በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኞቹ ቅዱሳን ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

እውነተኞቹ ቅዱሳን ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

እውነተኞቹ ቅዱሳን ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቅዱሳን” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የሚያመለክተው እነማንን ነው? አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠው “ቃሉ አማኞችን ለማመልከት በብዙ ቁጥር ሲሠራበት የተለየ ቅድስና ያላቸውን ሰዎች ብቻ ወይም የተለዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንዳከናወኑ የሚነገርላቸውን በሞት የተለዩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አማኞች ያመለክታል።”

በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በሙሉ እውነተኛ ቅዱሳን እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የላከውን ደብዳቤ “በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” እንደጻፈው ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 1:​1) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ‘ቅዱሳን ሊሆኑ ለተጠሩት በሮሜ ላሉት ሁሉ’ ደብዳቤ ጽፏል። (ሮሜ 1:​7) እነዚህ ቅዱሳን ገና በሕይወት እንደነበሩ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ባላቸው የላቀ ባሕርይ የተነሳ ከተቀሩት አማኞች የተለዩ ተደርገው አይታዩም ነበር። ታዲያ ቅዱስ ለመባል ያበቃቸው ምንድን ነው?

አምላክ ቀድሷቸዋል

አንድ ሰው ቅዱስ ተብሎ ሊሰየም የሚገባው በሰው ወይም በአንድ ድርጅት እንዳልሆነ የአምላክ ቃል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፣ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም” በማለት ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 1:​9) እነዚህ ሰዎች ቅዱስ ተብለው የተሰየሙት በይሖዋ ሲሆን ይህንንም ያደረገው ከዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ ይገባናል በማይሉት ቸርነቱ ነው።

በክርስቲያን ጉባኤ የታቀፉት ቅዱሳን “የአዲስ ኪዳን” ተካፋዮች ናቸው። ይህ አዲስ ቃል ኪዳን የጸናው በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት ሲሆን ደሙ የዚህን ቃል ኪዳን ተካፋዮች ይቀድሳቸዋል። (ዕብራውያን 9:​15፤ 10:​29፤ 13:​20, 24) በአምላክ ዓይን ንጹሕ ስለሆኑ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን የሚያቀርቡ ቅዱሳን ካህናት’ ሆነው ያገለግላሉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​5, 9

ቅዱሳንን እንደ አማላጅ አድርጎ መለመን

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ቅዱሳን” ለሚያምኑባቸው ሰዎች የተለየ ኃይል ይሰጣሉ በሚል እምነት እነርሱ ይገለገሉባቸው በነበሩ ዕቃዎች በመጠቀም አክብሮት ይሰጧቸዋል ወይም ከአምላክ ጋር እንደሚያማልዷቸው በማሰብ ልመና ያቀርቡላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራልን? ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ተከታዮቹ ወደ አምላክ እንዴት እንደሚቀርቡ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) ጸሎት መቅረብ የሚኖርበት ለይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።

አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን “ቅዱሳን” ያማልዳሉ የሚለው ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዳለው ለማሳየት “ወንድሞች ሆይ፣ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ” የሚለውን ሮሜ 15:​30ን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ። እዚህ ላይ ጳውሎስ አማኞች እንዲጸልዩለት መጠየቁ ነበር ወይስ አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማላቸው በስሙ እንዲለምኑ ማበረታታቱ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለቅዱሳን እንድንጸልይላቸው ተደጋጋሚ ማበረታቻ የተሰጠ ቢሆንም ወደ እነርሱ እንድንጸልይ ወይም በእነርሱ በኩል ወደ አምላክ እንድንጸልይ የሚገልጽ ሐሳብ አንድም ቦታ አይገኝም።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​1, 3, 4

ይሁን እንጂ አምላክ ጸሎታችን በማን አማላጅነት መቅረብ እንዳለበት አሳውቆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም “አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:6, 13, 14) ይሖዋ በኢየሱስ ስም የሚቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”​—⁠ዕብራውያን 7:25

ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ሊያማልደን ፈቃደኛ ከሆነ የሕዝበ ክርስትና ተከታዮች “ቅዱሳን” ከአምላክ ጋር እንዲያማልዷቸው የሚለምኑት ለምንድን ነው? ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ዚ ኤጅ ኦቭ ፌይዝ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ቅዱሳንን መለመን መቼ እንደጀመረ ተናግረዋል። ዱራንት እንደገለጹት ሰዎች በጣም ከሚያስፈራውና ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ይልቅ ኢየሱስን መቅረብ ሊቀልላቸው ቢችልም “የኢየሱስን የተራራ ስብከት በሕይወታቸው ስለማይሠሩበት በቀጥታ እርሱን መለመን ይከብዳቸዋል። ስለዚህ አንድ ሰው ጸሎቱን ሰማይ ቤት ገብተዋል ብሎ ለሚያምንባቸው ቅዱሳን አቅርቦ ክርስቶስን እንዲያማልዱት መጠየቅ ይመርጣል።” ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ በኩል “በነጻነትና በልበ ሙሉነት” ወደ አምላክ በጸሎት መቅረብ እንደምንችል ያስተምረናል። (ኤፌሶን 3:​11, 12 አ.መ.ት ) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከሰው ልጆች የራቀ ስላልሆነ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። መዝሙራዊው ዳዊት “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል” በማለት በትምክህት ጸልዮአል። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ኃይሉን ቀደም ባሉት ዘመናት የሞቱ “ቅዱሳን” ይጠቀሙባቸው በነበሩ ዕቃዎች አማካኝነት ከመስጠት ይልቅ ቅዱስ መንፈሱን በእምነት ለሚለምኑት ሰዎች በቀጥታ ይሰጣል። ኢየሱስ “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” በማለት ሁኔታውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል።​—⁠ሉቃስ 11:13

