በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ የሚያስከትለው ችግርና የሚያስገኘው በረከት

ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ የሚያስከትለው ችግርና የሚያስገኘው በረከት

ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ የሚያስከትለው ችግርና የሚያስገኘው በረከት

ብዙ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ለመኖር ሲሉ ወደ ውጭ አገር ይሄዳሉ። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት ነዋሪዎች መካከል ከ26 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የሌላ አገር ተወላጆች ናቸው። ከ21 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአውስትራሊያ ነዋሪዎችም ከሌሎች አገሮች የመጡ ናቸው። አብዛኞቹ ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸው የሄዱበትን አገር ቋንቋና ባሕል ለመልመድ ብዙ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል።

በአብዛኛው ወላጆች አዲስ ቋንቋ መማር ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድባቸው ሲሆን ልጆች ግን በቀላሉ ሊማሩና መናገር ሊጀምሩ ይችላሉ። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን በውጭ አገር በሚያሳድጉበት ጊዜ ቋንቋውን ቶሎ መማር አለመቻላቸው ከልጆቻቸው ጋር በሚያደርጉት የሐሳብ ልውውጥ ረገድ ከባድ እንቅፋት ሊፈጥርባቸው ይችላል።

በልጆቹ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ቋንቋው ብቻ ሳይሆን የአገሩ ባሕልም ጭምር ነው። ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያዩት አንዳንድ ለውጥ ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። በዚህ ምክንያት በውጭ አገር የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ በሚጥሩበት ጊዜ ፈታኝ ሁኔታ ይገጥማቸዋል።​—⁠ኤፌሶን 6:​4

አእምሮንና ልብን መንካት ትልቅ ጥረት ይጠይቃል

ክርስቲያን ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ‘ንጹሕ ልሳን’ ለልጆቻቸው የማስተማር ፍላጎት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል። (ሶፎንያስ 3:​9) ይሁንና ልጆቹ የወላጆቻቸውን ቋንቋ በደንብ የማያውቁ ከሆነና ወላጆቻቸው ደግሞ ልጆቻቸው በሚገባ በሚያውቁት ቋንቋ ሐሳባቸውን ጥሩ አድርገው መግለጽ ካልቻሉ የይሖዋን ሕግ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ እንዴት ሊተክሉ ይችላሉ? (ዘዳግም 6:​7) ልጆቹ ወላጆቻቸው የሚሉት ሊገባቸው ቢችልም ልባቸውን ካልነካው የተነገራቸውን ነገር ለመቀበል ሊቸገሩ ይችላሉ።

ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውስትራሊያ የሄዱት ፔድሮና ሳንድራ የተባሉ ባልና ሚስት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትን ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ጊዜ የዚህ ዓይነት ችግር ገጥሟቸዋል። a ፔድሮ እንዲህ ብሏል:- “ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ስትናገር ልብንና ስሜትን በሚነካ መንገድ መግለጽ ይኖርብሃል። ጥልቀት ያላቸውንና ትርጉም አዘል ሐሳቦችን ማብራራት ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ቋንቋውን በደንብ ማወቅ የግድ አስፈላጊ ነው።” በተጨማሪም ሳንድራ “ልጆቻችን የትውልድ ቋንቋችንን በሚገባ የማያውቁ ከሆነ መንፈሳዊነታቸው በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። ከሚማሩት ነገር በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ስለማይረዱት ለእውነት ያላቸው ፍላጎት ሊጠፋ ይችላል። መንፈሳዊ እድገታቸውን የሚገታ ሲሆን ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድናም አደጋ ላይ ይወድቃል” ብላለች።

ከስሪላንካ ወደ ጀርመን የሄዱትና ሁለት ልጆች ያሏቸው ንያናፒራካሳም እና ሄለን የተባሉ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል:- “ልጆቻችን የጀርመንኛ ቋንቋን እየተማሩ የእኛንም የትውልድ ቋንቋ መማራቸው ስሜታቸውን በግልጽ በመናገር ከእኛ ጋር የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል ብለን እናምናለን።”

ከኡራጓይ ወደ አውስትራሊያ የሄዱት ሚጌል እና ካርሜን የተባሉ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “እንደ እኛ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወላጆች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለልጆቻቸው በሚገባ ማስተማር ይችሉ ዘንድ የሄዱበትን አገር አዲስ ቋንቋ በደንብ ለመማር ወይም ደግሞ የራሳቸውን ቋንቋ ለልጆቻቸው ጥሩ አድርገው ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው።”

