በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚወዱ ወጣቶች

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚወዱ ወጣቶች

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚወዱ ወጣቶች

ከ2, 400 ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ዕብራዊ ዘማሪ “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል?” በማለት ጠይቆ ነበር። (መዝሙር 119:9) ወጣቶች በዓለም ላይ ብዙ ችግሮች ስለሚያጋጥሟቸው ይህ ጥያቄ ዛሬም መነሳቱ ተገቢ ነው። የሴሰኝነት አኗኗር ብዙ ወጣቶችን ለኤድስ እያጋለጠ ሲሆን በዚህ አሰቃቂ በሽታ ከተያዙት መካከል ግማሽ ያህሉ ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መውሰድም እንዲሁ ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው እንዲቀጩ ስለሚያደርግ ብዙ ችግሮች ይፈጥራል። ዓመፅና የሥነ ምግባር ርኩሰት የሚንጸባረቅባቸው ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ቪዲዮዎች እንዲሁም ወራዳ ሙዚቃና በኢንተርኔት የሚተላለፉ የብልግና ስዕሎች በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በመሆኑም መዝሙራዊው ያነሳው ጥያቄ ዛሬ ባሉ በብዙ ወላጆችና ወጣቶች አእምሮ ውስጥ ያለ ጥያቄ ነው።

ይኸው መዝሙራዊ ራሱ ላነሳው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “ቃልህን በመጠበቅ ነው” ብሏል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለወጣቶች የሚሆን ጥሩ መመሪያ እንደያዘ ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙ ወጣቶች ይህንን መመሪያ በመከተላቸው ሕይወታቸው የተሳካ ሊሆን ችሏል። (መዝሙር 119:105) ተድላ ወዳድ በሆነና ፍቅረ ነዋይ በተጠናወተው ዓለም ውስጥ አምላክን የሚወዱና በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ወጣቶችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ከወላጆቻቸው ላገኙት ድጋፍ አመስጋኝ ናቸው

ሃኮብ ኤማኑኤል ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ማገልገል ከመጀመሩ በፊት ለተወሰኑ ዓመታት የዘወትር አቅኚ ሆኖ አገልግሏል። አምላክን የማገልገል ፍቅር እንዲያድርበት የረዳው ምን እንደሆነ ሲናገር በአድናቆት ስሜት ተሞልቶ እንዲህ ይላል:- “እቀርባቸው የነበሩ ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ወንድሞች ጠቃሚ እርዳታ ቢያደርጉልኝም ከሁሉ ይበልጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩብኝ ወላጆቼ ናቸው። የስብከቱን ሥራ እንድወደው አድርገውኛል። ትክክለኛውን ጎዳና እንድከተል በእርጋታ ይመሩኝ ስለነበር እንደተጫኑኝ ሆኖ ተሰምቶኝ አያውቅም።”

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተወሰኑ ዓመታት ያሳለፈው ዳቪድ እሱና ወንድሙ ገና ትንንሽ ልጆች እያሉ ወላጆቹ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ማገልገል መጀመራቸው በጣም እንደነካው ይናገራል። አባቱ ሲሞት እናቱ ልዩ አቅኚ ሆና ማገልገልዋን ቀጠለች። ምሥራቹን ከመስበክ በተጨማሪ እነሱንም ትንከባከብ ነበር። ዳቪድ እንዲህ ይላል:- “በአቅኚነት እንዳገለግል አስገድደውኝ አያውቁም፤ ሆኖም በቤተሰብ ሆነን በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል በጣም ያስደስተን ስለነበር በቤተሰባችን ውስጥ የነበረው ወዳጅነትና አጠቃላይ ሁኔታ እኔም በዚሁ አገልግሎት እንድካፈል ገፋፉኝ።” ዳቪድ ከወላጆች ጥሩ መመሪያና ክትትል ማግኘት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እናታችን ሁልጊዜ ማታ ማታ ከጠፋችው ገነት ወደምትመለሰው ገነት a (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ ላይ ታሪኮች ታነብልን ነበር። ታሪኮቹን የምትተርክበት መንገድ ለመንፈሳዊ ምግብ ፍቅር አሳድሮብናል።”

ለስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት

አንዳንድ ወጣቶች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት ይከብዳቸዋል። በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ወላጆቻቸው ይዘዋቸው ስለሚሄዱ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ከቀጠሉ ከጊዜ በኋላ ስብሰባ አስደሳች ሊሆንላቸው ይችላል። በ11 ዓመቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል የጀመረው አልፍሬዞ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የአምስት ዓመት ልጅ እያለ ስብሰባ ላይ እንቅልፉ ስለሚመጣና ወላጆቹ ደግሞ ስብሰባ እየተካሄደ እያለ እንዲተኛ ስለማይፈቅዱለት ከስብሰባዎች ለመቅረት ሰበብ ይፈጥር እንደነበር ሳይሸሽግ ተናግሯል። “እያደግሁ ስሄድ በተለይም ማንበብና መጻፍ ስጀምር በራሴ አባባል መልስ መስጠት ስለቻልኩ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስደስተኝ ጀመር” በማለት ያስታውሳል።

በዘወትር አቅኚነት የምታገለግለው የ17 ዓመቷ ሲንቲያ አምላክን ለማገልገል ፍቅር እንድታዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው መልካም ባልንጀርነት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ወዳጆች ስላሉኝና አዘውትሬ በስብሰባዎች ላይ ስለምገኝ ከዓለማዊ ጓደኞች ጋር ባለመዋሌ ወይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ ወደ ሆኑት ዳንስ ቤቶች ባለመሄዴ የቀረብኝ ነገር እንዳለ ሆኖ አይሰማኝም። በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት ሐሳቦችና ተሞክሮዎች ለይሖዋ ያለኝን ሁሉ ለመስጠት እንድነሳሳ አድርገውኛል፤ አለኝ የምለው ትልቁ ነገር ደግሞ የወጣትነት ጉልበቴ በመሆኑ ይህን ጉልበቴን ለይሖዋ ሥራ ለማዋል ወሰንኩ።”

ሆኖም “ከመጠመቄ በፊት አስተማሪዎች በሚሰጡኝ የቤት ሥራና በሌሎች ነገሮች በማሳበብ ከስብሰባ የምቀርበት ጊዜ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “ደጋግሜ ከስብሰባዎች በመቅረቴ መንፈሳዊነቴ ተጎዳ። መጽሐፍ ቅዱስ ከማያጠና ልጅ ጋር ጓደኝነት ጀመርኩ። የከፋ ነገር ሳይከሰት ሁኔታዎችን ማስተካከል በመቻሌ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”

የግል ውሳኔ

ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የሚያገለግል ፓብሎ የተባለ ሌላ ወጣት ለአምላክ ቃል እውነት ፍቅር ለማዳበር ወሳኝ ናቸው የሚላቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል:- “ሁለት ነገሮች ማለትም ቋሚ የሆነ የግል ጥናትና በስብከቱ ሥራ ቀናተኛ መሆን ጠቃሚ እንደሆኑ ይሰማኛል። ወላጆቼ ስለ ይሖዋ እውነቱን ስላስተማሩኝ አመሰግናቸዋለሁ፤ ይህ ሊሰጡኝ ከሚችሉት ከማንኛውም ነገር የላቀ ስጦታ እንደሆነ ይሰማኛል። ያም ሆኖ ይሖዋን መውደድ ያለብኝ ለምን እንደሆነ ራሴን ማሳመን ያስፈልገኝ ነበር። ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ‘ስፋትና ጥልቀት’ ማወቅ ያስፈልጋል። ለይሖዋ ቃል ጉጉት ሊያድርብንና ለሌሎች እንድንናገር የሚገፋፋ ‘የሚነድድ እሳት’ በውስጣችን ሊኖር የሚችለው እንደዚህ ካደረግን ብቻ ነው። ለስብከቱ ሥራ እንደዚያ ያለ ቅንዓት ማዳበራችን ለእውነት ያለን አድናቆት ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳናል።”​—⁠ኤፌሶን 3:18፤ ኤርምያስ 20:9

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሃኮብ ኤማኑኤልም እያንዳንዱ ሰው ይሖዋን ለማገልገል የሚያደርገው ውሳኔ በራሱ የግል ምርጫ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል። ወላጆቹ እንዲጠመቅ ገፋፍተውት እንደማያውቁ ይናገራል። “እንዲህ አለማድረጋቸው በጣም ጠቅሞኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ጓደኞቼ የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች ለመጠመቅ የወሰኑት አንድ ላይ ነበር። መጠመቃቸው ጥሩ ቢሆንም አንዳንዶቹ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በስሜታዊነት ስለነበር ብዙም ሳይቆዩ ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበራቸው ቅንዓት ቀዘቀዘ። እኔ ግን ራሴን ለይሖዋ እንድወስን ወላጆቼ አልተጫኑኝም። በራሴ ተነሳሽነት ያደረግሁት ውሳኔ ነው።”

