በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’

‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’

‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’

“ከሰማናቸው ነገሮች ምናልባት እንዳንወሰድ ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባናል።”ዕብራውያን 2:​1 NW

1. የሐሳብ መከፋፈል እንዴት ለአደጋ ሊዳርግ እንደሚችል ግለጽ።

 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ 37,000 የሚሆኑ ሰዎች በመኪና አደጋ ይሞታሉ። አሽከርካሪዎች ይበልጥ በጥንቃቄ ቢያሽከረክሩ ኖሮ አብዛኞቹ ሰዎች ለሞት ባልተዳረጉ ነበር ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዳንድ አሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የተለጠፉ ምልክቶችና የንግድ ማስታወቂያዎች ሲመለከቱ ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ ሲያወሩ ትኩረታቸው ይሰረቃል። መኪና እያሽከረከሩ ምግብ የሚበሉም አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ትኩረትን የሚሰርቁ በመሆናቸው ለአደጋ ሊዳርጉ ይችላሉ።

2, 3. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጠ? ምክሩስ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

2 መኪና ከመፈልሰፉ ከ2, 000 ዓመታት ገደማ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን አደጋ ላይ የጣለ ትኩረት የሚሰርቅ ሁኔታ እንዳለ ተናግሮ ነበር። ጳውሎስ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ የተቀመጠ በመሆኑ ከመላእክት ሁሉ የላቀ ቦታ እንደተሰጠው ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከዚያ በመቀጠል ሐዋርያው “ስለዚህ ከሰማናቸው ነገሮች ምናልባት እንዳንወሰድ ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባናል” ሲል ተናገረ።​—⁠ዕብራውያን 2:1 NW

3 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስን በተመለከተ ‘ለሰሙት ነገር ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት’ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ምድርን ለቅቆ ከሄደ 30 የሚጠጉ ዓመታት አልፈውታል። አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች መሪያቸው ምድር ባልነበረበት በእነዚህ ጊዜያት ከእውነተኛው አምልኮ ወደ ኋላ ማለት ጀምረው ነበር። ቀድሞ ይከተሉት የነበረው የአይሁድ እምነት ትኩረታቸውን ስቦት ነበር።

የበለጠ ትኩረት መስጠት አስፈልጓቸው ነበር

4. አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ወደ አይሁድ እምነት ለመመለስ የተፈተኑት ለምን ሊሆን ይችላል?

4 አንድ ክርስቲያን ወደ አይሁድ እምነት እንዲመለስ የሚፈተነው ለምን ሊሆን ይችላል? በሕጉ መሠረት የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት በዓይን የሚታዩ ነገሮችን አካትቶ የያዘ ነበር። ሰዎች ቤተ መቅደሱ ውስጥ ካህናት ሲያገለግሉና የሚቃጠል መሥዋዕት ሲቀርብ መመልከት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ የክርስትና እምነት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ክርስቲያኖችም ሊቀ ካህን ያላቸው ሲሆን እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሆኖም ሊቀ ካህናቸው ለመጨረሻ ጊዜ ምድር ላይ ከታየ ሦስት አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። (ዕብራውያን 4:​14) ቤተ መቅደስም ያላቸው ቢሆንም ቅዱሱ ሥፍራ የሚገኘው በሰማይ ነው። (ዕብራውያን 9:​24) በሕጉ ሥር ከሰፈረው ሥጋዊ ግርዘት በተለየ የክርስቲያኖች ግርዘት “በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ” ነው። (ሮሜ 2:​29) በመሆኑም ዕብራውያን ክርስቲያኖች የክርስትና እምነት ተጨባጭ ነገር የሌለው እንደሆነ አድርገው ማሰብ ጀምረው ሊሆን ይችላል።

5. ኢየሱስ ያቋቋመው የአምልኮ ሥርዓት በሕጉ ሥር ከነበረው የላቀ መሆኑን ጳውሎስ ያሳየው እንዴት ነው?

