በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!”

“አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!”

የሕይወት ታሪክ

“አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!”

ግላዲስ አለን እንደተናገረችው

‘ሕይወትሽን እንደገና ሀ ብለሽ የመጀመር አጋጣሚ ብታገኚ በአኗኗርሽ ላይ ምን ለውጥ ታደርጊ ነበር?’ የሚል ጥያቄ አንዳንድ ጊዜ ይቀርብልኛል። እውነቱን ለመናገር “አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!” ለምን እንደዚህ እንደምል ልንገራችሁ።

በ1929 የበጋ ወራት ገና የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ማቲው አለን አንድ አስገራሚ ሁኔታ ገጠመው። ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም! የተባለውን በወቅቱ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ቡክሌት አገኘ። ጥቂት ገጾችን በጉጉት ካነበበ በኋላ “እንደዚህ ያለ መጽሐፍ አንብቤ አላውቅም!” በማለት በደስታ ተናገረ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባባ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያዘጋጅዋቸውን ሌሎች ጽሑፎች አገኘ። ወዲያው ያነበበውን ለጎረቤቶቹ ማካፈል ጀመረ። ሆኖም በምንኖርበት የገጠር መንደር ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አልነበረም። አባባ ክርስቲያን ከሆኑ ሰዎች ጋር አዘውትሮ መቀራረብ አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘቡ በ1935 ቤተሰቡን ይዞ ጉባኤ ወዳለበት ኦሬንጅቪል ኦንታሪዮ ካናዳ ተዛወረ።

በዚያን ጊዜ ልጆች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙ አይበረታቱም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ትልልቆቹ ስብሰባውን እስኪጨርሱ ድረስ ውጪ እየተጫወቱ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። አባባ በዚህ አልተደሰተም። “ስብሰባዎቹ ለእኔ ጠቃሚ ከሆኑ ለልጆቼም ጠቃሚ መሆን አለባቸው” በማለት አሰበ። ስለዚህ ገና አዲስ ተሰብሳቢ ቢሆንም እንኳ ወንድሜ ቦብን፣ ኤላ እና ሩቢ የተባሉትን እህቶቼንና እኔን ከትላልቆቹ ጋር በስብሰባው ላይ እንድንገኝ ነገረንና አብረን መሰብሰብ ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ የሌሎች ምሥክሮችም ልጆች በስብሰባው ላይ መገኘት ጀመሩ። በስብሰባ ላይ መገኘትና ሐሳብ መስጠት የሕይወታችን ዋነኛ ክፍል ሆነ።

አባባ መጽሐፍ ቅዱስን ይወድድ ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አስደሳች አድርጎ በድራማ መልክ ያቀርብልን ነበር። በዚህ ዘዴ እስካሁን ድረስ የማይረሱኝን በጣም ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች በለጋ አእምሯችን ውስጥ ቀርጾብናል። ይሖዋ ለእርሱ ታዛዥ የሆኑትን እንደሚባርካቸው የሰጠን ትምህርት እስከ አሁን ድረስ የማስታውሰው ነው።

አባባ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን እምነታችንን እንዴት ማስረዳት እንደምንችልም አስተምሮናል። በጨዋታ መልክ እንለማመድ ነበር። አባባ “ስሞት ወደ ሰማይ እንደምሄድ አምናለሁ። እስቲ ሰማይ እንደማልሄድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አሳዩኝ” ይለናል። እኔና ሩቢ የአባባን ሐሳብ ውድቅ የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማውጫ ኮንኮርዳንስ ማገላበጥ እንጀምራለን። ያገኘናቸውን ጥቅሶች ካነበብንለት በኋላ “ጥሩ ሐሳብ ነው፣ ቢሆንም ገና አላሳመናችሁኝም” ይለናል። እንደገና ኮንኮርዳንሱን ይዘን ፍለጋችንን እንቀጥላለን። አብዛኛውን ጊዜ አባታችን በመልሳችን እስኪረካ ድረስ ይህ ለሰዓታት ይዘልቅ ነበር። በዚህም የተነሳ እኔና ሩቢ የምናምንባቸውን ትምህርቶች በማብራራትና ለእምነታችን መከላከያ በማቅረብ ረገድ የተካንን ለመሆን ችለናል።

