በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ራስህን አሠልጥን”

“ራስህን አሠልጥን”

“ራስህን አሠልጥን”

በጥንት ዘመን በግሪክና ሮም ይኖሩ የነበሩ አትሌቶች ከምንጊዜውም የላቀ ፍጥነትና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጠንክረው ይሠሩ ነበር። ለብዙ መቶ ዓመታት በኦሎምፒያ፣ በደልፊ እና በኒሚያ እንዲሁም በቆሮንቶስ ይዘጋጁ በነበሩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዱ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች በውድድሮቹ ላይ ይገኙ ነበር። በእነዚህ ውድድሮች ላይ የመካፈል መብት ለማግኘት የበርካታ ዓመታት ልምምድ ይጠይቃል። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑት ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ከፍተኛ ክብር ያስገኛሉ።

እንዲህ ዓይነት ውድድር በሚዘወተርበት አካባቢ የኖሩ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች የአትሌቲክስ ውድድሮችን ክርስቲያኖች ለሚያደርጉት መንፈሳዊ ሩጫ ምሳሌ አድርገው መጥቀሳቸው ምንም አያስገርምም። ሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ ለማስተላለፍ የፈለጉትን ነጥብ ጎላ አድርገው ለመግለጽ በእነዚህ ውድድሮች ላይ የተመሠረቱ ምሳሌዎችን በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመዋል። በዘመናችንም ከፍተኛ ትግል የሚጠይቀው ይህ ክርስቲያናዊ ሩጫ ቀጥሏል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የአይሁድ ሥርዓት የሚያሳድርባቸውን ተጽእኖ ለማሸነፍ ይታገሉ የነበረ ሲሆን እኛ ደግሞ ለመጥፋት በቋፍ ላይ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ጋር ‘ትግል’ ገጥመናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​5፤ 3:​1-5) አንዳንዶች በግለሰብ ደረጃ የሚያደርጉት “የእምነት ሩጫ” ማቆሚያ የሌለውና አድካሚ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​12ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን በአትሌቲክስ ውድድሮችና በክርስቲያናዊ ሩጫ መካከል ያሉትን ተመሳሳይ ገጽታዎች መመርመራችን በጣም ይጠቅመናል።

የተዋጣለት አሠልጣኝ

አንድ አትሌት የሚያገኘው ውጤት በአመዛኙ በአሠልጣኙ ላይ የተመካ ነው። በጥንት ዘመን ይካሄዱ የነበሩ ውድድሮችን በተመለከተ አርካይኦሎጂኤ ግራይካ እንዲህ ይላል:- “ተወዳዳሪዎቹ ልምምድ በማድረግ ድፍን አሥር ወር ማሳለፋቸውን ለማረጋገጥ ቃለ መሃላ የመፈጸም ግዴታ ነበረባቸው።” ክርስቲያኖችም እንዲሁ ከፍተኛ ሥልጠና ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ጳውሎስ የጉባኤ ሽማግሌ ለሆነው ለጢሞቴዎስ “ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን” የሚል ምክር ሰጥቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​7 አ.መ.ት ) የአንድ ክርስቲያን “አትሌት” አሠልጣኝ ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም! ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጸጋ ሁሉ አምላክ . . . ራሱ ፍጹማን [“ሥልጠናችሁን እንድትፈጽሙ፣” NW ] ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” ሲል ጽፏል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​10

“ሥልጠናችሁን እንድትፈጽሙ ያደርጋችኋል” የሚለው አባባል ከግሪክኛ ግስ የተገኘ ሲሆን ቲኦሎጂካል ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚለው ከሆነ “አንድን ነገር [ወይም ሰው] ለተፈለገው ዓላማ ብቁ ማድረግ፣ የታቀደለትን ሥራ እንዲያከናውን ማዘጋጀትና ማመቻቸት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። በተመሳሳይ በሊደል እና በስኮትስ የተዘጋጀው ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን የተባለ መዝገበ ቃላት ይህ ግስ “ማዘጋጀት፣ ማሠልጠን ወይም በሚገባ ማስታጠቅ” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይናገራል። ይሖዋ ከባድ ለሆነው ክርስቲያናዊ ሩጫ ‘የሚያዘጋጀን፣ የሚያሠለጥነን ወይም በሚገባ የሚያስታጥቀን’ በምን መንገዶች ነው? የሁለቱን ተመሳሳይነት መረዳት እንድንችል አሠልጣኞች የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ ዘዴዎች እስቲ እንመልከት።

