በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል”

“በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል”

“በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል”

ሞቃታማ በሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ በጎች በየቀኑ ውኃ መጠጣት ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ አንድ እረኛ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ለመንጋው ውኃ ማቅረብ ነው። አንዳንድ ጊዜ እረኞች ከጉድጓድ ውኃ እያወጡ በገንዳ ውስጥ በመሙላት መንጎቻቸውን ያጠጣሉ። (ዘፍጥረት 29:1-3) ይሁን እንጂ በክረምት ወራት በትናንሽ ጅረቶችና ወንዞች አጠገብ የሚገኘው አካባቢ ‘ውኃ የሞላበት የዕረፍት ቦታ’ ሊሆን ይችላል።​—⁠መዝሙር 23:2

ጥሩ እረኛ ለመንጋው የሚሆን ውኃና ተስማሚ የሆነ የግጦሽ መስክ የት እንደሚገኝ ማወቅ አለበት። የበጎቹ ሕይወት የተመካው እረኛው አካባቢውን በሚገባ የሚያውቅ በመሆኑ ላይ ነው። በዮርዳኖስ ኮረብቶች ላይ ለበርካታ ዓመታት በግ ሲያግድ የኖረው ዳዊት የአምላክን መንፈሳዊ አመራር በጎቹን ጥሩ የግጦሽ መስክና ሕይወት ሰጪ ውኃ ወዳለበት ቦታ ከሚመራ እረኛ ጋር አወዳድሮታል። ዳዊት “በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል” ሲል ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 23:1-3

ከብዙ ዓመታት በኋላ ይሖዋ በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሞ ተናግሯል። ልክ እረኛ በጎቹን እንደሚሰበስብ ሕዝቦቹን ከተበተኑባቸው አገሮች እንደሚሰበስባቸው ቃል ገብቷል። “ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፣ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ . . . ላይ አሰማራቸዋለሁ።”​—⁠ሕዝቅኤል 34:13

ይሖዋ አምላክ ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ውኃ ማግኘታቸው ያሳስበዋል። የራእይ መጽሐፍ ከአምላክ ዙፋን ስለሚፈስስ ‘የሕይወት ውኃ ወንዝ’ ይናገራል። (ራእይ 22:1) ሁሉም ሰው ከዚህ ወንዝ እንዲጠጣ ግብዣ ቀርቦለታል። “የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።”​—⁠ራእይ 22:17

ይህ ምሳሌያዊ የሕይወት ውኃ አምላክ ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል። ማንኛውም ሰው ‘እውነተኛ አምላክ ብቻ ስለሆነውና እርሱ ስለላከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት’ በመቅሰም ከዚህ ውኃ መጠጣት መጀመር ይችላል።​—⁠ዮሐንስ 17:3