በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ንብረት የሆነን ሕንፃ ገዝቶ ወደ መንግሥት አዳራሽነት መለወጥ ሃይማኖትን እንደመቀላቀል ይቆጠራል?

በአጠቃላይ ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር እንዲህ የመሰለ ውል ከመፈጸም ይቆጠባሉ። ያም ሆኖ ግን እንዲህ ማድረጉ ሃይማኖትን እንደመቀላቀል ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። ከዚህ ይልቅ ለአንድ ጊዜ እንደተደረገ ግብይት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሁለቱም ወገኖች የሚጠቀሙበት የአምልኮ ቦታ ለመሥራት ሲል ከሌላ ሃይማኖት ጋር ውል አይፈጽምም።

ታዲያ በይሖዋ ዓይን ሃይማኖትን እንደመቀላቀል ተደርጎ የሚቆጠረው ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን መመሪያ ልብ በል:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? . . . ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 6:​14-17) ጳውሎስ እዚህ ላይ “ተካፋይነት” እና “ኅብረት” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው?

ጳውሎስ ተካፋይነት በማለት የገለጸው ቃል አምልኮንና ከጣዖት አምላኪዎች ብሎም ከማያምኑ ጋር የሚደረገውን መንፈሳዊ ግንኙነት ያመለክታል። የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ‘ከአጋንንት ማዕድ እንዳትካፈሉ’ በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:​20, 21) ስለዚህ ሃይማኖትን መቀላቀል ማለት ከሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን ጋር በአምልኮ መካፈል ወይም መንፈሳዊ ኅብረት መፍጠር ማለት ነው። (ዘጸአት 20:​5፤ 23:​13፤ 34:​12) የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ቀደም የሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ንብረት የነበረን ሕንፃ ቢገዙ እንኳን ይህን የሚያደርጉት ቦታውን ወደ መንግሥት አዳራሽነት ለመለወጥ ሲሉ ብቻ ነው። የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት ግን ከሐሰት አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮች በሙሉ እንዲወገዱ ይደረጋል። በዚህ መንገድ ከተስተካከለ በኋላ ለይሖዋ አምልኮ ይወሰናል። በእውነተኛውና በሐሰተኛው አምልኮ መካከል ምንም ዓይነት ተካፋይነት ወይም ኅብረት አይኖርም።

ግዢውን በተመለከተ ከሌላኛው ወገን ጋር የሚደረገው ግንኙነት በጣም ውስንና በሥራ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል። የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑ ሰዎች እንደምንበልጥ ባይሰማንም ከእነርሱ ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት መፍጠርም ሆነ በአምልኳቸው መካፈል አይኖርብንም። a

አንድ ጉባኤ የሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ንብረት የሆነን ሕንፃ ለመከራየት ቢያስብስ? አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ሕንፃ መከራየት ከሌላው ወገን ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት መፍጠርን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ሊወገድ የሚገባው ነገር ነው። እንዲህ ያለውን ሕንጻ ለአንድ ጊዜ ብቻ እንኳ መከራየት ቢያስፈልግ የጉባኤው የሽማግሌዎች አካል የሚከተሉትን ነጥቦች ማጤን ይኖርበታል:- በሕንፃው ውስጥ ወይም ውጪ ጣዖታት ወይም ሃይማኖታዊ ምስሎች አሉ? ይህንን ሕንፃ በመጠቀማችን የአካባቢው ሰዎች ምን ይሰማቸዋል? ይህንን ሕንፃ በመጠቀማችን የሚሰናከል የጉባኤ አባል ይኖር ይሆን? (ማቴዎስ 18:​6፤ 1 ቆሮንቶስ 8:​7-13) ሽማግሌዎች እነዚህን ነጥቦች ከመረመሩ በኋላ ይወስናሉ። እንዲህ ያለውን ሕንፃ ገዝተው ወደ መንግሥት አዳራሽነት ለመለወጥ ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት የራሳቸው የሽማግሌዎቹና የጠቅላላው የጉባኤ አባላት ሕሊና ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ከሌላቸው ድርጅቶች ጋር የሚደረግን የሥራ ግንኙነት በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28 እና 29ን ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀደም ሲል ምኩራብ የነበረው ይህ ሕንፃ ተገዝቶ ወደ መንግሥት አዳራሽነት ተለውጧል