“ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”
“ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”
“ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ . . . ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም።”—ማቴዎስ 13:34
1, 2. (ሀ) በጥሩ መንገድ የቀረቡ ምሳሌዎች በቀላሉ የማይረሱት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ዓይነት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል? ምሳሌዎችን ስለመጠቀሙ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ? (በተጨማሪም የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
ከብዙ ዓመታት በፊት ምናልባትም በሕዝብ ንግግር ላይ የሰማኸውን ምሳሌ አሁን ማስታወስ ትችላለህ? በጥሩ መንገድ የቀረቡ ምሳሌዎች ቶሎ አይረሱም። አንድ ደራሲ እንደተናገሩት ምሳሌዎች ሰዎች “የሚሰሙትን ነገር በዓይናቸው የሚያዩት ያህል ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ፤ አድማጮች የሚሰሙት ነገር በምናባቸው ቁልጭ ብሎ እንዲታያቸው የማድረግ ኃይል አላቸው።” የምንሰማውን ነገር በምናብ ማየት አንድን ትምህርት በደንብ ለመገንዘብ ስለሚረዳ ምሳሌዎች ትምህርቱ በቀላሉ እንዲገባን ያስችሉናል። ምሳሌዎች በቃላት ላይ ሕይወት ሊዘሩና አንድ ትምህርት በአእምሯችን ውስጥ ለዘለቄታው እንዲቀረጽ ሊያደርጉ ይችላሉ።
2 ምሳሌዎችን ግሩም አድርጎ በመጠቀም ረገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ያህል የተዋጣለት ሌላ አስተማሪ የለም። ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ በዛሬው ጊዜም በቀላሉ ማስታወስ ይቻላል። a ኢየሱስ በዚህ የማስተማሪያ ዘዴ አዘውትሮ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ምሳሌዎቹን ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረጋቸውስ ምንድን ነው?
ኢየሱስ በምሳሌዎች ያስተማረው ለምንድን ነው?
3. (ሀ) በማቴዎስ 13:34, 35 መሠረት ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ይህን የማስተማሪያ ዘዴ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በምሳሌዎች የተጠቀመበትን ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ይገልጽልናል። አንደኛው ምክንያት ትንቢት ለመፈጸም ነው። ሐዋርያው ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም:- በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም።” (ማቴዎስ 13:34, 35) እዚህ ላይ ማቴዎስ የጠቀሰው ‘ነቢይ’ መዝሙር 78:2ን ያቀናበረውን ሰው ነው። ይህ መዝሙራዊ የጻፈው ኢየሱስ ከመወለዱ ብዙ ሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ነው። ይሖዋ ልጁ በምሳሌዎች እንዲያስተምር ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አስቀድሞ መወሰኑ የሚያስገርም አይደለምን? ይሖዋ እንዲህ ያለውን የማስተማሪያ ዘዴ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም!
4. ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበትን ምክንያት የገለጸው እንዴት ነው?
4 ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው ምሳሌዎችን የተጠቀመው ልባቸው ደንዳና የሆኑ ሰዎችን ለመለየት ነው። ኢየሱስ ስለ ዘሪ የሚናገረውን ምሳሌ በፊቱ ለተሰበሰቡ “ብዙ ሰዎች” ከተናገረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” በማለት ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስም እንዲህ በማለት መለሰላቸው:- “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፣ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጀሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና።”—ማቴዎስ 13:2, 10, 11, 13-15፤ ኢሳይያስ 6:9, 10
5. የኢየሱስ ምሳሌዎች ትሑት ልብ የነበራቸውን አድማጮች ከኩሩዎቹ የለዩት እንዴት ነው?