ቅዱሳን የሚያከናውኑት ተግባር

ጳውሎስ ደብዳቤ የጻፈላቸው ቅዱሳን ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የሞቱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ‘የሕይወትን አክሊል’ ማለትም ሰማያዊ ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ነበራቸው። (ራእይ 2:​10) የላቀ ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚያሳዩ ሰዎች እንኳ ለእነዚህ እውነተኛ ቅዱሳን ልዩ አክብሮት መስጠት ከሕመም፣ ከተፈጥሮ አደጋዎች፣ ከኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ከእርጅና ወይም ከሞት ጥበቃ እንደማያስገኝ አምነው የሚቀበሉት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ‘የአምላክ ቅዱሳን በእርግጥ ስለ እኛ ያስባሉ? እንዲረዱን ልንጠይቃቸው እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ቅዱሳን በግልጽ የተጠቀሰው በዳንኤል ትንቢት ውስጥ ነው። ዳንኤል እስከዚህ ዘመን ድረስ ፍጻሜውን የሚያገኝ አንድ አስደናቂ ራእይ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተመልክቶ ነበር። የሰውን ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ማርካት የማይችሉ ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚወክሉ አራት አስፈሪ አራዊት ከባሕር ሲወጡ አየ። ከዚያም ዳንኤል እንዲህ የሚል ትንቢት ተናገረ:- “ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፣ እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ።”​—⁠ዳንኤል 7:17, 18

ጳውሎስ ይህ ‘በቅዱሳንም ዘንድ ያለው ርስት’ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ገዥ መሆን እንደሆነ አረጋግጧል። (ኤፌሶን 1:​18-21) የኢየሱስ ደም 144, 000 ቅዱሳን ለሰማያዊ ክብር ትንሣኤ እንዲያገኙ አጋጣሚውን ይከፍትላቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፣ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእይ 20:4, 6፤ 14:1, 3) ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ የሰማይ ሠራዊት ከፍተኛ ክብር በተቀዳጀው በኢየሱስ ፊት ወድቀው “በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ” ብለው ሲዘምሩ ሰምቷል። (ራእይ 5:9, 10) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! እነዚህን ወንዶችና ሴቶች በጥንቃቄ የመረጣቸው ይሖዋ አምላክ ራሱ ነው። ከዚህም በላይ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በሙሉ ተቋቁመው በምድር ላይ በታማኝነት አገልግለዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:​13) በመሆኑም ትንሣኤ ያገኙት እነዚህ ቅዱሳን ድክመቶቻችንንና አቅማችንን ጠንቅቀው የሚያውቁ ርኅሩኅና የሰው ችግር የሚገባቸው ገዥዎች እንደሚሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የሚገኙ በረከቶች

የአምላክ መንግሥት ክፋትንና መከራን ከምድር ላይ ጨርሶ ለማስወገድ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ከምን ጊዜውም በበለጠ ወደ አምላክ ይቀርባሉ። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ . . . ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” ይህም ከፍተኛ በረከት እንደሚያስገኝ በመግለጽ ትንቢቱ ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”​—⁠ራእይ 21:3, 4

ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ኢየሱስና የ144, 000 ቅዱሳኑ ፍጹም አገዛዝ ምን ውጤት እንዳለው በሚክያስ 4:​3, 4 ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል:- “[ይሖዋ] በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፣ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”

ቅዱሳን ሌሎች ሰዎች ከዚህ በረከት ተካፋይ እንዲሆኑ ሲጋብዙ ቆይተዋል። በሙሽራ የተመሰሉት እውነተኞቹ ቅዱሳን “ና” በማለት ይጣራሉ። ጥቅሱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 22:17) ይህ ‘የሕይወት ውኃ’ ምንን የሚጨምር ነው? አንደኛው ስለ አምላክ ዓላማዎች ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ነው። ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ያለው እውቀት የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በማጥናት ነው። በአምላክ ቃል አማካኝነት የእውነተኞቹን ቅዱሳን ትክክለኛ ማንነት ማስተዋል በመቻላችንና ይሖዋ ለሰው ልጅ ዘላለማዊ ጥቅም ሲል እንዴት እንደሚጠቀምባቸው በማወቃችን ምንኛ ደስተኞች ነን!

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ለእውነተኞቹ ቅዱሳን በመንፈስ አነሳሽነት ደብዳቤ ጽፎላቸዋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያት እውነተኛ ቅዱሳን ሆነዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በትምክህት ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰማያዊ ትንሣኤ ያገኙት ርኅሩኅ ቅዱሳን ምድርን ይገዛሉ