በቤተሰብ የሚደረግ ውሳኔ

በስደት ወደ ሌላ አገር የሄዱ ቤተሰቦች “ከእግዚአብሔር የተማሩ” መሆን ይችሉ ዘንድ የሚጠቀሙበትን ቋንቋ በተመለከተ የሚያደርጉት ውሳኔ ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ወሳኝ ነው። (ኢሳይያስ 54:​13) የትውልድ ቋንቋቸው የሚነገርበት ጉባኤ በአቅራቢያቸው የሚገኝ ከሆነ እዚያ ለመካፈል ሊወስኑ ይችላሉ። አለዚያም ደግሞ የአገሪቱ ቋንቋ በሚነገርበት ጉባኤ ለመካፈል ሊመርጡ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች ላይ እንዲደርሱ የሚያደርጓቸው ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ከቆጵሮስ ወደ እንግሊዝ አገር ከሄዱ በኋላ አምስት ልጆች ያሳደጉት ዲሚትሪዮስና ፓትሩላ የት ጉባኤ ቢካፈሉ እንደሚሻል እንዲወስኑ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “መጀመሪያ አካባቢ ቤተሰባችን የግሪክኛ ቋንቋ በሚነገርበት ጉባኤ መሰብሰብ ጀመረ። ይህ እኛን በጣም የጠቀመን ቢሆንም የልጆቻችንን መንፈሳዊነት በተወሰነ ደረጃ ጎድቶታል። ምንም እንኳ የግሪክኛ ቋንቋ መናገር ቢችሉም ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ይህ ደግሞ በአንጻራዊ ሁኔታ መንፈሳዊ እድገታቸውን አዝጋሚ አድርጎታል። ቤተሰባችን ወደ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ጉባኤ እንደተዛወረ ወዲያው በልጆቻችን ላይ ጥሩ ውጤት ማየት ችለናል። ጉባኤ መቀየሩ ከብዶን የነበረ ቢሆንም ልጆቻችን በመንፈሳዊ ጠንክረው በማየታችን ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዳደረግን መገንዘብ ችለናል።”

ያም ሆኖ ቤተሰቡ በትውልድ ቋንቋቸውም የሚጠቀሙ መሆናቸው ብዙ በረከት አስገኝቶላቸዋል። ልጆቹ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ከአንድ በላይ ቋንቋ ማወቅ ጥቅም አለው። ምንም እንኳ አፍ መፍቻ ቋንቋችን እንግሊዝኛ ቢሆንም ግሪክኛ ቋንቋን ማወቃችን ከቤተሰባችን በተለይ ደግሞ ከአያቶቻችን ጋር የተቀራረበና ጠንካራ ትስስር እንዲኖረን ረድቶናል። ከዚህም በላይ ለሌሎች ስደተኞች ሩኅሩኅ እንድንሆንና ሌላ ቋንቋም መማር እንደምንችል እንዲሰማን አድርጎናል። በመሆኑም ካደግን በኋላ ቤተሰባችን የአልባኒያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወዳሉበት ጉባኤ ተዛወረ።”

ክሪስቶፈርና ማርጋሪታ ከቆጵሮስ ወደ እንግሊዝ ተዛውረው ሦስት ልጆቻቸውን ያሳደጉ ሲሆን እነሱም የግሪክኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ አባል ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ የግሪክኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ልጃቸው ኒኮስ “ቤተሰባችን አዲስ ወደ ተቋቋመው የግሪክኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ እንዲዛወር ሐሳብ በቀረበልን ጊዜ ቲኦክራሲያዊ ሥራ እንደተሰጠን አድርገን ተቀብለነዋል” ብሏል።

ማርጋሪታ “ሁለቱ ወንዶች ልጆቻችን የሰባትና የስምንት ዓመት ልጆች ሳሉ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዘገቡ። የግሪክኛ ቋንቋ ችሎታቸው ውስን መሆኑ ቢያሳስበንም ረዘም ያለ ጊዜ በመመደብ የተሰጣቸውን ክፍል እናዘጋጃቸው ነበር” ስትል ተናግራለች።

ልጃቸው ጆአና “አባባ ቤት ውስጥ የግሪክኛ ፊደላትን በጥቁር ሰሌዳ ላይ እየጻፈ በደንብ ሲያስጠናን ትዝ ይለኛል። ብዙ ሰዎች አንድን ቋንቋ ለመማር ዓመታት ይፈጅባቸዋል። እኛ ግን በወላጆቻችን እርዳታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የግሪክኛ ቋንቋን መማር ችለናል” ብላለች።