5 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ክርስቶስ ያቋቋመውን የአምልኮ ሥርዓት በተመለከተ መገንዘብ የሚያስፈልጋቸው አንድ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ጉዳይ ነበር። አምልኮው የተመሠረተው በሚታይ ነገር ላይ ሳይሆን በእምነት ላይ ቢሆንም በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ከተላለፈው ሕግ የሚልቅ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብራውያን 9:13, 14) አዎን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን የሚያስገኘው የኃጢአት ይቅርታ በሕጉ ሥር የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ከሚያስገኙት የኃጢአት ይቅርታ በብዙ መንገዶች እጅግ የላቀ ነው።​—⁠ዕብራውያን 7:​26-28

6, 7. (ሀ) ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሳይዘገዩ ‘ለሰሙት ነገር ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት’ የሚያስፈልጋቸው ለምን ነበር? (ለ) ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ጥፋት ምን ያህል ተቃርቦ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስን በተመለከተ ለተማሩት ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ሌላም ምክንያት ነበራቸው። ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፣ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።”​—⁠ሉቃስ 19:43, 44

7 ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው? ኢየሱስ ቀኑንና ሰዓቱን አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ይህን መመሪያ ሰጠ:- “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ በነበሩት 30 ዓመታት ውስጥ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የጥድፊያ ስሜታቸውን ከማጣታቸውም በላይ ትኩረታቸው ተከፋፍሎ ነበር። መኪና እያሽከረከረ ትኩረቱ ወደ ሌላ ቦታ እንደተሰረቀ አሽከርካሪ ሆነው ነበር ለማለት ይቻላል። አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ በስተቀር አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀርም። ይህን አመኑም አላመኑ በኢየሩሳሌም ላይ ጥፋት አጥልቶ ነበር! a ጳውሎስ የሰጠው ምክር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በመንፈሳዊ ላንቀላፉ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ እንደሚያሰማ ደወል ሆኖላቸው ነበር።

በዛሬው ጊዜ “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት”

8. ለአምላክ ቃል እውነት “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” ያለብን ለምንድን ነው?

8 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ለአምላክ ቃል እውነት “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” ያስፈልገናል። ለምን? እኛም ብንሆን ከፊታችን ጥፋት ተጋርጦብናል። ይህ ጥፋት በአንድ ብሔር ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሥርዓት ላይ የሚመጣ ነው። (ራእይ 11:​18፤ 16:​14, 16) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህን እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛውን ቀንና ሰዓት አናውቅም። (ማቴዎስ 24:​36) ሆኖም “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር በግልጽ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ስለዚህ ትኩረታችን በምንም ነገር እንዳይከፋፈል መጠንቀቅ አለብን። የአምላክን ቃል በትኩረት መከታተልና የጥድፊያ ስሜታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ” እንችላለን።​—⁠ሉቃስ 21:​36

9, 10. (ሀ) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትኩረት እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ቃል ‘ለእግራችን መብራት፣ ለመንገዳችን ብርሃን’ የሆነልን በምን መንገድ ነው?

9 በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለመንፈሳዊ ነገሮች “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት” እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ በጉባኤ፣ በልዩና በወረዳ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ በመገኘት ነው። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረብ እንድንችል ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን አለብን። (ያዕቆብ 4:​8) በግል ጥናትና ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የይሖዋን እውቀት ከቀሰምን “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ብሎ ለአምላክ እንደተናገረው መዝሙራዊ እንሆናለን።​—⁠መዝሙር 119:​105

10 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ስለሚነግረን ‘ለመንገዳችን ብርሃን’ ሆኖ ያገለግለናል። ከዚህም በላይ ‘ለእግራችን መብራት’ ነው። በሌላ አባባል በሕይወታችን ውስጥ ከበድ ያሉ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ሊረዳን ይችላል። ስለዚህ ከእምነት ጓደኞቻችን ጋር አንድ ላይ ለመማር ስንሰበሰብ ወይም የአምላክን ቃል በግል ስናነብ ‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠታችን’ አስፈላጊ ነው። የምንቀስመው ትምህርት የይሖዋን ልብ የሚያስደስት ጥበብ የተሞላበትና ጠቃሚ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። (ምሳሌ 27:​11፤ ኢሳይያስ 48:​17) አምላክ ካደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅት የተቻለውን ያህል ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት በስብሰባዎች ላይና የግል ጥናት በምናደርግባቸው ወቅቶች ረዘም ላለ ሰዓት በትኩረት የመከታተል ችሎታችንን ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?

በስብሰባዎች ላይ በትኩረት የመከታተል ችሎታችንን ማሻሻል

11. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?

