በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉ

የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉ

የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉ

“ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:9

1, 2. በጥቅሉ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖተኛ እንደሆኑ በሚያስቡ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነውን? አብራራ።

 “ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ እየጨመረ ቢመጣም የሥነ ምግባር አቋም ግን እያሽቆለቆለ ነው።” ኢመርጂንግ ትሬንድስ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣው ይህ ርዕሰ ዜና በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደ ጥናት የተገኘውን ውጤት ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ነው። በግልጽ እንደሚታየው በዚህች አገር ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር የጨመረ ከመሆኑም በላይ ሃይማኖት በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንደያዘም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዘገባው እንደሚገልጸው:- “አኃዙ በአስደናቂ ሁኔታ ቢጨምርም ሃይማኖታዊ እምነት በግለሰቦች ሕይወትና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ብዙ አሜሪካውያን ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ።”

2 ይህ በአንድ አገር ውስጥ ብቻ የሚታይ ሁኔታ አይደለም። በመላው ዓለም የሚኖሩ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑና ሃይማኖተኛ እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎች በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩባቸው አይፈቅዱም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​5) አንድ የተመራማሪዎች ቡድን መሪ “አሁንም ቢሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ያለ ግምት አለን። ሆኖም መጽሐፉን ማንበብ፣ ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል” ብለዋል።

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል? (ለ) የኢየሱስ ተከታዮች ፊልጵስዩስ 4:​9 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

3 በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ከአምላክ ቃል ያገኙትን ምክር በሥራ ማዋላቸው በአስተሳሰባቸውና በባሕርያቸው ላይ ለውጥ እንዲያመጡ አድርጓቸዋል። እንዲሁም በእነርሱ ላይ የሚታየውን የአዲሱ ሰው ባሕርይ ሌሎች በቀላሉ ያስተውሉታል። (ቆላስይስ 3:​5-10) በኢየሱስ ተከታዮች ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ መደርደሪያ ላይ ተቀምጦ አቧራ የሚጠጣ መጽሐፍ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል:- “ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” (ፊልጵስዩስ 4:9፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል እውነት ከመቀበል ያለፈ ነገር ያደርጋሉ፤ የተማሩትን በሥራ ላይ ያውላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታ፣ በጉባኤና በሌሎች የሕይወታቸው ዘርፎች ሁሉ ሁልጊዜ ተግባራዊ ያደርጋሉ።

4. የአምላክን ሕግ በሥራ ላይ ማዋል ፈታኝ ያደረገው ምንድን ነው?

4 የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ቀላል አይደለም። የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ በሚጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) በመሆኑም በይሖዋ ፊት ጽኑ አቋም ይዘን እንዳንኖር ከሚያደርገን ከማንኛውም ነገር ራሳችንን መጠበቃችን የግድ አስፈላጊ ነው። ጽኑ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ ያዙ’

5. “ያለማቋረጥ ይከተለኝ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ምን ትርጉም ይዘዋል?

5 የተማርነውን ነገር በሥራ የምናውልበት አንደኛው ዘርፍ አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ተቃውሞ ቢደርስብንም እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት ደግፎ በመኖር ነው። ለመጽናት ጥረት ይጠይቃል። ኢየሱስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ [“ያለማቋረጥ፣” NW ] ይከተለኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:​24) ኢየሱስ እሱን መከተል ያለብን ለአንድ ሳምንት፣ ለአንድ ወር ወይም ለአንድ ዓመት ብቻ እንደሆነ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ “ያለማቋረጥ ይከተለኝ” ሲል ተናግሯል። የደቀ መዝሙርነት ሕይወት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ወይም ዛሬ ታይቶ ነገ የሚጠፋ የሃይማኖተኛነት ስሜት እንዳልሆነ የተናገራቸው ቃላት ያሳያሉ። እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት መደገፍ ማለት ምንም ይምጣ ምን በመረጥነው የሕይወት ጎዳና ላይ በታማኝነት ጸንቶ መኖር ማለት ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከጳውሎስ የተማሩት የጤናማ ቃል ምሳሌ ምንድን ነው?

