በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጨረሻው እየቀረበ በሄደ መጠን ታዛዥነትን አዳብሩ

መጨረሻው እየቀረበ በሄደ መጠን ታዛዥነትን አዳብሩ

መጨረሻው እየቀረበ በሄደ መጠን ታዛዥነትን አዳብሩ

“የአሕዛብ መታዘዝም [ለሴሎ] ይሆናል።”​—⁠ዘፍጥረት 49:10

1. (ሀ) በቀደሙት ዘመናት ይሖዋን መታዘዝ እነማንን መታዘዝንም ይጨምር ነበር? (ለ) ያዕቆብ ታዛዥነትን በሚመለከት ምን ትንቢት ተናግሯል?

 ይሖዋን መታዘዝ ለወኪሎቹ ታዛዥ መሆንንም ያጠቃልላል። ይህም ለመላእክት፣ ለፓትርያርኮች፣ ለመሳፍንት፣ ለካህናትና ለነገሥታት ታዛዥ መሆን ማለት ነው። የእስራኤል ነገሥታት የሚቀመጡበት ዙፋን እንኳን ሳይቀር የይሖዋ ዙፋን ተብሎ ተጠርቷል። (1 ዜና መዋዕል 29:​23 አ.መ.ት) የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ የእስራኤል ገዥዎች አምላክን ሳይታዘዙ ቀርተዋል፤ ይህም በራሳቸውና በዜጎቻቸው ላይ ወዮታ አምጥቷል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲሁ ያለ ተስፋ አልተዋቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ጻድቅ የሆኑ ሰዎች በደስታ የሚታዘዙለት ዘላለማዊ ንጉሥ እንደሚሾምላቸው ቃል በመግባት አጽናንቷቸዋል። (ኢሳይያስ 9:​6, 7) ፓትርያርኩ ያዕቆብ በሞት አፋፍ ላይ ሳለ ይህንን ገዥ በሚመለከት “‘ሴሎ’ ተብሎ የሚጠራው፣ ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለትና ለዘላለም የሚነግሠው እስኪመጣ ድረስ፣ በትረ መንግሥት (የገዥነት ሥልጣን) ከይሁዳ እጅ አይወጣም” በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 49:​10 የ1980 ትርጉም

2. “ሴሎ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ንጉሣዊ አገዛዙስ እነማንን ይጨምራል?

2 “ሴሎ” የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን “ባለቤት የሆነው” ወይም “ባለ መብት የሆነው” የሚል ትርጉም አለው። አዎን ሴሎ በበትር እንደተወከለው የመግዛት ሙሉ መብትና በገዥ ዘንግ እንደተወከለው የአዛዥነት ሥልጣን ይሰጠዋል። ከዚህም በላይ ንጉሣዊ አገዛዙ የያዕቆብን ዘሮች ብቻ ሳይሆን መላውን ‘ሕዝብ’ የሚያቅፍ ነው። ይህም ይሖዋ “ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” በማለት ለአብርሃም ከሰጠው ተስፋ ጋር የሚስማማ ነው። (ዘፍጥረት 22:17, 18) ይሖዋ በ29 እዘአ የናዝሬቱ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በቀባው ጊዜ የዚህን “ዘር” ማንነት ግልጽ አድርጓል።​—⁠ሉቃስ 3:​21-23, 34፤ ገላትያ 3:​16

የኢየሱስ የመጀመሪያ መንግሥት

3. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ የተረከበው የትኛውን አገዛዝ ነው?

3 ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንዳረገ ወዲያውኑ በዓለም ሕዝብ ላይ የመግዛት ሥልጣኑን አልተረከበም። (መዝሙር 110:​1) ይሁን እንጂ ታዛዥ የሆኑ ዜጎችን የሚያስተዳድርበትን “መንግሥት” ተረክቧል። ሐዋርያው ጳውሎስ “[አምላክ በመንፈስ የተቀባን ክርስቲያኖችን] ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” ብሎ በመናገር የዚህን መንግሥት ማንነት ገልጿል። (ቆላስይስ 1:13) ይህ የማዳን እርምጃ የጀመረው መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ላይ በፈሰሰበት በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለት ነው።​—⁠ሥራ 2:​1-4፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9

4. ጥንት የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ታዛዥ መሆናቸውን በየትኞቹ መንገዶች አሳይተዋል? ኢየሱስ በቡድን ደረጃ ማንነታቸውን ያሳወቀው እንዴት ነው?