11 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች በትኩረት መከታተል የምንቸገርባቸው ጊዜያት አሉ። ምናልባት ሕፃን ልጅ በሚያለቅስበት ወይም አርፍዶ የመጣ ሰው መቀመጫ በሚፈልግበት ጊዜ ሐሳባችን በቀላሉ ሊከፋፈል ይችላል። ቀኑን ሙሉ ስንሠራ ውለን ድክም ብሎን ይሆናል። ንግግር የሚያቀርበው ወንድም ትምህርት አሰጣጡ ብዙም የሚማርክ ላይሆንና ሳናስበው በሐሳብ ጭልጥ ብለን ልንሄድ አልፎ ተርፎም እንቅልፍ ሊጫጫነን ይችላል! ከሚቀርበው ትምህርት ጠቃሚነት አንጻር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት የመከታተል ችሎታችንን ለማሻሻል የተቻለንን ያህል ጥረት ማድረግ አለብን። ሆኖም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12. በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ለመከታተል ምን ሊረዳን ይችላል?

12 ጥሩ ዝግጅት አድርገን በስብሰባዎች ላይ የምንገኝ ከሆነ በትኩረት መከታተል ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ታዲያ በስብሰባ ላይ የሚጠናውን ትምህርት አስቀድመን ለመዘጋጀት ለምን ጊዜ አንመድብም? ለሳምንቱ የተመደቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ምዕራፎች ከፋፍሎ በየቀኑ ለማንበብና በዚያም ላይ ለማሰላሰል የሚወስደው ጥቂት ደቂቃ ብቻ ነው። አስቀድመን ዕቅድ ካወጣን ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናትና ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት የምንዘጋጅበት ጊዜም ማግኘት እንችላለን። ያወጣነው ፕሮግራም ምንም ይሁን ምን አስቀድሞ መዘጋጀት በጉባኤ ስብሰባ ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በትኩረት እንድንከታተል እንደሚረዳን የተረጋገጠ ነው።

13. በስብሰባ ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በጥሞና መከታተል እንድንችል ምን ብናደርግ ይጠቅመናል?

13 ጥሩ ዝግጅት ከማድረግ በተጨማሪ አንዳንዶች መንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከፊት ባሉት ወንበሮች ላይ ሲቀመጡ ይበልጥ በትኩረት መከታተል እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። ተናጋሪውን እያዩ ማዳመጥ፣ ጥቅስ ሲነበብ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ መከታተልና ማስታወሻ መያዝ አእምሯችን እንዳይባዝን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዘዴዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በትኩረት ለመከታተል ከሚረዳ ከየትኛውም ዘዴ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው የልብ ዝግጅት ማድረግ ነው። አንድ ላይ የምንሰበሰብበትን ዓላማ መገንዘብ ይኖርብናል። ከእምነት ጓደኞቻችን ጋር የምንሰበሰብበት ተቀዳሚ ዓላማ ይሖዋን ለማምለክ ነው። (መዝሙር 26:​12፤ ሉቃስ 2:​36, 37) ስብሰባ በመንፈሳዊ የምንመገብበት አስፈላጊ ዝግጅት ነው። (ማቴዎስ 24:​45-47) በተጨማሪም ‘እርስ በርሳችን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

14. አንድን ስብሰባ ስኬታማ የሚያደርገው ምንድን ነው?

14 አንዳንዶች የስብሰባውን ጥራት ተናጋሪዎቹ ባላቸው የማስተማር ችሎታ ለመመዘን ያስቡ ይሆናል። ተናጋሪዎቹ ጥሩ የማስተማር ችሎታ ካላቸው ስብሰባው አስደሳች እንደነበር ይነገራል። ካልሆነ ደግሞ ለስብሰባው ያለን አመለካከት አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች ጥሩ የማስተማር ጥበብ ለመጠቀምና በተለይ ደግሞ ልብ ለመንካት የተቻላቸውን ያህል መጣር እንዳለባቸው የታወቀ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16) ሆኖም አድማጮችም ከሚገባው በላይ ነቃፊ መሆን አይገባቸውም። የተናጋሪዎቹ የማስተማር ችሎታ ትልቅ ቦታ ቢኖረውም ለስብሰባው ስኬታማነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ብቸኛው መስፈርት ግን አይደለም። ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ተናጋሪው ንግግሩን ያቀረበበት መንገድ ሳይሆን እኛ በጥሞና ማዳመጥ መቻላችን ነው ቢባል አትስማማም? በስብሰባዎች ላይ ስንገኝና የሚቀርበውን ትምህርት በጥሞና ስናዳምጥ አምላክን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ እናመልከዋለን። ስብሰባውን የተሳካ የሚያደርገው ይህ ነው። የአምላክን እውቀት ለማግኘት ጉጉት ካሳደርን የተናጋሪው ችሎታ ምንም ይሁን ምን ከስብሰባ ጥቅም እናገኛለን። (ምሳሌ 2:​1-5) ስለዚህ በስብሰባዎቻችን ላይ በተቻለን መጠን ‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ለመስጠት’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