6 ጳውሎስ የሥራ ባልደረባውን ጢሞቴዎስን “በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፣ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ” የሚል ጥብቅ ምክር ሰጥቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? እዚህ ላይ “ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም አንድ ሠዓሊ ያወጣውን ንድፍ ያመለክታል። እንዲህ ዓይነቱ ንድፍ የሚቀሩት ነገሮች ቢኖሩትም እንኳ የሥዕሉን ዋና ዋና ገጽታዎች የያዘ ስለሚሆን አስተውሎ ለሚመለከተው ሰው ሥዕሉ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መረዳት አያቅተውም። በተመሳሳይም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ለሌሎች ያስተማረው የእውነት ምሳሌ ሊነሳ ለሚችል ለእያንዳንዱ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ለመስጠት ተብሎ የተዘጋጀ አልነበረም። ሆኖም ይህ ትምህርት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ይሖዋ ከእነሱ የሚፈልግባቸውን ነገር መገንዘብ እንዲችሉ በቂ መመሪያ፣ በሌላ አባባል ንድፍ ይዞላቸዋል። እርግጥ ነው፣ አምላክን ለማስደሰት የቀሰሙትን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ ይህን የእውነት ምሳሌ አጥብቀው መያዝ ነበረባቸው።

7. ክርስቲያኖች የጤናማውን ቃል ምሳሌ አጥብቀው መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ሄሜኔዎስ፣ እስክንድሮስ እና ፊሊጦስ ያሉ ሰዎች ‘ለጤናማው ቃል ምሳሌ’ የማይስማማ ትምህርት ያስፋፉ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:​18-20፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​16, 17) ታዲያ የጥንት ክርስቲያኖች በከሐዲዎች ትምህርት እንዳይወሰዱ ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ጽሑፎች በጥንቃቄ በማጥናትና በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ነው። የጳውሎስንና የሌሎች ታማኝ አገልጋዮችን ምሳሌ የሚከተሉ ክርስቲያኖች ከተማሩት የእውነት ምሳሌ ጋር የማይጣጣም ማንኛውንም ትምህርት ለይተው ማወቅና ማስወገድ ችለዋል። (ፊልጵስዩስ 3:​17፤ ዕብራውያን 5:​14) ‘ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ከመናፈቅ’ ይልቅ በትክክለኛው ለአምላክ የማደር ባሕርይ ወደፊት መጓዛቸውን ቀጥለዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​3-6) እኛም የተማርናቸውን እውነቶች በሥራ ላይ ማዋላችንን ስንቀጥል ተመሳሳይ ነገር እናደርጋለን። በመላው ምድር ላይ ይሖዋን የሚያገለግሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተማሯቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ምሳሌዎች አጥብቀው እንደያዙ መመልከት ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነው።​—⁠1 ተሰሎንቄ 1:​2-5

‘ከተረት’ ራቁ

8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት የሚጥረው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:​3, 4 ላይ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?

8 ሰይጣን በተማርናቸው ትምህርቶች ላይ ጥርጣሬ በመዝራት ጽኑ አቋማችንን ለማበላሸት ይጥራል። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ከሐዲዎችና ሌሎች የቅን ክርስቲያኖችን እምነት ለማጥፋት ይጥራሉ። (ገላትያ 2:​4፤ 5:​7, 8) አንዳንድ ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን አማካኝነት ስለ ይሖዋ ሕዝቦች እንቅስቃሴና ዓላማ የተዛባ አልፎ ተርፎም የሐሰት ወሬ ያሰራጫሉ። ጳውሎስ እንዳስጠነቀቀው አንዳንዶች እውነትን ይተዋሉ። “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፣ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ” በማለት ጽፏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

9. ጳውሎስ ‘ተረት’ ብሎ ሲናገር በአእምሮው የያዘው ምን ሊሆን ይችላል?

9 አንዳንዶች የጤናማውን ቃል ምሳሌ ከመያዝ ይልቅ ‘በተረት’ ተስበው ነበር። እነዚህ ተረቶች ምንድን ናቸው? ምናልባት ጳውሎስ በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ጦቢት ያሉ ምናባዊ አፈ ታሪኮችን አስመልክቶ መናገሩ ሊሆን ይችላል። a እነዚህ ተረቶች ስሜት የሚመስጡና ግምታዊ ሐሳቦችን የሚያካትቱ ሊሆኑ ይችላል። ከዚህም በላይ አንዳንዶች አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች አቅልሎ የማየት አመለካከትን በሚያራምዱ ወይም በጉባኤ ውስጥ ግምባር ቀደም ሆነው በሚያገለግሉ ወንዶች ላይ ነቀፋ በሚሰነዝሩ ሰዎች ተታልለው “እንደ ገዛ ምኞታቸው” መመላለስ ጀምረው ይሆናል። (3 ዮሐንስ 9, 10፤ ይሁዳ 4) ሰበብ የሆናቸው ነገር ምንም ይሁን ምን አንዳንዶች ከአምላክ ቃል እውነት ይልቅ ውሸትን እንደመረጡ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ብዙም ሳይቆይ የተማሯቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋል ያቆሙ ሲሆን ይህም በመንፈሳዊነታቸው ላይ ውድቀት አስከትሎባቸዋል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​15, 16

