በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታዛዥ ሰዎች የይሖዋን በረከትና ጥበቃ ያገኛሉ

ታዛዥ ሰዎች የይሖዋን በረከትና ጥበቃ ያገኛሉ

ታዛዥ ሰዎች የይሖዋን በረከትና ጥበቃ ያገኛሉ

“የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።”​—⁠ምሳሌ 1:33

1, 2. አምላክን መታዘዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

 በሰማይ ላይ የሚያንዣብብ ጭልፊት መኖሩን ያልተመለከቱ ጫጩቶች መሬት እየጫሩ ምግባቸውን ይለቃቅማሉ። እናታቸው በድንገት በኃይል ጮኸችና ክንፎቿን ዘረጋችላቸው። ጫጩቶቹም በፍጥነት ወደ እናታቸው በመሮጥ በክንፎችዋ ሥር ተሸሸጉ። ጭልፊቱ ተስፋ ቆርጦ ተመለሰ። a ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ታዛዥነት ሕይወትን እንደሚያድን እንማራለን!

2 ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች አድብቶ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ስለሚያደርግ ይህ ትምህርት ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች በእጅጉ ይሠራል። (ራእይ 12:​9, 12, 17) የሰይጣን ዓላማ የእኛን መንፈሳዊነት በማበላሸት የይሖዋን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን እንድናጣ ማድረግ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ተጠግተን የምንኖርና በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ ተቀብለን አፋጣኝ እርምጃ የምንወስድ ከሆነ የእርሱን ጥበቃ እናገኛለን ብለን በእርግጠኝነት ልንጠባበቅ እንችላለን። “በላባዎቹ ይጋርድሃል፣ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ” በማለት መዝሙራዊው ጽፏል።​—⁠መዝሙር 91:4

ሳይታዘዝ የቀረው ብሔር የጥቃት ሰለባ ሆነ

3. እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ታዛዥ ሳይሆኑ መቅረታቸው ምን አስከተለባቸው?

3 የእስራኤል ሕዝብ ይሖዋን ሲታዘዝ የእርሱን ጥበቃ ያገኝ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ፈጣሪያቸውን ትተው ‘ምናምንቴ፣ የማይረቡ፣ የማያድኑና ከንቱ’ የሆኑትን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ያመልኩ ነበር። (1 ሳሙኤል 12:​21) ለብዙ ዘመናት በዚህ የዓመፅ ድርጊት ከተመላለሱ በኋላ ሕዝቡ በአጠቃላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችለው የክህደት አዘቅት ውስጥ ተዘፈቀ። ስለሆነም ኢየሱስ እንዲህ ሲል የተሰማውን ሐዘን ገልጿል:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።”​—⁠ማቴዎስ 23:37, 38

4. ይሖዋ ኢየሩሳሌምን እንደተዋት በ70 እዘአ ግልጽ ሆኖ የታየው እንዴት ነበር?

4 ከሃዲዋ እስራኤል በ70 እዘአ የደረሰባት አሳዛኝ ሁኔታ ይሖዋ እርግፍ አድርጎ እንደተዋት የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር። በዚያ ዓመት የሮማ የጦር ሠራዊት የንስር ምስል ያለበት ዓርማ አንግቦ ከፍተኛ እልቂት ለማድረስ እንደ ጭልፊት በኢየሩሳሌም ላይ ተወረወረ። በወቅቱ ከተማይቱ የማለፍን በዓል ለማክበር በመጡ ሰዎች ተጨናንቃ ነበር። ይዘውት የመጡት የተትረፈረፈ መሥዋዕት የአምላክን ሞገስ ሊያስገኝላቸው አልቻለም። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሳሙኤል የይሖዋን ትእዛዝ ሳይጠብቅ ለቀረው ለንጉሥ ሳኦል “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት የሚያስታውስ ነበር።​—⁠1 ሳሙኤል 15:22

5. ይሖዋ ከሰዎች የሚፈልገው ምን ዓይነት ታዛዥነት ነው? እንዲህ ያለውን ታዛዥነት ማሳየት እንደሚቻል እንዴት እናውቃለን?

