በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ዲያብሎስን ተቃወሙ’

‘ዲያብሎስን ተቃወሙ’

‘ዲያብሎስን ተቃወሙ’

“ዲያብሎስን . . . ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል።”​ያዕቆብ 4:​7

1. ስላለንበት ዓለም ምን ለማለት ይቻላል? ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው ንቁ ሆነው መኖር ያለባቸው ለምንድን ነው?

 “ዛሬ ዲያብሎስ ብቻ እንጂ አምላክ ያለ አይመስልም።” ፈረንሳዊው ደራሲ አንድሬ ማልሮ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የምንኖርበትን ዓለም ጥሩ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። ብዙዎቹ የሰው ሥራዎች በአብዛኛው የአምላክን ፈቃድ ሳይሆን የዲያብሎስን እኩይ ምግባር የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሰይጣን ሰዎችን ‘በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችና በዓመፅ እያታለለ’ በተሳሳተ መንገድ እየመራቸው ነው። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ሆኖም ሰይጣን በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ዒላማውን በዋነኛነት ያነጣጠረው በአምላክ አገልጋዮች ላይ ሲሆን ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁትና ለኢየሱስ በሚመሠክሩት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ጦርነት ከፍቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ራእይ 12:9, 17) በመሆኑም እነዚህ የአምላክ ቅቡዕ ምሥክሮችና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው አጋሮቻቸው ንቁ ሆነው መኖር ይገባቸዋል።

2. ሰይጣን ሔዋንን ያሳታት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ፍርሃት እንደተሰማው ገልጿል?

2 ሰይጣን የለየለት አታላይ ነው። እባብን መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ሔዋን ያለ አምላክ እርዳታ ራሴን ብመራ ከፍተኛ ደስታ አገኛለሁ ብላ እንድታስብ አደረጋት። (ዘፍጥረት 3:1-6) ከአራት ሺህ ዓመት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰይጣን የማታለያ ወጥመድ ይያዙ ይሆናል የሚል ፍርሃት እንዳደረበት ተናግሯል። ጳውሎስ “እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ሰይጣን የሰዎችን አእምሮ በመበከል አስተሳሰባቸው እንዲበላሽ ያደርጋል። ሔዋንን እንዳሳታት ሁሉ ክርስቲያኖችም ይሖዋና ልጁ የሚያወግዟቸው ነገሮች ደስታ የሚገኝባቸው ነገሮች እንደሆኑ አድርገው በተሳሳተ መንገድ እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

3. ይሖዋ የዲያብሎስን ጥቃት መከላከል እንድንችል ምን ዝግጅት አድርጎልናል?

3 ሰይጣን ያልጠረጠረን እንስሳ ለመያዝ ወጥመድ ከሚያስቀምጥ አዳኝ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በሰይጣን ወጥመድ እንዳንያዝ ከፈለግን “በልዑል መጠጊያ [“መሸሸጊያ፣” NW ]” ውስጥ ማለትም ይሖዋ የእርሱን አጽናፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነት እንደተቀበሉ በተግባር የሚያሳዩ ሰዎችን ለመጠበቅ ባዘጋጀው ምሳሌያዊ ቦታ ‘መኖር’ ይገባናል። (መዝሙር 91:1-3) ሁላችንም ‘የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንችል ዘንድ’ ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን ጥበቃ ማግኘት ይኖርብናል። (ኤፌሶን 6:11) እዚህ ላይ “ሽንገላ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “መሠሪ ድርጊቶች” ወይም “መሠሪ ዘዴዎች” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በእርግጥም ዲያብሎስ የይሖዋን አገልጋዮች ለማጥመድ በተለያዩ የተንኮል ድርጊቶችና መሠሪ ዘዴዎች ይጠቀማል።

ሰይጣን ለጥንት ክርስቲያኖች አዘጋጅቶት የነበረው ወጥመድ

4. የጥንት ክርስቲያኖች በምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ይኖሩ ነበር?