ከግል ጥናት የተሟላ ጥቅም አግኙ

15. ማጥናትና ማሰላሰል ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

15 የግል ጥናት በማድረግና በማሰላሰል ለትምህርታችን ‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስንሰጥ’ ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ማንበብና በዚያም ላይ ማሰላሰል የአምላክን ቃል እውነት በልባችን ለመቅረጽ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልናል። ይህ ደግሞ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህም የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። (መዝሙር 1:​2፤ 40:​8) በመሆኑም ከጥናት ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን በትኩረት የመከታተል ችሎታችንን ማሳደግ ይኖርብናል። ሐሳባችን በቀላሉ ሊከፋፈል ይችላል! እንደ ስልክ ጥሪ ወይም ጫጫታ የመሳሰሉ ነገሮች ትኩረታችንን በቀላሉ ሊሰርቁ ይችላሉ። ወይም ለረጅም ጊዜ በትኩረት የመከታተል ችሎታ አይኖረን ይሆናል። በመንፈሳዊ ራሳችንን ለመመገብ ብለን ጥናት እንጀምርና ብዙም ሳይቆይ አእምሯችን ሌላ ነገር ማሰብ ሊጀምር ይችላል። የአምላክን ቃል በግል በምናጠናበት ወቅት ለትምህርታችን “ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” የምንችለው እንዴት ነው?

16. (ሀ) ለግል ጥናት የሚሆን ጊዜ መመደባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክን ቃል ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ ያገኘኸው እንዴት ነው?

16 ፕሮግራም ማውጣትና ለማጥናት የሚጋብዝ ሁኔታ መምረጥ ጠቃሚ ነው። ብዙዎቻችን ጸጥታ የሰፈነበት ጊዜ እንደልብ አናገኝ ይሆናል። በጅረት እየተነዳች እንደምትሄድ ጭራሮ የዕለት ተዕለት የሕይወት ሩጫም ፋታ እንዳሳጣን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ይሁንና ይህን የዕለት ተዕለት ሩጫ ተቋቁመን ለጥናት የሚሆን ትንሽ ፋታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ማጥናት የምንችልበት ጊዜ በራሱ እስኪመቻችልን ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ለጥናት የሚሆን ጊዜ በመመደብ ሁኔታችንን መቆጣጠር ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:​15, 16) አንዳንዶች ብዙም የሚረብሽ ነገር በሌለበት ማለዳ ላይ ጥቂት ጊዜ ይመድባሉ። ሌሎች ደግሞ ምሽት ላይ ጊዜ መመደቡን የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። ዋናው ቁም ነገር ስለ አምላክና ስለ ልጁ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም አስፈላጊ መሆኑን አለመዘንጋታችን ነው። (ዮሐንስ 17:​3) ስለዚህ የግል ጥናት የምናደርግበት ፕሮግራም እናውጣ፤ ፕሮግራሙንም በጥብቅ እንከተል።

17. ማሰላሰል ምንድን ነው? እንዴትስ ሊጠቅመን ይችላል?

17 ስናጠና ባገኘነው እውቀት ላይ ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክን ቃል አንብበን ማሰላሰላችን መልእክቱ በልባችን ውስጥ እንዲቀረጽ ይረዳናል። ማሰላሰል ‘ቃሉን የምናደርግ እንጂ ሰሚዎች ብቻ እንዳንሆን’ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ እንዴት ማዋል እንደምንችል እንድናስተውል ይረዳናል። (ያዕቆብ 1:​22-25) በተጨማሪም ማሰላሰል የይሖዋን ባሕርያትና የግል ጥናት ስናደርግ በምናጠናው ጽሑፍ ላይ እነዚህ ባሕርያቱ እንዴት ጎላ ብለው እንደተገለጹ እንድናስብ ስለሚያስችለን ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል።