5 ይሖዋ ታዛዥነትን ከሰዎች የሚጠብቅ ቢሆንም እንኳ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ዘሮች የአቅም ገደቦች እንዳሉባቸው በሚገባ ያውቃል። (መዝሙር 130:​3, 4) ከሰዎች የሚፈልገው የልብ ቅንነትን፣ በእምነትና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ታዛዥነትንና እርሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ማሳየትን ነው። (ዘዳግም 10:​12, 13፤ ምሳሌ 16:​6፤ ኢሳይያስ 43:​10፤ ሚክያስ 6:​8፤ ሮሜ 6:​17) ‘ከክርስትና ዘመን በፊት የኖሩ እንደ ደመና ያሉ ምሥክሮች’ ከባድ ፈተና ሌላው ቀርቶ ሞት ቢደርስባቸውም እንኳን ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው መኖራቸው እንዲህ ያለውን ታዛዥነት ማሳየት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። (ዕብራውያን 11:​36, 37፤ 12:​1) እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝተዋል። (ምሳሌ 27:​11) አንዳንዶች ደግሞ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ረገድ ጥሩ ጅምር ቢኖራቸውም ከጊዜ በኋላ ታዛዥ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የጥንቷ ይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮአስ ነው።

ክፉ ባልንጀርነት ያበላሸው ንጉሥ

6, 7. ዮዳሄ በሕይወት ሳለ ንጉሥ ኢዮአስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

6 ንጉሥ ኢዮአስ ሕፃን ሳለ በሰው እጅ ከመገደል ያመለጠው ለጥቂት ነበር። ኢዮአስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ሊቀ ካህናት የነበረው ዮዳሄ በድፍረት ከተደበቀበት አውጥቶ ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ዮዳሄ እንደ አባትና እንደ አማካሪ ሆኖ ኢዮአስን ስለረዳው ወጣቱ ንጉሥ “በካህኑ በዮዳሄ ዘመን ሁሉ . . . በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።”​—⁠2 ዜና መዋዕል 22:​10–23:​1, 11፤ 24:​1, 2

7 ኢዮአስ ካከናወናቸው መልካም ተግባሮች መካከል የይሖዋን ቤተ መቅደስ መጠገን ይገኝበታል። ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ለመጠገን የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን እንዲቻል ‘ሙሴ እንዳዘዘው’ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የቤተ መቅደስ ግብር መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ለሊቀ ካህናቱ ለዮዳሄ አሳሰበው። ወጣቱ ንጉሥ የአምላክን ሕግ እንዲያጠናና እንዲጠብቅ ዮዳሄ የሰጠው ማበረታቻ ውጤት እንዳስገኘ ከዚህ መረዳት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ቤተ መቅደሱን የመጠገንና የቤተ መቅደሱን ዕቃዎች የማሟላቱ ሥራ በፍጥነት ሊጠናቀቅ ችሏል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 24:​4, 6, 13, 14፤ ዘዳግም 17:​18

8. (ሀ) ለኢዮአስ መንፈሳዊ ውድቀት አስተዋጽኦ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ንጉሡ ታዛዥ አለመሆኑ ወደ ምን መርቶታል?

8 የሚያሳዝነው ግን ኢዮአስ ለይሖዋ ያሳየው ታዛዥነት እስከ መጨረሻው አልዘለቀም። ለምን? የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ ንጉሡም እሺ አላቸው። የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ ወረደ።” የይሁዳ አለቆች ያሳደሩበት መጥፎ ተጽእኖ ንጉሡ የአምላክ ነቢያት የሰጡትን ምክር ችላ እንዲል አድርጎታል። ከእነዚህ የአምላክ ነቢያት መካከል አንዱ የዮዳሄ ልጅ ዘካርያስ ሲሆን እርሱም ኢዮአስንም ሆነ ሕዝቡን ለይሖዋ ታዛዥ ባለመሆናቸው ምክንያት በድፍረት ገሥጿቸዋል። ኢዮአስ ንስሐ ከመግባት ይልቅ ዘካርያስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት አደረገ። ኢዮአስ የኋላ ኋላ እንዴት ያለ ጨካኝና ዓመፀኛ ሰው ሆኖ ነበር! ለዚህ ሁሉ ያበቃው በክፉ ባልንጀርነት መሸነፉ ነው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 24:​17-22፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​33