4 በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩት ክርስቲያኖች የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ በከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዚህ ወቅት በሮማ ግዛት ሰፍኖ የነበረው ሰላም ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ አድርጓል። ይህ ብልጽግና የገዢው መደብ ዘና የሚልበት ትርፍ ጊዜ እንዲያገኝ ያስቻለው ሲሆን ገዥዎቹ ሕዝቡ ለዓመፅ እንዳይነሳሳ ለማድረግ ሲሉ የተለያዩ መዝናኛዎች በየቦታው እንዲከፈቱ አድርገው ነበር። እንዲያውም በአንዳንድ ወቅቶች የበዓል ቀናት በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ ከሥራ ቀናት ጋር እኩል የሚሆኑባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሕዝቡ ጠግበው እንዲያድሩና አእምሯቸው በሌሎች ነገሮች እንዲያዝ መሪዎቹ በቂ ምግብ ለማቅረብና የተለያዩ መዝናኛዎችን ለማቋቋም ባጀት መድበው ነበር።

5, 6. (ሀ) ክርስቲያኖች በሮማ ቲያትር ቤቶችና ስታዲዮሞች ውስጥ መገኘታቸው ተገቢ ያልነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን ምን ዘዴ ተጠቅሟል? ክርስቲያኖችስ በዚህ ወጥመድ ከመያዝ መዳን ይችሉ የነበረው እንዴት ነው?

5 ታዲያ ይህ ሁኔታ በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ምን አደጋ አስከትሎባቸው ይሆን? ከሐዋርያት ሞት በኋላ የተነሱ እንደ ተርቱሊያን ያሉ ጸሐፊዎች ከጻፏቸው የማስጠንቀቂያ ሐሳቦች ለመረዳት እንደሚቻለው በጊዜው የነበሩት አብዛኞቹ መዝናኛዎች የእውነተኛ ክርስቲያኖችን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ አቋም በሚያበላሹ አደጋዎች የተሞሉ ነበሩ። አንደኛ ነገር፣ ብዙዎቹ የሕዝብ በዓላትና ጨዋታዎች አረማዊ አማልክትን ለማክበር የሚካሄዱ ነበሩ። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18) በቲያትር ቤቶች የሚቀርቡት ብዙዎቹ ባሕላዊ ቲያትሮች ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና የሚታይባቸው አሊያም ዘግናኝ በሆኑ ደም አፋሳሽ ድርጊቶች የተሞሉ ነበሩ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እነዚህ ቲያትሮች በሕዝብ ዘንድ እየተሰለቹ በመምጣታቸው በአብዛኛው አንድ ተዋናይ ብቻ የሚተውንባቸውን በአካላዊ እንቅስቃሴዎች የሚሠሩ በሙዚቃ የታጀቡ ድራማዎች ይቀርቡ ጀመር። ዤሮም ካርኮፒኖ የተባሉ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ዴይሊ ላይፍ ኢን ኤንሸት ሮም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በእነዚህ ድራማዎች ላይ የሚካፈሉት ሴት ተዋንያን እርቃናቸውን መድረክ ላይ እንዲወጡ ይፈቀድላቸው ነበር። . . . ደም እንደ ውኃ ይፈስሳል። . . . ልቅ የሆነ ብልግና ይታይ ስለነበር ድራማው የሕዝቡን ቀልብ በእጅጉ መሳብ ችሏል። በቲያትር ቤቶቹ በሚቀርቡት ሰቅጣጭና ዘግናኝ ድርጊቶች የሕዝቡ ልብ ደንድኖና ባሕርያቸው ተበላሽቶ ስለነበር ተመልካቹ በሚያየው ነገር አይዘገነንም ነበር።”​—⁠ማቴዎስ 5:27, 28

