በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ገንዘባችሁን የምመልሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?”

“ገንዘባችሁን የምመልሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?”

“ገንዘባችሁን የምመልሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?”

በጆርጅያ ሪፑብሊክ በካስፒ ግዛት የምትኖር ናና የተባለች ሦስት ወንዶች ልጆችን ብቻዋን የምታሳድግ እናት “ገንዘብ በጣም ቸግሮኝ ነበር” ትላለች። አንድ ቀን ጠዋት ገንዘብ የማግኘት ሕልምዋ እውን ሆነ። ፖሊስ ጣቢያው አጠገብ 300 ላሪ (1200 ብር ገደማ) ወድቆ ታገኛለች። በአካባቢው ማንም አልነበረም። ገንዘቡ ደግሞ በጣም ብዙ ነበር። እንዲያውም ላሪ የአገሪቱ ብሔራዊ የመገበያያ ገንዘብ ከሆነ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ናና ድፍን አንድ መቶ የላሪ ኖት (400 ብር ገደማ) አይታ አታውቅም። በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች በርከት ላሉ ዓመታት ከሠሩ በኋላም እንኳን ይህንን ያህል ገንዘብ አያገኙም።

ናና ‘እምነቴን፣ ለአምላክ ያለኝን ፍርሃትና መንፈሳዊነቴን ካጣሁ ይህ ገንዘብ ምን ያደርግልኛል?’ ስትል አሰበች። ለእምነትዋ ስትል ከባድ ስደትንና ድብደባን ጭምር በመቋቋም እነዚህን ክርስቲያናዊ ባሕርያት አዳብራለች።

ናና ወደ ፖሊስ ጣቢያው ስትሄድ አምስት የፖሊስ መኮንኖች በጭንቀት ተውጠው አንድ ነገር ሲፈልጉ ትመለከታለች። ገንዘቡን እየፈለጉ እንደሆነ ስለገባት ወደ እነሱ ቀረብ ብላ “የጠፋችሁ ነገር አለ?” ትላቸዋለች።

“አዎን፣ ገንዘብ ጠፍቶብናል” በማለት ይመልሱላታል።

“ምን ያህል ነው?”

“ሦስት መቶ ላሪ!”

ናና “ገንዘባችሁን አግኝቼዋለሁ” ትላቸዋለች። ከዚያም “ገንዘባችሁን የምመልሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” ስትል ትጠይቃቸዋለች። ለምን እንደዚያ እንዳደረገች አልገባቸውም።

ናና በመቀጠል “የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ ነው። የይሖዋ ምሥክር ባልሆን ኖሮ ገንዘባችሁን አልመልስም ነበር” ትላቸዋለች።

ገንዘቡ ጠፍቶበት የነበረው የፖሊስ አዛዥ ናና ላሳየችው ታማኝነት አመስጋኝነቱን ለመግለጽ 20 ላሪ (80 ብር ገደማ) ሰጣት።

ታሪኩ በካስፒ ግዛት በፍጥነት ተሰራጨ። በሚቀጥለው ቀን በፖሊስ ጣቢያው የምትሠራ የጽዳት ሠራተኛ ለናና እንዲህ አለቻት:- “የእናንተ ጽሑፍ ሁልጊዜ [ከአዣዡ] ቢሮ አይጠፋም። አሁን ደግሞ የበለጠ ሳያደንቀው አይቀርም።” እንዲያውም አንድ የፖሊስ መኮንን ‘ሰው ሁሉ የይሖዋ ምሥክር ቢሆን ኖሮ ወንጀለኛ አይኖርም ነበር’ በማለት ተናግሯል።