በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍጻሜው ዘመን ያሉ ገለልተኛ ክርስቲያኖች

በፍጻሜው ዘመን ያሉ ገለልተኛ ክርስቲያኖች

በፍጻሜው ዘመን ያሉ ገለልተኛ ክርስቲያኖች

“እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።”​—⁠ዮሐንስ 17:​16

1, 2. ኢየሱስ ተከታዮቹ ከዓለም ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ምን በማለት ተናግሯል? እርሱ የተናገራቸው ቃላት የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳሉ?

 ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ባሳለፈው ሕይወት የመጨረሻው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ እየሰሙ ረዥም ጸሎት አቅርቦ ነበር። ባቀረበው ጸሎት ላይ የሁሉንም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት የሚነካ አንድ አስፈላጊ ነገር ጠቅሷል። ተከታዮቹን አስመልክቶ እንዲህ አለ:- “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።”​—⁠ዮሐንስ 17:14-16

2 እዚህ ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከዓለም እንዳይደሉ ሁለት ጊዜ ጠቅሷል። ከዚህም በላይ ከዓለም የተለዩ መሆናቸው ሌላ ችግር ያስከትልባቸዋል ይኸውም ዓለም እንዲጠላቸው ያደርጋል። ቢሆንም ክርስቲያኖች ይሖዋ ስለሚጠብቃቸው መጠላታቸው ሊያስጨንቃቸው አይገባም። (ምሳሌ 18:​10፤ ማቴዎስ 24:​9, 13) ከእነዚህ የኢየሱስ ቃላት በመነሳት እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ ይሆናል:- ‘ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል ያይደሉት ለምንድን ነው? የዓለም ክፍል አለመሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ዓለም ክርስቲያኖችን የሚጠላቸው ከሆነ እነርሱ ለዓለም የሚኖራቸው አመለካከት ምንድን ነው? በተለይ ደግሞ ለዓለም መንግሥታት የሚኖራቸው አመለካከት ምንድን ነው?’ እነዚህ ጥያቄዎች ሁላችንንም የሚመለከቱ በመሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶች ማግኘታችን አስፈላጊ ነው።

‘ከአምላክ ነን’

3. (ሀ) ከዓለም የተለየን የሚያደርገን ምንድን ነው? (ለ) ዓለም “በክፉው እንደ ተያዘ” የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?

3 ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው የጠበቀ ዝምድና የዓለም ክፍል የማንሆንበት አንደኛው ምክንያት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) ዮሐንስ ስለ ዓለም የተናገረው ነገር እውነት መሆኑ ግልጽ ነው። ዛሬ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው ጦርነት፣ ወንጀል፣ የጭካኔ ድርጊት፣ ጭቆና፣ እምነት አጉዳይነትና የሥነ ምግባር ብልግና ዓለምን የሚቆጣጠረው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን እንደሆነ ያሳያል። (ዮሐንስ 12:​31፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ ኤፌሶን 6:​12) አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ ብልሹ በሆኑት በእነዚህ ድርጊቶች አይካፈልም ወይም ድርጊቶቹን አይደግፍም። ይህም ከዓለም የተለየ ያደርገዋል።​—⁠ሮሜ 12:​2፤ 13:​12-14፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9-11፤ 1 ዮሐንስ 3:​10-12

4. የይሖዋ መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

4 ክርስቲያኖች ከዓለም በተለየ ‘ከአምላክ መሆናቸውን’ ዮሐንስ ተናግሯል። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሁሉ የእርሱ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ [“ለይሖዋ፣” NW ] እንኖራለንና፣ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።” (ሮሜ 14:8፤ መዝሙር 116:15) የይሖዋ በመሆናችን ምክንያት እርሱን ብቻ እናመልካለን። (ዘጸአት 20:4-6) ስለሆነም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሕይወቱን ለዓለማዊ ጉዳይ አይወስንም። ለብሔራዊ አርማ አክብሮት የሚያሳይ ቢሆንም በድርጊትም ሆነ በሐሳብ አያመልከውም። የስፖርት ኮከቦችንም ሆነ ሌሎች ዘመን አመጣሽ ጣዖታትን ፈጽሞ አያመልክም። እርግጥ ነው ሌሎች ሰዎች የፈለጉትን የማምለክ መብት እንዳላቸው ያውቃል። እርሱ ግን ፈጣሪን ብቻ ያመልካል። (ማቴዎስ 4:​10፤ ራእይ 19:​10) ከዓለም የተለየ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ይህ ነው።

“መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም”

5, 6. ለአምላክ መንግሥት መገዛታችን ከዓለም የተለየን የሚያደርገን እንዴት ነው?