6 ቲያትር በሚታይባቸው ስታዲዮሞች ውስጥ ግላዲያተር ተብለው የሚታወቁ ሰዎች እርስ በርስ ወይም ከአራዊት ጋር እንዲታገሉ ይደረግ ነበር። ከአራዊት ጋር በሚታገሉበት ጊዜ አራዊቱን መግደል ካቃታቸው በአራዊቱ ይገደሉ ነበር። ሞት የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ከጊዜ በኋላ ደግሞ በርካታ ክርስቲያኖች አስፈሪ የሆኑ አራዊት ይለቀቁባቸው ነበር። ሰይጣን ይህን ዘዴ የተጠቀመው የሕዝቡን ስሜት በማደንደን የሥነ ምግባር ብልግናና የዓመፅ ድርጊቶች የተለመዱና አልፎ ተርፎም የሚፈለጉ ነገሮች እንዲሆኑ ለማድረግ ነበር። በዚህ ወጥመድ ከመያዝ ማምለጥ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ከቲያትር ቤቶችና ግላድያተሮች ትግል ከሚያደርጉባቸው ስታዲዮሞች መራቅ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:32, 33

7, 8. (ሀ) አንድ ክርስቲያን የሰረገላ ውድድር ለማየት ቢሄድ ጥበብ ያልነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን በሮማ የሚገኙ የገላ መታጠቢያ ቦታዎችን ክርስቲያኖችን ለማጥመድ የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?

7 በአውላላ ሜዳ ላይ ይደረግ የነበረው የሰረገላ ውድድር አስደሳች ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ተመልካቾችን ለጠብ የሚያነሳሳ ስለነበር እንዲህ ዓይነት ውድድሮችን መመልከት ለክርስቲያኖች ተገቢ አልነበረም። በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ አንድ ጸሐፊ አንዳንዶቹ ተመልካቾች እርስ በርሳቸው ጠብ ይፈጥሩ እንደነበረ የተናገረ ሲሆን ካርኮፒኖ የተባሉት ጸሐፊም “ኮከብ ቆጣሪዎችና ዝሙት አዳሪዎች” በውድድሩ ሥፍራ “ገበያቸውን የሚያጧጡፉበት ቦታ ነበራቸው” ብለዋል። በእርግጥም የሰረገላ ውድድር የሚደረግባቸው ቦታዎች ክርስቲያኖች ለመዝናናት ብለው የሚሄዱባቸው ቦታዎች አልነበሩም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

8 በሮማ ስለሚገኙ እውቅ የገላ መታጠቢያ ቦታዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ንጽሕናን ለመጠበቅ ገላን መታጠብ ምንም ስህተት የለበትም። ሆኖም በሮማ የሚገኙት ብዙዎቹ የገላ መታጠቢያ ቦታዎች የእሽት አገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ የስፖርት ማዕከል፣ ቁማር ቤቶች እንዲሁም የምግብና መጠጥ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አካትተው የያዙ ነበሩ። ወንዶችና ሴቶች በተራ የሚታጠቡበት ፕሮግራም የወጣ ቢሆንም እንኳ ሁለቱም ፆታዎች ለመታጠብ አብረው ቢገቡ አይከለከሉም ነበር። የእስክንድርያው ክሌመንት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የገላ መታጠቢያው እገሌ ከገሌ ሳይል ለወንዶችም ለሴቶችም ክፍት ነበር። እዚያም እርቃናቸውን ሆነው ያሻቸውን የብልግና ድርጊት ይፈጽሙ ነበር።” ሰይጣን ክርስቲያኖችን ለማጥመድ ለሕዝብ አገልግሎት የተዘጋጁ ተቋማትን እንደ ወጥመድ ተጠቅሞባቸው ነበር። ስለዚህ ብልህ የሆኑ ክርስቲያኖች ወደዚህ አካባቢ ከመሄድ ተቆጥበዋል።

9. የጥንት ክርስቲያኖች ከየትኞቹ ወጥመዶች መራቅ ነበረባቸው?

