በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በችግር ጊዜ መጽናኛ ማግኘት

በችግር ጊዜ መጽናኛ ማግኘት

በችግር ጊዜ መጽናኛ ማግኘት

በዛሬው ጊዜ የምንሰማው ዜና ጨርሶ የሚያጽናና አይደለም። አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘የጊዜያችን ሁኔታ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ከመሆኑ የተነሳ ዜና ለመስማት እንኳን ብዙ ጊዜ ድፍረት እናጣለን።’ ዓለም በጦርነት፣ በሽብር ድርጊቶች፣ በመከራና በሥቃይ፣ በወንጀልና በበሽታ ተውጧል። እነዚህ ችግሮች እስካሁን ያልደረሱብን እንኳ ቢሆን ውሎ አድሮ በእኛም ላይ መድረሳቸው አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ እንደሚደርስ አስቀድሞ ተንብዮአል። ኢየሱስ በዚህ በእኛ ዘመን ከባድ ጦርነት፣ መቅሰፍት፣ የምግብ እጥረትና የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚደርስ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:10, 11) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚመጣና ሰዎች ጨካኞች፣ ገንዘብን የሚወዱና መልካም የሆነውን የሚጠሉ እንደሚሆኑ ጽፏል። ይህን ጊዜ ‘የመጨረሻው ቀን’ ብሎ ጠርቶታል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

በዛሬው ጊዜ ዜናዎች የዓለምን ሁኔታ በተመለከተ የሚያቀርቡት ዘገባ መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት ከተናገረው ጋር የሚመሳሰል ነው። ሆኖም ዜናዎች የዓለምን ሁኔታ ከመግለጽ ያለፈ ነገር የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዜናዎች በተለየ መልኩ ስለ እነዚህ ችግሮች ተጨማሪ መግለጫ ይሰጣል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፋት እንዲህ የገነነበትን ምክንያት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣም ጭምር ለማወቅ ያስችለናል።

አምላክ ለክፋት ያለው አመለካከት

አምላክ በዛሬው ጊዜ ያሉትን አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዴት እንደሚመለከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አምላክ እነዚህ ችግሮች እንደሚመጡ አስቀድሞ ያውቅ የነበረ ቢሆንም በመኖራቸው አይደሰትም ወይም ለዘላለም እንዲቀጥሉም አይፈቅድም። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ለሰዎች ከልብ የሚያስብ ሲሆን ክፋትን ግን ጨርሶ ይጠላል። ይሖዋ ጥሩና ሩኅሩኅ ስለሆነ እንዲሁም ክፋትን ከምድር ገጽ ለማስወገድ ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ ስላለው መጽናኛ ለማግኘት ወደ እርሱ ዘወር ማለታችን ተገቢ ነው። መዝሙራዊው “[በአምላክ የተቀባው ሰማያዊው ንጉሥ] ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው” በማለት ጽፏል።​—⁠መዝሙር 72:12-14

መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች አዘኔታ ይሰማሃል? ሳይሰማህ አይቀርም። የተፈጠርነው በይሖዋ አምሳል ስለሆነ ይሖዋ የሌላውን ችግር እንደራስ የመመልከት ባሕርይ በውስጣችን ተክሎብናል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ስለዚህ ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ በቸልታ እንደማይመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋን ከማንም በላይ በቅርብ ያውቀው የነበረው ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለእኛ ከልቡ እንደሚያስብልንና ካንጀቱ እንደሚራራልን አስተምሯል።​—⁠ማቴዎስ 10:29, 31

አምላክ ለሰው ዘር እንደሚያስብ ፍጥረት ራሱ ይመሰክራል። አምላክ “በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:44, 45) ሐዋርያው ጳውሎስም በልስጥራን ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች “[አምላክ] ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም” በማለት ተናግሯል።​—⁠ሥራ 14:17

ለክፋት ተጠያቂው ማን ነው?

ጳውሎስ ለልስጥራን ሰዎች “እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው” ብሎ መናገሩም ትኩረት የሚስብ ነው። በእርግጥም ዛሬ ላሉት ችግሮች በዋነኛነት የሚጠየቁት ብሔራት ወይም ሰዎች ራሳቸው ናቸው። ተጠያቂው አምላክ አይደለም።​—⁠ሥራ 14:16

ይሖዋ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደው ለምንድን ነው? ችግሩን ለማስወገድ አንድ ዓይነት እርምጃ ይወስድ ይሆን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኘው በአምላክ ቃል ውስጥ ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት መልሱ ከአንድ ሌላ መንፈሳዊ አካልና ይህ አካል በዓይን በማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ካስነሳው አንድ ግድድር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች የሌላውን ችግር እንደራሳቸው አድርገው የመመልከት ባሕርይ አላቸው። ታዲያ አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ይበልጥ አይሰማውም?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ በስተግራ፣ ክሮኤሺያ:- UN PHOTO 159208/S. Whitehouse; በረሃብ የተጠቃ ሕፃን:- UN PHOTO 146150 BY O. MONSEN