9. ኢዮአስና መሳፍንቱ የደረሰባቸው ጥፋት አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውድቀት ጥሩ አድርጎ የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢዮአስና አብረውት ይገዙ የነበሩት ክፋት የተጠናወታቸው ባልንጀሮቹ ይሖዋን በመተዋቸው የእጃቸውን ያገኙት እንዴት ነው? ‘ጥቂት ቁጥር’ ብቻ ይዞ የመጣው የሶርያውያን የጦር ሠራዊት ይሁዳን በመውረር ‘የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፋ።’ ከዚህም በተጨማሪ ወራሪዎቹ ንጉሡ የራሱን ንብረትና የቤተ መቅደሱን ወርቅና ብር አሳልፎ እንዲሰጥ አስገደዱት። ኢዮአስ ከዚህ ጥፋት በሕይወት ቢተርፍም ደካማና ታማሚ ሰው ሆኖ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የገዛ አገልጋዮቹ አድመው ገደሉት። (2 ዜና መዋዕል 24:​23-25፤ 2 ነገሥት 12:​17, 18) ይሖዋ “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፣ . . . ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፣ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል” በማለት ለእስራኤላውያን የተናገረው ቃል ምንኛ በትክክል ተፈጽሟል!​—⁠ዘዳግም 28:15

ታዛዥነት በማሳየቱ ምክንያት የዳነው ጸሐፊ

10, 11. (ሀ) ይሖዋ ለባሮክ የሰጠውን ምክር መለስ ብሎ ማሰብ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለባሮክ ምን ምክር ሰጠው?

10 በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ የምታገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ለምሥራቹ ፍላጎት ባለማሳየታቸው ምክንያት ተስፋ የቆረጥክበት ጊዜ አለ? በብልጥግናቸውና በሚመሩት የተንደላቀቀ ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ቅናት ይሰማሃል? ከሆነ የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታና ይሖዋ የሰጠውን ፍቅራዊ ምክር ቆም ብለህ አስብ።

11 ባሮክ በኤርምያስ በኩል የሚተላለፈውን ትንቢታዊ መልእክት ጸሐፊ ሆኖ በማገልገል ላይ እያለ ከይሖዋ ምክር ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ለምን? ባሮክ ኑሮውን ማማረርና በአምላክ አገልግሎት ካገኘው ልዩ መብት የተሻለ ነገር መመኘት ጀምሮ ስለነበረ ነው። ይሖዋ የባሮክ ዝንባሌ እንደተለወጠ ሲገነዘብ “ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፣ እነሆ፣ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው፣ . . . ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ” በማለት በደግነት ግልጽ ምክር ሰጠው።​—⁠ኤርምያስ 36:4፤ 45:5

12. በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለራሳችን “ታላቅን ነገር” መመኘት የማይኖርብን ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ ከኤርምያስ ጎን ተሰልፎ በታማኝነትና በድፍረት ያገለግለው ለነበረው ለባሮክ ከተናገራቸው ከእነዚህ ቃላት ለዚህ ግሩም ሰው ምን ያህል የጠለቀ አሳቢነት እንዳሳየው መገንዘብ ትችላለህ? ዛሬም በተመሳሳይ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተሻለ ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማግኘት ለሚፈተኑ ሰዎች ይሖዋ ከልብ ያስብላቸዋል። ደስ የሚለው እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች የሰጧቸውን ፍቅራዊ ምክር ልክ እንደ ባሮክ ሳያንገራግሩ ተቀብለዋል። (ሉቃስ 15:​4-7) አዎን፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለራሳቸው “ታላቅን ነገር” ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች እውነተኛ ደስታ ማጣት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ዓለምና ከራስ ወዳድነት ምኞቶቹ ጋር አብሮ የመጥፋት የከፋ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 6:​19, 20፤ 1 ዮሐንስ 2:​15-17

