በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጦርነቱ ማግስት ለተገኘው እድገት አስተዋጽኦ የማድረግ መብት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ

በጦርነቱ ማግስት ለተገኘው እድገት አስተዋጽኦ የማድረግ መብት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ

የሕይወት ታሪክ

በጦርነቱ ማግስት ለተገኘው እድገት አስተዋጽኦ የማድረግ መብት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ

ፊሊፕ ኤስ ሆፍማን እንደተናገረው

ወቅቱ ግንቦት 1945 ሲሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገና ማቆሙ ነበር። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ የስብከት እንቅስቃሴ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው ወንድም ናታን ኤች ኖር የ25 ዓመት እድሜ ከነበረው ጸሐፊው ከሚልተን ጄ ሄንሽል ጋር ሆኖ ዴንማርክን ጎበኘ። በጉጉት ይጠበቅ ለነበረው ለዚህ ጉብኝት ትልቅ አዳራሽ ተከራየን። በተለይ ወንድም ሄንሽል በእድሜ እንደ እኛ ወጣት ስለሆነና ለንግግሩም የመረጠው ጭብጥ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚል ስለነበር ስሜታችንን ለመቀስቀስ ችሎ ነበር።​—⁠መክብብ 12:1

ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለማስፋፋት አስደናቂ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንዳለና እኛም በዚህ ዝግጅት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደምንችል በዚህ ጉብኝት ወቅት ተገነዘብን። (ማቴዎስ 24:14) ለምሳሌ ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን በሚስዮናዊነት ለማሰልጠን አዲስ ትምህርት ቤት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከፍቶ ነበር። ወንድም ኖር በዚህ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ከተጋበዝን የሚላክልን “የአንድ ጉዞ ትኬት ብቻ” እንደሆነና ከሥልጠናው በኋላ የት እንደምንመደብ እንደማናውቅ አጥብቆ ነገረን። ያም ሆኖ አንዳንዶቻችን በትምህርት ቤቱ ለመካፈል አመለከትን።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን ታሪኬን ከመተረኬ በፊት ግን ከተወለድኩበት ከ1919 ጀምሮ ስለነበረው ሁኔታ ልንገራችሁ። ከጦርነቱ በፊትና በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ በሕይወቴ ላይ የማይናቅ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ ክንውኖች አሉ።

እንደ አፈንጋጭ ከተቆጠረ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል

እናቴ የመጀመሪያ ልጅዋን እኔን ፀንሳ እያለች ወንድ ልጅ ከወለደች ሚስዮናዊ እንዲሆን ትጸልይ ነበር። ወንድሟ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሲሆን በቤተሰቡ ዘንድ ግን እንደ አፈንጋጭ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ቤታችን የሚገኘው በኮፐንሃገን አቅራቢያ ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዓመታዊ ስብሰባቸውን በዚያ ሲያደርጉ እናቴ ራቅ ባለ ቦታ የሚኖረውን ይህን አጎቴን ቶማስን እኛ ጋር እንዲሰነብት ትጋብዘው ነበር። ቶማስ የነበረው አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና የሚያቀርባቸው አጥጋቢ ምክንያቶች እናቴን ስላሳመኗት በ1930 እሷም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሆነች።

እናቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ነበራት። በዘዳግም 6:​7 ላይ ያለውን ትእዛዝ በመከተል እኔንና እህቴን ‘በቤት ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ሆነ ስትነሣ’ ታስተምረን ነበር። ከጊዜ በኋላ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸውን ነፍስ አትሞትም የሚለውንና የሲኦል እሳትን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን መወያየት ያስደስተኝ ነበር። እነዚህ ትምህርቶች የተሳሳቱ እንደሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥቼ በማሳየት ረገድ የተካንኩ ነበርኩ።​—⁠መዝሙር 146:3, 4 አ.መ.ት.መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4

