በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን”

“በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን”

“በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን”

“ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ።”​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​17

1, 2. (ሀ) የአንድ ጋዜጣ ዘጋቢ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን አስተያየት ጽፏል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ለመከተል ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

 ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በአሜሪካ ቴክሳስ አማሪሎ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ጋዜጣ ዘጋቢ በዚያ አካባቢ ያሉ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ከተመለከተ በኋላ አንድ ዘገባ አጠናቀረ። ይበልጥ ትኩረቱን ስለሳበው አንድ ቡድን እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች በአማሪሎ ከተማ በሚገኘው አዳራሽ በሚያደርጉት ዓመታዊ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሦስት ጊዜ ተገኝቻለሁ። ከእነርሱ ጋር በተሰበሰብኩባቸው ጊዜያት ሲጋራ የሚያጨስ፣ ቢራ የሚጠጣ ወይም አስጸያፊ ቃል የሚናገር ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። እንደነርሱ ያለ ንጹሕ፣ የታረመ ጠባይና ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸው ጨዋ ሰዎች አይቼ አላውቅም።” ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያሉ አስተያየቶች በብዛት በጽሑፍ ይወጣሉ። እምነታቸውን የማይጋሩ ሰዎች ይህን ያህል ሊያደንቋቸው የቻሉት ለምንድን ነው?

2 ሰዎች ብዙውን ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች የሚያደንቋቸው በጥሩ ሥነ ምግባራቸው ነው። በጥቅሉ ሲታይ የሥነ ምግባር አቋም እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን መጠበቅ ግዴታቸው ማለትም የአምልኳቸው ክፍል እንደሆነ ይሰማቸዋል። ድርጊታቸው የይሖዋና የክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ስም እንደሚነካ እንዲሁም መልካም ባሕርያቸው የሚሰብኩት እውነት በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሊያደርግ እንደሚችል ይገነዘባሉ። (ዮሐንስ 15:​8፤ ቲቶ 2:​7, 8) እንግዲያው መልካም ሥነ ምግባር በማሳየት ይሖዋንና ምሥክሮቹን ማስመስገን የምንችለው እንዴት እንደሆነና እኛም ከዚህ ምን ጥቅም እንደምናገኝ እንመልከት።

ክርስቲያን ቤተሰብ

3. ክርስቲያን ቤተሰቦች ራሳቸውን ከምን መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል?

3 በቤተሰብ ውስጥ የሥነ ምግባር አቋማችን ምን እንደሚመስል እስቲ እንመልከት። በጌርሃርት ቤዚር እና ኤርቪን ኬ ሾይክ የተዘጋጀው ዲ ኖየን ኢንክሲቶረን:- ሪሊጊኦንስፍራይሃይል ኡንድ ግላውቤንሽናይድ የተባለው መጽሐፍ (ጀርመንኛ) “[የይሖዋ ምሥክሮች] ቤተሰብ የተለየ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ተቋም ነው የሚል እምነት አላቸው” በማለት ተናግሯል። ዛሬ ቤተሰብ ጥበቃ እንዲደረግለት የሚያስገድዱ በርካታ አደጋዎች መኖራቸው የዚህን አባባል እውነተኝነት ያሳያል። ብዙ ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” ከመሆናቸውም በላይ ትልልቆችም “ፍቅር የሌላቸው” ወይም “ራሳቸውን የማይገዙ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​2, 3) ቤተሰብ በትዳር ጓደኛ ላይ ዓመፅ የሚፈጸምበት ቦታ እየሆነ መጥቷል። ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ግፍ ይፈጽማሉ ወይም ልጆቻቸውን ችላ ይላሉ። እንዲሁም ልጆች ያምፃሉ፣ አደገኛ ዕፅ ይወስዳሉ፣ የጾታ ብልግና ይፈጽማሉ ወይም ቤታቸውን ጥለው ይኮበልላሉ። ይህ ሁሉ ጎጂ የሆነው ‘የዓለም መንፈስ’ ውጤት ነው። (ኤፌሶን 2:​1, 2) ቤተሰባችን የዚህ መንፈስ ሰለባ እንዳይሆን ጥበቃ ልናደርግለት ይገባል። እንዴት? ይሖዋ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሰጠውን ምክርና መመሪያ በሥራ ላይ በማዋል ነው።

4. በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ አንዱ ለሌላው ምን የማድረግ ኃላፊነት አለበት?

