በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በባልካን አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደስ የሚሰኙበት ምክንያት አገኙ

በባልካን አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደስ የሚሰኙበት ምክንያት አገኙ

በባልካን አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደስ የሚሰኙበት ምክንያት አገኙ

ጊዜው 1922 ነበር። በወቅቱ ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በኦስትሪያ፣ ኢንስብሩክ ውስጥ ስብሰባ እያደረጉ ነበር። ከተሰብሳቢዎቹ መሃል በሰርቢያ ውስጥ በቮጅቮዲና ወረዳ ከምትገኘው አፓቲን የተባለች ከተማ የመጣ ፍራንዝ ብራንድ የተባለ ወጣት ይገኝበት ነበር። ተናጋሪው ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም እንደጠቀሰ ረብሸኞች እየጮሁ መቃወም ጀመሩ። ተናጋሪው ንግግሩን መቀጠል ባለመቻሉ ስብሰባው ተቋረጠ። ሆኖም ፍራንዝ በሰማው ነገር በጣም ስለተነካ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ጀመረ። ይህ አነስተኛ ጅምር ከባልካን አገሮች ውስጥ በአንዱ ለተገኘው አስደናቂ መንፈሳዊ እድገት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነበር።

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ዩጎዝላቪያ የሚለውን ስም ሲሰሙ ወዲያው ትውስ የሚላቸው ጦርነትና እልቂት ነው። ዘግናኝ የሆኑ ጭፍጨፋዎች፣ ተስፋቸው የጨለመባቸው ስደተኞች፣ የፈራረሱ ቤቶችና በሐዘን የተዋጡ ወላጅ አልባ ልጆች ምስል ወደ አእምሯቸው ይመጣል። ከ1991 እስከ 1995 ድረስ የባልካንን ባሕረ ገብ መሬት ሲያምሰው የነበረው ጦርነት የሰው ልጅ በራሱ ጥረት ብልጽግና የሰፈነበትና ከችግር ነጻ የሆነ ጊዜ ለማምጣት ሲያልመው የነበረውን ተስፋ መና በማስቀረት በፋንታው ያመጣውን ሥቃይና መከራ በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል። ጦርነቱ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሚኖሩትን ሰዎች በኢኮኖሚ ውድቀትና በከፋ ድህነት ሥር እንዲማቅቁ አድርጓል። a

ይሄን የመሰለ መከራ ባለበት የዓለም ክፍል ደስተኛ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ነገሩ አስገራሚ ቢመስልም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በዚህ የዓለም ክፍል ይገኛሉ። እንዲያውም እነዚህ ሕዝቦች በ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ በደስታ የተሞላ ልዩ ቀን አሳልፈዋል። ታዲያ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ፍራንዝ ብራንድ የተባለው ወጣት ለዚህ ደስታ አስተዋጽኦ ያበረከተው እንዴት ነው?

በባልካን አገሮች የተገኘ መንፈሳዊ እድገት

ፍራንዝ በሰማው አዲስ እውነት በጣም ተደስቶ ስለነበር ምሥራቹን ለማስፋፋት ወሰነ። ስሎቬንያ ውስጥ በኦስትሪያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ማሪቦር በተባለች ከተማ የፀጉር አስተካካይነት ሥራ አገኘና ፀጉራቸውን እየተስተካከሉ ለሚያዳምጡት ደንበኞቹ መስበክ ጀመረ። ይህ ጥረቱ ባስገኘው ውጤት በ1920ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በማሪቦር ጥቂት ሰዎችን ያቀፈ አንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቡድን ተቋቋመ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ከጊዜ በኋላ ኖቪ ስቬት (አዲስ ዓለም) የዓሳ ሬስቶራንት የሚል ተስማሚ ስያሜ በተሰጠው አንድ ሬስቶራንት ውስጥ ይሰጥ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ምሥራቹ በመላ አገሪቱ ተስፋፋ። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” (ፊልሞችን፣ ስላይዶችንና የድምፅ ቅጂዎችን ያካተተ የስምንት ሰዓት ትዕይንት ነው) የተሰኘው ፊልም ለምሥራቹ መስፋፋት አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። ከዚያም በ1930ዎቹ በጀርመን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተነሳውን ከባድ ተቃውሞ ሸሽተው ወደ ዩጎዝላቪያ የተሰደዱት የጀርመን አቅኚዎች በዩጎዝላቪያ ግዛት ውስጥ የነበሩትን ምሥክሮች ይበልጥ አጠናከሯቸው። የግል ምቾታቸውን መሥዋዕት በማድረግ ርቀው በሚገኙት የአገሪቱ ተራራማ አካባቢዎች ለመስበክ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ ለመልእክታቸው ያገኙት ምላሽ እምብዛም አበረታች አልነበረም። በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውን የመለሱት አስፋፊዎች 150 ብቻ ነበሩ።