የነበረብኝን የሰው ፍርሃት ማሸነፍ

ምንም እንኳን በቤትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ሥልጠና ያገኘሁ ብሆንም በጣም ፈታኝ ሆነው ያገኘኋቸው አንዳንድ ክርስቲያናዊ ዘርፎች እንደነበሩ አልክድም። እንደ ብዙዎቹ ወጣቶች እኔም ከሌሎች ሰዎች በተለይም ከክፍል ጓደኞቼ የተለየሁ ሆኜ መታየቱ ደስ አያሰኘኝም ነበር። በዚህ ረገድ እምነቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈተነው የማስታወቂያ ሰልፍ ብለን የምንጠራውን የአገልግሎት ዘርፍ ባከናወንበት ጊዜ ነበር።

ሰልፉ የሚካሄደው ወንድሞችና እህቶች የተለያዩ መልእክቶች የተጻፉባቸውን ሰሌዳዎች ተሸክመው በቡድን በከተማይቱ አውራ ጎዳናዎች ላይ ቀስ ብለው እንዲጓዙ በማድረግ ነበር። ሦስት ሺህ ወይም ከዚያ ብዙም የማይበልጥ ነዋሪ በነበረው ከተማችን ውስጥ ሁሉም ሰው እርስ በእርስ ይተዋወቅ ነበር። በአንድ የማስታወቂያ ሰልፍ ላይ “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” የሚል መልእክት የተጻፈበት ሰሌዳ ይዤ በሰልፉ መጨረሻ ላይ እጓዝ ነበር። እኔ በምማርበት ትምህርት ቤት የሚማሩ ጥቂት ልጆች አዩኝና ወዲያውኑ “እግዚአብሔር ንጉሣችንን ጠብቅ” የሚለውን የሀገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር እየዘመሩ ከኋላዬ ይከተሉኝ ጀመር። ይህን ሁኔታ መቋቋም የቻልኩት እንዴት ነበር? ይሖዋ በሰልፉ ለመቀጠል የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠኝ አጥብቄ በጸሎት ለመንኩት። በመጨረሻም ሰልፉ ሲጠናቀቅ የያዝኩትን ሰሌዳ አስረክቤ ወደ ቤቴ ለመሄድ በጥድፊያ ወደ መንግሥት አዳራሹ አቀናሁ። ይሁን እንጂ ሰልፉን ይመራ የነበረው ሰው ሌላ የማስታወቂያ ሰልፍ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆኑና አንድ ሰሌዳ የሚይዝላቸው ተጨማሪ ሰው እንደሚፈልጉ ነገረኝ። ስለዚህ ከበፊቱ አብልጬ እየጸለይኩ በድጋሚ በሰልፉ ተካፈልኩ። በዚህ ጊዜ ግን የክፍል ጓደኞቼ ደክሟቸው ወደየቤታቸው ተበታትነው ነበር። ስለዚህ ብርታት እንዲሰጠኝ መጸለዬን ትቼ ይሖዋን በጸሎት ማመስገን ጀመርኩ።​—⁠ምሳሌ 3:5

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሁልጊዜ ወደ ቤታችን ይመጡ ነበር። ደስተኞች ስለነበሩ እነርሱን ማስተናገድ የሚያስደስት ነበር። ወላጆቻችን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሁሉም የተሻለ ሙያ እንደሆነ ይነግሩን እንደነበር አስታውሳለሁ።

ለማበረታቻቸው ምላሽ በመስጠት በ1945 የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጀመርኩ። ቆየት ብሎም በለንደን ኦንታሪዮ አቅኚ ሆና ታገለግል ከነበረችው እህቴ ከኤላ ጋር አብረን ማገልገል ጀመርን። እዚያም ፈጽሞ ላደርገው እችላለሁ ብዬ አስቤ የማላውቀውን የአገልግሎት ዓይነት አሳዩኝ። ወንድሞች በአካባቢው ባሉ መጠጥ መሸጫ ቤቶች ውስጥ ከጠረጴዛ ወደ ጠረጴዛ እየተዘዋወሩ ለደንበኞች መጠበቂያ ግንብ እና መጽናናት (አሁን ንቁ! የተባለውን) መጽሔቶች ያበረክቱ ነበር። አገልግሎቱ የሚካሄደው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ስለነበር አብሬያቸው ለመሄድ የሚያስችለኝን ድፍረት ለማግኘት የምጸልይበት አንድ ሙሉ ሳምንት አግኝቼ ነበር። በዚህ አገልግሎት መካፈል ፈታኝ ቢሆንም በረከት የሚያስገኝ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞቻችን በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሚደርስባቸውን ስደት የሚያሳዩ የመጽናናት መጽሔት ልዩ እትሞችን ለትላልቅ ኩባንያ ፕሬዚዳንቶችና ታዋቂ ለሆኑ የካናዳ ነጋዴዎች ማበርከትን ተምሬያለሁ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ብርታት ለማግኘት በይሖዋ ላይ ከተደገፍን እርሱ ምንጊዜም ከጎናችን እንደሚቆም ተገንዝቤያለሁ። አባቴ ይል እንደነበረው ይሖዋ ለእርሱ ታዛዥ የሆኑትን ይባርካል።

በኩቤክ እንዳገለግል ለቀረበልኝ ጥሪ ምላሽ መስጠት

የይሖዋ ምሥክሮች በካናዳ የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ሐምሌ 4, 1940 ታግዶ ነበር። እገዳው ከጊዜ በኋላ የተነሳ ቢሆንም የሮማ ካቶሊኮች በሚበዙበት በኩቤክ አውራጃ ስደቱ አልቆመም ነበር። እዚያ በሚኖሩ ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል ለማሳወቅ ኃይለኛ መልእክት ያዘለውን ኩቤክ ለአምላክ፣ ለክርስቶስና ለነፃነት ያሳየችው ጥላቻ ለመላው ካናዳ የሚያሳፍር ነው (እንግሊዝኛ) የተባለ ትራክት ለማሰራጨት ልዩ ዘመቻ ተደርጎ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል አባል የነበረው ናታን ኤች ኖር በሞንትሪያል ከተማ በመቶዎች ከሚቆጠሩ አቅኚዎች ጋር ተሰበሰበና ሊደረግ ስለታቀደው ዘመቻ ማብራሪያ ሰጠ። ወንድም ኖር በዚህ ዘመቻ ላይ ከተሳተፍን ተይዘን ወኅኒ ልንወርድ እንደምንችል ነገረን። የደረሰውም ይኸው ነበር! በአጠቃላይ 15 ያህል ጊዜ ታስሬአለሁ። ወደ መስክ አገልግሎት ስንወጣ ሌሊቱን ወኅኒ ቤት እናድር ይሆናል በሚል የጥርስ ብሩሽና የፀጉር ማበጠሪያ እንይዝ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ብዙም ትኩረት ላለመሳብ ስንል ትራክቱን የምናሰራጨው በምሽት ነበር። ተጨማሪ ትራክቶችን የያዘ ቦርሳ አንገቴ ላይ አንጠለጥልና ካፖርቴ ሥር እከተዋለሁ። በትራክቶች የታጨቀው ይህ ቦርሳ ትልቅ በመሆኑ እርጉዝ ያስመስለኝ ነበር። ይህ በተጨናነቀ የከተማ ውስጥ ባቡር ተሳፍሬ ወደ አገልግሎት ክልሌ ስጓዝ ጠቅሞኛል። ከአንዴም ብዙ ጊዜ እርጉዝ የመሰልኳቸው ሰዎች ከተቀመጡበት እየተነሱ ቦታቸውን ይለቁልኝ ነበር።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትራክቱን በቀንም ማሰራጨት ጀመርን። ለሦስት ወይም ለአራት ቤቶች ትራክቱን ከሰጠን በኋላ ወደ ሌላ ክልል እንሄዳለን። ይህ ዘዴ አብዛኛውን ጊዜ ውጤታማ ሆኖልናል። ይሁን እንጂ አንድ የካቶሊክ ቄስ በዚያ አካባቢ እንዳለን ካወቀ ችግር ሊገጥመን እንደሚችል እናውቅ ነበር። አንድ ጊዜ አንድ ቄስ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ ትልልቅ ሰዎችንና ልጆችን አነሳስቶ ቲማቲምና እንቁላል እንዲወረውሩብን አደረገ። በአንዲት ክርስቲያን እህታችን ቤት ውስጥ ተጠለልንና ሌሊቱን እዚያው መሬት ላይ ተኝተን ለማሳለፍ ተገደድን።

በኩቤክ ለሚኖሩት ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ሊሰብኩ የሚችሉ አቅኚዎች በጣም ያስፈልጉ ስለነበር ታኅሣሥ 1958 እኔና እህቴ ሩቢ ፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር ጀመርን። ከዚያም በአውራጃው ውስጥ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች እንድናገለግል ተመደብን። በእያንዳንዱ አካባቢ የተለየ ሁኔታ ያጋጥመን ነበር። በአንድ አካባቢ ለሁለት ዓመት ያህል በየቀኑ ለስምንት ሰዓታት ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ብናገለግልም ሊያነጋግረን ፈቃደኛ የሆነ አንድም ሰው አላገኘንም! ሰዎቹ ወደ በሩ መጥተው ይመለከቱንና የበሩን መጋረጃ ከጋረዱ በኋላ ተመልሰው ይሄዳሉ። ቢሆንም ተስፋ አልቆረጥንም። በአሁኑ ወቅት በዚያ ከተማ ውስጥ ጥሩ እድገት እያደረጉ ያሉ ሁለት ጉባኤዎች አሉ።

ይሖዋ በሁሉም ነገር ደግፎናል

በ1965 ልዩ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል በተመደብንበት አንድ ቦታ በ1 ጢሞቴዎስ 6:​8 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት ፍሬ ሐሳብ ለመረዳት ችለን ነበር። ወጪዎቻችንን ለመሸፈን እንድንችል የተመደበልንን በጀት በቁጠባ መጠቀም ነበረብን። ስለዚህ ለቤት ማሞቂያ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለመብራትና ለምግብ የሚያስፈልገውን ከሸፈንን በኋላ በቀሪው ወር ውስጥ በእጃችን ላይ የሚቀረን 25 ሳንቲም ብቻ ነበር።

ገንዘባችን አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ማታ ማታ ቤታችን ውስጥ ማሞቂያ መለኮስ የምንችለው ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ነበር። ስለዚህ የመኝታ ክፍላችን ከ15 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት ኖሮት የማያውቅ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ከዚያ በላይ ይቀዘቅዝ ነበር። አንድ ቀን ሩቢ ከምታስጠናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የአንዷ ልጅ ሊጠይቀን መጣ። እቤቱ ከሄደ በኋላ ቤታችን በጣም ቀዝቃዛ እንደሆነ ለእናቱ ነግሯት መሆን አለበት ማሞቂያው ሁልጊዜ እንዲሠራ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን በየወሩ 10 ዶላር ትልክልን ጀመር። የጎደለብን ምንም ነገር እንዳለ ሆኖ አይሰማንም ነበር። ሃብታም ባንባልም ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች አላጣንም። ወጪዎቻችንን ሸፍነን የሚተርፈን ነገር ካለ ለእኛ እንደ ትልቅ ነገር ነው። በመዝሙር 37:​25 ላይ የሚገኙት “ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” የሚሉት ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!

ተቃውሞ ይደርስብን የነበረ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኋቸው በርካታ ሰዎች እውነትን ሲቀበሉ የመመልከት አስደሳች መብት አግኝቻለሁ። አንዳንዶቹ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሙያዬ ብለው የያዙት ሲሆን ይህም ልዩ ደስታ አምጥቶልኛል።

አዳዲስ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም

በ1970 በኮርንዎል ኦንታሪዮ እንድናገለግል ተመደብን። እዚያ ከሄድን ከአንድ ዓመት በኋላ እናታችን ታመመች። አባባ የሞተው በ1957 ስለነበር እኔና ሁለት እህቶቼ በ1972 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ እናታችንን በየተራ መንከባከብ ጀመርን። ልዩ አቅኚ ሆነው አብረውን ያገለግሉ የነበሩት ኤላ ሊዚቲሳ እና አን ኮአሌንኮ በዚህ ወቅት ከጎናችን ሆነው አበረታተውናል እንዲሁም ፍቅራዊ ድጋፋቸውን ሰጥተውናል። እኛ በማንኖርበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን በማስጠናትና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት ይረዱን ነበር። “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” የሚሉት የምሳሌ 18:24 ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!

በእርግጥም ሕይወት በፈተናዎች የተሞላ ነው። ይሖዋ በሚያደርግልኝ ፍቅራዊ እርዳታ እነዚህን ፈተናዎች መቋቋም ችያለሁ። አሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ በመካፈል ላይ እገኛለሁ። በ1993 የሞተው ቦብ ከባለቤቱ ከዶል ጋር ያገለገለባቸውን 10 ዓመታት ጨምሮ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት አቅኚ ሆኖ ሠርቷል። ጥቅምት 1998 ያረፈችው ታላቋ እህቴ ኤላ ደግሞ ከ30 ዓመታት በላይ አቅኚ ሆና ያገለገለች ሲሆን በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከፍተኛ የአቅኚነት መንፈስ አሳይታለች። በ1991 ሌላዋ እህቴ ሩቢ ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ተረጋገጠ። እንደዚያም ሆና ምሥራቹን ትሰብክ ነበር። መስከረም 26, 1999 ጠዋት እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ተጫዋች ነበረች። እህቶቼ ቢለዩኝም እኔም ተጫዋች ሆኜ እንድቀጥል የረዱኝን መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ያቀፈ ቤተሰብ አግኝቻለሁ።

ሕይወቴን መለስ ብዬ ስመለከት ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ የምለው ምንም ነገር የለም። ያላገባሁ ቢሆንም በሕይወታቸው ውስጥ እውነትን ያስቀደሙ አፍቃሪ ወላጆች፣ ወንድምና እህቶች በማግኘት ተባርኬያለሁ። ሁሉም በትንሳኤ ተነስተው ላያቸው እናፍቃለሁ። አባባ እቅፍ ሲያደርገኝ፣ ከእማማ ጋርም ስንተቃቀፍ እንባዋ በፊቷ ላይ ኩልል እያለ ሲወርድ፣ ኤላ፣ ሩቢና ቦብ የደስታ ሲቃ ይዟቸው ሲፈነድቁ በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል።

እስከዚያው ግን ጤንነቴና አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን ይሖዋን ማወደሴንና ማስከበሬን እቀጥላለሁ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግሩምና የሚክስ ሥራ ነው። ሁኔታው መዝሙራዊው በይሖዋ መንገድ የሚሄዱ ሰዎችን አስመልክቶ ‘ደስተኛ ትሆናለህ መልካምም ይሆንልሃል’ ብሎ እንደተናገረው ነው።​—⁠መዝሙር 128:1, 2

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባባ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ለእምነታችን እንዴት መከላከያ ማቅረብ እንደምንችል አስተምሮናል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ:- ሩቢ፣ እኔ፣ ቦብ፣ ኤላ፣ እማማና አባባ በ1947

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፊት ለፊት ከግራ ወደ ቀኝ:- 1998 በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ እኔ፣ ሩቢና ኤላ