4 ክርስቲያን ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:​3-5፤ ኤፌሶን 5:​21-23፤ 1 ጴጥሮስ 3:​7) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ምሳሌ 22:​6፤ 2 ቆሮንቶስ 12:​14፤ ኤፌሶን 6:​4) እንዲሁም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ልጆች አድገው ራሳቸውን ሲችሉ ብድራት መመለስ እንደሚኖርባቸው ያውቃሉ። (ምሳሌ 1:​8, 9፤ 23:​22፤ ኤፌሶን 6:​1፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​3, 4, 8) በቤተሰብ ውስጥ ያሉንን ኃላፊነቶች መወጣት ጥረት፣ ቁርጠኝነት እንዲሁም የፍቅርና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት ባደረገ መጠን በዚያው ልክ ለቤተሰቡና ለጉባኤው በረከት ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ እንዲከበር ያደርጋል።​—⁠ዘፍጥረት 1:​27, 28፤ ኤፌሶን 3:​15

ክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር

5. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ምን በረከቶች ያስገኝልናል?

5 በተጨማሪም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን አልፎ ተርፎም ‘ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር’ ጋር በተያያዘ የምንወጣው ኃላፊነት አለብን። (1 ጴጥሮስ 5:​9) ከጉባኤው ጋር ያለን ግንኙነት ለመንፈሳዊ ጤንነታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በአንድነት በምንሰበሰብበት ጊዜ ከእነርሱ ማበረታቻ የምናገኝ ከመሆኑም በላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርበውን ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ እንመገባለን። (ማቴዎስ 24:​45-47) ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ቅዱሳን ጽሑፎች በያዟቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ምክር እንዲሰጡን ቀርበን መጠየቅ እንችላለን። (ምሳሌ 17:​17፤ መክብብ 4:​9፤ ያዕቆብ 5:​13-18) እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ወንድሞቻችን ይደርሱልናል። በእርግጥም የአምላክ ድርጅት አባል መሆን እንዴት ያለ በረከት ነው!

6. ጳውሎስ ለሌሎች ክርስቲያኖች ያለንን ኃላፊነት የገለጸው እንዴት ነው?

6 ይሁን እንጂ በጉባኤ የምንገኘው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም ጭምር ነው። እንዲያውም ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣ NW ] ነው” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 20:35) ሐዋርያው ጳውሎስ “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” ብሎ በጻፈ ጊዜ በፈቃደኝነት መንፈስ ለሌሎች መስጠት እንደሚኖርብን ጎላ አድርጎ ገልጿል።​—⁠ዕብራውያን 10:23-25

7, 8. በጉባኤያችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ለሚገኙ ክርስቲያኖች በመስጠት እንደምንደሰት እንዴት ማሳየት እንችላለን?

7 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ወይም በፕሮግራሙ ላይ በሌሎች መንገዶች ተሳትፎ በማድረግ ‘ስለ ተስፋችን ምሥክርነት እንሰጣለን።’ እንዲህ ማድረጋችን ወንድሞቻችንን እንደሚያበረታታ ምንም ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ከስብሰባ በፊትና በኋላ ከእነርሱ ጋር ሐሳብ በመለዋወጥ ልናበረታታቸው እንችላለን። ይህ የደከሙትን ለማበረታታት፣ የተጨነቁትንና የታመሙትን ለማጽናናት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርልናል። (1 ተሰሎንቄ 5:​14) ልበ ቅን ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ልግስና ያሳያሉ። በመሆኑም ብዙ ሰዎች በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገኙ በመካከላችን በሚታየው ፍቅር በእጅጉ ይማረካሉ።​—⁠መዝሙር 37:​21፤ ዮሐንስ 15:​12፤ 1 ቆሮንቶስ 14:​25

