በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሁሉም ሰው ክፍት የሆኑ የመንግሥት አዳራሾች

ለሁሉም ሰው ክፍት የሆኑ የመንግሥት አዳራሾች

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

ለሁሉም ሰው ክፍት የሆኑ የመንግሥት አዳራሾች

ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ሲያሰለጥናቸው “በሰገነት ላይ ስበኩ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:​27) አዎን፣ ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን ከሕዝብ ዕይታ ሳይሰወሩ በግልጽ ማከናወን ነበረባቸው። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንን ምክር በመከተል አገልግሎታቸውን በግልጽ ያከናውናሉ። እንዲህ ያለው ግልጽነት ምሥክሮቹ ተቃውሞን እንዲያሸንፉና ተገቢውን እውቅና እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ሁሉም ሰው መገኘት ቢችልም በእነርሱ ላይ የሚነገረው የጥላቻ ወሬ አንዳንዶች ወደ መንግሥት አዳራሽ እንዳይመጡ አድርጓቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በፊንላንድ ደርሶ ነበር። ሌሎች ደግሞ አዲስ ወደሆነ አካባቢ መሄድ ያስፈራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ ወይም ሲታደስ አዳራሹ ለጉብኝት ክፍት የሚሆንበት ፕሮግራም ይዘጋጃል። ከዚያም ጎረቤቶችንና ዘመዶችን ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመጋበዝና ከይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ ልዩ ጥረት ይደረጋል።

በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የተገነባ የመንግሥት አዳራሻቸው ለጉብኝት ክፍት የሚሆንበትን ፕሮግራም አዘጋጅተው በነበረበት ዕለት የመጽሔት ዘመቻ ለማካሄድ ወሰኑ። ሁለት ወንድሞች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ የሚያስደስታቸው አንድ አዛውንት አገኙ። ስለ ጉብኝት ፕሮግራሙ ነገሯቸውና ወደ መንግሥት አዳራሹ ሊወስዷቸው እንደሚችሉ ገለጹላቸው። አዛውንቱም ለመሄድ ተስማሙ። ቤት ሆነው ውይይቱን ያዳምጡ የነበሩት የአዛውንቱ ባለቤት “ጥለኸኝ እንዳትሄድ!” በማለት ተናገሩ።

አዛውንቱ ልክ ወደ መንግሥት አዳራሹ እንደገቡ ዞር ዞር አሉና “ግድግዳው ጥቁር እንደሚሆን ጠብቄ ነበር። ሆኖም በጣም የሚያምርና ፈካ ያለ ቀለም ያለው ነው። መንግሥት አዳራሻችሁን ጥቁር ቀለም እንደምትቀቡት ተነግሮኝ ነበር!” በማለት ተናገሩ። ባልና ሚስቱ በመንግሥት አዳራሹ ጥቂት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ለእይታ ቀርበው ከነበሩት መጽሔቶች መካከል አንዳንዶቹን ወሰዱ።

አንድ ጉባኤ የመንግሥት አዳራሹ ከመወሰኑ በፊት ለጉብኝት ክፍት የሚሆንበት ፕሮግራም እንደሚኖር የሚገልጽ ማስታወቂያ በአንድ የአገሪቱ ጋዜጣ ላይ ለማውጣት ፈለገ። የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ማመልከቻው እንደደረሳት ጉዳዩን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ሐሳብ አቀረበች። ወንድሞችም በሐሳቧ ተስማሙ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ጋዜጣው በግማሽ ገጹ ላይ የጉብኝቱን ፕሮግራምና የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚገልጽ ጽሑፍ ይዞ ወጣ።

ጋዜጣው አንባቢ እጅ ከደረሰ በኋላ አንዲት ሴት ጎረቤታቸው ለሆኑ አንዲት በእድሜ የገፉ እህት “ዛሬ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚገልጽ ጥሩ ሐሳብ በጋዜጣ ላይ ወጥቷል!” በማለት ነገሯቸው። እህት ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ምሥክርነት የሰጡ ሲሆን በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች በሃያኛው መቶ ዘመን የተባለውን ብሮሹር ማበርከት ችለዋል።

ከጉብኝት ፕሮግራሞችና ከአዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ውሰና ጋር በተያያዘ የተደረገው እንዲህ ያለው ዝግጅት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚናፈሰውን መሠረተ ቢስ ወሬ ለማክሸፍ ከማስቻሉም በላይ አስፋፊዎች ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ስብሰባዎች እንዲጋብዙ አበረታቷቸዋል። አዎን፣ ፊንላንድን ጨምሮ በብዙ አገሮች የሚገኙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ለሁሉም ሰው ክፍት እንደሆነ ተገንዝበዋል።