5 የኢየሱስ ምሳሌዎች ሰዎችን ለመለየት ያገለገሉት እንዴት ነው? በአንዳንድ ወቅቶች አድማጮቹ እርሱ የተናገራቸውን ቃላት ትርጉም ለመረዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። ትሑት ልብ የነበራቸው ግለሰቦች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ጥያቄ እንዲጠይቁ ተገፋፍተዋል። (ማቴዎስ 13:36፤ ማርቆስ 4:34) በዚህም የተነሳ የኢየሱስ ምሳሌዎች እውነትን ለተጠሙ ሰዎች እውነትን ገልጠውላቸዋል። በተመሳሳይም ምሳሌዎቹ ልበ ኩሩ የሆኑ ሰዎች እውነትን እንዳያገኙ ሸሽገውባቸዋል። ኢየሱስ እንዴት ያለ ድንቅ አስተማሪ ነበር! እስቲ ምሳሌዎቹን ውጤታማ ያደረጓቸውን አንዳንድ ምክንያቶች እንመርምር።
አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ መጠቀም
6-8. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን የማግኘት አጋጣሚ አልነበራቸውም? (ለ) ኢየሱስ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ ይጠቅስ እንደነበር የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
6 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ሲናገር በቀጥታ ሲያዳምጡት ምን ተሰምቷቸው እንደነበር መገመት ትችላለህ? ኢየሱስ ሲናገር በአካል ተገኝተው የመስማት ልዩ መብት አግኝተው የነበረ ቢሆንም እንኳ እርሱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ዳግመኛ ማንበብ የሚችሉበት በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ አልነበራቸውም። ከዚያ ይልቅ የኢየሱስን ቃላት ሰምተው በልብና በአእምሯቸው መያዝ ነበረባቸው። ኢየሱስ ምሳሌ የመናገር ችሎታውን በመጠቀም እርሱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በቀላሉ ማስታወስ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እንዴት?
7 ኢየሱስ ምሳሌዎችን በሚናገርበት ጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ ይጠቅስ ነበር። አንድ ጉዳይ ለሚናገረው ታሪክ የሚያስፈልግ ወይም ነጥቡን ጎላ አድርጎ ለመግለጽ የሚረዳ ከሆነ በምሳሌው ውስጥ ያካትተው ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙ በጎች የነበሩት አንድ ሰው የጠፋበትን በግ ፍለጋ በሄደ ጊዜ ምን ያህል በጎችን ትቶ እንደሄደ፣ በወይን የእርሻ ቦታ ሠራተኞች ምን ያህል ሰዓት እንደሚሠሩ እንዲሁም ምን ያህል መክሊት በአደራ እንደተሰጠ ቁጥሩን በትክክል ተናግሯል።—ማቴዎስ 18:12-14፤ 20:1-16፤ 25:14-30
8 በተመሳሳይም ኢየሱስ የምሳሌዎቹን ትርጉም ሊያድበሰብሱ የሚችሉ አስፈላጊ ያልሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን አይጠቅስም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ ስላልነበረው ባሪያ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ይህ ባሪያ 60, 000, 000 ዲናሬ የሚያህል ዕዳ ውስጥ እንዴት ሊገባ እንደቻለ የሚጠቅስ ምንም ሐሳብ አልሰጠም። እዚህ ላይ ኢየሱስ ትኩረት የሰጠው ይቅር ባይ ስለመሆን ነው። አስፈላጊው ጉዳይ ባሪያው ዕዳ ውስጥ የገባበት ምክንያት ሳይሆን