8 ፍቅር የምናሳየው በጉባኤያችን ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። ፍቅራችን ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ያቅፋል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ለማኅበሩ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የሚውል መዋጮ ሣጥን የሚቀመጠው በዚህ ምክንያት ነው። የራሳችን የሆነ የመንግሥት አዳራሽ ቢኖረንም በሌሎች አገሮች ያሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነት ባልደረቦቻችን ግን የሚሰበሰቡበት ተስማሚ አዳራሽ እንደሌላቸው እናውቃለን። ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ መዋጮ ማድረጋችን እነዚህን ወንድሞች በግለሰብ ደረጃ ባናውቃቸውም እንኳን ለእነርሱ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው።

9. የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ የሚዋደዱበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

9 የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ የሚዋደዱት ለምንድን ነው? ኢየሱስ እርስ በርስ እንዲዋደዱ ስላዘዛቸው ነው። (ዮሐንስ 15:​17) እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር የአምላክ መንፈስ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ በእነርሱ ላይ እንደሚሠራ የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው። ፍቅር ‘ከመንፈስ ፍሬዎች’ መካከል አንዱ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) የይሖዋ ምሥክሮች ‘የብዙ ሰዎች ፍቅር በቀዘቀዘበት’ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያጠኑ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለሚገኙና ዘወትር ወደ አምላክ ስለሚጸልዩ ፍቅር የስብዕናቸው ክፍል ይሆናል።​—⁠ማቴዎስ 24:​12

በዙሪያችን ካለው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት

10. በዙሪያችን ያለውን ዓለም በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለብን?

10 ጳውሎስ ‘የተስፋችን ምሥክርነት’ በማለት መናገሩ ሌላም ኃላፊነት እንዳለብን ያስታውሰናል። ስለ ተስፋችን የምንሰጠው ይህ ምሥክርነት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ላልሆኑ ሰዎች ምሥራቹን መስበክን የሚጨምር ነው። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20፤ ሮሜ 10:​9, 10, 13-15) ይህ የስብከት ሥራ አንድ ተጨማሪ የመስጠት ገጽታ ነው። በስብከቱ ሥራ ላይ መካፈል ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ዝግጅት ማድረግን፣ ሥልጠና ማግኘትንና ገንዘባችንን መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ሆኖም ጳውሎስ “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ” ሲልም ጽፏል። (ሮሜ 1:14, 15) እኛም ይህን “ዕዳ” በመክፈል ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል እንጂ በዚህ ረገድ ንፉግ መሆን አይኖርብንም።

11. ከዓለም ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት መመሪያ የሚሆኑን ሁለት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? ሆኖም ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል?

11 የእምነት ባልንጀሮቻችን ላልሆኑ ሰዎች ምሥራቹን ከመስበክ ሌላ ኃላፊነት ይኖርብን ይሆን? እንዴታ። እርግጥ ነው፣ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” እንገነዘባለን። (1 ዮሐንስ 5:​19) ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” በማለት እንደተናገረም እናውቃለን። ያም ሆኖ የምንኖረውም ሆነ መተዳደሪያ የምናገኘው እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን የምናገኘው ከዚሁ ዓለም ነው። (ዮሐንስ 17:11, 15, 16) ስለሆነም በዚህ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ልናሟላቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉብን። እነዚህ ግዴታዎቻችን ምንድን ናቸው? ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ በትንሿ እስያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎላቸው የነበረ ሲሆን ደብዳቤው ከዓለም ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል።

12. ክርስቲያኖች “እንግዶችና መጻተኞች” የሆኑት በምን መንገድ ነው? በመሆኑም ከምን መታቀብ ይኖርባቸዋል?