አንዳንድ ቤተሰቦች የራሳቸው ቋንቋ በሚነገርበት ጉባኤ የሚካፈሉት ‘መንፈሳዊ እውቀትን’ ለማዳበር በራሳቸው ቋንቋ መማር እንደሚያስፈልጋቸው ስለሚሰማቸው ነው። (ቆላስይስ 1:​9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​13, 15) ወይም ደግሞ የራሳቸውን ቋንቋ መጠቀማቸው ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ስደተኞችን እውነትን እንዲያውቁ ለመርዳት እንደሚያስችላቸው ያምናሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ቤተሰቡ ተሰድደው በሄዱበት አገር በስፋት የሚነገረውን ቋንቋ በሚጠቀም ጉባኤ መካፈላቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 2:​4፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​5) አንድ ላይ ሆነው ከተወያዩ በኋላ የቤተሰቡ ራስ የይሖዋን አመራር ለማግኘት በጸሎት ወደ አምላክ በመቅረብ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል። (ሮሜ 14:​4፤ 1 ቆሮንቶስ 11:​3፤ ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ የደረሱ ቤተሰቦችን ምን ነገር ሊረዳቸው ይችላል?

ሊረዷቸው የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች

ከላይ የተጠቀሱት ፔድሮና ሳንድራ “የራሳችን ቋንቋ እንዳይረሳ ስንል ቤት ውስጥ በስፓኝ ቋንቋ ብቻ ለመነጋገር ወሰንን። ልጆቻችን እንግሊዝኛ መናገር እንደምንችል ስለሚያውቁ በስፓኝ ቋንቋ ብቻ መናገሩ ያስቸግራቸው ነበር። ያወጣነውን መመሪያ ባንሠራበት ኖሮ ወዲያው ቋንቋውን ሊረሱት ይችሉ ነበር” ብለዋል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሚጌል እና ካርሜን “ወላጆች የቤተሰብ ጥናት ሲያደርጉና በዕለት ጥቅስ ላይ ሲወያዩ በራሳቸው ቋንቋ የሚነጋገሩ ከሆነ ልጆቻቸው ቋንቋውን መማር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጉዳዮችንም በቋንቋው የማብራራት ችሎታ እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሚጌል አክሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የስብከቱን ሥራ አስደሳች ለማድረግ ጣሩ። ክልላችን በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የእኛን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ለማግኘት በመኪና ብዙ ሰዓት የሚፈጅ ጉዞ የምናደርግ በመሆኑ አጋጣሚውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጨዋታዎችን ለመጫወትና አስፈላጊ ጉዳዮችን ለመወያየት እንጠቀምበታለን። ለስብከት በምናደርገው ጉዞ ውጤታማ የሆኑ ተመላልሶ መጠየቆች ለማድረግ እንድንችል አስቀድሜ ጥሩ ዕቅድ አወጣለሁ። በዚህ መንገድ ልጆቹ ለአገልግሎት በወጣንበት ቀን ቢያንስ አንድ ጥሩ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ።”

የአካባቢው ባሕል የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም

የአምላክ ቃል ወጣቶችን “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” በማለት ያበረታታቸዋል። (ምሳሌ 1:​8) ወላጆቹ ቀደም ሲል ይከተሉት የነበረው ባሕል ለልጆቻቸው በሚሰጡት ምክርና “ሕግ” ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከሆነና ልጆቹ በአካባቢያቸው ከሚያዩት ባሕል የሚለይ ከሆነ አንዳንድ ችግሮች ብቅ ማለታቸው አይቀርም።

እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ የሌላ ቤተሰብ አኗኗር ተጽዕኖ ሳያሳድርበት ቤተሰቡን እንዴት መምራት እንዳለበት መወሰን መቻል ይኖርበታል። (ገላትያ 6:​4, 5) ያም ሆኖ ግን በልጆችና በወላጆች መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መኖሩ ወላጆች በአካባቢው ያለውን የተለየ ልማድ እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችል ይሆናል።

በበለጸጉ አገሮች የሚዘወተሩ አብዛኞቹ ድርጊቶች ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ጤንነት አደገኛ ናቸው። ተወዳጅነት ያላቸው አብዛኞቹ ሙዚቃዎችና መዝናኛዎች የጾታ ብልግናን፣ ስግብግብነትንና ዓመፅን የሚያበረታቱ ናቸው። (ሮሜ 1:​26-32) ክርስቲያን ወላጆች ቋንቋውን ስለማይረዱት ብቻ የልጆቻቸውን የሙዚቃና የመዝናኛ ምርጫ ከመቆጣጠር ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም። ጥብቅ የሆነ መመሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል። እርግጥ ይህ ከባድ ሊሆን ይችላል።

