ጥሩ ጎረቤቶች ውድ ሀብት ናቸው
ጥሩ ጎረቤቶች ውድ ሀብት ናቸው
“ሩቅ ካለ ወንድም ቅርብ ያለ ጎረቤት ይሻላል።”—ምሳሌ 27:10 አ.መ.ት
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረ አንድ ምሁር “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። በምላሹም ኢየሱስ ባልንጀራው ማን እንደሆነ ሳይሆን እውነተኛ ባልንጀራ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ነገረው። ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ አንተም ሳታውቀው አትቀርም። ታሪኩ በሉቃስ ወንጌል ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን በብዙዎች ዘንድ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ በመባል ይታወቃል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ታሪኩን ተናገረ:-
“አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ፤ አይቶትም አዘነለት፣ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፣ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና:- ጠብቀው፣ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?”—ሉቃስ 10:29-36
ሉቃስ 10:37) እውነተኛ ባልንጀራ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ የሚያሳይ እንዴት ያለ ውጤታማ ምሳሌ ነው! የኢየሱስ ምሳሌ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን እንድንጠይቅም ሊያነሳሳን ይችላል:- ‘እኔ ምን ዓይነት ጎረቤት ነኝ? የዘር ወይም የብሔር ልዩነት በጉርብትናዬ ላይ ተጽዕኖ ያደርግብኛልን? እንዲህ ያሉ ነገሮች ችግር ላይ ወድቆ የማየውን ማንኛውንም ሰው የመርዳት ግዴታዬን እንዳልወጣ እንቅፋት ይሆኑብኛልን? ጥሩ ጎረቤት ለመሆን የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁን?’
ምሁሩ የምሳሌው ፍሬ ነገር እንደገባው ግልጽ ነው። ምንም ሳያመነታ፣ ለተጎዳው ሰው ባልንጀራ የሆነው “ምሕረት ያደረገለት” ሰው እንደሆነ በትክክል ተናግሯል። ኢየሱስም “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” አለው። (ቀዳሚው እርምጃ
በዚህ ረገድ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባን ከተሰማን በቅድሚያ ልንወስደው የሚገባው እርምጃ አመለካከታችንን መለወጥ ይሆናል። በዋነኛነት ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ጥሩ ጎረቤት መሆናችን ነው። ይህ እኛም ጥሩ ጎረቤቶች እንዲኖሩን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ልንከተለው የሚገባንን ይህን አስፈላጊ መሠረታዊ መመሪያ ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጾታል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:12) ሌሎችን በአክብሮትና በደግነት ስንይዛቸው እነሱም እንዲሁ ለማድረግ ይነሳሳሉ።
ሊዛ ፈንደርበርግ የተባሉ ጋዜጠኛና ጸሐፊ ዘ ኔሽን ሲንስ 1865 በተባለው መጽሔት ላይ በወጣ “ጎረቤትህን መውደድ” በሚል ርዕስ ሥር መልካም ጉርብትናን ለማዳበር የሚረዱ አንዳንድ ቀላል ነገሮች ጠቅሰዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ጎረቤታሞች አንዳቸው ለሌላው . . . ልጆችን እንደ መጠበቅ እና ከሱቅ ዕቃ እንደ መግዛት ያሉ ቀላል ውለታዎችን በመዋል እርስ በርስ ሊቀራረቡ ይገባል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራራቀ በሚሄድና ፍርሃትና ወንጀል በሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በዚህ መንገድ መቀራረብ ያስፈልጋል።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “እናንተ ራሳችሁ መጀመር አለባችሁ። ምናልባትም በቅርባችሁ ካለው ጎረቤታችሁ መጀመር ትችላላችሁ።”
