምነቶቼን የሚያንጸባርቅ መሆን እንዳለበት አሰብኩ። ወላጆቼ የክርስትናን ጎዳና ቢተዉም የእነርሱን አርዓያ መከተል አልፈለግሁም። ስለዚህ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመኖር ወሰንኩና የዘወትር አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ። በዘወትር አቅኚነት አራት አስደሳች ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ ውሳኔዬ በእርግጥም ትክክለኛ እንደነበር ተገንዝቤያለሁ።”

መንፈሳዊ ማዕበሎችን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም

ዛሬ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው? መርከበኞች ማዕበል ሊነሳ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በንቃት መከታተል አለባቸው። የአየሩ ሁኔታ በፍጥነት ከቀዘቀዘና ንፋሱ እየበረታ ከመጣ በመርከቡ ወለል ላይ ያሉትን በሮች አጥብቀው በመዝጋት ለሚመጣው የከፋ አደጋ ይዘጋጃሉ። እኛም በተመሳሳይ የዚህ ክፉ ሥርዓት ማክተሚያ እየተቃረበ ሲሄድ የሚያጋጥሙንን ኃይለኛ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም መዘጋጀት አለብን። የኅብረተሰብ የሥነ ምግባር መዋቅር እየተፈረካከሰ ሲሆን ‘ክፉዎች በክፋት እየባሱ ሄደዋል።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:13) መርከበኞች የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን አዘውትረው እንደሚከታተሉ ሁሉ እኛም በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ በንቃት መከታተል አለብን።​—⁠መዝሙር 19:7-11

የማመዛዘን ችሎታችንን ስንጠቀም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን እውቀት ተግባራዊ እናደርጋለን። (ዮሐንስ 17:3) ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ችግሮች አስቀድመን ማወቅና እንዴት እንደምንወጣቸው መወሰን እንችላለን። በዚህ መንገድ ከክርስቲያናዊው ጎዳና ተገፍተን ላለመውጣት ራሳችንን በቁርጠኝነት እናዘጋጃለን፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ግቦችን በማውጣትና በመከታተል ‘ለሚመጣው ዘመን ለራሳችን መልካም መሠረት’ መጣል እንችላለን።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​18, 19

ተግባራዊ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ ካለን ‘ድንገት የሚያስፈራ ነገር’ ቢያጋጥመንም አንፈራም። (ምሳሌ 3:21, 25, 26) ከዚህ ይልቅ “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል” በማለት አምላክ በሰጠን ቃል ልንበረታታ እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 2:10, 11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ክርስቲያኖች በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ በሰፈረው ምክር መሠረት ሰላም ለማስፈን መጣር አለባቸው። ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ከሆነ ግን በማቴዎስ 18:15-17 ላይ በሠፈረው መሠረት ወንድማቸውን ለማዳን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-22 ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘወትር የሚደረግ የሐሳብ ግንኙነት ትዳርን ያጠነክራል