ዚ ኦሊምፒክ ጌምስ ኢን ኤንሸንት ግሪስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ለወጣቶች ሥልጠና የሚሰጡ ሰዎች ሁለት መሠረታዊ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። የመጀመሪያው ሠልጣኙ ከሁሉ የተሻለውን ውጤት ማግኘት እንዲችል አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ እንዲያደርግ በማበረታታት ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚጠቀምበትን ስልትና ዘዴ እንዲያሻሽል በመርዳት ላይ ያተኮረ ነበር።”

በተመሳሳይ ይሖዋ በአገልግሎቱ አቅማችን የፈቀደውን ያህል እንድንሠራና ችሎታችንን እንድናሻሽል ማበረታቻና ጥንካሬ ይሰጠናል። አምላካችን በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በምድራዊ ድርጅቱና በጎለመሱ ክርስቲያኖች አማካኝነት ብርታት ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ ተግሳጽ በመስጠት ያሠለጥነናል። (ዕብራውያን 12:​6) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ልዩ ልዩ ፈተናዎችና መከራዎች እንዲደርሱብን በመፍቀድ ጽናት እንድናዳብር ሊያደርግ ይችላል። (ያዕቆብ 1:​2-4) እንዲሁም ይሖዋ አስፈላጊውን ጥንካሬ ይሰጠናል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ . . . ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።”​—⁠ኢሳይያስ 40:31

ከሁሉም በላይ አምላክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ማቅረባችንን እንድንቀጥል ለመርዳት ብርታት የሚጨምርልንን ቅዱስ መንፈሱን አብዝቶ ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:​13) በበርካታ አጋጣሚዎች የአምላክ አገልጋዮች ለረጅም ጊዜ የዘለቁ ከባድ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት አሳልፈዋል። የደረሰባቸውን ፈተና በጽናት ያሳለፉት እነዚህ ወንዶችና ሴቶች እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ሆኖም ትምክህታቸውን ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ መጣላቸው እንዲጸኑ አስችሏቸዋል። በእርግጥም ለመጽናት የሚያስችለው ይህ ‘ታላቅ ኃይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእነርሱ የመነጨ አይደለም።’​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7

አሳቢ የሆነ አሠልጣኝ

በጥንት ጊዜ አንድ አሠልጣኝ ካሉት ኃላፊነቶች አንዱ “ለእያንዳንዱ አትሌትና ለሚወዳደርበት የስፖርት ዓይነት የሚያስፈልገውን ልምምድና በቀን ስንት ጊዜ መደረግ እንዳለበት መወሰን” ነበር ሲሉ አንድ ምሁር ተናግረዋል። አምላክ ሥልጠና ሲሰጠን በግለሰብ ደረጃ ያለንበትን ሁኔታ፣ ችሎታዎቻችንን፣ አፈጣጠራችንንና አቅማችንን ግምት ውስጥ ያስገባል። አብዛኛውን ጊዜ ይሖዋ ሥልጠና በሚሰጠን ወቅት “እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ” ሲል ኢዮብ ያቀረበውን ዓይነት ልመና እናሰማለን። (ኢዮብ 10:​9) አሳቢ የሆነው አሠልጣኛችን ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? ዳዊት ስለ ይሖዋ “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” ሲል ጽፏል።​—⁠መዝሙር 103:14

በአገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ የሚገድብ አንድ ከባድ የጤና እክል ይኖርብህ ወይም ለራስህ ካለህ አፍራሽ አመለካከት ጋር እየታገልክ ይሆናል። ምናልባት ከአንድ መጥፎ ልማድ ለመላቀቅ እየታገልክ አሊያም በሰፈር፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት የሚያጋጥምህን የእኩዮች ተጽዕኖ በድፍረት መጋፈጥ እንደማትችል ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ከአንተው ከራስህም ሆነ ከሌላ ከማንም ሰው በላይ ችግርህን እንደሚረዳልህ ፈጽሞ አትዘንጋ! ወደ እሱ ከቀረብህ አንድ አሳቢ አሠልጣኝ እንደሚያደርገው ሁሉ አንተን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው።​—⁠ያዕቆብ 4:​8

በጥንት ዘመን የነበሩ አሠልጣኞች “በልምምድ ምክንያት ሳይሆን በሥነ ልቦና ችግር፣ በመንፈስ ጭንቀት ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች ሳቢያ የተፈጠረን ድካም ለይተው ማወቅ ይችሉ ነበር . . . የአሠልጣኞቹ ሥልጣን በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የአትሌቶቹን የግል ሕይወት ይከታተሉ የነበረ ሲሆን አስፈላጊ እንደሆነ ሲሰማቸው ጣልቃም ይገቡ ነበር።”