በ1941 የተነሳው ከባድ ስደት እስከ 1952 ድረስ ዘለቀ። በመጨረሻም መስከረም 9, 1953 በጄኔራል ቲቶ የኮምኒስት አገዛዝ ሥር የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሲያገኙ ምንኛ ተደስተው ይሆን! በዚያ ዓመት 914 የሚያህሉ የምሥራቹ አስፋፊዎች የነበሩ ሲሆን ቁጥራቸው በፍጥነት ማደግ ጀመረ። በ1991 የአስፋፊዎቹ ቁጥር ወደ 7,420 የደረሰ ሲሆን በዚያ ዓመት በተካሄደው የመታሰቢያው በዓል ላይም 16,072 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

ከነሐሴ 16 እስከ 18, 1991 በዚህ አገር የመጀመሪያ የሆነው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ በዛግሬብ ክሮኤሺያ ተደረገ። ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር የመጡ 14,684 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። ይህ የማይረሳ ስብሰባ የይሖዋን ሕዝቦች ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው መከራ አዘጋጅቷቸዋል። ከክሮኤሺያ ወደ ሰርቢያ የሚያስገባውን የድንበር ኬላ ከተሻገሩት የመጨረሻ መኪናዎች ውስጥ ከሰርቢያ የመጡትን የስብሰባው ልዑካን ወደ አገራቸው የሚመልሷቸው አውቶቡሶች ይገኙበት ነበር። የመጨረሻው አውቶቡስ ኬላውን እንደተሻገረ ድንበሩ ተዘጋና ጦርነት ጀመረ።

የይሖዋ ሕዝቦች የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው

የጦርነቱ ዓመታት በባልካን አገሮች ለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ የፈተና ጊዜ ነበሩ። ሆኖም ይሖዋ በዚያ የሚገኙ ሕዝቦቹን ከፍተኛ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ ስለባረካቸው ለደስታ ምክንያት ሆኗቸዋል። ከ1991 ጀምሮ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሚገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ ጨምሯል። በ2001 የአገልግሎት ዓመት 13, 472 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ተገኝቶ ነበር።

በዛግሬብና በቤልግሬድ (ሰርቢያ) የሚገኙት ቢሮዎች በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ይካሄድ የነበረውን እንቅስቃሴ ይከታተሉ ነበር። ይሁን እንጂ በተገኘው ከፍተኛ እድገትና በአካባቢው በተከሰቱት ፖለቲካዊ ለውጦች የተነሳ በሉብሊያና (ስሎቬንያ) እና በስኮፒዬ (መቄዶንያ) አዳዲስ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ማቋቋምና በቤልግሬድና በዛግሬብ ተጨማሪ አዳዲስ ቢሮዎችን ማግኘት አስፈላጊ ነበር። በእነዚህ ቢሮዎች ውስጥ በግምት 140 የሚያህሉ ሠራተኞች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ ለይሖዋ ልባዊ የሆነ ቅንዓትና ፍቅር አላቸው። ከእነዚህ ውስጥ በቁጥር የሚበዙት የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን ወደ ክሮኤሽያ፣ መቄዶንያ፣ ሰርቢያና ስሎቬንያ ቋንቋዎች በመተርጎሙ ሥራ የሚሳተፉ ናቸው። በይሖዋ ምሥክሮች ከሚታተሙት መጽሔቶችና ጽሑፎች ውስጥ አብዛኞቹ ከእንግሊዝኛው እትም እኩል በእነዚህ ቋንቋዎች የሚታተሙ መሆናቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! እነዚህ ጽሑፎች በርካታ ሰዎች መጽናኛና ተስፋ እንዲያገኙ ይረዳሉ።

ሌላው እንዲደሰቱ የሚያደርጋቸው ምክንያት ደግሞ ከሌሎች አገሮች የሚመጡት በርካታ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚሰጧቸው ድጋፍ ነው። በቅርብ ዓመታት ብዙ የሚያማምሩ የመንግሥት አዳራሾች መገንባታቸው ደግሞ የጉባኤዎችን ደስታ እጥፍ ድርብ አድርጎታል። ይሁን እንጂ ገና ተጨማሪ ደስታ ይጠብቃቸው ነበር። ምን ይሆን?

በዓይነቱ ልዩ የሆነ ፕሮጀክት

በርካታ አስፋፊዎች ‘የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን በቋንቋችን እናገኝ ይሆን?’ እያሉ ያስቡ ነበር። በየዓመቱ የአውራጃ ስብሰባ በተደረገ ቁጥር እንዲህ ያለውን ማስታወቂያ ለመስማት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ይሁን እንጂ የእነዚህ ቋንቋዎች የትርጉም ቡድኖች ገና በቅርብ ዓመታት የተመሠረቱ ከመሆናቸውና ከተርጓሚዎቹ ቁጥር አነስተኛነት አኳያ ይሄን የመሰለ ከባድ ሥራ ማከናወን የሚቻለው እንዴት ይሆን?

የአስተዳደር አካሉ ሁኔታዎችን ከመረመረ በኋላ የክሮኤሺያ፣ የመቄዶንያና የሰርቢያ የትርጉም ቡድኖች ተባብረው በመሥራት አንዳቸው ከሌላው ሥራና ሐሳብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት የጋራ ፕሮጀክት እንዲቋቋም አጸደቀ። የክሮኤሺያ ቡድን ሥራውን በግንባር ቀደምትነት እንዲመራ ተደረገ።

የደስታ ቀን

ሐምሌ 23, 1999 በባልካን አገሮች በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ፈጽሞ የሚረሳ ቀን አይደለም። “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የተሰኘውን የአውራጃ ስብሰባ በተመሳሳይ ቀናት በቤልግሬድ፣ በሳራዬቮ (ቦስኒያ-​ሄርዜጎቪና)፣ በስኮፒዬና በዛግሬብ ለማድረግ እቅድ ወጥቶ ነበር። ኔቶ በሚያደርገው የአየር ድብደባ ምክንያት በቤልግሬድ የሕዝብ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ ስለነበር በዚያ የአውራጃ ስብሰባ ማድረግ መቻሉ ለተወሰነ ጊዜ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር። ከብዙ ወራት አለመረጋጋት በኋላ ወንድሞች እርስ በእርስ እንደሚገናኙ በማወቃቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! ይሁንና በስብሰባው ላይ ያገኙት ነገር ፈጽሞ ከጠበቁት በላይ ነበር።

አርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ በአራቱም ስብሰባዎች ላይ አንድ ልዩ የሆነ ማስታወቂያ ተነገረ። በጠቅላላው 13,497 የሚያህሉት ተሰብሳቢዎች በዝምታ ተውጠው የሚነገረውን ማስታወቂያ በጉጉት ይከታተሉ ነበር። በመጨረሻም ተናጋሪው የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በክሮኤሺያና በሰርቢያ ቋንቋ ታትሞ መውጣቱንና በመቄዶንያ ቋንቋም የትርጉም ሥራው በመካሄድ ላይ እንደሆነ ሲናገር ተሰብሳቢዎቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። እንደ ነጎድጓድ ያስተጋባው ጭብጨባ ተናጋሪው ማስታወቂያውን ተናግሮ እንዲጨርስ እንኳ ጊዜ አልሰጠውም። በሳራዬቮ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ማስታወቂያው ፈጽሞ ያልጠበቁት በመሆኑ ለጥቂት ሰኮንዶች ድንገተኛ ጸጥታ ሰፈነ። ከዚያም ለረጅም ጊዜ የቆየ ጭብጨባ ተከተለ። በቤልግሬድ አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የደስታ እምባ ያነቡ ሲሆን ተናጋሪው ማስታወቂያውን ተናግሮ ከመጨረሱ በፊት ተደጋጋሚ ጭብጨባ ንግግሩን ያቋርጠው ነበር። ሁሉም ምንኛ ተደስተው ነበር!

የይሖዋ ምሥክሮች በክሮኤሺያና በሰርቢያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን የማሳተም መብት ማግኘታቸውም የዚህን ስጦታ ዋጋማነት ይበልጥ ከፍ አድርጎታል። በመሆኑም በክሮኤሺያና በሰርቢያ ቋንቋዎች የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በእነዚሁ ቋንቋዎች ከተዘጋጀ ከሌላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ጋር በአንድ ጥራዝ እንዲታተም ተደረገ። በሰርቢያ ቋንቋ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው በላቲንና በሲሪሊክ ፊደላት ነበር።

በባልካን አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ላገኟቸው ግሩም በረከቶችና መመሪያዎች አመስጋኝ በመሆን “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” በሚሉት የዳዊት ቃላት ከልብ ይስማማሉ። ምንም እንኳን ከባድ መከራዎች እየደረሱባቸው ቢሆንም ‘የይሖዋን ደስታ ኃይላቸው’ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል።​—⁠መዝሙር 23:4፤ ነህምያ 8:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ቦስኒያ-ሄርዜጎቪና፣ ክሮኤሽያ፣ መቄዶንያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ሰርቢያና ስሎቬኒያ የተባሉትን ስድስት ሪፑብሊኮች ያቀፈች አገር ነበረች።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ርቀው በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ለመስበክ ከማሊቦር፣ ስሎቬንያ የመጣው የመጀመሪያው የአስፋፊዎች ቡድን