10. በጊዜያችን የሚነገሩ አንዳንድ ተረቶች የትኞቹ ናቸው? ሐዋርያው ዮሐንስ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

10 እኛም የምናዳምጠውንና የምናነበውን ነገር በጥንቃቄ የምንመርጥ ከሆነ ተማርከን ተረት አናዳምጥም። ለምሳሌ ያህል አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን የሥነ ምግባር ብልግና ይቀርባል። ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ወይም ከነጭራሹ አምላክ የሚባል የለም የሚል ትምህርት ያስፋፋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ በሚናገረው ሐሳብ ላይ ይሳለቃሉ። እንዲሁም በዘመናችን ያሉ ከሃዲዎች የክርስቲያኖችን እምነት ለማዳከም የጥርጣሬ ዘር ለመዝራት ጥረት ያደርጋሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሐሰተኛ ነቢያት የፈጠሩትን ተመሳሳይ አደጋ በተመለከተ ሲያስጠነቅቅ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” ብሏል። (1 ዮሐንስ 4:1) ስለዚህ ጠንቃቃ መሆን ይገባናል።

11. በሃይማኖት እንደምንኖር ራሳችንን መፈተንና መመርመር የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

11 ጳውሎስ ይህን በማስመልከት “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 13:​5) ሐዋርያው ከአጠቃላዩ የክርስትና እምነት ጋር ተስማምተን የምንኖር መሆናችንን ለማወቅ አለማቋረጥ ራሳችንን እንድንመረምር አሳስቦናል። ባላቸው የማይረኩ ሰዎች የሚናገሩትን የማዳመጥ ዝንባሌ ካለን ራሳችንን በጸሎት መመርመር ይገባናል። (መዝሙር 139:​23, 24) በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስህተት የመለቃቀም ዝንባሌ አለን? ከሆነ፣ ለምን? አንድ ወንድም በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ተጎድተናል? እንደዚያ ከሆነ፣ ለሁኔታው ተገቢ አመለካከት መያዝ እንችላለን? በዚህ ሥርዓት የሚደርስብን ማንኛውም ዓይነት መከራ ጊዜያዊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:​17) በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን እንኳ አምላክን ማገልገል የምናቆምበት ምን ምክንያት አለ? የተጎዳንበት ነገር ካለ ችግሩን ለመፍታት የቻልነውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ መተዉ የተሻለ አይሆንም?​—⁠መዝሙር 4:​4፤ ምሳሌ 3:​5, 6፤ ኤፌሶን 4:​26

12. የቤሪያ ሰዎች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት ነው?

12 የተቺነት ዝንባሌ ከመያዝ ይልቅ በግል ጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት ለምናገኛቸው ትምህርቶች በመንፈሳዊ ጤናማ የሆነ አመለካከት እንያዝ። (1 ቆሮንቶስ 2:​14, 15) ደግሞም የአምላክን ቃል ከመጠራጠር ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቅ ይመረምሩ የነበሩትን የቤሪያ ሰዎች ዝንባሌ መያዙ ምንኛ የተሻለ ነው! (ሥራ 17:​10, 11) እንዲሁም ከተረት ርቀን እውነትን አጥብቀን በመያዝ የተማርነውን በሥራ ላይ እናውል።

13. እንደ ተረት ያለ መሠረተ ቢስ ወሬ ሳናስበው ልናሰራጭ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ልናስወግደው የሚገባ ሌላም የተረት ዓይነት አለ። አብዛኛውን ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰራጩ እጅግ በርካታ ቀልብ የሚስቡ ዘገባዎች አሉ። በተለይ አንድ መረጃ ከማን እንደተላከ የማናውቅ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረጋችን ጥበብ ነው። አንድ ተሞክሮ ወይም ታሪክ የደረሰን ከአንድ ከምናምነው ክርስቲያን ቢሆንም እንኳ ግለሰቡ እውነታዎቹን በተመለከተ በቀጥታ የሚያውቀው ነገር ላይኖር ይችላል። ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ለሌሎች ማውራትን ወይም መላክን በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ‘እግዚአብሔርን የማያስከብር ርባና ቢስ አፈ ታሪክ’ [አ.መ.ት ] ወይም ‘ለዚህ ዓለም የሚመች ተረት’ ለሌሎች ማውራት እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​7) በተጨማሪም እርስ በርሳችን እውነትን የመነጋገር ግዴታ ስላለብን ሳናስበው ውሸት እንድንናገር የሚያደርገንን ማንኛውንም ነገር ማስወገዳችን የጥበብ እርምጃ ነው።​—⁠ኤፌሶን 4:​25