ካናዲያን ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት ጎረቤታሞች አንዳቸው ለሌላው ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ ሰንዝሯል። ማርኒ ጃክሰን የተባሉት ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ልክ እንደ ቤተሰባችን አባላት ሁሉ ጎረቤቶችም ሁል ጊዜ በእኛ ምርጫ የምናገኛቸው አይደሉም። ግንኙነቱ ብልሃትን፣ አክብሮትንና መቻቻልን የሚጠይቅ ነው።”
ጥሩ ጎረቤቶች ለጋሶች ናቸው
እርግጥ ነው አብዛኞቻችን ከጎረቤቶቻችን ጋር መቀራረብ ይከብደን ይሆናል። ከማንም ጋር ግንኙነት ሳንፈጥር የራሳችንን ኑሮ መኖሩ የሚቀልል ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” ይላል። (ሥራ 20:35) በመሆኑም ጥሩ ጎረቤት ለመሆን የሚፈልግ ሰው ከጎረቤቶቹ ጋር ለመተዋወቅ ጥረት ያደርጋል። የግድ የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ባያስፈልገውም እንኳን አልፎ አልፎ ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ሰላምታ በመስጠት ጭውውት ለመጀመር ይሞክራል።
ከላይ እንደተጠቀሰው ጎረቤታሞች አንዳቸው ለሌላው የሚውሏቸው “ቀላል ውለታዎች” ጥሩ ጉርብትና ለመመሥረትና ይህንን ዝምድና ጠብቆ ለማቆየት ጠቃሚ ናቸው። በመሆኑም ለጎረቤቶቻችሁ ልታደርጉላቸው የምትችሏቸውን አሳቢነታችሁን የሚገልጹ አንዳንድ ቀላል የሆኑ ነገሮች አስቡ፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህ በመካከላችሁ የትብብርና የመከባበር መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል። ከዚህም በላይ እንደዚህ በማድረግ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን።—ምሳሌ 3:27፤ ያዕቆብ 2:14-17
ጥሩ ጎረቤቶች አድናቂዎች ናቸው
ሁሉም ሰው የሚደረግለትን እርዳታና ስጦታ በአድናቆት የሚቀበል ቢሆን ጥሩ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሁሉም ሰው እንደዚያ አይደለም። ብዙውን ጊዜ እርዳታ ለመለገስ የሚደረጉ ጥረቶችና በቅን ልቦና የሚቀርቡ ስጦታዎች አድናቆት ሳያገኙ የሚቀሩ በመሆናቸው ሰጪው ወገን ‘ምነው እጄን በቆረጠው!’ ብሎ
ሊጸጸትና ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። አንዳንዴም ወዳጃዊ ሰላምታ ለመስጠት ለምታደርጉት ጥረት ጎረቤታችሁ ከአንገት በላይ የሆነ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።ሆኖም ምንም እንኳን ከውጪ ሲታይ እንደዚያ ቢመስልም አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠረው ተቀባዩ ምስጋና ቢስ ሆኖ አይደለም። ምናልባትም ፈራ ተባ እንዲል ወይም እንዲሸማቀቅና ምንም ግድ እንዳልሰጠው የሚያስመስል ምላሽ እንዲሰጥ ያደረገው አስተዳደጉ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ምስጋና በጠፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ ሰዎች ወዳጃዊ ስሜት ሲመለከቱ ያልተለመደ ሊሆንባቸውና ጥርጣሬ ሊያድርባቸው ይችላል። ጥርጣሬያቸውን የሚያስወግድላቸው አሳማኝ ነገር ማየት ይፈልጉ ይሆናል። በመሆኑም ወዳጃዊ ግንኙነት መመሥረት ጊዜ የሚወስድና ትዕግሥት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ለጋስና አመስጋኝ የሆኑ ጎረቤቶች ሰላማዊና አስደሳች ጉርብትና ለመመሥረት ጥሩ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በመከራ ወቅት
የጎረቤት ጥቅም የበለጠ የሚታየው በመከራ ወቅት ነው። አደጋ ሲያጋጥመን እውነተኛ ጉርብትና በግልጽ ይታያል። በእነዚህ ወቅቶች ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ተግባር ያከናወኑ ብዙ ጎረቤቶች አሉ። ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ሲተባበሩና ሲረዳዱ ይታያል። አብዛኛውን ጊዜ የአመለካከት ልዩነት ያላቸው ሰዎች እንኳን ተባብረው ይሠራሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው በ1999 ቱርክ በኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ስትመታ ለወትሮው ጠላቶች የነበሩ ሰዎች ወዳጃዊ ትብብር አሳይተዋል። አና ስታርዪዩ የተባሉ ግሪካዊት የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ በአንድ የአቴንስ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ለብዙ ዓመታት ቱርኮችን በክፉ ዓይን ስናያቸው ኖረናል። ቢሆንም በደረሰባቸው ከባድ መከራ ልባችን በሐዘን ተሰብሯል። በአደጋው የሞቱ ሕፃናትን አስከሬን ስንመለከት ለዘመናት የዘለቀውን ጥላቻ ረስተን ስቅስቅ ብለን አለቀስን።” የነፍስ አድን ሥራው ከተቋረጠም በኋላ እንኳን ግሪካውያን የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለማግኘት ፍለጋ ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር።
አደጋ ከደረሰ በኋላ በነፍስ አድን ተግባር መሰማራት ከፍተኛ ድፍረት የሚጠይቅና እጅግ የሚደነቅ የደግነት ተግባር ነው። ሆኖም አደጋ ከመድረሱ በፊት ማስጠንቀቂያ በማሰማት የጎረቤቶቻችንን ሕይወት ማዳን ደግሞ ከዚህ የላቀ የአሳቢነት መግለጫ ነው። የሚያሳዝነው ግን ታሪክ እንደሚያሳየው አደጋ ከመድረሱ በፊት ጎረቤቶቻቸውን ለማስጠንቀቅ የሞከሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን በሰጡበት ወቅት የሚመጣው ጥፋት በግልጽ የሚታይ ስላልነበረ ጥሩ ምላሽ አላገኙም። ማስጠንቀቂያ የሚያሰሙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተቀባይነት አያገኙም። አደጋ ላይ እንዳሉ ያልተገነዘቡ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የሚጥሩ ሰዎች እንዲህ ያለው ኃላፊነት ከፍተኛ ጽናትና ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ይጠይቅባቸዋል።
ከሁሉ የላቀው ወዳጃዊ ተግባር
ዛሬ ከተፈጥሮ አደጋዎች የበለጠ አሳሳቢ የሆነ ጥፋት በሰው ዘር ላይ አንዣቧል። ይህም በትንቢት የተነገረውና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ምድርን ከወንጀል፣ ከክፋትና ከመሳሰሉት ችግሮች ለማጽዳት የሚወስደው እርምጃ ነው። (ራእይ 16:16፤ 21:3, 4) ይህ ታላቅ ክስተት ፍጻሜውን ማግኘቱ አይቀሬ ነው! የይሖዋ ምሥክሮች በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በቅርቡ ከሚመጣው ዓለምን የሚያናውጥ ጥፋት ይተርፉ ዘንድ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን እውቀት እንዲቀስሙ ለመርዳት ይፈልጋሉ። በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን የስብከት እንቅስቃሴያቸውን ያላንዳች መታከት በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱትም ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህንን ተግባር የሚያከናውኑት ተገድደው ሳይሆን ለአምላክ እና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ነው።
እንግዲያው የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤትህ ሲመጡ ወይም በሌላ ቦታ ሊመሰክሩልህ ሲሞክሩ መሠረተ ቢስ በሆነ ጥላቻ ተነሳስተህ ወይም ተናድደህ ከመስማት ወደ ኋላ አትበል። ከጥሩ ጎረቤት የሚጠበቀውን ነገር ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን አትዘንጋ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ከአንተ ጋር ለማጥናት የሚያቀርቡትን ግብዣ ተቀበል። የአምላክ ቃል በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ተስማምተው በደስታ የሚኖሩበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ የሚናገረው ተስፋ እንዴት እንደሚፈጸም ትማራለህ። በዚያን ጊዜ ሁላችንም የምንናፍቀውን ወዳጃዊ ግንኙነት የሚያበላሽ የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የመደብ ልዩነት አይኖርም።
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጎረቤቶችህ ደግነት ማሳየት ጥሩ ነው
[ምንጭ]
ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.