13. ስለ ባሮክ ከሚናገረው ታሪክ ትሕትናን አስመልክቶ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 ስለ ባሮክ የሚናገረው ታሪክ ስለ ትሕትናም ግሩም ትምህርት ይዞልናል። ይሖዋ ለባሮክ ምክር የሰጠው በቀጥታ ሳይሆን ጉድለቶቹንና ጠባዩን በደንብ በሚያውቀው በኤርምያስ በኩል እንደሆነ ልብ በል። (ኤርምያስ 45:​1, 2) ሆኖም ባሮክ ኩራት እንዲያሸንፈው አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ ምክሩ የመጣው በቀጥታ ከይሖዋ እንደሆነ በትሕትና ተቀብሏል። (2 ዜና መዋዕል 26:​3, 4, 16፤ ምሳሌ 18:​12፤ 19:​20) ስለሆነም እኛም ሳናውቅ አንድ ዓይነት ስህተት ብንሠራና ከአምላክ ቃል አስፈላጊው ምክር ቢሰጠን የባሮክን ጉልምስና፣ መንፈሳዊ ማስተዋልና የትሕትና መንፈስ እንኮርጅ።​—⁠ገላትያ 6:​1

14. ለዋኖቻችን ታዛዥነት ማሳየታችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

14 እንዲህ ያለውን የትሕትና መንፈስ ማሳየታችን ምክር ለሚሰጡን ሰዎችም ይጠቅማቸዋል። ዕብራውያን 13:​17 እንዲህ ይላል:- “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።” ሽማግሌዎች በእረኝነት ሥራቸው ውስጥ የሚካተተውን ይህን ኃላፊነት ዘዴ በተሞላበት መንገድ መወጣት ይችሉ ዘንድ ድፍረት፣ ጥበብና ብልሃት እንዲሰጣቸው ወደ ይሖዋ በተደጋጋሚ ይጸልያሉ። እንግዲያው ሁላችንም ‘እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች እንወቃቸው።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​18

15. (ሀ) ኤርምያስ በባሮክ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ባሮክ በትሕትና በመታዘዙ ምክንያት የተካሰው እንዴት ነው?

15 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ባሮክ ምክር ከተሰጠው በኋላ አስተሳሰቡን አስተካክሏል። ምክንያቱም ኤርምያስ እርሱ እየነገረው ባሮክ የጻፈውን የፍርድ መልእክት ድምፁን ከፍ አድርጎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንዲያነብብ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቶት ነበር። ታዲያ ባሮክ የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ ይሆን? አዎን “ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ” አድርጓል። እንዲያውም ያንኑ መልእክት በኢየሩሳሌም ለሚገኙ አለቆችም አንብቦላቸዋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ ድፍረት እንደሚጠይቅ ምንም ጥርጥር የለውም። (ኤርምያስ 36:1-6, 8, 14, 15) ከተማይቱ ከ18 ዓመታት ገደማ በኋላ በባቢሎናውያን እጅ በወደቀችበት ጊዜ ባሮክ ይሖዋ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምቶ ለራሱ “ታላቅን ነገር” መፈለጉን በማቆሙ ምክንያት እንደዳነ ሲገነዘብ ምን ያህል እንደሚደሰት አስብ!​—⁠ኤርምያስ 39:​1, 2, 11, 12፤ 43:​6

በከበባው ወቅት ታዛዥ የነበሩ ሰዎች ድነዋል

16. በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በከበቡበት ወቅት ይሖዋ ለአይሁዳውያን ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?

16 በተጨማሪም ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ በጠፋችበት ወቅት አምላክ እርሱን ለሚታዘዙ ሰዎች እንደሚራራ በግልጽ ታይቷል። ኢየሩሳሌምን የከበበው ሠራዊት ከተማይቱን ሰብሮ ከመግባቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ይሖዋ አይሁዳውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እነሆ፣ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ። በዚህች ከተማ ውስጥ የሚዘገይ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፣ ነፍሱም ምርኮ ትሆንለታለች።” (ኤርምያስ 21:8, 9) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ጥፋት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በዚያ ወሳኝ ወቅት ለሚታዘዙት ሰዎች ርኅራኄውን አሳይቷቸዋል። b

17. (ሀ) ኤርምያስ ተከብበው የነበሩት አይሁዳውያን ለከለዳውያን እጅ እንዲሰጡ እንዲናገር ይሖዋ ባዘዘው ጊዜ ታዛዥነቱ በምን ሁለት መንገዶች ተፈትኖ ነበር? (ለ) ኤርምያስ ካሳየው ድፍረት የተሞላበት የታዛዥነት ምሳሌ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