18. ጥሩ አድርጎ ለማሰላሰል መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

18 ከጥናትና ከማሰላሰል የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ሐሳባችንን ከሚከፋፍሉ ነገሮች ራሳችንን ነፃ ማድረግ አለብን። በምናሰላስልበት ጊዜ አዲስ እውቀት ማግኘት እንድንችል ሐሳብን የሚከፋፍሉ የኑሮ ጭንቀቶችን ከአእምሯችን ማውጣት ይኖርብናል። ለማሰላሰል ጊዜና ፀጥ ያለ ቦታ ማግኘትን ይጠይቃል፤ ሆኖም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መንፈሳዊ ምግብና የእውነት ውኃ መመገብ ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው!

19. (ሀ) የግል ጥናት ማድረግን በተመለከተ አንዳንዶች ረዘም ላለ ጊዜ በትኩረት የማጥናት ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ የረዳቸው ምንድን ነው? (ለ) ለጥናት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? ከዚህም ምን ጥቅም እናገኛለን?

19 ረዘም ላለ ጊዜ በትኩረት መከታተል የማንችል ቢሆንና ገና ማጥናት እንደጀመርን አእምሯችን መባዘን ቢጀምርስ? አንዳንዶች መጀመሪያ ላይ አጠር ያለ የጥናት ፕሮግራም በማውጣት፣ ከዚያም ቀስ በቀስ ጊዜውን በማራዘም በሚያጠኑበት ጊዜ በትኩረት የመከታተል ችሎታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። ግባችን በጥናት ላይ በቂ ጊዜ ማሳለፍ እንጂ ቶሎ ለመጨረስ መጣደፍ መሆን የለበትም። ለምናጠናው ርዕስ ከፍተኛ ጉጉት ማሳደር ይኖርብናል። እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያ ያዘጋጃቸውን ሰፊ መጠን ያላቸውን ጽሑፎች ተጠቅመን ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንችላለን። “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መመርመር ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል። (1 ቆሮንቶስ 2:​10) እንዲህ ማድረጋችን ስለ አምላክ ያለንን እውቀት እንድናሳድግና የማስተዋል ችሎታችንን እንድናጎለብት ያስችለናል። (ዕብራውያን 5:​14) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ትጉ ተማሪዎች ከሆንን ‘ሌሎችን ለማስተማር ብቃት’ ያለን እንሆናለን።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​2 አ.መ.ት

20. ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረትና ዝምድናውን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

20 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የግል ጥናት ማድረግ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ የቅርብ ዝምድና እንድንመሠርትና ዝምድናውን ጠብቀን እንድንኖር ከፍተኛ እገዛ ያደርግልናል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” በማለት ለአምላክ ሊናገር የቻለው እንዲህ ዓይነት ዝምድና መሥርቶ ስለነበር መሆን አለበት። (መዝሙር 119:97) በመሆኑም ሁኔታችን በፈቀደ መጠን በጉባኤ፣ በልዩና በወረዳ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት እንጣር። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ እንዋጅ። በዚህ መንገድ ለአምላክ ቃል ‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ለመስጠት’ የምናደርገው ጥረት ከፍተኛ ወሮታ ያስገኝልናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተላከው ደብዳቤ የተጻፈው በ61 እዘአ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ከሆነ ኢየሩሳሌም በሴስትየስ ጋለስ በሚመራው ሠራዊት የተከበበችው ከአምስት ዓመታት በኋላ ነበር ማለት ነው። ብዙም ሳይቆይ ሠራዊቱ ወደኋላ ማፈግፈጉ ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች አካባቢውን ለቅቀው እንዲሸሹ አስችሏቸዋል። ከአራት ዓመታት በኋላ ከተማዋ በጄኔራል ቲቶ በሚመራው ጦር ተደመሰሰች።

ታስታውሳለህን?

• አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከእውነተኛው እምነት ወደ ኋላ ያሉት ለምን ነበር?

• በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በንቃት መከታተል የምንችለው እንዴት ነው?

• ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከማሰላሰል ጥቅም እንድናገኝ የሚረዳን ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዕብራውያን ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ላይ ያጠላውን ጥፋት በንቃት መጠባበቅ ነበረባቸው

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ልጆቻቸው ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጥቅም እንዲያገኙ መርዳት ይችላሉ