እውነትን በተግባር ማዋል የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

14. ከአምላክ ቃል የቀሰምናቸውን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

14 በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት የምንቀስማቸውን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል በእምነት ከሚዛመዱን ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እየተሻሻለ ሊሄድ ይችላል። (ገላትያ 6:​10) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ስናውል በአመለካከታችን የተሻለ ለውጥ እናደርጋለን። (መዝሙር 19:​8) በተጨማሪም የቀሰምናቸውን ትምህርቶች ተግባራዊ ካደረግን ‘የእግዚአብሔርን ትምህርት የምናስመሰግን’ እንዲሁም ሌሎች በእኛ ተስበው ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመጡ ልናደርግ እንችላለን።​—⁠ቲቶ 2:​6-10

15. (ሀ) አንዲት ወጣት በትምህርት ቤት ለመመስከር ድፍረት ያሳየችው እንዴት ነው? (ለ) ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

15 መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በግል በማጥናት እንዲሁም አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የተማሯቸውን ነገሮች በሥራ ላይ የሚያውሉ በርካታ ወጣቶች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ይገኛሉ። መልካም ጠባያቸው በትምህርት ቤት ውስጥ ለአስተማሪዎችና አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆች ከፍተኛ ምሥክርነት ይሰጣል። (1 ጴጥሮስ 2:​12) በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን የ13 ዓመቷን የሌዝሊን ሁኔታ ተመልከት። ስለ እምነቷ ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ መናገር ትፈራ እንደነበር ትናገራለች። ሆኖም አንድ ቀን ሁኔታው ተለወጠ። “ሰዎች ዕቃ ለመሸጥ ሰዎችን እንዴት እንደሚያግባቡ ክፍል ውስጥ ውይይት ተደረገ። አንዲት ልጅ እጅዋን አውጥታ የይሖዋ ምሥክሮችን እንደ ምሳሌ አድርጋ ጠቀሰች።” ሌዝሊ የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኗ መጠን ምን ምላሽ ሰጠች? “እምነቴን ደግፌ መናገር ጀመርኩ። ትምህርት ቤት ውስጥ የምታወቀው በዝምተኛነቴ ስለሆነ መልስ መስጠቴ ሁሉንም ሳያስገርማቸው አልቀረም” ስትል ተናግራለች። ሌዝሊ በድፍረት መናገሯ ምን ውጤት አስገኘ? “ልጅቷ ሌሎች ጥያቄዎችም ስለነበሯት አንድ ብሮሹርና አንድ ትራክት ላበረክትላት ችያለሁ” ስትል ተናግራለች። የተማሩትን በሥራ ላይ የሚያውሉ ወጣቶች በትምህርት ቤት በድፍረት ሲመሰክሩ ይሖዋ ምንኛ ይደሰታል!​—⁠ምሳሌ 27:​11፤ ዕብራውያን 6:​10

16. ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለአንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ጥቅም ያስገኘላት እንዴት ነው?

16 ሌላው ደግሞ የኤልዛቤት ተሞክሮ ነው። ይህች ወጣት ከሰባት ዓመቷ አንስቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ባላት ቁጥር አስተማሪዎቿን ወደ ጉባኤ እንዲመጡ ትጋብዛቸው ነበር። አንድ አስተማሪ ወደ ስብሰባው መምጣት ካልቻለ ኤልዛቤት ከትምህርት ሰዓት በኋላ እዚያው ቆይታ ንግግሩን ለአስተማሪው ታቀርብለታለች። እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በምታጠናቅቅበት ዓመት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በተመለከተ ባለ አሥር ገጽ ሪፖርት የጻፈች ከመሆኑም በላይ አራት አስተማሪዎች በተገኙበት ሪፖርቱን በንግግር አቀረበች። በተጨማሪም ለናሙና የሚሆን የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ንግግር እንድታቀርብ የተጋበዘች ሲሆን በዚህ ጊዜም ለማቅረብ የመረጠችው ርዕስ “አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚል ነበር። ኤልዛቤት የይሖዋ ምሥክሮች በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጡት የትምህርት ፕሮግራም ጥቅም አግኝታለች። ከይሖዋ ቃል የተማሯቸውን ነገሮች ተግባራዊ በማድረግ ለይሖዋ ውዳሴ ከሚያመጡ በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች መካከል ኤልዛቤት አንዷ ብቻ ናት።