ይህ ዓለም ከሚያደርስብህ የማያባራ ተጽዕኖና ፈተና የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ኃይልህ እንደተሟጠጠ ወይም አቅም እንዳጣህ ሆኖ ይሰማሃል? ይሖዋ አሠልጣኝህ እንደመሆኑ መጠን ስለ አንተ በጣም ያስባል። (1 ጴጥሮስ 5:​7) ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ድካም ወይም ችግር ቢኖርብህ በቀላሉ ማስተዋል ይችላል። ይሖዋ ነፃነታችንንና የግል ምርጫችንን ያከብርልናል። ሆኖም ለዘላለማዊ ደኅንነታችን በማሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በቂ እርዳታና እርማት ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 30:​21) እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ በጉባኤ በሚገኙ መንፈሳዊ ሽማግሌዎች እንዲሁም አፍቃሪ በሆነው የወንድማማች ማኅበራችን አማካኝነት ነው።

‘በነገር ሁሉ ሰውነትን መግዛት’

እርግጥ ነው፣ አንድ አትሌት ጥሩ አሠልጣኝ ማግኘቱ ብቻውን ለውጤት አያበቃውም። ስኬታማነቱ በራሱ በአትሌቱና አድካሚ የሆነውን ሥልጠና ለማድረግ በሚያሳየው ቁርጠኝነት ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። ሥልጠናው ከአንዳንድ ነገሮች መታቀብንና የተሰጠውን የአመጋገብ ሥርዓት መከተልን ስለሚያጠቃልል መመሪያው በጣም ጥብቅ ነበር ማለት ይቻላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረው ሆራስ የተባለ ባለቅኔ ተወዳዳሪዎቹ “ተፈላጊው ግብ ላይ ለመድረስ ከሴትና ከመጠጥ ይርቁ” እንደነበር ተናግሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኤፍ ሲ ኩክ እንዳሉትም በውድድሮቹ የሚካፈሉት ሰዎች “ለአሥር ወራት ያህል ራሳቸውን መግዛት [እና] የተፈቀደላቸውን ምግብ ብቻ መመገብ” ነበረባቸው።

ጳውሎስ በአቅራቢያቸው የሚካሄዱትን የኢስሚያን ውድድሮች በደንብ ለሚያውቁት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህን ጉዳይ ምሳሌ አድርጎ ጠቅሶታል። (1 ቆሮንቶስ 9:​25) እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ከሚታየው የፍቅረ ነዋይ፣ የብልግናና የረከሰ አኗኗር ይርቃሉ። (ኤፌሶን 5:​3-5፤ 1 ዮሐንስ 2:​15-17) በተጨማሪም አምላክን የማያስከብሩና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕርያትን አስወግደው የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት መልበስ ይኖርባቸዋል።​—⁠ቆላስይስ 3:​9, 10, 12

ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” የሚል ኃይለኛ ምሳሌ ተጠቅሞ የሰጠውን መልስ ተመልከት።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​27

ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ ምንኛ ጠንከር ያለ ነው! ይሁንና ጳውሎስ የራስን አካል ማሠቃየት አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አድርጎ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሐሳቡ እርስ በርስ ይዋጋ እንደነበር መግለጹ ነው። አንዳንድ ጊዜ ማድረግ የማይፈልጋቸውን ነገሮች ያደርግ የነበረ ሲሆን ማድረግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ደግሞ ሳያደርግ ይቀር ነበር። ሆኖም ያሉበት ድክመቶች ሕይወቱን እንዲቆጣጠሩት ላለመፍቀድ ከባድ ትግል አድርጓል። ሥጋዊ ፍላጎቶቹንና ዝንባሌዎቹን በማሸነፍ ‘ሥጋውን ጐስሟል።’​—⁠ሮሜ 7:​21-25

ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ጳውሎስ በፊት በዝሙት፣ በጣዖት አምልኮ፣ በግብረ ሰዶም፣ በስርቆትና በሌሎች ድርጊቶች ይካፈሉ የነበሩ በቆሮንቶስ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ለውጥ ማድረጋቸውን ተናግሯል። እንዲለወጡ ያስቻላቸው ምንድን ነው? የአምላክ ቃልና መንፈስ ቅዱስ በሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲሁም ከዚያ ጋር ተስማምተው ለመኖር በወሰዱት ቁርጥ አቋም የተነሳ ነው። ጳውሎስ “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9-11) ጴጥሮስም በተመሳሳይ እንደዚህ ያሉ መጥፎ ልማዶችን ስለተዉ ሰዎች ጽፏል። ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ሁሉም ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​3, 4