17 አይሁዳውያን እጃቸውን እንዲሰጡ መናገር የኤርምያስን ታዛዥነት ፈተና ላይ እንደጣለው ምንም ጥርጥር የለውም። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ኤርምያስ ለአምላክ ስም ቅንዓት የነበረው መሆኑ ነው። ላገኙት ድል በድን ለሆኑ ጣዖቶቻቸው ምስጋና በሚሰጡ ጠላቶች የአምላክ ስም እንዲሰደብ አልፈለገም። (ኤርምያስ 50:​2, 11፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:16) ከዚህም በተጨማሪ ኤርምያስ ሕዝቡ እጁን እንዲሰጥ በሚናገርበት ጊዜ ብዙዎች የሕዝቡን ወኔ አዳክሟል ብለው ስለሚያስቡ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያውቅ ነበር። ሆኖም በፍርሃት ተሸማቆ ከመናገር ወደኋላ አላለም፤ ከዚህ ይልቅ የይሖዋን የፍርድ መልእክት በመናገር ታዛዥነቱን አሳይቷል። (ኤርምያስ 38:​4, 17, 18) እንደ ኤርምያስ እኛም የምናውጀው መልእክት ብዙዎችን ደስ እንደማያሰኝ እናውቃለን። ኢየሱስም በሰዎች ዘንድ እንዲናቅ ያደረገው ይኸው መልእክት ነው። (ኢሳይያስ 53:​3፤ ማቴዎስ 24:​9) ስለሆነም ‘ሰውን ሳንፈራ’ ልክ እንደ ኤርምያስ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን በድፍረት እርሱን እንታዘዝ።​—⁠ምሳሌ 29:​25

በጎግ ጥቃት ወቅት ታዛዥነት ማሳየት

18. የይሖዋ አገልጋዮች ምን የታዛዥነት ፈተና ይጠብቃቸዋል?

18 መላው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ “ታላቅ መከራ” በቅርቡ ይወገዳል። (ማቴዎስ 24:​21) መከራው ከመምጣቱ በፊትም ሆነ በመከራው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች እምነትና ታዛዥነት በእጅጉ እንደሚፈተን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ሰይጣን እንደ ‘ማጎግ ጎግ’ ሆኖ ‘ምድርን እንደሚሸፍን ደመና’ ያለ “ብርቱ ሠራዊት” ተጠቅሞ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እንደሚሰነዝር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ሕዝቅኤል 38:​2, 14-16) ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ራሱን የሚከላከልበት መሣሪያ የሌለው የአምላክ ሕዝብ ይሖዋ የሚታዘዙትን ለመጋረድ በዘረጋው “ክንፍ” በታች ይሸሸጋል።

19, 20. (ሀ) እስራኤላውያን ወደ ቀይ ባሕር ባደረጉት ጉዞ ታዛዥነት ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ቀይ ባሕር በሚናገረው ታሪክ ላይ በጸሎት ማሰላሰላችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

19 ይህ ሁኔታ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በወጡበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር ያስታውሰናል። ይሖዋ ግብፃውያንን በአሥር መቅሰፍቶች ከመታቸው በኋላ ሕዝቡን አቋራጭ መንገድ ተጠቅሞ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመምራት ይልቅ ጠላቶቻቸው ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው ማምለጫ ቀዳዳ ወደማያገኙበት ወደ ቀይ ባሕር እንዲያቀኑ አደረጋቸው። ከወታደራዊ ስልት አንጻር ይህ አደገኛ አካሄድ ይመስላል። አንተ እዚያ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርሰው መንገድ ይህ እንዳልሆነ እያወቅህ ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠውን ትእዛዝ ተቀብለህ በሙሉ ትምክህት ወደ ቀይ ባሕር አቅጣጫ ትጓዝ ነበርን?​—⁠ዘጸአት 14:​1-4