4 በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘የክርስቶስ አምባሳደሮች’ ሆነው በመሥራት እንደ እነርሱ የመንፈሳዊው መንግሥት ‘ዜጎች’ የሚሆኑትን ሰዎች በታዛዥነት ሰብስበዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:​20 አ.መ.ት፤ ኤፌሶን 2:​19 አ.መ.ት፤ ሥራ 1:​8) ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሰዎች በንጉሣቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ‘በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ’ ሆነው መኖር ይጠበቅባቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:​10) በቡድን ደረጃ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወይም ታማኝና ልባም መጋቢ ሆነው ያገለግላሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​45፤ ሉቃስ 12:​42

የአምላክን ‘መጋቢ’ መታዘዝ በረከት ያስገኛል

5. ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ ሕዝቡን ያስተምር የነበረው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ሕዝቦቹን ያለ አስተማሪ የተወበት ጊዜ የለም። ለምሳሌ ያህል አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ ዕዝራና ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያላቸው ሌሎች ሰዎች የአምላክን ሕግ ለሕዝቡ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ የአምላክን ቃል ‘እንዲያስተውሉ’ ለመርዳት ‘ያብራሩላቸው’ ነበር።​—⁠ነህምያ 8:​8 NW

6, 7. የባሪያው ክፍል በአስተዳደር አካሉ በኩል ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርብ የቆየው እንዴት ነው? ለባሪያው ክፍል መገዛታችን ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?

6 በ49 እዘአ ግዝረትን በሚመለከት ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ በነበረ ጊዜ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የባሪያው ክፍል የአስተዳደር አካል ሁኔታውን በጸሎት ከመረመረ በኋላ አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ መደምደሚያ ላይ ደረሰ። የደረሱበትን ውሳኔ በደብዳቤ ሲያስታውቁ ጉባኤዎች የተሰጣቸውን መመሪያ ታዘዙ፤ ይህም የአምላክን የተትረፈረፈ በረከት አስገኘላቸው። (ሥራ 15:​6-15, 22-​29፤ 16:​4, 5) ዛሬም በተመሳሳይ ታማኙ ባሪያ በአስተዳደር አካሉ በኩል ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን፣ የደም ቅድስናንና አደገኛ ዕፆችንና ትንባሆን በሚመለከት ለተነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የተለያዩ ማብራሪያዎችን ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 2:​4፤ ሥራ 21:​25፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1) ይሖዋ ሕዝቦቹ ቃሉንና ታማኙን ባሪያ በመታዘዛቸው ምክንያት ባርኳቸዋል።

7 በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች ለባሪያው ክፍል በመታዘዝ ለጌታቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን እንደሚገዙ ያሳያሉ። ያዕቆብ በሞት አፋፍ ላይ ሳለ በተናገረው ትንቢት መሠረት ኢየሱስ በዚህ ዘመን ተጨማሪ ሥልጣን በማግኘቱ እንዲህ ያለው መገዛት ለእኛ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል።

ሴሎ መብት ያለው የምድር ገዥ ሆነ

8. የክርስቶስ ሥልጣን እየጨመረ የመጣው እንዴትና መቼ ነበር?

8 ያዕቆብ በትንቢቱ ውስጥ ለሴሎ ‘ሕዝብ ሁሉ እንደሚታዘዝለት’ ተናግሯል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ክርስቶስ የሚገዛው መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ብቻ አይደለም። ታዲያ እነማንን ይጨምራል? ራእይ 11:​15 ‘የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል’ ሲል መልሱን ይሰጠናል። ኢየሱስ ይህን ሥልጣኑን ያገኘው በትንቢታዊዎቹ ‘ሰባት ዘመናት’ ማብቂያ ላይ ማለትም ‘የአሕዛብ ዘመን’ በተፈጸመበት በ1914 እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። a (ዳንኤል 4:​16, 17፤ ሉቃስ 21:​24) ክርስቶስ “በጠላቶችህም መካከል ግዛ” የተባለው ወይም መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት በማይታይ ሁኔታ ‘መገኘት’ የጀመረው በዚያ ዓመት ነበር።​—⁠ማቴዎስ 24:​3 NW፤ መዝሙር 110:​2

9. ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ሲይዝ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ምንድን ነው? ይህስ መላውን የሰው ዘር በተለይ ደግሞ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት የነካው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ካገኘ በኋላ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ቀንደኛውን ዓመፀኛ ሰይጣንንና አጋንንቱን “ወደ ምድር” መጣል ነበር። እነዚህ ክፉ መናፍስት ወደ ምድር ከተጣሉበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋን መታዘዝ አስቸጋሪ የሚያደርግ ሥርዓት ከመፍጠራቸው ባሻገር በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ወዮታ አምጥተዋል። (ራእይ 12:​7-12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) እንዲያውም ሰይጣን የከፈተው መንፈሳዊ ውጊያው በዋነኛነት ያነጣጠረው ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁት የኢየሱስ ምስክር ባላቸው’ በይሖዋ ቅቡዓንና አጋሮቻቸው በሆኑት ‘በሌሎች በጎች’ ላይ ነው።​—⁠ራእይ 12:17፤ ዮሐንስ 10:16

10. ሰይጣን በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ የከፈተው ውጊያ ስኬታማ እንደማይሆን የሚያሳየው የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜአቸውን ማግኘታቸው ነው?

10 ሰይጣን ሽንፈት መከናነቡ የማይቀር ነው። ምክንያቱም አሁን የምንገኘው “በጌታ ቀን” ውስጥ ሲሆን ኢየሱስም የጀመረውን ‘ድል እንዳያጠናቅቅ’ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር አይኖርም። (ራእይ 1:​10፤ 6:​2) ለምሳሌ ያህል የ144, 000 መንፈሳዊ እስራኤላውያን የመጨረሻ አባላት እንዲታተሙ ያደርጋል። በተጨማሪም ‘አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው ለማይችለው ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ’ ለተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጥበቃ ያደርግላቸዋል። (ራእይ 7:1-4, 9, 14-16) እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች እንደ ቅቡዓኑ ሰማያዊ ዜግነት ያላቸው ሳይሆን የኢየሱስ ምድራዊ ተገዥዎች ናቸው። (ዳንኤል 7:​13, 14) የእጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ማለት ሴሎ በእርግጥም ‘በዓለም መንግሥት’ ላይ ገዥ መሆኑን የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው።​—⁠ራእይ 11:​15

‘ለወንጌል የምንታዘዝበት’ ጊዜ አሁን ነው

11, 12. (ሀ) አሁን ካለው ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚተርፉት እነማን ብቻ ናቸው? (ለ) ‘የዓለም መንፈስ’ ተጽእኖ ያደረገባቸው ሰዎች ምን ባሕርይ አዳብረዋል?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔርን የማያውቁና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙ’ ሰዎች ከአምላክ የበቀል ቀን እንደማያመልጡ በግልጽ ስለሚናገር የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ በሙሉ ታዛዥነትን መማር ይኖርባቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:​8) ይሁን እንጂ አሁን ያለንበት ክፉ ሥርዓትና በውስጡ ተስፋፍቶ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ሕግና መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የማመፅ መንፈስ ለወንጌል ታዛዥ ለመሆን የሚደረገውን ጥረት ተፈታታኝ አድርጎታል።

12 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን በአምላክ ላይ የማመፅ ዝንባሌ ‘የዓለም መንፈስ’ በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:​12) ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህ መንፈስ በሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቊጣ ልጆች ነበርን።”​—⁠ኤፌሶን 2:​2, 3

13. ክርስቲያኖች የዓለም መንፈስ እንዳይጋባባቸው መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