ካርሜን “ብዙውን ጊዜ ልጆቻችን የሚሰሙት ሙዚቃ ዜማው ጥሩ ቢመስልም ግጥሙ ሌላ ትርጉም ያለው ይሁን አይሁን ወይም ደግሞ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ የአራዳ ቋንቋ ይኑረው አይኑረው አናውቅም” ብላለች። ይህንን ሁኔታ እንዴት እንደተወጡት ሚጌል ሲናገር “ለልጆቻችን ሥነ ምግባር የጎደለው ሙዚቃ መስማት የሚያስከትለውን አደጋ በማሳወቅ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሙዚቃ እንዲመርጡ እንረዳቸዋለን” ብሏል። አዎን፣ የባሕል ልዩነት የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ንቁና ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል።​—⁠ዘዳግም 11:​18, 19፤ ፊልጵስዩስ 4:​5

የሚያስገኛቸው በረከቶች

ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ ተጨማሪ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ቢሆንም ወላጆችም ሆኑ ልጆች እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋቸው ተጨማሪ በረከቶች ሊያስገኝላቸው ይችላል።

አዛምና ባለቤቱ ሳራ ከቱርክ ወደ ጀርመን ከሄዱ በኋላ ሦስት ወንዶች ልጆች ያሳደጉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያ ልጃቸው በጀርመን አገር ዜልተርስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ያገለግላል። አዛም ሲናገር “ልጆቹ በእኛም ሆነ ባደጉበት አገር ባሕል ተወዳጅ የሆኑ ባሕርያትን ማዳበራቸው በጣም ጠቅሟቸዋል” ብሏል።

ከአንጎላ ወደ ጀርመን የሄዱት አንቶኒዮና ሉቶናዲዮ ዘጠኝ ልጆች የሚያሳድጉ ሲሆን ቤተሰባቸው ሊንጋሊኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ መናገር ይችላል። “የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር መቻላችን ከብዙ አገሮች ለሚመጡ ሰዎች መስበክ አስችሎናል። ይህ በእርግጥም ታላቅ ደስታ አስገኝቶልናል።”

ከወላጆቻቸው ጋር ከጃፓን ወደ እንግሊዝ የመጡ ሁለት ልጆች ጃፓንኛንም ሆነ እንግሊዝኛን ማወቃቸው እንደጠቀማቸው ገልጸዋል። ልጆቹ እንዲህ ይላሉ:- “ሁለት ቋንቋ ማወቃችን ሥራ ማግኘት እንድንችልና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚዎች መሆን እንድንችል ረድቶናል። እንዲሁም ብዙ እርዳታ በሚያስፈልገው የጃፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ የማገልገል ልዩ መብት አግኝተናል።”

ሊሳካልህ ይችላል

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮችም ልጆቻቸውን የተለየ ባሕልና የሥነ ምግባር ደንብ ባላቸው ሕዝቦች መካከል ማሳደግ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። የሙሴ ወላጆች ሙሴን ያሳደጉት በግብጽ አገር ቢሆንም በጥሩ ሥነ ምግባር አንጸው ሊያሳድጉት ችለዋል። (ዘጸአት 2:​9, 10) ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደው የነበሩ አይሁዳውያንም ልጆቻቸውን በሚገባ ኮትኩተው በማሳደጋቸው ልጆቹ ካደጉ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ እንደገና ሊያቋቁሙ ችለዋል።​—⁠ዕዝራ 2:​1, 2, 64-70

በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆችም ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። የአንድ ባልና ሚስት ልጆች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ከእማማና አባባ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እናደርጋለን። የሚያደርጉልን ፍቅራዊ እንክብካቤ በመካከላችን የጠበቀ ዝምድና እንዲፈጠር አድርጓል። ይሖዋን የሚያገለግለው ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ክፍል በመሆናችን ደስተኞች ነን።” ልጆቻቸውን ስኬታማ በሆነ መንገድ ያሳደጉ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲህ ያለ አድናቆት የተሞላበት አስተያየት ሲሰጡ በመስማት ሊደሰቱ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤት ውስጥ ስትሆኑ ልጆቻችሁን በራሳችሁ ቋንቋ ብቻ የምታነጋግሯቸው ከሆነ ልጆቹ ቋንቋውን በደንብ እንዲያውቁት ሊረዳቸው ይችላል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቹ የወላጆቻቸውን ቋንቋ ማወቃቸው ከአያቶቻቸው ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጆቻችሁ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችሁ “መንፈሳዊ እውቀታቸው” እንዲዳብር ይረዳቸዋል