ቤተሰባችን አንድ ሆነ

በ1937 በኮፐንሃገን ከተካሄደው ትልቅ ስብሰባ በኋላ ዴንማርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በጽሑፍ መጋዘን ውስጥ በጊዜያዊነት የሚረዳ ሰው ያስፈልግ ነበር። ከንግድ ሥራ ኮሌጅ ገና መመረቄ ስለነበርና ምንም ኃላፊነቶች ስላልነበሩብኝ በጽሑፍ መጋዘኑ ውስጥ ለመርዳት ራሴን አቀረብኩ። በመጋዘኑ የነበረው ሥራ ሲጠናቀቅ በቅርንጫፍ ቢሮው እንድረዳ ግብዣ ቀረበልኝ። ገና ያልተጠመቅኩ ብሆንም እንኳ ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቦቼን ተሰናብቼ ኮፐንሃገን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መኖር ጀመርኩ። ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በየዕለቱ እገናኝ ስለነበር በመንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ረዳኝ። በቀጣዩ ዓመት ማለትም በጥር 1, 1938 ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።

መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። ከዚያም ሚያዝያ 9, 1940 የጀርመን ወታደሮች ዴንማርክን ተቆጣጠሩ። ዴንማርካውያን በነጻነት መንቀሳቀስ ይችሉ ስለነበር የስብከት እንቅስቃሴያችንን ያለችግር መቀጠል ችለን ነበር።

ከዚያም አንድ ደስ የሚል ሁኔታ ተከሰተ። አባባ ቀናተኛና ታማኝ ምሥክር ሆነና የቤተሰባችንን ደስታ የተሟላ አደረገው። ከሌሎች አራት የዴንማርክ ተወላጆች ጋር ጊልያድ ትምህርት ቤት በሚካሄደው በስምንተኛው ክፍል እንድካፈል በተጋበዝኩ ጊዜ መላው ቤተሰቤ ድጋፍ ሰጠኝ። ከመስከረም 1946 ጀምሮ አምስት ወር ለሚያህል ጊዜ የተሰጠን ይህ ኮርስ የተካሄደው በኒው ዮርክ ግዛት ከሳውዝ ላንሲንግ ከተማ ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኘው የሚያምር ቅጥር ግቢ ውስጥ ነበር።

ጊልያድና ከጊልያድ ከተመረቅኩ በኋላ ያገኘኋቸው ሥልጠናዎች

ጊልያድ ግሩም የሆኑ አዳዲስ ወዳጆች እንዳፈራ አጋጣሚ ሰጥቶኛል። አንድ ቀን ምሽት ከእንግሊዝ ከመጣው ከሃሮልድ ኪንግ ጋር በግቢው ውስጥ እየተንሸራሸርን ሳለን ሥልጠናችንን ስንጨርስ ወዴት ልንላክ እንደምንችል እናወራ ነበር። ሃሮልድ “በዶቨር [በደቡባዊ እንግሊዝ የሚገኝ ቦታ ነው] የሚገኙትን ነጫጭ ቋጥኞች ዳግመኛ ማየቴ እንደማይቀር እርግጠኛ ነኝ” በማለት ተናገረ። እውነቱን ነበር። ይሁን እንጂ ወደ እንግሊዝ በድጋሚ የሄደው ከ17 ዓመታት በኋላ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራት ዓመት ተኩል የሚያህለውን ጊዜ ያሳለፈው በቻይና ወኅኒ ቤት ውስጥ ለብቻው ተገልሎ ታስሮ ነበር። a

ከተመረቅን በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን እየጎበኘሁ በመንፈሳዊ እንድረዳ ወደ ቴክሳስ ዩ ኤስ ኤ ተላክሁ። እዚያም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልኝ። የቴክሳስ ወንድሞች ከጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀ ወጣት አውሮፓዊ ወንድም በማግኘታቸው ተደስተው ነበር። ሆኖም ቴክሳስ ሰባት ወር ከቆየሁ በኋላ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተጠራሁ። እዚያም ወንድም ኖር በቤቴል ውስጥ ስለሚካሄዱ የተለያዩ ሥራዎች በቂ እውቀት እንዳገኝ ቢሮ ውስጥ እንድሠራ መደበኝ። ከዚያ ወደ ዴንማርክ ስመለስ ሁሉም ነገር ከብሩክሊን ጋር በሚመሳሰል መንገድ የሚሠራ መሆኑን በማረጋገጥ የተማርኩትን በሥራ ላይ ማዋል ነበረብኝ። ዓላማው በዓለም ዙሪያ ባሉት ቅርንጫፎች ውስጥ አንድ ዓይነት አሠራር እንዲኖር በማድረግ ሥራውን ይበልጥ ማቀላጠፍ ነበር። ከዚያ በኋላ ወንድም ኖር ወደ ጀርመን አዛወረኝ።