13 ደስ የሚለው የኤፌሶን ክርስቲያኖች በዓመፀኝነት ጎዳና መመላለሳቸውን አልቀጠሉም። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ መንፈስ ራሳቸውን በማስገዛትና የመንፈሱን ምርጥ ፍሬ በብዛት በማጨድ የእርሱ ታዛዥ ልጆች ሆነዋል። (ገላትያ 5:​22, 23) ዛሬም በተመሳሳይ በዓጽናፈ ዓለሙ ውስጥ አቻ የማይገኝለት የአምላክ መንፈስ ‘እያንዳንዱ ሰው ተስፋውን እስከ መጨረሻ እንዲያሳይ’ በማገዝ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለይሖዋ ታዛዥ እንዲሆኑ እየረዳ ነው።​—⁠ዕብራውያን 6:11፤ ዘካርያስ 4:6

14. ኢየሱስ ታዛዥነትን የሚፈትኑ ችግሮችን ለይቶ በመጥቀስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ያስጠነቀቀው እንዴት ነው?

14 ከዚህም በተጨማሪ ሴሎ እንደሚደግፈንና እርሱም ሆነ አባቱ ታዛዥነታችን በአጋንንትና በሰዎች ከአቅማችን በላይ እንዲፈተን እንደማይፈቅዱ መገንዘብ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 10:​13) እንዲያውም ኢየሱስ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ እኛን ለማገዝ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ምን ምን ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ገልጾልናል። ይህንን ያደረገው ሐዋርያው ዮሐንስ በተገለጠለት ራእይ መሠረት በጻፋቸው ሰባት ደብዳቤዎች አማካኝነት ነው። (ራእይ 1:​10, 11) በዚያን ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እነዚህ ደብዳቤዎች ከሚሰጡት ምክር ጥቅም ያገኙ ቢሆንም እንኳ በዋነኛነት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ግን በ1914 በጀመረው ‘በጌታ ቀን’ ውስጥ ነው። በመሆኑም እነዚህን መልእክቶች በትኩረት መከታተላችን ምንኛ የተገባ ነው! b

ግዴለሽነትን፣ የጾታ ብልግናንና ፍቅረ ነዋይን አስወግድ

15. በኤፌሶን ጉባኤ የታየው ችግር እኛንም እንዳያጠቃን ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ጥንቃቄ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 1:​5-8)

15 ኢየሱስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ የላከው በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ ነበር። ኢየሱስ ጉባኤው ያሳየውን ትዕግሥት ካመሰገነ በኋላ “ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 2:1-4) ዛሬም በአንድ ወቅት ቀናተኛ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለአምላክ የነበራቸው የጋለ ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ፈቅደዋል። የፍቅር መቀዝቀዝ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት ስለሚያዳክምበት ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ፍቅርን እንደገና ማደስ የሚቻለው እንዴት ነው? ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ ያለማሰለስ በመጸለይና በማሰላሰል ነው። (1 ዮሐንስ 5:​3) እንዲህ ማድረግ “ትጋትን” እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። (2 ጴጥሮስ 1:​5-8) በዚህ ረገድ ራስህን በሐቀኝነት ስትመረምር ፍቅርህ እንደቀዘቀዘ ሆኖ ከተሰማህ ኢየሱስ “ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ በመታዘዝ ችግሩን ለማስተካከል ፈጣን እርምጃ ውሰድ።​—⁠ራእይ 2:5

16. በጴርጋሞን እና በትያጥሮን ጉባኤዎች ውስጥ ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ተከሰተ? ኢየሱስ ለእነርሱ የሰጣቸው ምክር ዛሬም ቢሆን የሚሠራው እንዴት ነው?

16 በጴርጋሞንና በትያጥሮን የነበሩ ክርስቲያኖች ታማኝነትን፣ ጽናትንና ቅንዓትን በማሳየታቸው ተመስግነዋል። (ራእይ 2:​12, 13, 18, 19) ሆኖም በጾታ ብልግናና በበኣል አምልኮ የጥንቱን እስራኤል ያረከሱትን የበለዓምንና የኤልዛቤልን መንፈስ በሚያንጸባርቁ አንዳንድ ሰዎች ተጽእኖ ተሸንፈው ነበር። (ዘኍልቍ 31:16፤ 1 ነገሥት 16:​30, 31፤ ራእይ 2:14, 16, 20-23) በዚህ ‘በጌታ ቀንስ’ ሁኔታው ምን ይመስላል? እንዲህ ያለው መጥፎ ተጽእኖ አሁንም ይታያል? አዎን፣ በአምላክ ሕዝቦች ውስጥ ለሚፈጸመው ውገዳ ዋነኛው መንስዔ የጾታ ብልግና ነው። እንግዲያው በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጪ በሥነ ምግባር መጥፎ ተጽእኖ ሊያሳድሩብን ከሚችሉ ግለሰቦች ጋር ፈጽሞ ወዳጅነት እንዳንመሠርት ጥንቃቄ ማድረጋችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! (1 ቆሮንቶስ 5:​9-11፤ 15:​33) ሴሎን በመታዘዝ ለእርሱ መገዛት የሚፈልጉ ሁሉ አጠያያቂ ከሆኑ መዝናኛዎች እንዲሁም በጽሑፍና በኢንተርኔት ከሚሰራጩ ወሲባዊ ሥዕሎች ይርቃሉ።​—⁠አሞጽ 5:​15፤ ማቴዎስ 5:​28, 29