ጉባኤው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ

አንዳንድ ወጣቶች የአምላክን ቃል እውነት የተማሩት ያለ ወላጆቻቸው እርዳታ በራሳቸው ነው። በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ሥር ትክክል የሆነውን ማድረግን መማርና በተማሩት ነገር መጽናት ከባድ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ኖኤ እውነት ምን ያህል እንደጠቀመው ያስታውሳል። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ቁጡና ዓመፀኛ ነበረ። በ14 ዓመቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ባሕርዩ መሻሻል ጀመረ፤ በወቅቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምንም ፍላጎት ያልነበራቸው ወላጆቹ የልጃቸው ባሕርይ መሻሻሉን ሲመለከቱ በጣም ተደሰቱ። ኖኤ በመንፈሳዊ እያደገ ሲሄድ ሕይወቱን ይበልጥ ለይሖዋ አገልግሎት ለማዋል ፈለገ። አሁን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርቷል።

በተመሳሳይም አሌኻንድሮ ምንም እንኳን ወላጆቹ ለክርስቲያናዊው እውነት ፍላጎት ባይኖራቸውም እሱ ግን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለእውነት ፍላጎት ነበረው። ለእውነት ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ያደግሁት ካቶሊክ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኗ ገና ከትንሽነቴ ጀምሮ በአእምሮዬ ይጉላሉ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ ልትሰጠኝ ስላልቻለች አምላክ የለም ወደሚለው የኮምዩኒዝም ፍልስፍና አዘነበልኩ። የይሖዋ ድርጅት አምላክን እንዳውቅ ረድቶኛል። ቃል በቃል ሕይወቴን አትርፎልኛል ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ባላጠና ኖሮ በሥነ ምግባር ብልግና፣ በአልኮል ወይም በዕፅ ሱሰኝነት እጠመድ ነበር። ወይም የአንድ አብዮታዊ እንቅስቃሴ አባል እሆንና አሳዛኝ ውድቀት ይገጥመኝ ነበር።”

አንድ ወጣት ከወላጆቹ ድጋፍ ሳያገኝ በራሱ እውነትን ፈልጎ ሊያገኝና ያገኘውን እውነት አጥብቆ ሊይዝ የሚችለው እንዴት ነው? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ኖኤ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “ይሖዋ ምንጊዜም አጠገቤ ስለሆነ ብቻዬን እንደሆንኩ ፈጽሞ ተሰምቶኝ አያውቅም። ከዚህም በላይ አፍቃሪ የሆኑ ብዙ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ አባቶች፣ እናቶች እና ወንድሞች በመሆን ደግፈውኛል።” አሁን በቤቴል እያገለገለ ሲሆን ጊዜውን አምላክን ለማገልገል ተጠቅሞበታል። አሌኻንድሮም በተመሳሳይ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በግለሰብ ደረጃ የሚወዱኝና የሚያስቡልኝ ሽማግሌዎች ባሉበት ጉባኤ ውስጥ የመኖር መብት በማግኘቴ ሁልጊዜ አመስጋኝ ነኝ። በ16 ዓመቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመርኩበት ወቅት ፈታኝ በሆነው የወጣትነት ዕድሜ ላይ ስለነበርኩ ያደረጉልኝን እርዳታ በጣም አደንቀዋለሁ። በጉባኤ ውስጥ ያሉት ቤተሰቦች ፈጽሞ ብቻዬን አልተዉኝም። ምን ጊዜም ቢሆን በእንግድነት በቤቱ ተቀብሎ የሚያስተናግደኝ እንዲሁም ምግብ የሚጋብዘኝ ብቻ ሳይሆን ወዳጅ ጭምር የሚሆነኝ ሰው አላጣም ነበር።” አሌኻንድሮ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ከጀመረ ከ13 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል።

አንዳንዶች ሃይማኖት ለትላልቅ ሰዎች እንጂ ለወጣቶች እንደማይሆን አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ብዙ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩት ገና በልጅነታቸው ቢሆንም ለይሖዋ ፍቅር አዳብረው በታማኝነት እያገለገሉት ነው። በመዝሙር 110:​3 [አ.መ.ት] ላይ የሚገኙት የሚከተሉት የዳዊት ቃላት በእነዚህ ወጣቶች ላይ ይሠራሉ:- “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ [ወይም “ጎልማሶችህ እንደ ንጋት ወዳንተ ይመጣሉ፣” የግርጌ ማስታወሻ]።”

ወጣቶች እውነትን መማርና በተማሩት ነገር ጸንተው መኖር ፈታኝ ይሆንባቸዋል። ብዙ ወጣቶች ከይሖዋ ድርጅት ጋር ተጣብቀው በመኖር፣ በስብሰባዎች አዘውትረው በመገኘትና መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ለአምላክ ቃልና ለአገልግሎቱ ልባዊ ፍቅር ማዳበራቸው ምንኛ አስደሳች ነው!​—⁠መዝሙር 119:15, 16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1958 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።