12 በመጀመሪያ ደረጃ ጴጥሮስ “ወዳጆች ሆይ፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ” በማለት የተናገረውን እንመልከት። (1 ጴጥሮስ 2:​11) እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሁኔታ “እንግዶችና መጻተኞች” በመሆናቸው በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛው ግባቸው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው። ይህም በመንፈስ የተቀቡት በሰማይ፣ “ሌሎች በጎች” ደግሞ ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። (ዮሐንስ 10:​16፤ ፊልጵስዩስ 3:​20, 21፤ ዕብራውያን 11:​13፤ ራእይ 7:​9, 14-17) ታዲያ ጴጥሮስ ሥጋዊ ምኞት በማለት የጠቀሳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሃብታም የመሆን፣ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ፣ የጾታ ብልግና የመፈጸም እንዲሁም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ቅንዓትና” “መጐምጀት” ተብለው የተገለጹት ምኞቶች ይገኙበታል።​—⁠ቆላስይስ 3:​5፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​4, 9፤ 1 ዮሐንስ 2:​15, 16

13. ሥጋዊ ምኞቶች ‘ከነፍሳችን ጋር ውጊያ የሚገጥሙት’ እንዴት ነው?

13 እነዚህ ምኞቶች ‘ከነፍሳችን ጋር ውጊያ’ እንደሚገጥሙ ተገልጿል። ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ቀስ በቀስ በመሸርሸር ክርስቲያናዊው ተስፋችን (‘ነፍሳችን’ ወይም ሕይወታችን) አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል የጾታ ብልግና የመፈጸም ፍላጎት በውስጣችን ካሳደርን ሰውነታችንን “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት” አድርገን እንዴት ማቅረብ እንችላለን? በፍቅረ ነዋይ ወጥመድ ከተያዝን እንዴት ‘መንግሥቱን ማስቀደም’ እንችላለን? (ሮሜ 12:​1, 2፤ ማቴዎስ 6:​33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​17-19) ከዚህ ይልቅ የሙሴን ምሳሌ በመኮረጅ ዓለም የሚያቀርብልንን ማባበያዎች ችላ ብለን ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያውን መስጠታችን የተሻለ አኗኗር ነው። (ማቴዎስ 6:​19, 20፤ ዕብራውያን 11:​24-26) ይህ ከዓለም ጋር ያለን ግንኙነት ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል አስፈላጊ እርምጃ ነው።

“ኑሮአችሁ መልካም ይሁን”

14. ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ጥሩ ሥነ ምግባር ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

14 ጴጥሮስ “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” በማለት ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ መመሪያ ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 2:​12) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሌሎች ምሳሌ ሆነን ለመገኘት ጥረት እናደርጋለን። በትምህርት ቤት ትምህርታችንን በትጋት እንከታተላለን። ተቀጥረን በምንሠራበት ቦታ ቀጣሪያችንን ማስደሰት ቀላል ሆኖ ባናገኘውም እንኳን ታታሪዎችና ሐቀኞች ነን። በእምነት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ አማኝ የሆነው ወገን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓትን ለመከተል ልዩ ጥረት ያደርጋል። ይህ ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም በምሳሌነት የሚጠቀስ ጥሩ ሥነ ምግባር ማሳየታችን ይሖዋን እንደሚያስደስትና የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ የትዳር ጓደኞች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት እንደሚያስችል እናውቃለን።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​18-20፤ 3:​1

15. የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ደረጃ የብዙ ሰዎችን ትኩረት እንደሳበ እንዴት እናውቃለን?