9 የሮማ ኃያል መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት ቁማር በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ የጊዜ ማሳለፊያ ነበር። የጥንት ክርስቲያኖች የሰረገላ ውድድር ከሚደረግበት አካባቢ በመራቅ ቁማር ከመጫወት ታቅበዋል። የገንዘቡ መጠን አነስተኛ ቢሆንም የቁማር ጨዋታዎች በየመሸታ ቤቱና በየሆቴል ቤቱ በድብቅ ይካሄዱ ነበር። አንዱ ተጫዋች በእጁ ጠጠሮችን ይይዝና ሌሎቹ ጎዶሎ ወይም ሙሉ በማለት ይወራረዱ ነበር። ያለ ምንም ልፋት ገንዘብ አገኛለሁ የሚለው ተስፋ ሕዝቡ ለቁማር ከፍተኛ ቦታ እንዲሰጥ አድርጎታል። (ኤፌሶን 5:5) ከዚህም በላይ በእነዚህ መጠጥ ቤቶች ውስጥ አስተናጋጅ ሆነው የሚሠሩት ሴቶች ዝሙት አዳሪዎች በመሆናቸው አካባቢው ለፆታ ብልግና የሚያጋልጥ ነበር። ሰይጣን በሮማ ግዛት ሥር በሚገኙ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ለማጥመድ ይጠቀምባቸው ከነበሩት መሣሪያዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። በዛሬው ጊዜስ ሁኔታው ከዚህ የተለየ ይሆን?

በዛሬው ጊዜ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው ወጥመዶች

10. በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ በጥንቱ የሮማ ግዛት ተስፋፍቶ ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

10 ሰይጣን በዛሬ ጊዜ የሚጠቀምባቸው ወጥመዶች ካለፉት ጊዜያት እምብዛም የተለዩ አይደሉም። ብልሹ በሆነችው የቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ‘በሰይጣን እንዳይታለሉ’ ሐዋርያው ጳውሎስ ጠንካራ ምክር ሰጥቷቸዋል። “የእርሱን [የሰይጣንን] አሳብ አንስተውም” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) በዛሬ ጊዜ በብዙ ያደጉ አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ጊዜ ተስፋፍቶ ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ብዙ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሰፊ የእረፍት ጊዜ አላቸው። በመንግሥት የሚተዳደሩ የሎተሪ ድርጅቶች ለድሆች ተስፋን ይሸጣሉ። የሰዎችን አእምሮ ማርከው የሚይዙ ዓይነታቸው የበዛ ርካሽ መዝናኛዎች አሉ። ስፖርት የሚታይባቸው ስታዲዮሞች በሰዎች ይሞላሉ፣ ሰዎች ቁማር ይጫወታሉ፣ አንዳንድ ጊዜ በተመልካቾችም ሆነ በተጨዋቾች መካከል ጠብ ይፈጠራል። በየጊዜው የሚወጡት ዘፈኖች ወራዳ ግጥሞችን የያዙ ሲሆኑ በየቲያትር ቤቶች መድረክ ላይ፣ በሲኒማ ቤቶች እንዲሁም በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ቲያትሮችና ድራማዎች በብልግና የተሞሉ ናቸው። በባሕር ዳርቻዎች ራቁታቸውን የሚዝናኑ ሰዎችን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች ወንዶችና ሴቶች በሳውና እና በፍል ውኃ መታጠቢያ ቦታዎች አንድ ላይ ገላቸውን ሲታጠቡ ማየት የተለመደ ነው። ሰይጣን በጥንት ክርስቲያኖች ላይ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም የአምላክን አገልጋዮች ለማሳሳት የዓለምን መዝናኛ እንደ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም ይሞክራል።

11. በመዝናኛው ዓለም ምን ወጥመዶች ተዘርግተዋል?