17. በሰርዴስ እና በሎዶቅያ የነበሩት ጉባኤዎች ስለራሳቸው የነበራቸው አመለካከትና ዝንባሌ ኢየሱስ መንፈሳዊ ሁኔታቸውን በተመለከተ ለእነርሱ ከነበረው አመለካከት ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

17 ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር በሰርዴስ የሚገኘው ጉባኤ ምንም ዓይነት የምስጋና ቃል አላገኘም። ጉባኤው “ስም” ያለው ወይም ሕያው የሆነ ቢመስልም እንኳ ለመንፈሳዊ ነገር ከፍተኛ የግዴለሽነት መንፈስ ተጠናውቶት ስለነበር በኢየሱስ ፊት እንደ ‘ሞተ’ ያህል ተቆጥሮ ነበር። ወንጌሉን የሚታዘዘው እንዲያው በዘልማድ ስለነበር መወገዙ የሚገባው ነበር! (ራእይ 3:​1-3) የሎዶቅያ ጉባኤም ከዚህ ባልተለየ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር። በቁሳዊ ነገሮች ‘ሃብታም ነኝ’ እያለ ይኩራራ የነበረ ቢሆንም ክርስቶስ “ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም” ነህ በማለት ተናግሮታል።​—⁠ራእይ 3:14-17

18. አንድ ሰው በአምላክ ፊት በመንፈሳዊ ለብ ያለ ከመሆን የሚድነው እንዴት ነው?

18 ዛሬም ቢሆን በአንድ ወቅት ታማኝ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ የሆነ ያለመታዘዝ መንፈስ አንጸባርቀዋል። የዓለም መንፈስ የጥድፊያ ስሜታቸውን ቀስ በቀስ እንዲሸረሽርባቸው ፈቅደው ሊሆን ይችላል ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለጸሎት፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለአገልግሎት ያላቸው አመለካከት ለብ ያለ ሆኗል። (2 ጴጥሮስ 3:​3, 4, 11, 12) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች መንፈሳዊውን ሃብት ወይም “በእሳት የነጠረውን ወርቅ” እንዲገዙ ክርስቶስ የሰጣቸውን ትእዛዝ ቢቀበሉ ምንኛ ይጠቀማሉ! (ራእይ 3:​18) ይህ እውነተኛ ሃብት ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጋ መሆንን፣ መርዳትንና ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ መሆንን’ ይጨምራል። በእርግጥም እጅግ ውድ የሆኑትን እነዚህን መንፈሳዊ ሃብቶች በመግዛት ‘እውነተኛውን ሕይወት እንድንይዝ የሚያስችለንንና ለሚመጣው ዘመን መልካም መሠረት የሚሆንልንን መዝገብ ለራሳችን እናከማች።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​17-19

ታዛዥ በመሆናቸው ተመስግነዋል

19. ኢየሱስ በሰምርኔስና በፊልድልፍያ ለነበሩ ክርስቲያኖች ምን በማለት አመስግኗቸዋል? ምን ጥብቅ ማሳሰቢያስ ሰጥቷቸዋል?