15 ባለፉት ዓመታት በአንዳንድ ጽሑፎች ላይ የወጡ በጎ አስተያየቶች አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በአርአያነት የሚጠቀስ ግሩም ሥነ ምግባር በማሳየት ረገድ እንደተሳካላቸው ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል ኢል ቴምፖ የተባለ አንድ የኢጣሊያ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኛ ሠራተኞች መሆናቸውን የሥራ ባልደረቦቻቸው ይመሠክራሉ። እምነታቸውን በጥብቅ የሚከተሉ ከመሆናቸው የተነሳ ከዚያ ሌላ ምንም የሚታያቸው ነገር ያለ አይመስልም። ይሁን እንጂ ለሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸው አክብሮት ሊቸራቸው ይገባል።” በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ የሚታተመው ሄራልድ ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ትጉህ ሠራተኞች፣ ቁም ነገረኞች፣ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቆችና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ዜጎች መሆናቸውን አስመስክረዋል።” ሰርጌይ ኢቫንዬንኮ የተባሉ አንድ ሩሲያዊ ምሁር “የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪ ሕዝቦች እንደሆኑ በተለይ ደግሞ ግብር በመክፈል ረገድ ሐቀኞች መሆናቸውን ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ዚምባብዌ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ያደረጉበት የአንድ አዳራሽ ሥራ አስኪያጅ የሆኑ አንዲት ሴት እንዲህ ብለዋል:- “አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የወዳደቁ ወረቀቶችን ሲለቃቅሙና መጸዳጃ ቤቱን ሲያጸዱ ተመልክቻለሁ። አዳራሹ እንደዚያ ቀን ጸድቶ አይቼ አላውቅም። ልጆቻችሁ ሥርዓታማ ናቸው። የዓለም ሕዝብ ሁሉ የይሖዋ ምሥክር ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር።”

ክርስቲያናዊ ተገዥነት

16. ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? ለምንስ?

16 ጴጥሮስ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት እንደሚከተለው ሲል ጨምሮ ተና​ግሯል:- “ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፣ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፣ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። በጎ እያደረጋችሁ፣ የማያውቁትን ሞኞች [“የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር፣” አ.መ.ት ] ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።” (1 ጴጥሮስ 2:13-15) ከመንግሥት ለምናገኛቸው ጥቅሞች በእጅጉ አመስጋኞች ነን። ጴጥሮስ በሰጠው ምክር ስለምንመራ መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች እንታዘዛለን እንዲሁም የሚጣልብንን ግብር እንከፍላለን። መንግሥታት ሕግ የሚጥሱ ሰዎችን የመቅጣት መብት ከአምላክ እንደተሰጣቸው የምንቀበል ቢሆንም ለመንግሥት ባለሥልጣናት የምንገዛበት ተቀዳሚ ምክንያት ‘ለጌታ ብለን’ ነው። ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው። ከዚህም በላይ ሕግ በመጣሳችን ምክንያት በሚደርስብን ቅጣት የይሖዋን ስም ማስነቀፍ አንፈልግም።​—⁠ሮሜ 13:​1, 4-7፤ ቲቶ 3:​1፤ 1 ጴጥሮስ 3:​17

17. ‘አላዋቂዎች’ በሚቃወሙን ጊዜ ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 የሚያሳዝነው ግን በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንድ ‘አላዋቂዎች’ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማቀነባበርና በሌሎች መንገዶች ስደት ይቆሰቁሱብናል ወይም ይቃወሙናል። ቢሆንም ይሖዋ በፈቀደው ቀን ይህ ውሸታቸው መጋለጡና ‘ከንቱ ንግግራቸውን’ መተዋቸው አይቀርም። ክርስቲያናዊ ባሕርያችን ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን ይመሰክራል። ሐቀኛ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብዙውን ጊዜ ስለ መልካም ሥራችን የሚያመሰግኑን ለዚህ ነው።​—⁠ሮሜ 13:​3፤ ቲቶ 2:​7, 8

የአምላክ ባሪያዎች

18. ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ነጻነታችንን ያለአግባብ ከመጠቀም የምንርቅባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