11 ውጥረት በበዛበት በዚህ ዓለም ውስጥ ለመዝናናት መፈለግና ከለመድነው የዘወትር እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ ዘወር ማለት የተለመደ ነው። ሆኖም የሮማ የገላ መታጠቢያ ቤቶች ለጥንት ክርስቲያኖች አደገኛ እንደነበሩ ሁሉ በዛሬውም ጊዜ ያሉት አንዳንዶቹ የመዝናኛ ዓይነቶችና የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ቦታዎች ሰይጣን ዘመናዊ ክርስቲያኖችን ሥነ ምግባር በጎደላቸው ድርጊቶች እንዲካፈሉ ወይም ከመጠን በላይ እንዲጠጡ ለማድረግ እንደ መሣሪያ የሚጠቀምባቸው ወጥመዶች መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና” በማለት ጽፎላቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:33, 34

12. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ያሉትን የይሖዋ አገልጋዮች ለማጥመድ የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

12 ሰይጣን የሔዋንን አስተሳሰብ ለማበላሸት መሠሪ በሆነ ዘዴ እንዴት እንደተጠቀመ በራሷ በሔዋን ላይ ከደረሰው ሁኔታ ማየት እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ዛሬ ሰይጣን የሚጠቀምበት አንደኛው ወጥመድ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዓለማዊ መንገዶችን በመከተል ከሌላው ሰው የተለዩ አለመሆናቸውን ማሳየትና በዚህም አንዳንዶችን ወደ ክርስትና እምነት መሳብ እንደሚችሉ ሆኖ እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከመጠን በላይ ወደ ዓለም ይቀርቡና ተቃራኒው ይፈጸማል። (ሐጌ 2:12-14) ሌላው የሰይጣን ዘዴ ደግሞ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወጣትም ሆኑ አዋቂ ክርስቲያኖች ሁለት ዓይነት ኑሮ እየኖሩ ‘ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ እንዲያሳዝኑ’ ማድረግ ነው። (ኤፌሶን 4:30) አንዳንዶች በኢንተርኔት አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቆች ሳይሆኑ በመቅረት በዚህ ወጥመድ ለመያዝ በቅተዋል።

13. ሰይጣን ለማሳሳቻ የሚጠቀምበት አንዱ መሠሪ ዘዴ ምንድን ነው? በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የትኛውን ምክር መከተሉ ተገቢ ነው?

13 ሌላው የሰይጣን ወጥመድ ደግሞ ጉዳት የሚያስከትሉ የማይመስሉ መናፍስታዊ ድርጊቶች ናቸው። ሆነ ብሎ በሰይጣናዊ አምልኮ ወይም በመናፍስታዊ ድርጊት የሚካፈል ክርስቲያን እንደማይኖር የታወቀ ነው። ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደዚህ ያሉትን ድርጊቶች በፊልም ወይም በቴሌቪዥን በመመልከት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወትና ሌላው ቀርቶ በዓመፅ ወይም በምሥጢራዊ ድርጊቶች የተሞሉ ለልጆች የሚዘጋጁ ጽሑፎችን በማንበብ ሳይታወቃቸው ትጥቃቸውን አላልተዋል። ከመናፍስታዊ አምልኮ ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ነገር በሩቁ ልንሸሸው ይገባል። አንድ ጥበብ የሞላበት ምሳሌ “እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ናቸው፤ ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 22:5) ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን በሕዝብ ዘንድ ከፍ ተደርጎ በሚታይ አንድ ነገር ውስጥ አንድ ዓይነት ወጥመድ ሊያስቀምጥ እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16

ኢየሱስ ዲያብሎስን ተቃውሟል

14. ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ያቀረበለትን የመጀመሪያ ፈተና የተቋቋመው እንዴት ነው?

14 ዲያብሎስን በመቃወምና ከእርሱ እንዲርቅ በማድረግ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ ከተጠመቀና ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ በሰይጣን ተፈትኖ ነበር። (ማቴዎስ 4:1-11) ሰይጣን፣ ኢየሱስ ለበርካታ ቀናት ከጾመ በኋላ የተሰማውን ረሃብ እንደ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም የመጀመሪያውን ፈተና አቀረበለት። ኢየሱስ የተሰማውን የረሃብ ስሜት ለማስታገስ የመጀመሪያውን ተዓምር እንዲሠራ ሰይጣን ጠየቀው። ኢየሱስ ዘዳግም 8:​3ን በመጥቀስ ኃይሉን በራስ ወዳድነት መንፈስ የራሱን ፍላጎት ለማርካት እንደማይጠቀምበትና ከሥጋዊ ምግብ ይልቅ መንፈሳዊ ምግብን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ተናገረ።

15. (ሀ) ሰይጣን ኢየሱስን ለመፈተን በምን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ተጠቅሟል? (ለ) ሰይጣን በዛሬ ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች ለመፈተን የሚጠቀምበት አንደኛው መሠሪ ዘዴ ምንድን ነው? ሆኖም እንዴት ልንቃወመው እንችላለን?

