በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጎረቤቶቻችንን ሁሉ ምን ዋጣቸው?

ጎረቤቶቻችንን ሁሉ ምን ዋጣቸው?

ጎረቤቶቻችንን ሁሉ ምን ዋጣቸው?

“ዘመናዊው ኅብረተሰብ ጉርብትና የሚባል ነገር አያውቅም።”—የ19ኛው መቶ ዘመን የእንግሊዝ መሪ የነበሩት ቤንጃሚን ዲዝሬሊ

ዕድሜ የገፉ ኩባውያን እርስ በእርስ የመደጋገፍን ባሕል የሚያዳብር ማኅበር አላቸው፤ ይህን የጎረቤታሞች ሕብረት የአያቶች ማኅበር ብለው ይጠሩታል። በ1997 የተዘጋጀ አንድ ዘገባ እንደሚያሳየው በዕድሜ ከገፉ 5 ኩባውያን መካከል አንዱ በእነዚህ ማኅበራት ውስጥ የታቀፈ ነው፤ በማኅበሩ ውስጥ ወዳጅነት፣ ማበረታቻና ጤናማ የሆነ አኗኗር እንዲከተሉ የሚረዳ ተግባራዊ እገዛ ያገኛሉ። ዎርልድ ሄልዝ የተሰኘው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “እነዚህ የአያቶች ማኅበራት በአካባቢው ያሉ የቤተሰብ ሐኪሞች የክትባት ዘመቻ በሚያካሂዱበት ጊዜ በፈቃደኝነት እገዛ ያደርጋሉ።”

የሚያሳዝነው ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች ለጎረቤት አሳቢነት ማሳየት እየቀረ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አውሮፓ በአንድ አፓርታማ ላይ ይኖር የነበረው ቮልፍጋንግ ዲርክስ የተባለ ሰው የደረሰበትን አሳዛኝ ሁኔታ ተመልከት። ዘ ካንቤራ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደዘገበው ቮልፍጋንግ በሚኖርበት አፓርታማ ላይ የሚኖሩት 17 ቤተሰቦች ቮልፍጋንግን ካዩት ረዘም ያለ ጊዜ ቢያልፍም ምን ሆኖ እንደጠፋ ለማወቅ “በሩን ያንኳኳ አንድም ሰው አልነበረም።” በመጨረሻም አከራዩ ወደ አፓርታማው ሲመጣ “ቴሌቪዥኑ ፊት ለፊት የተቀመጠ የሰው አጽም አገኘ።” አፅሙ ጭን ላይ የታኅሣሥ 5, 1993 የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተቀምጦ ነበር። ቮልፍጋንግ ከሞተ አምስት ዓመታት አልፈው ነበር። በጎረቤታሞች መካከል መተሳሰብ መጥፋቱን የሚያሳይ እንዴት ያለ አሳዛኝ ታሪክ ነው! ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ሜጋዚን ላይ አንድ ጸሐፊ እንደ ሌሎቹ ብዙ ማኅበረሰቦች ሁሉ እሳቸው የሚኖሩበት አካባቢም “እርስ በእርስ በማይተዋወቁ ሰዎች የተሞላ መንደር” እንደሆነ መጻፋቸው አያስገርምም። አንተ በምትኖርበት አካባቢም ሁኔታው እንደዚህ ነውን?

እርግጥ ነው በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች አሁንም ቢሆን እውነተኛ ጉርብትና አልጠፋም፤ አንዳንድ የከተማ ሰዎችም ለጎረቤቶቻቸው የበለጠ አሳቢነት ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ። ያም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የከተማ ነዋሪዎች ከጎረቤቶቻቸው የተገለሉና ለጥቃት የተጋለጡ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለማይተዋወቁ ተገልለው ይኖራሉ። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

ተራርቆ ከመኖር ተለይቶ የማይታይ ጉርብትና

እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን በአቅራቢያችን የሚኖሩ ጎረቤቶች አሉን። የቴሌቪዥናቸውን ብርሃን እንመለከታለን። በመስኮት በኩል የሰው ጥላ ውልብ ሲል ወይም መብራት ሲበራና ሲጠፋ እናያለን። መኪኖች ሲገቡና ሲወጡ፣ በመተላለፊያዎች ላይ ሰዎች ወዲያ ወዲህ ሲመላለሱ፣ በር ሲከፈትና ሲዘጋ እንሰማለን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች በአቅራቢያችን “የሚኖሩ” ሰዎች እንዳሉ ይጠቁሙናል። ይሁን እንጂ በአንድ አካባቢ ያሉ ጎረቤታሞች እርስ በርስ ሳይተዋወቁ አንዳቸው ከሌላው ተገልለው ሲኖሩ ወይም በውጥረት በተሞላ ሕይወት ተውጠው የራሳቸው ሕይወት ላይ ብቻ ሲያተኩሩ ጉርብትና የሚባለው ነገር ይጠፋል። ሰዎች ከጎረቤቶቻቸው ጋር የመቀራረቡ ወይም ጎረቤቶቻቸውን የመርዳቱ አስፈላጊነት አይታያቸው ይሆናል። ሄራልድ ሰን የተሰኘው የአውስትራሊያ ጋዜጣ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች ከቅርብ ጎረቤቶቻቸው ጋር እምብዛም የማይተዋወቁና ለማኅበራዊ ግዴታዎች የማይገዙ ሆነዋል። በማኅበራዊ ግንኙነቶች የማይካፈሉ ሰዎችን ማግለል ቀላል እየሆነ ነው።”

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ ምንም አያስደንቅም። ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” በሆኑበት ዓለም ውስጥ ብዙዎች የሚከተሉት የራስ ወዳድነት አኗኗር የሚያስከትለው ውጤት እየታየ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2) ብዙዎች ብቸኛ እንዲሆኑና ከሌሎች ተገልለው እንዲኖሩ አድርጓል። ራስን ማግለል፣ በተለይ ዓመፅና ወንጀል በተስፋፋበት አካባቢ አለመተማመንን የሚያስከትል ሲሆን ይህ ደግሞ ሰብዓዊ ርኅራኄ እንዳይኖር ያደርጋል።

አንተ በምትኖርበት አካባቢ ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ጥሩ ጎረቤቶች ለማኅበረሰቡ ውድ ሀብት ናቸው ቢባል እንደምትስማማ አያጠራጥርም። ሰዎች ለጋራ ግብ በቅንጅት ሲሠሩ ብዙ ማከናወን ይቻላል። ጥሩ ጎረቤቶች በረከትም ሊሆኑ ይችላሉ። የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ያብራራል።