18 ጴጥሮስ “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጴጥሮስ 2:​16፤ ገላትያ 5:​13) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቃችን ከሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነጻ አውጥቶናል። (ዮሐንስ 8:​32) ከዚህም በላይ ነጻ ምርጫ ያለን ሰዎች በመሆናችን የመምረጥ መብት አለን። ሆኖም ነጻነታችንን ያለ አግባብ መጠቀም አንፈልግም። የጓደኛ፣ የልብስ፣ የአጋጌጥ፣ የመዝናኛና ሌላው ቀርቶ የምግብና የመጠጥ ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለማስደሰት የቆሙ ሳይሆን የአምላክ ባሪያዎች መሆናቸውን ፈጽሞ አንዘነጋም። ለሥጋዊ ምኞቶቻችን ወይም ይህ ዓለም በየጊዜው ለሚለዋውጠው ፋሽን ባሪያዎች ከመሆን ይልቅ ይሖዋን ማገልገል እንመርጣለን።​—⁠ገላትያ 5:​24፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​22፤ ቲቶ 2:​11, 12

19-21. (ሀ) ለበላይ ባለሥልጣናት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) አንዳንዶች ‘ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር’ የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ሐ) ከሁሉም በላይ ክብደት የምንሰጠው ኃላፊነት የትኛው ነው?

19 ጴጥሮስ በመቀጠል “ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:​17) ይሖዋ አምላክ ሰዎች የተለያዩ የሥልጣን ቦታዎችን እንዲይዙ ስለፈቀደላቸው ለእነዚህ ሰዎች ተገቢውን አክብሮት እናሳያለን። አልፎ ተርፎም አገልግሎታችንን ለአምላክ ያደርን ሆነን በሰላም ማከናወን እንድንችል ስለ እነርሱ እንጸልያለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:​1-4) ከዚሁ ጎን ‘ለመላው የወንድማማች ማኅበር’ ፍቅር እናሳያለን። ምንጊዜም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም ነገር እናደርጋለን።

20 ለምሳሌ ያህል አንዲት አፍሪካዊት አገር በጎሣ ግጭት ታምሳ በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ግሩም የሆነ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንደሚከተሉ በግልጽ ታይቷል። በስዊዘርላንድ የሚታተመው ሬፎርሚርቴ ፕሬሴ የተባለ ጋዜጣ “በ1995 . . . ከይሖዋ ምሥክሮች በስተቀር ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት [በግጭቱ ውስጥ] እጃቸው እንዳለበት አፍሪካን ራይትስ የተባለው ድርጅት ማረጋገጥ ችሏል” የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር። የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ በመላው ዓለም ሲሰማ በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ግጭቱ በተቀሰቀሰበት አገር ለሚኖሩ ወንድሞቻቸውና ሌሎች ሰዎች የምግብና የመድኃኒት እርዳታ በአፋጣኝ ልከዋል። (ገላትያ 6:​10) “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” የሚለውን የምሳሌ 3:27 ምክር በተግባር አውለዋል።

21 ይሁን እንጂ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከማክበርና መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን ከማፍቀር የበለጠ ሌላ ከባድ ኃላፊነት አለብን። ይህ ምን ይሆን? ጴጥሮስ “እግዚአብሔርን ፍሩ” በማለት ተናግሯል። ለይሖዋ ያለብን ግዴታ ለማንኛውም ሰው ካለብን ግዴታ የላቀ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለአምላክና ለመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉብንን ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ያገኛሉ።

ታስታውሳለህን?

• ክርስቲያኖች በቤተሰብ ክልል ውስጥ ምን ግዴታዎች አሉባቸው?

• በጉባኤ ውስጥ በመስጠት እንደምንደሰት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በዙሪያችን ለሚገኘው ዓለም ያሉብን ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?

• ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን በመጠበቅ የምናገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ቤተሰብ የደስታ ምንጭ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው የሚዋደዱት ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግል ለማናውቃቸው ወንድሞቻችንም ፍቅር ልናሳያቸው እንችል ይሆን?