15 በዚህ ወቅት ሰይጣን ኢየሱስን ለመፈተን ከፆታ ብልግና ጋር የተያያዘ ፈተና እንዳላቀረበለት ልብ ማለት ያስፈልጋል። ረሃብ ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ ሰይጣን፣ ኢየሱስ የነበረውን ምግብ የመመገብ ከፍተኛ ፍላጎት እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሟል። ሰይጣን በዛሬ ጊዜ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ለማሳሳት የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ፈተናዎቹ ብዙና የተለያዩ ናቸው። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች ጽኑ አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎቹ መካከል አንዱ የፆታ ብልግና ነው። እኛም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ሰይጣንን መቃወምና ፈተናዎቹን መቋቋም እንችላለን። ኢየሱስ ተስማሚ የሆኑ ጥቅሶችን በመጥቀስ የሰይጣንን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረገ ሁሉ እኛም በምንፈተንበት ጊዜ እንደ ዘፍጥረት 39:​9 እና 1 ቆሮንቶስ 6:​18 ያሉትን ጥቅሶች ወደ አእምሯችን ማምጣት እንችላለን።

16. (ሀ) ሰይጣን ኢየሱስን ለሁለተኛ ጊዜ የፈተነው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን ይሖዋን እንድንፈታተነው ለማድረግ ምን ዘዴ ሊጠቀም ይችላል?

16 ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ማማ ላይ እንዲዘል በመጠየቅ አምላክ በመላእክቱ አማካኝነት እርሱን ለማዳን ያለውን ችሎታ ተፈታተነ። ኢየሱስ ዘዳግም 6:​16ን በመጥቀስ አባቱን እንደማይፈታተን ተናገረ። ሰይጣን ከቤተ መቅደስ ማማ ላይ እንድንዘል ጥያቄ አያቀርብልን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋን እንድንፈታተን የሚያደርግ ፈተና ሊያቀርብልን ይችላል። ተግሣጽ በማያሰጥ ደረጃ በአለባበሳችንና በአበጣጠራችን የዓለምን ፋሽን እስከ ምን ድረስ መከተል እንደምንችል ለማየት እንፈተናለንን? አጠያያቂ በሆኑ መዝናኛዎች ለመካፈል እንፈተናለንን? እንደዚያ ከሆነ ይሖዋን እየተፈታተንነው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለውን ዝንባሌ የምናስተናግድ ከሆነ ሰይጣን እኛን ትቶ ከመሄድ ይልቅ በውስጣችን ሊያድርና ከእርሱ ጋር እንድናብር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይችላል።

17. (ሀ) ዲያብሎስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ የፈተነው እንዴት ነው? (ለ) ያዕቆብ 4:​7 ለእኛ በትክክል እንደሚሠራ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 ሰይጣን አንድ ጊዜ ቢሰግድለት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው በነገረው ጊዜ ኢየሱስ አባቱን ብቻ የማምለክ ጽኑ አቋም እንዳለው ከቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሶ መልስ በመስጠት ሰይጣንን በድጋሚ ተቃውሞታል። (ዘዳግም 5:9, 10፤ 6:13፤ 10:20) ሰይጣን የዓለምን መንግሥታት ለእኛ ለመስጠት አይጋብዘን ይሆናል፤ ሆኖም ቁሳዊ ሃብት እንዲያማልለን በማድረግ በፍቅረ ነዋይ ሊፈትነን ይችላል። ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ በመስጠት የኢየሱስ ዓይነት መልስ መስጠት እንችላለን? እንደዚያ ካደረግን ሰይጣን ከኢየሱስ እንደራቀ ሁሉ ከእኛም ይሸሻል። የማቴዎስ ዘገባ “ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው” በማለት ይነግረናል። (ማቴዎስ 4:11) ተስማሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የምናስታውስና በሥራ ላይ በማዋል በጽናት የምንቃወመው ከሆነ ሰይጣን ከእኛም ይርቃል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:7) አንድ ክርስቲያን ፈረንሳይ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ በማለት ጻፈ:- “ሰይጣን በእርግጥም መሠሪ ነው። ምንም ያህል ጥረት ባደርግ ስሜቴንና ምኞቴን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖብኛል። ሆኖም ድፍረትና ትዕግሥት በማሳየት ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ እርዳታ በአቋሜ ለመጽናትና እውነትን አጥብቄ ለመያዝ ችያለሁ።”