17, 18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነትን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል? (ለ) አንድ ሰው አንድ የይሖዋ ምሥክር ባሳየው የሐቀኝነት ባሕርይ የተነካው እንዴት ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሁሉም ነገር በሐቀኝነት እንዲመላለሱ ይመክራቸዋል። (ዕብራውያን 13:​18) ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር ከሰዎች፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከራሱ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። (ምሳሌ 12:​22) እምነት የሚጣልብን መሆናችን የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ላይ እንደምናውል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ከዚህም በላይ ብዙዎች ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍ ያለ አክብሮት እንዲኖራቸው አድርጓል።

18 የጦር ሠራዊት አባል የሆነው ፊሊፕ ያጋጠመውን ሁኔታ ተመልከት። የገንዘቡ መጠን ያልተጻፈበት ሆኖም የተፈረመበት የባንክ ቼክ ጣለ። ይሁን እንጂ በፖስታ ቤት በኩል እስኪመለስለት ድረስ መጥፋቱን አላወቀም ነበር። ቼኩን ያገኘው አንድ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ቼኩን እንዲመልስ ያደረገው ሃይማኖታዊ እምነቱ እንደሆነ የሚገልጽ ማስታወሻ አያይዞ ላከ። ፊሊፕ ነገሩን ማመን አቃተው። “ያለኝን 9, 000 የአሜሪካ ዶላር ጥርግ አድርጎ መውሰድ ይችል ነበር!” ሲል ተናገረ። በሌላ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባርኔጣው በመሰረቁ ምክንያት በጣም አዝኖ ነበር። የሚያውቀው ሰው ባርኔጣውን ሲሰርቀው ከእሱ ጋር ምንም ትውውቅ የሌለው ሰው ግን በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ያለው ቼክ መመለሱ የሚያስገርም ነበር! በእርግጥም ሐቀኛ የሆኑ ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላክን ያስከብራሉ!

የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉ

19, 20. ካገኘናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ጋር ተስማምተን በመኖራችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

19 ከአምላክ ቃል የተማሯቸውን ነገሮች ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች በርካታ ጥቅሞች ያገኛሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:25) አዎን፣ ከተማርናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ጋር ተስማምተን ከኖርን እውነተኛ ደስታ እናገኛለን እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተጽዕኖዎች በተሻለ ብቃት እንቋቋማለን። ከሁሉም በላይ የይሖዋን በረከት እናገኛለን፤ የዘላለም ሕይወት ተስፋም ይኖረናል!​—⁠ምሳሌ 10:​22፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​6

20 በመሆኑም በተቻላችሁ መጠን የአምላክን ቃል ማጥናታችሁን ቀጥሉ። ከይሖዋ አምላኪዎች ጋር አዘውትራችሁ ተሰብሰቡ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች በጥሞና ተከታተሉ። የተማራችሁትን በሥራ ላይ ማዋላችሁን ቀጥሉ፤ “የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​9

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጽሐፈ ጦቢት በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደተጻፈ የሚገመት ሲሆን ጦቢያስ ስለተባለ አንድ አይሁዳዊ ሰው የሚናገር በአጉል እምነት የተሞላ ታሪክ ነው። ይህ ሰው የአንድ አስፈሪ አሣ ልብ፣ የሐሞት ከረጢትና ጉበት በመጠቀም በሽታ የመፈወስና አጋንንት የማውጣት ኃይል እንዳለው ይነገርለት ነበር።

ታስታውሳለህን?

• ‘የጤናማው ቃል ምሳሌ’ ምንድን ነው? ይዘን መቀጠል የምንችለውስ እንዴት ነው?

• ልናስወግዳቸው የሚገቡ ‘ተረቶች’ የትኞቹ ናቸው?

• ከአምላክ ቃል የቀሰሟቸውን ትምህርቶች በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ምን ጥቅሞች ያገኛሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንት ክርስቲያኖች በከሐዲዎች ከመወሰድ እንዴት መራቅ ይችሉ ነበር?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥርጣሬ ዘር በመገናኛ ብዙሐን፣ በኢንተርኔትና በዘመናዊ ከሐዲዎች ሊሰራጭ ይችላል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያልተረጋገጠ ወሬ ማሰራጨት ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ቃል ያነበቡትን በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች ተግባራዊ ያደርጋሉ