19 ኢየሱስ በሰምርኔስና በፊልድልፍያ ለነበሩ ጉባኤዎች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ምንም ዓይነት የወቀሳ ቃል አለመኖሩ በታዛዥነት ረገድ ግሩም ምሳሌ እንደሚሆኑ ያሳያል። በሰምርኔስ የሚገኙት ክርስቲያኖችን “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፣ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ” ብሏቸዋል። (ራእይ 2:9) በመንፈሳዊ ድሆች ሆነው ሳለ በዓለማዊ ሃብታቸው ይኩራሩ ከነበሩት የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ጋር ሲወዳደሩ ምንኛ የተለዩ ነበሩ! እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ሰው ለክርስቶስ ታማኝና ታዛዥ ሲሆን ማየት ዲያብሎስን አያስደስተውም። ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፣ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፣ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” (ራእይ 2:10) በተመሳሳይም ኢየሱስ በፊልድልፍያ የነበሩ ክርስቲያኖችን “ቃሌን ጠብቀሃልና፣ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ፣ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ” በማለት አመስግኗቸዋል።​—⁠ራእይ 3:8, 11

20. ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስን ቃል የጠበቁት እንዴት ነው? ይህን ያደረጉት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነው?

20 የታመኑ ቀሪዎችና በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው በሚልዮን የሚቆጠር የሆኑት ሌሎች በጎች በ1914 በጀመረው በዚህ ‘የጌታ ቀን’ ውስጥ በአገልግሎት በቅንዓት በመካፈልና ከጽኑ አቋማቸው ዝንፍ ባለማለት የኢየሱስን ቃል ጠብቀዋል። ክርስቶስን በመታዘዛቸው ምክንያት አንዳንዶቹ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞቻቸው እስር ቤትና ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ መጣልን ጨምሮ ልዩ ልዩ መከራዎች ተፈራርቀውባቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ በቃኝን በማያውቀውና ስግብግብ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ቢኖሩም ‘ቀና ዓይን’ በመያዝ የኢየሱስን ቃል ጠብቀዋል። (ማቴዎስ 6:​22, 23 NW ) አዎን፣ በየትኛውም አካባቢ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ታዛዥነትን በማሳየት የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘታቸውን ይቀጥላሉ።​—⁠ምሳሌ 27:​11

21. (ሀ) የባሪያው ክፍል የትኞቹን መንፈሳዊ ኃላፊነቶች መወጣቱን ቀጥሏል? (ለ) ሴሎን ከልብ መታዘዝ እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

21 ወደ ታላቁ መከራ በተቃረብን መጠን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከአቋሙ ፍንክች ሳይል ለጌታው ለክርስቶስ መታዘዙን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ይህም ለአምላክ ቤተሰቦች ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማዘጋጀትን ይጨምራል። በመሆኑም ግሩም የሆነውን የይሖዋን ቲኦክራሲያዊ ድርጅትና የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ ማድነቃችንን እንቀጥል። በዚህ መንገድ ለሚታዘዙት ተገዥዎቹ በሙሉ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ለሚባርካቸው ለሴሎ ራሳችንን የምናስገዛ መሆናችንን እናሳያለን።​—⁠ማቴዎስ 24:​45-47፤ 25:​40፤ ዮሐንስ 5:​22-24

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ “ሰባት ዘመናት” ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት።

b ስለ ሰባቱ ደብዳቤዎች ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ​—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 33 ጀምሮ ተመልከት።

ታስታውሳለህን?

• ያዕቆብ ሞት አፋፍ ላይ እያለ በተናገረው ትንቢት መሠረት ኢየሱስ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?

• ኢየሱስ ሴሎ መሆኑን እንደምንቀበል የምናሳየው እንዴት ነው? የትኛውን መንፈስስ ማስወገድ ይኖርብናል?

• በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ለተጠቀሱት ሰባት ጉባኤዎች በተላከው ደብዳቤ ላይ ለዘመናችን የሚሆን ምን ጠቃሚ ምክር ይገኛል?

• በጥንቶቹ ሰምርኔስና በፊልድልፍያ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ያሳዩትን ምሳሌ በየትኞቹ መንገዶች መኮረጅ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሕዝብ ታማኙን “መጋቢ” ስለሚታዘዝ ይባረካል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰይጣን ተጽእኖ ለአምላክ መታዘዝን ፈታኝ ያደርግብናል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ ጋር የምንመሠርተው ጠንካራ ወዳጅነት ለእርሱ ታዛዥ እንድንሆን ይረዳናል