መመሪያዎችን በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ መተግበር

በሐምሌ 1949 ቪስባደን ጀርመን ስደርስ አብዛኞቹ የጀርመን ከተሞች እንደፈራረሱ ነበሩ። ሂትለር ሥልጣን ከያዘበት ከ1933 ጀምሮ ስደት ይደርስባቸው የነበሩ ወንድሞች በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው ሲመሩ የቆዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከስምንት እስከ አሥር ወይም ከዚያም በላይ ለሚሆን ዓመት በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሳለፉ ናቸው። እነዚህን ከመሰሉ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ሦስት ዓመት ተኩል ለሚያህል ጊዜ አብሬያቸው የመሥራት መብት አግኝቻለሁ። ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምሳሌነታቸው የጀርመኑ ታሪክ ጸሐፊ ገብርኤሌ ዮናን የሰጡትን የሚከተለውን አስተያየት ያስታውሰኛል። “በብሔራዊ ሶሻሊዝም አምባገነን አገዛዝ ሥር ይህ ክርስቲያን ቡድን ያሳየውን የጽናት ምሳሌ ባንመለከት ኖሮ ከኦሽዊትዝና ከሆሎኮስት እልቂት በኋላ ኢየሱስ ያስተማረውን የክርስትና ትምህርት መፈጸም ይቻል ይሆን ብለን መጠራጠራችን አይቀርም ነበር።”

በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የነበረኝ ሥራ በዴንማርክ እንዳከናወንኩት አዲስና ወጥ የሆነ ድርጅታዊ አሠራርን ማስተዋወቅ ነበር። የጀርመን ወንድሞች ማስተካከያዎቹ ያስፈለጉት እስካሁን ነገሮችን ሲያከናውኑበት የነበረው መንገድ የተሳሳተ ሆኖ ስለተገኘ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ባሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎችና በዋናው መሥሪያ ቤት መካከል የቅርብ ትብብር እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ሲገነዘቡ ደስ ብሏቸው ግሩም የሆነ የትብብር መንፈስ አሳይተዋል።

በ1952 ወደ በርን ስዊዘርላድ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድዛወር የሚያዝዝ ደብዳቤ ከወንድም ኖር ደረሰኝ። ከጥር 1, 1953 ጀምሮ በዚያ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ።

በስዊዘርላንድ ያገኘኋቸው አዳዲስ ደስታዎች

ስዊዘርላንድ ከደረስኩ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከኤስተር ጋር ተገናኘንና ብዙም ሳይቆይ ለመጋባት ተስማማን። ነሐሴ 1954 ወንድም ኖር ወደ ብሩክሊን እንድመጣ አስጠራኝና አዲስና አስደሳች አሠራር ሊጀመር እንደሆነ ነገረኝ። በዓለም ዙሪያ ያሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች በብዛትም ሆነ በመጠን በጣም ስለጨመሩ የአደረጃጀት ለውጥ እየተደረገ ነበር። መላው ዓለም በዞኖች ይከፋፈልና እያንዳንዱ ዞን በአንድ የበላይ ተመልካች ይጎበኛል። እኔም ከእነዚህ ዞኖች ውስጥ በሁለቱ ማለትም በአውሮፓና በሜዲትራንያን ክልል እንዳገለግል ተመደብኩ።

በብሩክሊን አጭር ቆይታ ካደረግኩ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ስዊዘርላንድ ተመለስኩና የዞን አገልግሎቴን ለመጀመር ተዘጋጀሁ። ከኤስተር ጋር ተጋባንና በስዊዘርላንድ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አብራኝ ማገልገል ጀመረች። የመጀመሪያ ጉብኝቴን ያደረግሁት በኢጣሊያ፣ በግሪክ፣ በቆጵሮስ፣ በሰሜን አፍሪካ ጠረፍ የሚገኙ አገሮችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በስፔይንና በፖርቱጋል ውስጥ የሚገኙ የሚስዮናውያን መኖሪያዎችና ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሲሆኑ በድምሩ 13 አገሮችን የሚያካትት ነበር። ወደ በርን ተመልሼ ለጥቂት ጊዜ ከቆየሁ በኋላ በወቅቱ በእገዳ ሥር ከነበሩት በስተቀር ሌሎቹን የአውሮፓ አገሮች በሙሉ መጎብኘቴን ቀጠልኩ። ባገባሁ በመጀመሪያው ዓመት ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ለማገልገል ለስድስት ወር ከቤት ርቄ ነበር።

የሁኔታዎች መለዋወጥ

በ1957 ኤስተር ጸነሰች። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ልጆች ይዞ መኖር ስለማይቻል ወደ ዴንማርክ ለመሄድ ወሰንን። እዚያም አባቴ ተቀብሎን ከእርሱ ጋር መኖር ጀመርን። ኤስተር ሴት ልጃችንን ራኬልንና አባቴን ስትንከባከብ እኔ ደግሞ አዲስ በተገነባው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እሠራ ነበር። ለጉባኤ የበላይ ተመልካቾች በሚሰጠው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኜ ከማገልገሌም በላይ የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜም መሥራቴን ቀጥዬ ነበር።

የዞን የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል በጉዞ ላይ ረዥም ጊዜ ማሳለፍን የሚጠይቅ በመሆኑ ከልጄ ጋር ሳንገናኝ ለብዙ ጊዜያት እንድንቆይ ያደርገን ነበር። ይህም የራሱ ችግሮች ነበሩት። በአንድ ወቅት በፓሪስ አነስተኛ ማተሚያ ለማቋቋም የተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ነበር። ኤስተርና ራኬል እኔን ለማየት ባቡር ተሳፍረው ጋር ዱ ኖር ባቡር ጣቢያ መጡ። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ከሚያገለግለው ከሊዮፖልድ ዦንታ ጋር ሆኜ ልንቀበላቸው ወደ ባቡር ጣቢያው ሄድን። ራኬል በባቡሩ ፉርጎ ደረጃ ላይ ቆማ መጀመሪያ ሊዮፖልድን ቀጥሎ እኔን አየችኝ፤ ከዚያ መልሳ ሊዮፖልድን ተመለከተችውና አቀፈችው!

አርባ አምስት ዓመት ሲሞላኝ በሕይወቴ ውስጥ ሌላ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። ቤተሰቤን ለመደገፍ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን አቁሜ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ባካበትኩት ልምድ በወጪ ንግድ አስተዳዳሪነት ሥራ ለማግኘት ቻልኩ። በዚሁ ኩባንያ ውስጥ ዘጠኝ ዓመት ለሚያህል ጊዜ ከሠራሁና ራኬል ትምህርት ከጨረሰች በኋላ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገልን በተመለከተ ለተሰጠው ማበረታቻ ምላሽ ለመስጠት ወሰንን።

በኖርዌይ ሥራ አገኝ እንደሆነ ለማወቅ ወደ አንድ አስቀጣሪ ድርጅት ሄጄ ሥራ ማግኘት እችል እንደሆነ ጠየቅኩ። ያገኘሁት መልስ ተስፋ ሰጪ አልነበረም። ሃምሳ አምስት ዓመት ለሞላው ሰው ሥራ የማግኘት ተስፋው በጣም የመነመነ ነበር። ቢሆንም ሥራው ጊዜውን ጠብቆ እንደሚገኝ ተስፋ በማድረግ በኦስሎ ካለው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ግንኙነት አደረግሁና በድሮባክ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ቤት ተከራይቼ መኖር ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ሥራ አገኘሁና በኖርዌይ በመንግሥቱ አገልግሎት በጣም አስደሳች የሆነ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርን።

በተለይ ከአብዛኞቹ የጉባኤያችን አባላት ጋር ሆነን በስተሰሜን በሚገኙት ገለልተኛ ክልሎች ውስጥ እናገለግል የነበረበት ወቅት በጣም ልዩ ጊዜያት ነበሩ። በምናርፍበት አካባቢ ያሉ ጎጆ ቤቶችን እንከራይና ግርማ ሞገስ በተላበሱት ተራራማ አካባቢዎች ተበታትነው የሚገኙ እርሻዎችን በየቀኑ እንጎበኝ ነበር። ለእነዚህ ተግባቢ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት መናገር በጣም የሚያስደስት ነበር። ብዙ ጽሑፎች የምናበረክት ቢሆንም ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ ግን እስከሚቀጥለው ዓመት መጠበቅ ነበረብን። ሆኖም ሰዎቹ አይረሱንም ነበር! ተመላልሶ መጠይቅ ልናደርግላቸው ስንሄድ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንዳገኙት የቤተሰብ አባል እቅፍ እያደረጉ ሰላም ይሉን የነበረበትን ጊዜ ኤስተርና ራኬል አሁንም ያስታውሳሉ። በኖርዌይ ሦስት ዓመት ከቆየን በኋላ ወደ ዴንማርክ ተመለስን።

በቤተሰብ ሕይወት ያገኘናቸው ደስታዎች

ብዙም ሳይቆይ ራኬል ኒልስ ሆዮ ከተባለ ቀናተኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ጋር ተጫጨች። ከተጋቡ በኋላ ኒልስና ራኬል ልጆች እስከወለዱበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግለዋል። ኒልስ ለቤተሰቡ ከልብ የሚያስብ ጥሩ ባልና አባት ነው። አንድ ቀን ፀሐይ ስትወጣ ለመመልከት በማለዳ ልጁን ይዞ በብስክሌት ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደ። ከተመለሱ በኋላ አንድ ጎረቤት ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደው ምን እንዳደረጉ ልጁን ጠየቀው። “ወደ ይሖዋ ጸለይን” ሲል መለሰለት።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔና ኤስተር ትልልቆቹ የልጅ ልጆቻችን ቤንያሚንና ናድያ ሲጠመቁ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ከተመልካቾቹ መካከል ኒልስም የነበረ ሲሆን በድንገት ፊት ለፊት ተገናኘን። እርሱም ዓይን ዓይኔን እያየኝ “ቆፍጣና የሆነ ወንድ አያለቅስም” አለኝ። ሆኖም እዚያው ተቃቅፈን መላቀስ ጀመርን። አብሮህ የሚስቅና የሚያለቅስ አማች ማግኘት ምንኛ መታደል ነው!

ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማት

እኔና ኤስተር ዴንማርክ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተመልሰን እንድናገለግል ጥያቄ ሲቀርብልን ደግሞ ተጨማሪ በረከት አገኘን። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንጻ በሆልቤክ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነበር። ደመወዝ በማይከፈላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚካሄደውን ይህን ግንባታ በበላይነት የመቆጣጠር መብት አግኝቼ ነበር። ከባድ የሆነ የክረምት ወቅት ቢያጋጥመንም በ1982 መገባደጃ ላይ ፕሮጄክቱ ከሞላ ጎደል ተጠናቀቀና ሰፊና የተሻለ ወደሆኑት ሕንጻዎች ለመዛወር በመቻላችን ተደሰትን።

ወዲያው ቢሮ ውስጥ መሥራት የጀመርኩ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል። ኤስተር ደግሞ የስልክ ኦፕሬተር ሆና መሥራት ጀመረች። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በዳሌዋ አጥንት ላይ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈለጋት። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ደግሞ የሐሞት ከረጢት ቀዶ ሕክምና አደረገች። የቅርንጫፍ ቢሮው አባላት ደግነት የተሞላበት አሳቢነት ቢያሳዩንም ቅርንጫፍ ቢሮውን ለቀን ብንወጣ የተሻለ እንደሚሆን ወሰንና ልጃችንና ቤተሰቧ ወዳሉበት ጉባኤ ተዛወርን።

በአሁኑ ወቅት ኤስተር ጥሩ ጤና የላትም። ቢሆንም አብረን ባገለገልንባቸው ዓመታት ሁሉ ሁኔታዎች የቱንም ያህል ቢለዋወጡም ግሩም አጋዥና ረዳት ሆናልኝ እንደነበር ከልቤ መናገር እችላለሁ። የጤንነታችን ሁኔታ ቢያሽቆለቁልም ሁለታችንም በስብከቱ ሥራ የተወሰነ ተሳትፎ ማድረጋችንን አላቆምንም። ሕይወቴን መለስ ብዬ ስመለከት “አምላኬ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት በደስታ ስሜት አስታውሳቸዋለሁ።​—⁠መዝሙር 71:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሐምሌ 15, 1963 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 437-​442 ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1949 በግንባታ ላይ በነበረው የጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ጽሑፎችን ከመኪና ላይ ስናወርድ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሥራ ባልደረቦቼ መካከል ከማጎሪያ ካምፕ የተረፉ እነዚህን የመሰሉ ምሥክሮች ይገኙበታል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኤስተር ጋር በዛሬው ጊዜ እንዲሁም ጥቅምት 1955 በበርን ቤቴል በተጋባንበት ዕለት