‘በነፃ ይቅር ተባባሉ’
‘በነፃ ይቅር ተባባሉ’
አምላክ ኃጢአትህን ይቅር እንዳለልህ ይሰማሃል? በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አብዛኞቹ ትልልቅ ሰዎች እንደዚያ ይሰማቸዋል። በሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ምርምር ተቋም የተደረገውን ጥናት በጽሑፍ ያሰፈሩት ዶክተር ሎርን ቱሴንት ጥያቄ ከቀረበላቸው ከ45 ዓመት እድሜ በላይ የሆኑ 1, 423 አሜሪካውያን መካከል 80 በመቶዎቹ አምላክ ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳለላቸው እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል ሌሎችን ይቅር እንደሚሉ የተናገሩት 57 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ አኃዛዊ መረጃ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ያስታውሰናል:- “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፣ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴዎስ 6:14, 15) አዎን፣ የአምላክን ይቅርታ ማግኘታችን በከፊል የተመካው ሌሎችን ይቅር በማለታችን ላይ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖችን እንደሚከተለው ሲል አሳስቧቸዋል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ [“በነፃ፣” NW ] ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13) እርግጥ ነው፣ እንዲህ ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰው አሳቢነት ወይም ደግነት የጎደለው አንድ ዓይነት ድርጊት ቢፈጽምብህ ያንን ሰው ይቅር ማለት ይከብድህ ይሆናል።
ያም ሆኖ ሌሎችን ይቅር ማለት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ዶክተር ዴቪድ አር ዊልያምስ የተባሉ አንድ የኅብረተሰብ አጥኚ የምርምራቸውን ውጤት አስመልክተው ሲናገሩ “ሌሎችን ይቅር በማለትና በመካከለኛ ዕድሜ በሚገኙትም ሆነ በእድሜ በገፉት አሜሪካውያን የአእምሮ ጤንነት መካከል ጠንካራ ተዛምዶ እንዳለ ተገንዝበናል” ብለዋል። ይህም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ከ3, 000 ዓመታት አካባቢ በፊት “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” በማለት ከሰጠው ምክር ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 14:30 አ.መ.ት ) የይቅር ባይነት መንፈስ ከአምላክ ጋርም ሆነ ከባልንጀሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ስለሚያደርግ አንዳችን ሌላውን ከልባችን በነፃ ይቅር እንድንል የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን።—ማቴዎስ 18:35