በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቁን አስተማሪ ምሰሉ

ታላቁን አስተማሪ ምሰሉ

ታላቁን አስተማሪ ምሰሉ

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

1, 2. (ሀ) ሁላችንም አስተማሪዎች ነን ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ማስተማርን በተመለከተ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ልዩ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል?

 አስተማሪ ነህ? በተወሰነ መጠን ሁላችንም አስተማሪዎች ነን። መንገድ ለጠፋበት ሰው አቅጣጫ ስትጠቁም፣ አንድን ሥራ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል ለአንድ ሠራተኛ ስታሳይ ወይም የጫማ ክር እንዴት እንደሚታሠር ለአንድ ትንሽ ልጅ ስታሳይ ማስተማርህ ነው። እንዲህ ባለ መንገድ ሰዎችን መርዳት በተወሰነ መጠን እርካታ ያስገኛል ቢባል አት​ስማማም?

2 ማስተማርን በተመለከተ እውነተኛ ክርስቲያኖች ልዩ የሆነ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ‘አሕዛብን እያስተማርን ደቀ መዛሙርት’ እንድናደርግ ተልእኮ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዚህም በላይ በጉባኤ ውስጥ የምናስተምርበት ጊዜ አለ። ብቃት ያላቸው ወንዶች ጉባኤውን ለመገንባት “እረኞችና አስተማሪዎች” ሆነው ያገለግላሉ። (ኤፌሶን 4:11-13) የጎለመሱ ሴቶች በዕለታዊ እንቅስቃሴያቸው ለወጣት ሴቶች ‘በጎ የሆነውን ነገር ያስተምራሉ።’ (ቲቶ 2:3-5) ሁላችንም የእምነት ባልደረቦቻችንን እንድናበረታታ ማሳሰቢያ የተሰጠን ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ሌሎችን በመገንባት ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:11) የአምላክ ቃል አስተማሪ መሆንና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙ መንፈሳዊ እሴቶችን ማካፈል ምንኛ ልዩ መብት ነው!

3. የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

3 ታዲያ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ የታላቁን አስተማሪ የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ነው። ሆኖም አንዳንዶች ‘ኢየሱስ ፍጹም ስለነበር እርሱን እንዴት መምሰል እንችላለን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ፍጹም አስተማሪዎች መሆን እንደማንችል የታወቀ ነው። ያለን ችሎታ ምንም ያህል ውስን ቢሆን ኢየሱስ በማስተማር ረገድ የተወልንን ምሳሌ ለመኮረጅ አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ጥረት ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን አራቱን የማስተማሪያ ዘዴዎች እንዴት ልንኮርጅ እንደምንችል እስቲ እንመልከት። ዘዴዎቹ ቀላል በሆነ መንገድ ማስተማር፣ ጥያቄዎችን ጥሩ አድርጎ መጠቀም፣ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብና ተስማሚ ምሳሌዎችን መናገር ናቸው።

ቀላል በሆነ መንገድ አስተምሩ

4, 5. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊገባ በሚችል መንገድ የተዘጋጀው ለምንድን ነው? (ለ) ቀላል በሆነ መንገድ ለማስተማር ስለ ቃላት ምርጫችን በጥንቃቄ ማሰባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 የአምላክ ቃል ያዘለው መሠረታዊ እውነት የተወሳሰበ አይደለም። ኢየሱስ ባቀረበው ጸሎት ላይ “አባት ሆይ፣ . . . ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:25) ይሖዋ ቅንና ትሑት ልብ ለነበራቸው ሰዎች ዓላማዎቹን ገልጦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:26-28) በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ እንዲዘጋጅ አድርጓል።

5 መጽሐፍ ቅዱስ ስታስተምር ወይም ፍላጎት ላሳየ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ቀላል በሆነ መንገድ ማስተማር የምትችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ከታላቁ አስተማሪ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ኢየሱስ፣ አብዛኞቹ አድማጮች “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” ስለነበሩ ትምህርቱ በደንብ እንዲገባቸው ለማድረግ ቀላል በሆኑ ቃላት ተጠቅሟል። (ሥራ 4:13) ስለዚህ ቀለል ባለ መንገድ ለማስተማር የሚያስችለው አንደኛው ብቃት ስለምንጠቀምባቸው ቃላት ማሰብ ነው። ሰዎች የአምላክ ቃል እውነት በደንብ ገብቷቸው እንዲቀበሉት ለማድረግ የተወሳሰቡ ቃላት ወይም ሐረጎች መጠቀም አይኖርብንም። እንዲህ ያለው ‘የረቀቀ ንግግር’ በተለይ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ወይም የመረዳት ችሎታቸው ውስን የሆኑትን ሰዎች ሊያሸማቅቅ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:1, 2 አ.መ.ት ) ከኢየሱስ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው በጥንቃቄ የተመረጡ በቀላሉ ሊገቡ የሚችሉ ቃላትን መጠቀም እውነትን በተሻለ መንገድ ለማስተላለፍ ያስችላል።

6. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን በአንድ ጊዜ በጣም ብዙ ነገሮችን እንዲያውቅ ለማድረግ ከመሞከር መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

6 በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማስተማር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ሊረዱት ከሚችሉት በላይ በአንድ ጊዜ በርካታ እውቀቶችን ከማዥጎድጎድ መቆጠብንም ያጠቃልላል። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱ አቅም ውስን እንደሆነ ስለሚያውቅ ያስብላቸው ነበር። (ዮሐንስ 16:12) እኛም የተማሪያችንን የአቅም ገደብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ለማብራራት መጣር አይኖርብንም። a ዋነኛው ዓላማችን የተወሰኑ ክፍሎችን መሸፈን እንደሆነ አድርገን በማሰብ ጥድፊያ በሞላበት መንገድ ማስተማርም አይኖርብንም። ከዚያ ይልቅ የጥናቱን ፍጥነት እንደ ተማሪው ፍላጎትና አቅም መሠረት ማድረጉ ጥበብ ይሆናል። ግባችን ተማሪው የክርስቶስ ደቀ መዝሙርና የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን መርዳት ነው። ስለዚህ ምንም ያህል ጊዜ ይፍጅ ፍላጎት ያሳየው ተማሪ የሚማረው ትምህርት ግልጽ ሆኖ እንዲገባው መርዳት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን እውነት ልቡን ሊነካውና እርምጃ እንዲወስድ ሊያነሳሳው ይችላል።​—⁠ሮሜ 12:2

7. በጉባኤ ውስጥ ንግግር በምናቀርብበት ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ ለማስተማር የትኞቹ ሐሳቦች ሊረዱን ይችላሉ?

7 በጉባኤ ውስጥ ንግግር በምናቀርብበት ጊዜ በተለይ ደግሞ በስብሰባው ላይ የተገኙ አዳዲስ ሰዎች ካሉ ንግግራችንን በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 14:9) በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ሦስት ሐሳቦችን እንመልከት። በመጀመሪያ፣ እንግዳ የሆኑ ቃላትን የምትጠቀም ከሆነ ግልጽ ለማድረግ ማብራሪያ መስጠት ይኖርብሃል። የአምላክን ቃል ስንማር በሌሎች ዘንድ የማይታወቁ በርካታ ቃላትን አውቀናል። “ታማኝና ልባም ባሪያ፣” “ሌሎች በጎች” እና “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚሉትን የመሳሰሉ አባባሎችን በምንጠቀምበት ጊዜ ቀለል ባሉ ሐረጎች በማብራራት ትርጉማቸውን ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ሁለተኛ፣ ቃላት አታብዛ። ብዙ ቃላት ተጠቅሞ አንድን ጉዳይ በሰፊው ለማብራራት መሞከር የአድማጮችን የመስማት ፍላጎት ሊያጠፋ ይችላል። አንድ ትምህርት ግልጽ እንዲሆን ከተፈለገ አስፈላጊ ያልሆኑ ቃላት ወይም ሐረጎች መወገድ ይኖርባቸዋል። ሦስተኛ፣ በተሰጠህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊካተት የማይችል ብዙ ትምህርት ለመሸፈን አትሞክር። ምርምር ስናደርግ ትኩረት የሚስቡ በርካታ ነጥቦችን ልናገኝ እንችላለን። ሆኖም ቀደም ሲል የቀረቡትን ነጥቦች የሚደግፉና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ማብራሪያ ሊሰጥባቸው የሚችሉ ሐሳቦችን ብቻ በመጠቀም ትምህርቱን በጥቂት ዋና ዋና ነጥቦች መከፋፈሉ የተሻለ ይሆናል።

በጥያቄዎች ጥሩ አድርጎ መጠቀም

8, 9. ለእያንዳንዱ የቤት ባለቤት የሚስማማ ጥያቄ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

8 ኢየሱስ ጥያቄዎችን ተጠቅሞ ደቀ መዛሙርቱ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ በማድረግ እንዲሁም የማሰብ ችሎታቸውን በመቀስቀስና በማሰልጠን ረገድ የተዋጣለት ሰው እንደነበር አስታውስ። ኢየሱስ በጥያቄዎች አማካኝነት የደቀ መዛሙርቱን ልብ መንካትና ለሥራ ማንቀሳቀስ ችሏል። (ማቴዎስ 16:13, 15፤ ዮሐንስ 11:26) እኛም እንደ ኢየሱስ በጥያቄዎች ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

9 ከቤት ወደ ቤት በምንሰብክበት ጊዜ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት በመቀስቀስ ስለ አምላክ መንግሥት ለመነጋገር የሚያስችል መንገድ ለመጥረግ በጥያቄዎች መጠቀም እንችላለን። የቤቱን ባለቤት የመስማት ፍላጎት ሊቀሰቅስ የሚችል ጥያቄ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጥሩ ተመልካች ሁን። ወደ አንድ ሰው ግቢ ስትገባ ዙሪያውን ተመልከት። በቤቱ ውስጥ ልጆች እንዳሉ የሚጠቁሙ የልጆች መጫወቻዎች ይታያሉ? ከሆነ እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ልጆችዎ አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑ ዓለም ምን ይመስል ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ?’ (መዝሙር 37:10, 11) ቤቱ በደንብ የታጠረና ብዙ መቀርቀሪያዎች ያሉት ነውን? እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘እንደ እኔና እንደርስዎ ያሉ ሰዎች ቤታችን ስንሆንም ሆነ በመንገድ ላይ ስንሄድ ምንም ዓይነት ስጋት ሳይሰማን መኖር የምንችልበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ?’ (ሚክያስ 4:3, 4) ቤት ውስጥ የታመመ ሰው እንዳለ የሚጠቁም ነገር ይኖር ይሆን? እንዲህ ልንል እንችላለን:- ‘ሁሉም ሰው የተሟላ ጤና አግኝቶ የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ (ኢሳይያስ 33:24) ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል። b

10. የተማሪውን የልብ ስሜትና አስተሳሰብ ‘ለመቅዳት’ በጥያቄዎች መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ሆኖም ምን ነገር መዘንጋት አይኖርብንም?

10 መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ በጥያቄዎች ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? እንደ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ማንበብ አንችልም። ይሁን እንጂ ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ጥያቄ በዘዴ ማቅረብ የተማሪውን ውስጣዊ ስሜትና አስተሳሰብ ‘ለመቅዳት’ ያስችላል። (ምሳሌ 20:5) ለምሳሌ ያህል፣ በእውቀት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን “አምላካዊ አኗኗር ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ እያጠናን ነው እንበል። ምዕራፉ አምላክ ስለ ማጭበርበር፣ ስለ ዝሙትና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ይናገራል። ተማሪው በመጽሐፉ ላይ ለሰፈሩት ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ መስጠት ይችል ይሆናል፤ ሆኖም የሚማረውን ትምህርት ይስማማበታል? እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ይሖዋ ለእነዚህ ጉዳዮች ያለው አመለካከት ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃል?’ ‘እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው?’ የተማሪውን ክብር መጠበቅ እንዳለብህ አስታውስ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪውን የሚያሳፍር ወይም ዝቅ የሚያደርጉ ጥያቄዎችን መጠየቅ አንፈልግም።​—⁠ምሳሌ 12:18

11. የሕዝብ ተናጋሪዎች በጥያቄዎች ጥሩ አድርገው መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?

11 የሕዝብ ተናጋሪዎችም በጥያቄዎች ጥሩ አድርገው መጠቀም ይችላሉ። መልስ የማይሰጥባቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ አድማጮች እንዲያስቡና እንዲመራመሩ ሊረዳ ይችላል። ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። (ማቴዎስ 11:7-9) በተጨማሪም አንድ ተናጋሪ የመግቢያ ሐሳብ ከተናገረ በኋላ በንግግሩ ውስጥ የሚሸፍናቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በጥያቄ መልክ ሊያቀርብ ይችላል። “ዛሬ በሚቀርበው ንግግር ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እንሞክራለን . . .” ብሎ መናገር ይችላል። ከዚያም በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ዋና ዋና ነጥቦችን ለመከለስ እነዚያን ጥያቄዎች እንደገና ጠቀስ ማድረግ ይችላል።

12. ሽማግሌዎች የእምነት ባልደረቦቻቸው ከአምላክ ቃል ማጽናኛ እንዲያገኙ ለመርዳት ጥያቄዎችን እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

12 ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእረኝነት ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ በጥያቄዎች በመጠቀም አንድ ‘የተጨነቀ ነፍስ’ ከይሖዋ ቃል ማጽናኛ እንዲያገኝ መርዳት ይችላሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሽማግሌ መዝሙር 34:​18ን ጠቅሶ መንፈሱ የተደቆሰን አንድ ሰው መርዳት ይፈልግ ይሆናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” መንፈሱ የተደቆሰበት ይህ ግለሰብ ጥቅሱ ለእርሱ በግሉ እንዴት እንደሚሠራ ለመርዳት ሽማግሌው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል:- “ይሖዋ ቅርብ ነው የተባለው ለእነማን ነው? አንተም አንዳንድ ጊዜ ‘ልብህና መንፈስህ እንደተሰበረ’ ሆኖ ይሰማሃል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ ለእነዚህ ዓይነት ሰዎች ቅርብ ከሆነ ለአንተም በተመሳሳይ ቅርብ ሊሆን አይችልም?” እንዲህ ያለው በርኅራኄ ላይ የተመሠረተ ማጽናኛ ልቡ የተሰበረበትን ሰው መንፈስ ሊያነቃቃ ይችላል።​—⁠ኢሳይያስ 57:15

አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ

13, 14. (ሀ) ላየው በማልችለው አምላክ አላምንም ብሎ ለሚናገር ሰው አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሁሉም ሰው ይቀበለናል ብለን መጠበቅ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

13 በአገልግሎታችን አሳማኝ ምክንያቶችን በማቅረብ የሰዎችን ልብ መንካት እንፈልጋለን። (ሥራ 19:8፤ 28:23, 24) ታዲያ እንዲህ ሲባል ሌሎች የአምላክን ቃል እውነት እንዲቀበሉ ለማድረግ የግድ ጥልቀት ያላቸውን ማስረጃዎች እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል መማር አለብን ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። አሳማኝ ምክንያቶች የተወሳሰቡ መሆን አያስፈልጋቸውም። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚያስገኙት ቀለል ባለ መንገድ የሚቀርቡ አሳማኝ ምክንያቶች ናቸው። አንድ ምሳሌ እንመልከት።

14 አንድ ሰው በማያየው አምላክ እንደማያምን ቢናገር ምን ብለን ልንመልስ እንችላለን? ምክንያትና ውጤት ተብሎ የሚታወቀውን ተፈጥሯዊ ሕግ መጠቀም እንችላለን። አንድን ውጤት ስንመለከት ለዚህ ነገር መከሰት አንድ ምክንያት መኖር እንዳለበት እንቀበላለን። እንዲህ ልንል እንችላለን:- ‘ወደ አንድ ሩቅ አካባቢ ብትሄድና በውስጡ የተትረፈረፈ ምግብ ያለበት አንድ የሚያምር ቤት (ውጤት) ብትመለከት ቤቱን የሠራውና (ምክንያት) ጓዳውን በምግብ የሞላው አንድ ሰው አለ ብለህ ለማመን አትገደድም? በተመሳሳይም በአካባቢያችን የሚገኙ ነገሮች የተሠሩበትን ንድፍና በምድር “ጓዳ” (ውጤት) ውስጥ የሚገኘውን ምግብ ስንመለከት እነዚህን ነገሮች አንድ አካል (ምክንያት) ወደ ሕልውና አምጥቷቸዋል ብለን ብናምን ምክንያታዊ አይሆንም?’ መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” በማለት ይህን ሐቅ በግልጽ አስቀምጦታል። (ዕብራውያን 3:4) የምናቀርበው ምክንያት ምንም ያህል አሳማኝ ቢሆን ሁሉም ሰው ይቀበለናል ማለት አይደለም። አማኝ የሚሆኑት “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎች ብቻ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።​—⁠ሥራ 13:48፤ 2 ተሰሎንቄ 3:2

15. የይሖዋን ባሕርያትና መንገዶች ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ምን ዓይነት የማሳመኛ ምክንያት መጠቀም እንችላለን? እንዲህ ያለውን የማሳመኛ ምክንያት እንዴት መጠቀም እንደምንችል የሚያሳዩት ሁለት ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

15 በመስክ አገልግሎትም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ስናስተምር የይሖዋን ባሕርያትና መንገዶች ጎላ አድርጎ ለማቅረብ አሳማኝ ምክንያቶችን መጠቀም እንችላለን። በተለይ ኢየሱስ አልፎ አልፎ ይጠቀምበት እንደነበረው “እንዴት አብልጦ” እንደሚለው ያሉ ምክንያታዊ አቀራረቦችን መጠቀምም ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (ሉቃስ 11:13፤ ሉቃስ 12:24) ሁለት ነገሮችን እያነጻጸሩ በዚህ መንገድ ማስረዳት ትምህርቱን በደንብ ለማስጨበጥ ይረዳል። ሲኦል እሳታማ ቦታ ነው የሚለው ትምህርት ስህተት መሆኑን ለማጋለጥ እንዲህ ልንል እንችላለን:- ‘የልጁን እጅ በእሳት እያቃጠለ ልጁን መቅጣት የሚፈልግ አፍቃሪ ወላጅ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ሰዎችን በሲኦል እሳት ይቀጣል ብሎ ማሰብ ምን ያህል የሚከብድ ነው!’ (ኤርምያስ 7:31) ይሖዋ ለእያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብ ለማስተማር እንዲህ ልንል እንችላለን:- ‘ይሖዋ በቢልዮን የሚቆጠሩትን ከዋክብት እያንዳንዳቸውን በስም የሚያውቃቸው ከሆነ ለእርሱ ፍቅር ያላቸውንና በልጁ ክቡር ደም የተገዙትን ሰዎችማ ምን ያህል ያስብላቸዋል!’ (ኢሳይያስ 40:26፤ ሥራ 20:28) በምናስተምረበት ጊዜ እንዲህ ያለውን አሳማኝ ምክንያት መጠቀማችን የሰዎችን ልብ ለመንካት ይረዳናል።

ተስማሚ ምሳሌዎች

16. ምሳሌዎች በማስተማሩ ሥራ ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው?

16 በጥሩ መንገድ የሚቀርቡ ምሳሌዎች ሰዎች ትምህርታችንን በጉጉት እንዲከታተሉ የሚያደርጉ ግሩም ዘዴዎች ናቸው። ስናስተምር ምሳሌዎችን መጠቀማችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ አስተማሪ “አንድን ነገር በምናባችን ለመሳል ሳንሞክር እንዲሁ ማሰብ በጣም አዳጋች ነው” በማለት ተናግረዋል። ምሳሌዎች በአእምሯችን ውስጥ ምስል እንድንስልና አዳዲስ አሳቦችን በተሻለ ሁኔታ እንድንቀስም ይረዱናል። ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ ኢየሱስን የሚያህል የለም። (ማርቆስ 4:33, 34) በዚህ የማስተማሪያ ዘዴ እንዴት መጠቀም እንደምንችል እንመልከት።

17. አንድ ምሳሌ ውጤት እንዲያስገኝ የትኞቹን አራት ነጥቦች ማሟላት አለበት?

17 አንድን ምሳሌ ጥሩ የሚያሰኘው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ለአድማጮቻችን የሚስማማ መሆን አለበት። አድማጮቻችን ከሚነገረው ጉዳይ ጋር ሊያገናዝቡት የሚችሉት መሆን አለበት። ኢየሱስ አብዛኞቹን ምሳሌዎቹን የተናገረው ከአድማጮቹ የዕለት ተዕለት ኑሮ በመነሳት እንደሆነ እናስታውሳለን። በሁለተኛ ደረጃ፣ አንድ ምሳሌ በተቻለ መጠን እየቀረበ ካለው ነጥብ ጋር የሚሄድ መሆን አለበት። የሚነገረው ምሳሌ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ከሆነ አድማጮቻችንን ከማደናገር በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። በሦስተኛ ደረጃ፣ አንድ ምሳሌ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ በመግባት የተንዛዛ መሆን የለበትም። ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ እየጠቀሰ የማያስፈልጉትን ይተው እንደነበረ አስታውስ። አራተኛ፣ በንግግራችን ውስጥ ምሳሌ የምንጠቀም ከሆነ ምሳሌውን ከነጥቡ ጋር ማዛመድ አለብን። እንደዚያ ካላደረግን አንዳንዶች ነጥቡን ሊስቱ ይችላሉ።

18. ተስማሚ ምሳሌዎችን እንዴት መጠቀም እንችላለን?

18 ተስማሚ ምሳሌዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ረዥምና የተንዛዙ ታሪኮችን መናገር እንዳለብን አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። አጫጭር ምሳሌዎች ይበልጥ ውጤታማ ናቸው። ማብራሪያ በሚሰጥበት ነጥብ ውስጥ የሚጠቀሱትን ምሳሌዎች ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ይቅር ባይ እንደሆነ የሚገልጽ ትምህርት ስናቀርብ ይሖዋ ኃጢአታችንን ‘እንደሚደመስስልን’ ወይም እንደሚጠርግልን የሚናገረውን በሐዋርያት ሥራ 3:​19 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በምሳሌ ማስረዳት ፈለግን እንበል። ‘መደምሰስ’ የሚለው ቃል ራሱ ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። ሆኖም ጉዳዩን በግልጽ ለማስረዳት ምን ተጨባጭ ምሳሌ መጠቀም እንችላለን? ላጲስን እንደ ምሳሌ ጠቅሰን እንዲህ ማለት እንችላለን:- ‘ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር በሚልበት ጊዜ ላጲስ ተጠቅሞ ሙልጭ አድርጎ የሚያጠፋው ያህል ነው።’ እንዲህ ባለ ቀላል ምሳሌ የሚቀርብ ሐሳብ ለመረዳት ፈጽሞ አያዳግትም።

19, 20. (ሀ) ጥሩ ምሳሌዎችን ከየት ማግኘት እንችላለን? (ለ) በጽሑፎቻችን ላይ ከወጡት ጥሩ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ከቀረቡት ምሳሌዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ። (በተጨማሪም ሣጥኑን ተመልከት።)

19 እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን ጨምሮ ተስማሚ ምሳሌዎችን ከየት ማግኘት ትችላለህ? ከራስህ ሕይወት ወይም የተለያየ አስተዳደግና ተሞክሮ ካላቸው የእምነት ባልደረቦችህ ማግኘት ትችላለህ። ሕይወት ያላቸውንና ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ወይም በአካባቢው የታወቀ በቅርቡ የተፈጸመ አንድ ክንውንን ጨምሮ ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት ይቻላል። ጥሩ ምሳሌዎችን ማግኘት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ንቁ በመሆን በአካባቢያችን የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን ልብ ብሎ ‘በመመልከት’ ነው። (ሥራ 17:22, 23) በሕዝብ ፊት ንግግር ማቅረብን በተመለከተ አንድ የማስተማሪያ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “የሰዎችን አኗኗርና ሥራቸውን በትኩረት የሚከታተል፣ የተለያዩ ሰዎችን የሚያነጋግር፣ ነገሮችን ቀረብ ብሎ የሚመረምር፣ እስኪገባው ድረስ ጥያቄዎችን የሚጠይቅ ተናጋሪ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ እንደ ምሳሌ አድርጎ ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ሐሳቦች ይሰበስባል።”

20 ውጤታማ የሆኑ ምሳሌዎችን ማግኘት የሚቻልበት ሌላም ምንጭ አለ። እነዚህም መጠበቂያ ግንብ፣ ንቁ! እና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁዋቸው ጽሑፎች ናቸው። እነዚህ ጽሑፎች ምሳሌዎችን እንዴት አድርገው እንደሚጠቀሙ በመመርመር ብቻ ብዙ ግንዛቤ ማግኘት ትችላለህ። c ለምሳሌ ያህል፣ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 17 አንቀጽ 11 ላይ የሚገኘውን ምሳሌ ተመልከት። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ባሕርያት ያላቸውን ሰዎች መንገድ ላይ አብረውህ ከሚሄዱት የተለያዩ መኪናዎች ጋር ያወዳድራቸዋል። ይህን ምሳሌ ጥሩ የሚያሰኘው ምንድን ነው? ምሳሌው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምናየው ነገር ላይ የተመሠረተ፣ ከሚብራራው ሐሳብ ጋር የሚዛመድ፣ ተግባራዊነቱም ግልጽ እንደሆነ ልብ በል። በምናስተምርበት ጊዜ በጽሑፍ ላይ የወጡትን ምሳሌዎች መጠቀም እንችላለን፤ ምናልባትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ወይም ለምናቀርበው ንግግር እንዲስማማ ለማድረግ ትንሽ ለወጥ አድርገን መጠቀም እንችላለን።

21. የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጎ ማስተማር ምን በረከቶችን ያስገኛል?

21 ጥሩ አስተማሪ መሆን ታላቅ በረከት ያስገኛል። በምናስተምርበት ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ያለንን እናካፍላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው’ ብሎ ስለሚናገር በዚህ መንገድ የምንሰጠው ስጦታ ደስታ ያስገኝልናል። (ሥራ 20:35) የአምላክ ቃል አስተማሪዎች በመሆን ስለ ይሖዋ የሚናገረውንና ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኘውን እውነት ለሰዎች ስንናገር እንዲህ ያለውን ደስታ እናገኛለን። ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን እየመሰልን እንዳለን ማወቃችንም ከፍተኛ እርካታ ይሰጠናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b ከገጽ 9-15 ላይ የሚገኘውን “ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ መግቢያዎች” የሚለውን ክፍል ተመልከት።​—⁠በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

c በጽሑፎቻችን ላይ የወጡትን ምሳሌዎች ፈልገህ ለማግኘት የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ 1986-2000 “Illustrations” የሚለውን ተመልከት።​—በይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ቋንቋዎች የታተመ።

ታስታውሳለህ?

• መጽሐፍ ቅዱስን በምናስጠናበትና በጉባኤ ውስጥ ንግግር በምናቀርብበት ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው?

• ከቤት ወደ ቤት በምንሰብክበት ጊዜ በጥያቄዎች ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

• የይሖዋን ባሕርያትና መንገዶች ጎላ አድርገን ለመግለጽ አሳማኝ ምክንያቶችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

• ተስማሚ ምሳሌዎችን ከየት ማግኘት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እነዚህን ምሳሌዎች ታስታውሳቸዋለህን?

ውጤታማ ከሆኑት ምሳሌዎች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል። ምሳሌዎቹ ትምህርቱን እንዴት እንዳጎሉ ለማየት ለምን ጽሑፎቹን አውጥተህ አትመለከትም?

 ከጅዋጅዌ ገመድ ላይ እየዘለሉ በአየር ላይ ትርዒት እንደሚያሳዩ ጥንድ ስፖርተኞች ሁሉ ጥሩ ትዳርም ተስማሚ ጓደኛ በማግኘት ላይ የተመካ ነው።​—⁠መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 15, 2001 ገጽ 16

 ስሜትን አውጥቶ መናገር ኳስ ከመወርወር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኳሱን ቀስ አድርጋችሁ አሊያም ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መንገድ በኃይል ልትወረውሩት ትችላላችሁ።​—⁠ንቁ! ጥር 2001 ገጽ 10

 ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን መማር አንድን አዲስ ቋንቋ ከመማር ጋር ይመሳሰላል።​—⁠መጠበቂያ ግንብ የካቲት 15, 1999 ገጽ 18, 22-23

 አንድ ሠዓሊ አንድ ውብ ሥዕል ለመሥራት ብሩሹን ብዙ ጊዜ በሥዕሉ ላይ ማሳረፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መልካም ስምም ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ በሚፈጸሙ ብዙ ድርጊቶች የሚገኝ ነው።​—⁠መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 1, 1999 ገጽ 32

 በወጥመድ ላይ የተቀመጠ የእንስሳት መደለያ ለአዳኞች የሚሰጠው አገልግሎት እንዳለ ሁሉ መናፍስታዊ ሥራም ለአጋንንት የሚፈይደው ነገር አለ። ዓላማው ሰለባውን መሳብ ነው።​—⁠ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ገጽ 111

 ኢየሱስ የአዳምን ዘሮች ለማዳን የወሰደው እርምጃ የአንድን ፋብሪካ ዕዳ በመክፈል ፋብሪካው እንደገና እንዲከፈት በማድረግ ለሠራተኞቹ እፎይታ ካመጣ አንድ በጎ አድራጊ ጋር ሊመሳሰል ይችላል።​—⁠መጠበቂያ ግንብ የካቲት 15, 1991 ገጽ 13

 የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች ጉዳት የደረሰበትን ድንቅ የሥነ ጥበብ ሥራ ውጤት ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ሁሉ ይሖዋም ጉድለቶቻችንን ሳይሆን በእኛ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ሊመለከትና አዳም ወዳጣው የፍጽምና ደረጃ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል።​—⁠መጠበቂያ ግንብ 4-111 ገጽ 4

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ናቸው

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች የእምነት ባልደረቦቻቸውን በአምላክ ቃል ለማጽናናት በጥያቄዎች መጠቀም ይችላሉ