ዕዳው እንዴት እንደተሰረዘለትና እርሱ ግን አንድ ባልንጀራው የተበደረውን በጣም አነስተኛ ዕዳ እንዲከፍለው እንዴት እንዳስጨነቀው መግለጽ ነው። (ማቴዎስ 18:23-35) በተመሳሳይም ስለ አባካኙ ልጅ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ታናሹ ልጅ በድንገት ውርሱ እንዲሰጠው ለምን እንደጠየቀም ሆነ ለምን እንዳባከነው ምንም ማብራሪያ አልተሰጠም። ሆኖም ኢየሱስ ልጁ ተለውጦ ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ አባትዬው ምን እንደተሰማውና እንዴት አድርጎ እንደተቀበለው ዝርዝር ሐሳብ ሰጥቷል። የአባትየውን አቀባበል በተመለከተ የተሰጠው ዝርዝር ሐሳብ ኢየሱስ መናገር ለፈለገው ጉዳይ ማለትም ይሖዋ ‘ይቅርታው ብዙ እንደሆነ’ ለመግለጽ የግድ አስፈላጊ ነበር።—ኢሳይያስ 55:7፤ ሉቃስ 15:11-32
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ውስጥ ስለጠቀሳቸው ሰዎች በሚናገርበት ጊዜ ትኩረት ያደረገው በምን ላይ ነበር? (ለ) ኢየሱስ አድማጮቹም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ምሳሌዎቹን በቀላሉ ማስታወስ እንዲችሉ አድርጎ ያቀረበው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ ስለሚገኙት ባለ ታሪኮች በሚናገርበት ጊዜ ማስተዋል ተጠቅሟል። ስለ ባለ ታሪኮቹ መልክና ቁመና ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ይልቅ ትኩረት ያደረገው በጠቀሰው ታሪክ ውስጥ ምን እንዳደረጉ ወይም ምን ምላሽ እንደሰጡ ነበር። በዚህም የተነሳ የደጉ ሳምራዊ መልክ ምን ይመስል እንደነበር ሰፊ ሐተታ ከመስጠት ይልቅ ሳምራዊው ጉዳት ደርሶበት መንገድ ላይ የወደቀውን አይሁዳዊ በርኅራኄ እንዴት እንደረዳው በመግለጽ ከዚያ ይበልጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ገልጿል። ኢየሱስ የእኛ ዘር ወይም ጎሣ ለሆኑት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር የጎረቤት ፍቅር ማሳየት እንዳለብን ለማስተማር የሚጠቅሙ ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ ገልጿል።—ሉቃስ 10:29, 33-37
10 ኢየሱስ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ እየመረጠ መናገሩ ምሳሌዎቹ እጥር ምጥን ያሉና ያልተንዛዙ እንዲሆኑ አስችሎታል። በዚህ መንገድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አድማጮቹም ሆኑ ከዚያ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ስለ እርሱ የተጻፈውን ወንጌል የሚያነቡ ሰዎች ምሳሌዎቹንና የሚያስተላልፉትን ትምህርት በቀላሉ እንዲያስታውሱ ረድቷቸዋል።
ከተለመዱ ዕለታዊ ሕይወት የተወሰዱ ምሳሌዎች
11. የኢየሱስ ምሳሌዎች የልጅነት ሕይወቱን ባሳለፈበት በገሊላ ከተመለከታቸው ነገሮች የተወሰዱ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
11 ኢየሱስ ከሰዎች ሕይወት ጋር የተያያዙ ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት ነበር። ብዙዎቹ ምሳሌዎች የልጅነት ሕይወቱን ባሳለፈበት በገሊላ የተመለከታቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቁ ናቸው። እስቲ የልጅነት ሕይወቱን በጥቂቱ እንመልከት። እናቱ ዳቦ ጋግራ ከጨረሰች በኋላ ለሚቀጥለው ጊዜ ለእርሾ የሚሆናትን ጥቂት ሊጥ ስታስቀር ብዙ ጊዜ ተመልክቷል። (ማቴዎስ 13:33) ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን ጥርት ባለው የገሊላ ባሕር ላይ ሲጥሉ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። (ማቴዎስ 13:47) ልጆች በገበያ ቦታዎች ሲጫወቱ ማየት ለእርሱ የተለመደ ነገር ነበር። (ማቴዎስ 11:16) ኢየሱስ ዘር ለመዝራት ስለወጣው ሰው፣ ስለ አስደሳች የሠርግ ግብዣ፣ ለአጨዳ ስለደረሰ ሰብልና ሌሎች ምሳሌዎች የተናገረው በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከተመለከታቸው ነገሮች ተነስቶ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው።—ማቴዎስ 13:3-8፤ 25:1-12፤ ማርቆስ 4:26-29
12, 13. ኢየሱስ ስለ ስንዴውና እንክርዳድ የተናገረው ምሳሌ የአካባቢውን ሁኔታ ያውቅ እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች በብዙዎቹ የኢየሱስ ምሳሌዎች ውስጥ መጠቀሳቸው ምንም አያስደንቅም። ስለዚህ በዚህ የማስተማሪያ ዘዴ ጥሩ አድርጎ የመጠቀም ችሎታ እንደነበረው ለመገንዘብ እርሱ የተናገራቸው ቃላት ለአይሁድ አድማጮቹ ምን ትርጉም እንዳዘሉ መመርመሩ ይጠቅማል። ይህን ለማየት ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።
13 አንደኛ፣ ኢየሱስ ስለ ስንዴና እንክርዳድ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ አንድ ሰው በእርሻው ላይ ጥሩ ስንዴ እንደዘራና “ጠላቱ” ደግሞ በስንዴው መካከል እንክርዳድ እንደዘራ ገልጿል። ኢየሱስ ይህንን ዓይነቱን እኩይ ድርጊት ለመናገር የመረጠው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ምሳሌውን የተናገረው በገሊላ ባሕር አጠገብ እንደሆነና ከሁኔታዎቹም መረዳት እንደሚቻለው የገሊላ ሰዎች ዋነኛ መተዳደሪያቸው ግብርና እንደሆነ አስታውስ። አንድ ጠላት አንድን ገበሬ ለመጉዳት በድብቅ ወደ እርሻው መጥቶ እንክርዳድ ከመዝራት የበለጠ ምን ሊያደርግ ይችላል? በዘመኑ ከነበረው ሕግ መገንዘብ እንደሚቻለው በዚያን ጊዜ እንዲህ ያለ ጥቃት ይሰነዘር ነበር። ኢየሱስ አድማጮቹ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያውቁትን ሁኔታ ይጠቀም እንደነበር ይህ በግልጽ አያሳይምን?—ማቴዎስ 13:1, 2, 24-30
14. ስለ ደጉ ሳምራዊ በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ኢየሱስ መልእክቱን በግልጽ ለማስተላለፍ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መምረጡ ትርጉም ያለው የሚያደርገው ምንድን ነው?
14 ሁለተኛ፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ምሳሌውን መናገር ጀመረ:- “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።” (ሉቃስ 10:30) ኢየሱስ መልእክቱን ለማስጨበጥ በምሳሌው ውስጥ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መጠቀም የፈለገው ሆን ብሎ ነው። ይህን ምሳሌ የተናገረው ከኢየሩሳሌም እጅግም በማትርቀው በይሁዳ ሆኖ ነው። ስለዚህም አድማጮቹ መንገዱን ጥሩ አድርገው የሚያውቁት መሆን አለበት። ይህ መንገድ በተለይ ለብቻው ለሚጓዝ ሰው በጣም አደገኛ ነው። መንገዱ ጠመዝማዛ በመሆኑ አድብተው ለሚዘርፉ ወንበዴዎች የተመቻቸ ነበር።
15. ስለ ደጉ ሳምራዊ ከሚናገረው ምሳሌ ውስጥ ካህኑና ሌዋዊው ላሳዩት ግዴለሽነት ማስተባበያ ማቅረብ የማይቻለው ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ” ብሎ መናገሩ ሌላም ትኩረት የሚስብ ነገር አለው። በታሪኩ መሠረት በመጀመሪያ አንድ ካህን ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ያለፉ ሲሆን አንዳቸውም ቢሆኑ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የእርዳታ እጃቸውን አልዘረጉም። (ሉቃስ 10:31, 32) ካህናት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሲሆን ሌዋውያን ደግሞ በሥራ ያግዟቸው ነበር። በኢያሪኮና በኢየሩሳሌም መካከል ያለው ርቀት 23 ኪሎ ሜትር ብቻ በመሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሥራ በማይኖራቸው ጊዜ ኢያሪኮ ይቀመጡ ነበር። በዚህም የተነሳ በዚያ መንገድ ላይ ካህን ወይም ሌዋዊ ሲያልፍ ማየት የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ካህኑም ሆነ ሌዋዊው የተነሱት ‘ከኢየሩሳሌም’ እንደሆነ ልብ በል። ስለሆነም ከቤተ መቅደሱ እየተመለሱ ነበር። b በመሆኑም ‘ጉዳት የደረሰበትን ሰው ሳይረዱት የቀሩት የሞተ መስሏቸው ነው፤ ሬሳ መንካት ደግሞ ስለሚያረክስ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሰጡትን አገልግሎት ለጊዜውም ቢሆን ያስተጓጉልባቸው ነበር’ በማለት እነዚህ ሰዎች ላሳዩት ግዴለሽነት ማንም ማስተባበያ ማቅረብ አይችልም። (ዘሌዋውያን 21:1, 2፤ ዘኍልቍ 19:11, 16) ኢየሱስ ምሳሌውን የሚናገረው አድማጮቹ ከሚያውቁት ነገር ተነስቶ እንደነበር ይህ በግልጽ አያሳይምን?
ከተፈጥሮ የተወሰዱ ምሳሌዎች
16. ኢየሱስ ስለ ፍጥረት ከፍተኛ እውቀት ያለው መሆኑ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?
16 ኢየሱስ የተናገራቸው በርካታ ምሳሌዎች ስለ ተክሎች፣ ስለ እንስሳትና ስለ አየር ንብረት በቂ ግንዛቤ እንደነበረው ያሳያሉ። (ማቴዎስ 6:26, 28-30፤ 16:2, 3) ይህን ሁሉ ያወቀው ከየት ነው? ያደገው በገሊላ እንደመሆኑ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ለመመልከት ሰፊ አጋጣሚ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” ሲሆን ይሖዋም ሁሉን ሲፈጥር እንደ “ዋና ሠራተኛ” አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ቆላስይስ 1:15, 16፤ ምሳሌ 8:30, 31) ኢየሱስ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች በቂ እውቀት ቢኖረው ሊያስገርመን አይገባም! በሚያስተምርበት ጊዜ ይህን እውቀቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት አድርጎ እንደተጠቀመበት እንመልከት።
17, 18. (ሀ) ዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ቃላት ኢየሱስ የበጎችን ጠባይ ያውቅ እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን የጎበኙ ሰዎች በእረኞችና በበጎቻቸው መካከል ስላለው ቅርርብ ምን ነገር ተመልክተዋል?
17 ኢየሱስ ከተናገራቸው ሞቅ ያለ የፍቅር ስሜት ከተንጸባረቀባቸው ምሳሌዎች መካከል አንዱ በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሲሆን እዚያም ላይ በእርሱና በተከታዮቹ መካከል ያለውን የቅርብ ዝምድና አንድ እረኛ ከበጎቹ ጋር ካለው ቅርርብ ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ስለ በጎች ባሕርይ ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር ያሳያሉ። በጎች ለጥበቃ የማያስቸግሩ እንደሆኑና እረኛቸውን በታማኝነት እንደሚከተሉ አመልክቷል። (ዮሐንስ 10:2-4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን የጎበኙ ሰዎች በእረኞችና በበጎች መካከል ልዩ የሆነ ቅርርብ እንዳለ ተመልክተዋል። የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ ኤች ቢ ትሪስትራም እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “አንድ ጊዜ አንድ እረኛ ከመንጎቹ ጋር ሲጫወት አይቻለሁ። እርሱ ትቷቸው የሚሄድ መስሎ ሲሮጥ በጎቹ ተከትለውት ይሮጡና መሃል ያስገቡታል። . . . በመጨረሻም በጎቹ ዙሪያውን ይከብቡትና ይቦርቁበታል።”
18 በጎች እረኛቸውን የሚከተሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንደተናገረው ‘ድምፁን ስለሚያውቁ ነው።’ (ዮሐንስ 10:4) በእርግጥ በጎች የእረኛቸውን ድምፅ ለይተው ያውቃሉ? ጆርጅ ኤ ስሚዝ በዓይናቸው የተመለከቱትን ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት አስፍረዋል:- “አንዳንድ ጊዜ የምሳ ሰዓት እረፍታችንን በይሁዳ ከሚገኙት የውኃ ጉድጓዶች መካከል አንደኛው አጠገብ ቁጭ ብለን እናሳልፋለን። በዚህ ወቅት ሦስት ወይም አራት እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ወደዚያ ይመጣሉ። በጎቹ ወደ ውኃው ጉድጓድ ሲቃረቡ ይደባለቃሉ። እረኞች የየራሳቸውን በግ እንዴት አድርገው መለየት ይችላሉ ብለን አሰብን። በጎቹ ውኃ ከጠጡና ወዲያ ወዲህ እያሉ ከቦረቁ በኋላ እረኞቹ ተራ በተራ ወደተለያዩ አቅጣጫ ይሄዱና ሁሉም ለበጎቻቸው የተለየ የጥሪ ድምፅ ያሰማሉ። በጎቹም ከመንጋው እየተለዩ ወደ እረኞቻቸው ይሰበሰቡና እንዳመጣጣቸው ተመልሰው ይሄዳሉ።” ኢየሱስ ነጥቡን ለማስረዳት ከዚህ የተሻለ ምን ሌላ ምሳሌ ሊያገኝ ይችላል? እኛም ትምህርቶቹን ለይተን የምናውቅና ትእዛዛቱን እንዲሁም አመራሩን የምንከተል ከሆነ ‘የመልካሙን እረኛ’ ፍቅራዊ እንክብካቤ እናገኛለን።—ዮሐንስ 10:11
አድማጮች ከሚያውቋቸው ክስተቶች የተወሰዱ
19. የሃሰት አመለካከትን ውድቅ ለማድረግ ኢየሱስ በአካባቢው የደረሰን አደጋ እንዴት አድርጎ ተጠቀመበት?
19 ተሞክሮዎችን ወይም ታሪኮችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ አንድን ነጥብ ጥሩ አድርጎ ማስተማር ይቻላል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ አደጋ የሚደርሰው በክፉ ሰዎች ላይ ነው የሚለው አመለካከት ስህተት መሆኑን ለማስረዳት በጊዜው የደረሰ አንድ ክስተት ምሳሌ አድርጎ ጠቅሷል። “በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን?” በማለት ተናገረ። (ሉቃስ 13:4) ኢየሱስ ዕድል ተወስኗል የሚለው እምነት የተሳሳተ መሆኑን ጥሩ አድርጎ አስረድቷል። እነዚህ 18 ነፍሳት የሞቱት በሠሩት ኃጢአት ምክንያት የአምላክ ቁጣ ወርዶባቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ አደጋው ሊደርስባቸው የቻለው ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ በፈጠረው ሁኔታ ነው። (መክብብ 9:11) ኢየሱስ በአድማጮቹ ዘንድ በደንብ የሚታወቅ አንድ ክስተት በመጥቀስ የሃሰት ትምህርትን ለማፍረስ ችሏል።
20, 21. (ሀ) ፈሪሳውያን የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት የኮነኑት ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ስለ ሰንበት ያወጣው ሕግ በማያፈናፍን መንገድ እንዲሠራበት እንደማይፈልግ ለማስረዳት ኢየሱስ በየትኛው በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በሚገኝ ታሪክ ተጠቀመ? (ሐ) በሚቀጥለው ርዕስ የሚብራራው ምንድን ነው?