20 በዘጸአት ምዕራፍ 14 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ስናነብ ይሖዋ ሕዝቡን በከፍተኛ ኃይል እንዴት እንዳዳነ እንገነዘባለን። ጊዜ መድበን እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ስናጠናና ስናሰላስልባቸው እምነታችን ምንኛ ይጠናከራል! (2 ጴጥሮስ 2:​9) ጠንካራ እምነት ደግሞ ይሖዋ የሚፈልግብን ነገር ከሰው አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ በሚመስልበት ጊዜም እንኳን እርሱን እንድንታዘዘው ብርታት ይጨምርልናል። (ምሳሌ 3:​5, 6) ስለሆነም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት፣ በጸሎትና በማሰላሰል እንዲሁም ዘወትር ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመሰብሰብ እምነቴን ለመገንባት ጥረት እያደረግኩ ነውን?’​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25፤ 12:​1-3

ታዛዥነት ተስፋችንን በትምክህት እንድንጠባበቅ ያደርጋል

21. ይሖዋን የሚታዘዙ ሰዎች ዛሬም ሆነ ወደፊት ምን በረከቶችን ያገኛሉ?

21 ይሖዋን መታዘዝ የሕይወት መንገዳቸው ያደረጉ ሰዎች “የሚሰማኝ [የሚታዘዘኝ] ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል” የሚሉት የምሳሌ 1:33 ቃላት አሁንም ቢሆን በእነርሱ ላይ ሲፈጸሙ ይመለከታሉ። እነዚህ አጽናኝ ቃላት በመጪው የይሖዋ የበቀል ቀን አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። እንዲያውም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ሲል ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 21:28) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህን ቃላት በልበ ሙሉነት የሚከተሉት አምላክን የሚታዘዙ ሰዎች ብቻ ናቸው።​—⁠ማቴዎስ 7:​21

22. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች በእርሱ እንዲተማመኑ የሚያደርግ ምን መሠረት አላቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የትኞቹ ጉዳዮች ይብራራሉ?

22 ትምክህት እንዲኖረን የሚረዳን ሌላው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” የሚለው ማረጋገጫ ነው። (አሞጽ 3:7) ዛሬ ይሖዋ እንደ ጥንቱ ጊዜ በመንፈሱ ተነሳስተው ትንቢት የሚናገሩ ሰዎችን አያስነሳም፤ ከዚያ ይልቅ ለቤተሰቡ ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ ታማኝና ልባም ባሪያ ሾሟል። (ማቴዎስ 24:​45-47) እንግዲያው ለዚህ “ባሪያ” የታዛዥነት መንፈስ ማሳየታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው እንዲህ ያለው ታዛዥነት ‘የባሪያው’ ጌታ ለሆነው ለኢየሱስ ያለንን ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። “የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል” ተብሎ የተነገረው ለእርሱ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 49:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዶሮ በአብዛኛው ፈሪ እንደሆነች ተደርጋ ብትታይም አንድ የእንስሳት ጥበቃ ድርጅት ጽሑፍ “ሴት ዶሮ ጫጩቶቿን ከአደጋ ለመጠበቅ ስትል እስከሞት ድረስ ትፋለማለች” በማለት ገልጿል።

b ኤርምያስ 38:​19 ብዙ አይሁዳውያን ወደ ከለዳውያን እንደ ‘ኮበለሉና’ ከግዞት ባይድኑም እንኳ ከሞት እንደተረፉ ይጠቁማል። ወደ ከለዳውያን የኮበለሉት የኤርምያስን ቃል ስለሰሙ ይሁን የምናውቀው ነገር የለም። የሆነ ሆኖ በሕይወት መትረፋቸው ነቢዩ የተናገራቸው ቃላት በትክክል መፈጸማቸውን ያረጋግጣል።

ታስታውሳለህን?

• እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ሳይታዘዙ መቅረታቸው ምን አስከተለባቸው?

• ንጉሥ ኢዮአስ በልጅነቱና በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ የመሠረተው ባልንጀርነት በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ ለውጥ ያመጣው እንዴት ነው?

• ከባሮክ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

• ታዛዥ የሆነው የይሖዋ ሕዝብ ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲመጣ ፍርሃት ሊሰማው የማይገባው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቱ ኢዮአስ በዮዳሄ እርዳታ ለይሖዋ ታዛዥነት አሳይቷል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮአስ በክፉ ባልንጀርነት ተገፋፍቶ የአምላክን ነቢይ አስገድሏል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋን በመታዘዝህ ምክንያት በሕይወትህ ውስጥ የእርሱን የማዳን ኃይል የተመለከትክበት ወቅት አለ?