ዲያብሎስን ለመቃወም ሙሉ በሙሉ የታጠቁ መሆን

18. ሰይጣንን ለመቃወም የትኞቹ መንፈሳዊ የጦር ትጥቆች ይረዱናል?

18 ይሖዋ ‘የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንችል ዘንድ’ የተሟላ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 6:11-18) ለእውነት ያለን ፍቅር በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ለመካፈል ወገባችንን ታጥቀን እንድንነሳ ወይም ዝግጁ እንድንሆን ያደርገናል። ይሖዋ ለጽድቅ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ጠብቀን ለመኖር ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ልባችንን ለመጠበቅ እንደ ጥሩር ሆኖ ያገለግለናል። እግሮቻችን በምሥራቹ ተጫምተው ከቆሙ አዘውትረው ወደ ስብከቱ ሥራ ይወስዱናል፤ ይህም መንፈሳዊ ጥንካሬና ጥበቃ ይሆንልናል። ከትልቅ ጋሻ ጋር የተመሳሰለው እምነታችን “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች” ማለትም የሰይጣንን መሠሪ ጥቃቶችና ፈተናዎች እንድንመክት ይረዳናል። ይሖዋ ቃል የገባቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያለን የተረጋገጠ ተስፋ እንደ ራስ ቁር ሆኖ የማሰብ ችሎታችንን ይከላከልልናል እንዲሁም የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:7) በሰይፍ የተመሰለውን የአምላክ ቃል የመጠቀም ችሎታችንን የምናዳብር ከሆነ በመንፈሳዊ ባርነት ውስጥ ገብተው በሰይጣን ቁጥጥር ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ነፃ ለማውጣት ልንጠቀምበት እንችላለን። ኢየሱስ ፈተና በገጠመው ጊዜ እንዳደረገው እኛም ራሳችንን ለመጠበቅ ልንጠቀምበት እንችላለን።

19. ‘ዲያብሎስን ከመቃወም’ በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 “የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ” ዘወትር የምንለብስና በጸሎት የምንጸና ከሆነ ሰይጣን ጥቃት በሚሰነዝርብን ጊዜ ይሖዋ እንደሚጠብቀን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 17:15፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) ሆኖም ያዕቆብ ‘ሰይጣንን መቃወም’ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተናግሯል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለእኛ ለሚያስብልን ‘አምላክ መገዛትም’ ይገባናል። (ያዕቆብ 4:7, 8) በሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንዴት ማድረግ እንደምንችል እንመረምራለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የጥንት ክርስቲያኖች ከየትኞቹ የሰይጣን ወጥመዶች መራቅ ነበረባቸው?

• ሰይጣን በዛሬ ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች ለማጥመድ በምን ስውር ዘዴ ይጠቀማል?

• ኢየሱስ የዲያብሎስን ፈተና የተቃወመው እንዴት ነው?

• ዲያብሎስን ለመቃወም የሚረዳን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ የትኛው ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሰይጣንን በጽኑ ተቃውሟል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዓመፅና የሥነ ምግባር ብልግና ከሚፈጸምባቸው መዝናኛዎች ርቀዋል

[ምንጭ]

The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck