በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያኖች መቅናት ይኖርባቸዋልን?

ክርስቲያኖች መቅናት ይኖርባቸዋልን?

ክርስቲያኖች መቅናት ይኖርባቸዋልን?

ቅንዓት ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ ነውን? ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ‘ፍቅርን እንድንከታተል’ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። በተጨማሪም ‘ፍቅር እንደማይቀና’ ተነግሮናል። (1 ቆሮንቶስ 13:​4፤ 14:​1) በሌላው በኩል ደግሞ ‘ይሖዋ . . . ቀናተኛ አምላክ’ እንደሆነም ተነግሮናል። እንዲሁም አምላክን ‘እንድንመስል’ ታዝዘናል። (ዘጸአት 34:​14፤ ኤፌሶን 5:​1 NW ) እነዚህ ሐሳቦች እርስ በርስ የሚጋጩ የሚመስሉት ለምንድን ነው?

ይህ የሆነበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቅንዓት” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ሰፊ ትርጉም ያዘሉ በመሆናቸው ነው። እንደ ዓረፍተ ነገሩ አገባብ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልእክት ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል “ቅንዓት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ለሌላ ለማጋራት ፈቃደኛ አለመሆን፤ ተቀናቃኝን ፈጽሞ አለመታገስ፤ የጋለ ስሜት፣ ቅንዓት [የጽድቅ ወይም የክፋት]፤ መመቅኘት” ማለት ሊሆን ይችላል። የግሪክኛው ቃልም ተመሳሳይ ትርጉም አለው። እነዚህ ቃላት ተቀናቃኛችን እንደሆነ ለምናስበው ሰው የሚኖረንን የተዛባና ሚዛኑን የሳተ አመለካከት ሊያመለክቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 14:​30) በተጨማሪም አንድ ግለሰብ የሚወደውን ሰው ከጉዳት እንዲጠብቀው የሚገፋፋውን ከአምላክ የሚገኝን ጥሩ ባሕርይም ሊያመለክቱ ይችላሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:​2

ከሁሉ የላቀ ምሳሌ

ተገቢ ቅንዓት በማሳየት ረገድ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ሕዝቡን ከመንፈሳዊና ከሥነ ምግባራዊ አደጋ ለመጠበቅ የሚያነሳሳው ውስጣዊ ግፊት ንጹሕና የጠራ ነው። ጽዮን እያለ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይጠራው ስለነበረው የጥንት ሕዝቡ ሲናገር “ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፣ በታላቅም ቁጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ” ብሏል። (ዘካርያስ 8:​2) አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን ከአደጋ ለመጠበቅ ዘወትር ዝግጁ እንደሆነ ሁሉ ይሖዋም አገልጋዮቹን ከአካላዊም ሆነ ከመንፈሳዊ አደጋ ለመጠበቅ ዝግጁ ነው።

ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲል ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቷል። ይህ መጽሐፍ ሕዝቡ በጥበብ መጓዙን እንዲቀጥል ለመርዳት የሚያስችሉ በርካታ ማበረታቻዎችንና በጥበብ የተመላለሱ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ ይዟል። በኢሳይያስ 48:​17 ላይ እንዲህ የሚል እናነብባለን:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” የይሖዋ ቅንዓት እኛን እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ እንደሚያነሳሳው ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሖዋ ጠቃሚ በሆነ መንገድ የሚቀና ባይሆን ኖሮ ተሞክሮ የጎደለን ከመሆናችን የተነሣ ብዙ ችግሮች ይደርሱብን ነበር። ይሖዋ የሚቀናው ራስ ወዳድ ስለሆነ አይደለም።

ታዲያ በአምላካዊ ቅንዓትና ተገቢ ባልሆነ ቅንዓት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ይህንን ለመገንዘብ የማርያምንና የፊንሐስን ምሳሌ እንመልከት። ለተግባር ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ ልብ በል።

ማርያምና ፊንሐስ

ማርያም፣ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይመሩ የነበሩት የሙሴና የአሮን ታላቅ እህት ነች። እስራኤላውያን በምድረ በዳ እየተጓዙ ሳለ ማርያም በወንድሟ በሙሴ ላይ ቀናች። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና . . . ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። እነርሱም:- በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” በሙሴ ላይ የተሸረበውን ሴራ የቆሰቆሰችው ማርያም ሳትሆን አትቀርም። ምክንያቱም ይሖዋ አክብሮት የጎደለው ጠባይ በማሳየቷ ለአንድ ሳምንት በሥጋ ደዌ የቀጣው ማርያምን እንጂ አሮንን አልነበረም።​—⁠ዘኍልቅ 12:​1-15

ማርያም በሙሴ ላይ እንድትነሳ የገፋፋት ምንድን ነው? ለእውነተኛው አምልኮ ተቆርቁራ ወይም ሌሎች እስራኤላውያንን ከአደጋ ለመጠበቅ ባላት ፍላጎት ተገፋፍታ ይሆን? እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ማርያም በልብዋ ውስጥ ታዋቂ የመሆን ፍላጎትና የሥልጣን ጥም እንዲያቆጠቁጥ የፈቀደች ይመስላል። በእስራኤል ውስጥ ነቢይት እንደመሆኗ መጠን በሰዎች በተለይም በሴቶች ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት አትርፋ ነበር። እስራኤል ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ቀይ ባሕርን በተሻገረ ጊዜ በዘፈንና በሙዚቃ መርታቸው ነበር። ይሁን እንጂ አሁን የሙሴ ሚስት እንደምትቀናቀናትና ክብሯን ልትጋራት እንደምትችል በማሰብ ተጨንቃ ሊሆን ይችላል። ራስ ወዳድ በሆነ የቅንዓት ስሜት ተገፋፍታ ይሖዋ በቀባው በሙሴ ላይ አንጎራጎረች።​—⁠ዘጸአት 15:​1, 20, 21

በሌላው በኩል ደግሞ ፊንሐስን ለድርጊት የገፋፋው ከዚህ የተለየ ስሜት ነበር። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜያት በፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ሳለ ሞዓባውያንና ምድያማውያን ሴቶች ብዙ እስራኤላውያን ወንዶችን አባብለው የጾታ ብልግና እና የጣዖት አምልኮ እንዲፈጽሙ አደረጓቸው። ሰፈሩን ለማጽዳትና የይሖዋን የሚነድድ ቁጣ ለመመለስ ሲባል የእስራኤል መሳፍንት ኃጢአት የሠራውን እያንዳንዱን እስራኤላዊ ወንድ እንዲገድሉ ትእዛዝ ተሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዘንበሪ የተባለ አንድ ስምዖናዊ የሕዝብ አለቃ የፆታ ብልግና ለመፈጸም ከስቢ የተባለችን አንዲት ምድያማዊት ሴት “በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት” ወደ ሰፈሩ ይዟት ገባ። በዚህ ወቅት ፊንሐስ አንድ ወሳኝ እርምጃ ወሰደ። ለይሖዋ አምልኮ በመቅናትና የሰፈሩን ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ለመጠበቅ በማሰብ እነዚህን ዘማውያን በድንኳናቸው ውስጥ እንዳሉ ገደላቸው። ፊንሐስ ይሖዋን ‘የሚቀናቀን አንዳችም ነገር ለመታገሥ’ ባለመፍቀድ ላሳየው ‘የቅንዓት ቁጣ’ ተመስግኗል። ፊንሐስ ወዲያውኑ የወሰደው እርምጃ 24, 000 ሰዎችን ያጠፋው መቅሰፍት እንዲቆም አድርጓል። ይሖዋም በፊንሐስ የዘር ሐረግ የክህንነት አገልግሎት ለዘላለም እንዲቀጥል በማድረግ ክሶታል።​—⁠ዘኍልቅ 25:​4-13 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል

በእነዚህ ሁለት የቅንዓት መግለጫዎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ማርያም በወንድሟ ላይ የተነሳሳችው ከራስ ወዳድነት በመነጨ ቅንዓት ሲሆን ፊንሐስ ግን በአምላካዊ ቅንዓት ተገፋፍቶ ፍትህ አስፍኗል። ልክ እንደ ፊንሐስ እኛም ለይሖዋ ስም፣ ለአምልኮውና ለሕዝቡ በመቆም በድፍረት እንድንናገር ወይም አንድ ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ የሚያስገድድ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል።

የተሳሳተ ቅንዓት

ተገቢ ያልሆነ ወይም የተሳሳተ ቅንዓት ሳናውቀው ሊጠናወተን ይችላልን? አዎን፣ ይችላል። ይህ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት አይሁዳውያን ላይ ደርሷል። በቅንዓት በመነሳሳት ከአምላክ የተሰጣቸውን ሕግና ወጋቸውን ለመጠበቅ ጥረት አድርገዋል። ሕጉን ለመጠበቅ ባደረጉት ጥረት በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም የሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዝርዝር ሕጎችና ደንቦች አውጥተው ነበር። (ማቴዎስ 23:​4) አምላክ የሙሴን ሕግ ጥላ በሆነለት አካል እንደተካው አልተገነዘቡም ወይም ለመገንዘብ ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለዚህም የተሳሳተው ቅንዓታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ላይ በቁጣ እንዲነሱ አድርጓቸዋል። በአንድ ወቅት በተሳሳተ መንገድ ለሕጉ ይቀና የነበረው ጳውሎስ ራሱ ለሕጉ የሚከራከሩ ሰዎች ‘በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንደሚቀኑ’ ተናግሯል።​—⁠ሮሜ 10:​2፤ ገላትያ 1:​14

እንዲያውም ክርስቲያን የሆኑ በርካታ አይሁዳውያን እንኳ ሳይቀሩ ለሕጉ ከነበራቸው ተገቢ ያልሆነ ቅንዓት መላቀቅ ከብዷቸው ነበር። ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ካጠናቀቀ በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው የአስተዳደር አካል የአሕዛብን መለወጥ አስመልክቶ ሪፖርት አቅርቧል። በወቅቱ የነበሩት በሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን አይሁዳውያን ‘ለሕግ ይቀኑ ነበር።’ (ሥራ 21:​20) ይህ የሆነው አስተዳደር አካሉ አሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው የሚገልጽ መመሪያ ካወጣ በኋላ ነው። ሕጉን ከመጠበቅ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጉባኤው ውስጥ መከፋፈልን ፈጥረው ነበር። (ሥራ 15:​1, 2, 28, 29፤ ገላትያ 4:​9, 10፤ 5:​7-12) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይሖዋ ሕዝቡን የሚይዝበትን መንገድ በትክክል ባለመገንዘባቸው የራሳቸውን አመለካከት በማራመድ ሌሎችን ይነቅፉ ነበር።​—⁠ቆላስይስ 2:​17፤ ዕብራውያን 10:​1

እንግዲያው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለውን የገዛ ራሳችንን አስተሳሰብ ለማራመድ በመሞከር በተሳሳተ የቅንዓት ወጥመድ እንዳንያዝ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በሚጠቀምበት መገናኛ መስመር በኩል የሚመጣልንን አዲስና የተሻሻለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ መቀበላችን ተገቢ ነው።

ለይሖዋ የምትቀኑ ሁኑ

ሆኖም አምላካዊ ቅንዓት በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የራሱ የሆነ ቦታ አለው። ስለ ስማችን ወይም መብታችን ከልክ በላይ የመጨነቅ አዝማሚያ ሲያድርብን አምላካዊ ቅንዓት ትኩረታችንን በይሖዋ ላይ እንድናደርግ ይረዳናል። ስለ እርሱ የሚናገረውን እውነት ለማወጅ የሚያስችሉ መንገዶች እንድንፈልግና ለመንገዶቹና ለሕዝቦቹ ጠበቆች ሆነን እንድንቆም ይገፋፋናል።

የአምላክ ሕግ ስለ ደም የሚናገረውን በተሳሳተ መንገድ የተረዳች አንዲት ሴት ታነጋግራት የነበረችውን አኪኮ የተባለች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ክፉኛ አጣጣለቻት። አኪኮ ደምን በደም ሥር መውሰድ በሕክምናው መስክ የሚያስከትለውን ችግር በመጥቀስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ሞከረች። አኪኮ ስለ ይሖዋ ለመናገር ካላት ፍላጎት የተነሳ ውይይቱን የሴትዮዋ ተቃውሞ ዋና መሠረት ነው ብላ ወዳሰበችው ርዕስ ለወጠችው። ሴትዮዋ በአምላክ መኖር አታምንም ነበር። ፍጥረት የአምላክን መኖር ምን ያህል እንደሚደግፍ በመግለጽ አወያየቻት። በድፍረት የሰጠችው ምሥክርነት ሴትዮዋ የነበራትን መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንድታስወግድ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠናም በር ከፍቷል። በዛሬው ጊዜ የቀድሞዋ ቁጡ የቤት ባለቤት ይሖዋን የምታወድስ ሆናለች።

ለእውነተኛው አምልኮ ያለን ተገቢ ቅንዓት በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በገበያ ቦታዎችና በጉዞ ላይ እያለን ስለ እምነታችን እንድንናገርና ለእምነታችን እንድንቆም የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንድንጠቀምባቸው ያደርገናል። ለምሳሌ ያህል ሚዶሪ እምነቷን ለሥራ ባልደረቦቿ ለመናገር ቆርጣ ተነሳች። በ40ዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት የሥራ ባልደረባዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጨርሶ መነጋገር እንደማትፈልግ ነገረቻት። በኋላም በሌላ ወቅት ከዚህችው ሴትዮ ጋር እየተጨዋወቱ ሳለ ሴትዮዋ ስለ ልጅዋ መጥፎ ጠባይ አማርራ ትነግራታለች። ሚዶሪ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች  a የተባለውን መጽሐፍ አሳየቻትና ከልጅዋ ጋር መጽሐፉን ለማጥናት ዝግጅት እንድታደርግላት ጠየቀቻት። ጥናቱ ቢጀመርም እናትዬው ግን በጥናቱ ላይ አብራቸው አትሆንም ነበር። ሚዶሪ ለሴትዮዋ የይሖዋ ምሥክሮች —⁠ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት * የተባለውን ቪድዮ ልታሳያት ወሰነች። ይህም ሴትዮዋ ስለ ምሥክሮቹ የነበራትን የተሳሳተ አመለካከት እንድታስወግድ ረዳት። ባየችው ነገር በመነካቷ “እንደ ይሖዋ ምሥክሮች መሆን እፈልጋለሁ” በማለት ተናገረች። በኋላም ከልጅዋ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች።

ተገቢ ቅንዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም የሚያበረክተው የራሱ የሆነ ድርሻ አለው። ሞቅ ያለ የፍቅርና የመተሳሰብ መንፈስ እንዲሰፍን ከማድረጉም በላይ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን ሊጎዱ የሚችሉ እንደ ጎጂ ሐሜትና ክሕደት የመሰሉ አፍራሽ ተጽዕኖዎችን እንድንዋጋ ያነሳሳናል። አምላካዊ ቅንዓት የጉባኤ ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ መጥፎ ድርጊት የፈጸሙትን በመገሰጽ የሚያሳልፉትን ውሳኔ እንድንደግፍ ይገፋፋናል። (1 ቆሮንቶስ 5:​11-13፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​20) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ አማኞች ያለውን ቅንዓት አስመልክቶ ሲጽፍ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፣ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 11:​2) የእኛም ቅንዓት የጉባኤውን መሠረተ ትምህርት እንዲሁም መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ለመጠበቅ የቻልነውን ሁሉ እንድናደርግ የሚያነሳሳን ይሁን።

አዎን፣ በተገቢው መንገድ የዳበረ ቅንዓት ማለትም አምላካዊ ቅንዓት በሌሎች ላይ በጎ ተጽእኖ ያሳድራል። የይሖዋን ሞገስ ያስገኛል እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሊያሳዩት የሚገባ ባሕርይ መሆንም ይኖርበታል።​—⁠ዮሐንስ 2:​17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፊንሐስ በአምላካዊ ቅንዓት ተነሳስቶ እርምጃ ወስዷል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተሳሳተ የቅንዓት ወጥመድ ውስጥ እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላካዊ ቅንዓት እምነታችንን ለሌሎች እንድናካፍልና የወንድማማች ኅብረታችንን ከፍ አድርገን እንድንመለከት ያነሳሳናል