በሚገባ የታሰበበት ጥረት ማድረግ

ጳውሎስ ሐሳቡ መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ሲገልጽ “ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። (1 ቆሮንቶስ 9:​26) አንድ ተጋጣሚ እጁን የሚሰነዝረው እንዴት ነው? ዘ ላይፍ ኦቭ ዘ ግሪክስ ኤንድ ሮማንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “ኃይለኛ ቡጢ መሰንዘር ብቻ ሳይሆን የባላጋራን ደካማ ጎኖች ማወቅ ያስፈልግ ነበር። አንድ ተጋጣሚ በትምህርት የሚያገኘው የቡጢ አሰነዛዘር ቴክኒክና ከባላጋራው ልቆ እንዲገኝ የሚያስችለው ቅልጥፍናም እንዲሁ ወሳኝ የሆኑ ነገሮች ናቸው።”

ፍጽምና የሚጎድለው ሥጋችን አንዱ ባላጋራችን ነው። ታዲያ የራሳችንን “ደካማ ጎኖች” ለይተን አውቀናቸዋል? ሌሎች እኛን በሚያዩን መንገድ በተለይ ደግሞ ሰይጣን በሚያየን መንገድ ራሳችንን ለማየት ፈቃደኞች ነን? ይህ ራስን በሐቀኝነት መመርመርንና ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። ራስን መሸንገል ቀላል ነው። (ያዕቆብ 1:​22) ለወሰድነው ጥበብ የጎደለው እርምጃ ሰበብ ማቅረብ በጣም ቀላል ነው! (1 ሳሙኤል 15:​13-15, 20, 21) ይህ ‘ነፋስን ከመጎሰም’ ተለይቶ አይታይም።

በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ይሖዋን ማስደሰትና የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ስህተት ከሆነው ነገር ይልቅ ትክክል የሆነውን፣ ብልሹ ከሆነው ዓለም ይልቅ የአምላክን ጉባኤ ከመምረጥ ማመንታት አይኖርባቸውም። ‘ሁለት አሳብ ይዘው በመንገዳቸው ሁሉ ከመወላወል’ መራቅ አለባቸው። (ያዕቆብ 1:​7, 8) ፍሬ ቢስ የሆኑ ጉዳዮችን በማሳደድ በከንቱ መድከም የለባቸውም። አንድ ሰው ያለ አንዳች ማወላወል ይህን የመሰለ አካሄድ የሚከተል ከሆነ ደስታ የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ ‘ማደጉ በሰው ሁሉ ፊት ይገለጣል።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​15

አዎን፣ ክርስቲያናዊው ሩጫ ገና አላበቃም። ታላቁ አሠልጣኛችን ይሖዋ ለመጽናትና የመጨረሻውን ድል ለመጨበጥ የሚያስችለንን አስፈላጊውን መመሪያና እርዳታ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 48:​17) በጥንት ዘመን እንደነበሩት አትሌቶች ሁሉ እኛም ራሳችንን መገሠጽና ራሳችንን መግዛት ያለብን ከመሆኑም በተጨማሪ በአንድ ልብ ለእምነት መጋደል ይኖርብናል። በዓላማ የምናደርገው ጥረት ከፍተኛ ወሮታ ያስገኝልናል።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ዘይት ይቀቡት’

በጥንቷ ግሪክ ለአትሌቶች ከሚሰጠው ሥልጠና ውስጥ የተወሰነውን ድርሻ የሚያበረክተው ወጌሻው ነበር። የወጌሻው ሥራ ልምምድ ለማድረግ የተዘጋጁትን አትሌቶች ሰውነት ዘይት መቀባት ነው። ዚ ኦሊምፒክ ጌምስ ኢን ኤንሸንት ግሪስ የተባለው መጽሐፍ እንዳስቀመጠው አሠልጣኞቹ “ከልምምድ በፊት የሰውነት ጡንቻዎችን በዘይት ማሸት ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ከዚህም በላይ አንድ አትሌት ረዘም ላለ ሰዓት ልምምድ አድርጎ ሲያበቃ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በቀስታ ቢታሽ ጡንቻው እንዲፍታታና ጉልበቱ እንዲታደስ ሊረዳው እንደሚችል ተገንዝበው” እንደነበር ይናገራል።

ሰውነትን በዘይት ማሸት ዘና ሊያደርግና ፈዋሽ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ አንድን የደከመ ክርስቲያን “አትሌት” ለማበረታታት የአምላክን ቃል መጠቀማችን እንዲስተካከል፣ እንዲጽናናና እንዲፈወስ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም የጉባኤ ሽማግሌዎች በይሖዋ አመራር ሥር ሆነው እንዲህ ዓይነቱን ሰው በምሳሌያዊ አነጋገር ‘በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው’ እንዲጸልዩለት የተመከሩ ሲሆን ይህም ግለሰቡ በመንፈሳዊ እንዲያገግም የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው።​—⁠ያዕቆብ 5:​13-15፤ መዝሙር 141:​5

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሥዋዕት ቀርቦ ሲያበቃ አትሌቶቹ የአሥር ወር ሥልጠና ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ

[ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Copyright British Museum