20 ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተመዘገቡ ታሪኮችን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀም ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በሰንበት ቀን እሸት ቀጥፈው በመብላታቸው ምክንያት ፈሪሳውያን የሰነዘሩትን ወቀሳ አስታውስ። እንደ እውነቱ ከሆነ ደቀ መዛሙርቱ የተላለፉት የአምላክን ሕግ ሳይሆን ፈሪሳውያን በሰንበት ቀን እንዳይሠሩ የተከለከሉ የሥራ ዓይነቶች ናቸው ብለው ለሕጉ የሰጡትን የማያፈናፍን ትርጓሜ ነው። አምላክ ስለ ሰንበት ያወጣው ሕግ እንዲህ ባለ መንገድ በሥራ ላይ እንዲውል ግትር አቋም እንደሌለው ለማመልከት ኢየሱስ በ1 ሳሙኤል 21:3-6 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አንድ ታሪክ ገለጸ። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ተርበው ሳለ ወደ ማደሪያው ድንኳን ሄዱና በሌላ ተተክቶ ከቦታው የተነሳውን የገጹን ኅብስት በሉ። በሌላ የተተካው ኅብስት ካህናቱ እንዲበሉት ይቀመጣል። ሆኖም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ከነበሩበት ሁኔታ አንፃር ኅብስቱን መብላታቸው አላስወገዛቸውም። ጊዜ ያለፈባቸውን ኅብስት ካህን ያልሆኑ ሰዎች እንደበሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ኢየሱስ በየትኛው ታሪክ መጠቀም እንዳለበት በትክክል አውቋል። የአይሁድ አድማጮቹም ታሪኩን በሚገባ እንደሚያውቁት ግልጽ ነው።—ማቴዎስ 12:1-8
21 በእርግጥም ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ነው! ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸውን እውነቶች አድማጮቹ ሊገባቸው በሚችል መንገድ የማስተላለፍ አቻ የማይገኝለትን ችሎታውን እናደንቃለን። ታዲያ እኛም በምናስተምርበት ጊዜ የእርሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ አንድን ነጥብ በግልጽ ለማስረዳት ምሳሌዎችንና ንጽጽሮችን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀም ነበር። ኢየሱስ አጫጭር ታሪኮች እየጠቀሰ የማስተማር ልማድ የነበረው ሲሆን እነዚህ ታሪኮች በአብዛኛው ‘ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ ትምህርት የሚገኝባቸው ልብ ወለድ ትረካዎች’ ናቸው።
b ኢየሩሳሌም ከኢያሪኮ ይልቅ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ትገኝ ነበር። ስለዚህ በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጸው አንድ ሰው “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” ጉዞ ሲያደርግ “ወረደ” ተብሎ መነገሩ ምክንያታዊ ነው።
ታስታውሳለህን?
• ኢየሱስ በምሳሌ ያስተማረው ለምንድን ነው?
• ኢየሱስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አድማጮቹ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያውቁትን ጉዳይ ምሳሌ አድርጎ እንደተጠቀመ የሚያሳየው ምንድን ነው?
• ኢየሱስ ስለ ፍጥረት የነበረውን እውቀት ውጤታማ ምሳሌዎችን ለመናገር የተጠቀመበት እንዴት ነው?
• ኢየሱስ አድማጮቹ የሚያውቋቸውን ክንውኖች በምን መንገዶች ተጠቅሞባቸዋል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ጥቂት ዲናር ዕዳ ያለበትን ባሪያ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ሳይሆን ስለ ቀረ ባሪያና ጠቅላላ ድርሻውን ወስዶ ከቤት የኮበለለውን አባካኝ ልጅ ይቅር ስላለ አንድ አባት ተናገረ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ የተናገረው ምን ለማስረዳት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእርግጥ በጎች የእረኛቸውን ድምፅ ለይተው ያውቃሉ?