5 ክርስቲያኖች የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮችና የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆናቸው የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ነው። ኢየሱስ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበበት ወቅት “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) የይሖዋን ስም የሚያስቀድሰው፣ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጠውና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም እንዲሆን የሚያደርገው ይህ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:​9, 10) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበኩም ባሻገር ተከታዮቹ እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ መንግሥቱን እንደሚሰብኩ ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:​23፤ 24:​14) በራእይ 11:​15 ላይ የሚገኙት “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚሉት ትንቢታዊ ቃላት በ1914 ፍጻሜአቸውን አግኝተዋል። ይህ ሰማያዊ መንግሥት በቅርቡ መላውን የሰው ዘር ያለ አንዳች ተቀናቃኝ ይገዛል። (ዳንኤል 2:​44) በአንድ ወሳኝ ወቅት ላይ የዓለም ገዥዎች ሳይቀሩ ሥልጣኑን ለመቀበል ይገደዳሉ።​—⁠መዝሙር 2:​6-12

6 በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ራሳቸውን የአምላክ መንግሥት ዜጎች አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆን ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” በማለት የሰጠውን ምክር ይከተላሉ። (ማቴዎስ 6:33) ይህ አቋማቸው አገራቸውን ከድተዋል ሊያሰኛቸው አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈሳዊ ሁኔታ ከዚህ ዓለም የተለዩ ያደርጋቸዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ተቀዳሚ ሥራ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖሩት አማኞች ሁሉ ‘ስለ አምላክ መንግሥት መመስከር’ ነው። (ሥራ 28:​23) ማንኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ቢሆን አምላክ ያዘዘውን ይህን ሥራ የማገድ መብት ሊኖረው አይችልም።

7. እውነተኛ ክርስቲያኖች የገለልተኝነት አቋም የሚይዙት ለምንድን ነው? ይህንን ያደረጉትስ እንዴት ነው?

7 የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ወገን፣ የኢየሱስ ተከታዮችና የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን በ20ኛውና በ21ኛው መቶ ዘመናት በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀሰቀሱት ግጭቶች ረገድ የገለልተኝነት አቋም ወስደዋል። የትኛውንም ተፋላሚ ወገን አልደገፉም፣ በማንም ላይ የጦር መሣሪያ አላነሱም እንዲሁም የትኛውንም ዓለማዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ፕሮፓጋንዳ አላሰራጩም። ከባድ ተቃውሞ በደረሰባቸው ጊዜያት ሁሉ በ1934 ለናዚ ጀርመን መሪዎች እንደሚከተለው ተብሎ በግልጽ የተነገራቸውን አቋም በመያዝ ጠንካራ እምነት አሳይተዋል:- “በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አንገባም። ከዚህ ይልቅ በንጉሡ በክርስቶስ የሚመራውን የአምላክን መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን። በማንም ላይ ጉዳት ወይም አደጋ አናደርስም። በሰላም መኖርና ባገኘነው አጋጣሚ ለሰዎች ሁሉ ደግነት ብናሳይ ደስ ይለናል።”

የክርስቶስ አምባሳደሮችና መልእክተኞች

8, 9. ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች አምባሳደሮችና መልእክተኞች ሆነው የሚያገለግሉት እንዴት ነው? ይህ ከመንግሥታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ ራሱንና ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች [“አምባሳደሮች፣” የ1980 ትርጉም ] ነን” ሲል ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 5:20፤ ኤፌሶን 6:20 የ1980 ትርጉም ) የአምላክ መንግሥት “ልጆች” የሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከ1914 ጀምሮ የመንግሥቱ አምባሳደሮች ሆነው አገልግለዋል ቢባል የተገባ ነው። (ማቴዎስ 13:​38፤ ፊልጵስዩስ 3:​20፤ ራእይ 5:​9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ከሕዝብ የተውጣጡና ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ የመረጠ ሲሆን ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ ክርስቲያኖች በመንፈስ የተቀቡትን ልጆች በአምባሳደርነት ሥራቸው ይደግፏቸዋል። (ራእይ 7:​9፤ ዮሐንስ 10:​16) እነዚህ “ሌሎች በጎች” የአምላክ መንግሥት “መልእክተኞች” ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።

9 አንድ አምባሳደርና ሌሎች የኤምባሲው ሠራተኞች መንግሥታቸውን ወክለው በተሾሙበት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም መንግሥታት የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ አይገቡም። በብሔር፣ በጎሣ፣ በመደብ ወይም በኢኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ በሚፈጠር ልዩነት ከየትኛውም ጎራ አይወግኑም። (ሥራ 10:​34, 35) ከዚህ ይልቅ ‘ለሰው ሁሉ መልካም ያደርጋሉ።’ (ገላትያ 6:​10) የይሖዋ ምሥክሮች ገለልተኞች በመሆናቸው ማንኛውም ሰው ቢሆን አንድን ዘር፣ ብሔር ወይም ጎሣ ይደግፋሉ በማለት መልእክታቸውን አልቀበልም ሊል የሚችልበት አጥጋቢ ምክንያት አይኖረውም።

በፍቅራቸው ተለይተው ይታወቃሉ

10. ፍቅር በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ምን ቦታ አለው?

10 ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ክርስቲያኖች በዓለም ጉዳዮች ገለልተኛ የሚሆኑት ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባላቸው ዝምድና የተነሳ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) አንድን ክርስቲያን በእርግጥ ክርስቲያን የሚያሰኘው ዋነኛው ነገር ለእምነት ወንድሞቹ የሚያሳየው ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 3:​14) ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር የመሠረተው ዝምድና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠነክረዋል። ይህ ፍቅር እርሱ ባለበት ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ‘በዓለም ዙሪያ ያሉትን ወንድሞቹንም’ ያቅፋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​9

11. የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር በባሕርያቸው ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

11 የይሖዋ ምሥክሮች “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” የሚሉትን የኢሳይያስ 2:​4 ቃላት ተግባራዊ በማድረግ ለእምነት ወንድሞቻቸው ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከይሖዋ የተማሩ በመሆናቸው ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ሰላም አላቸው። (ኢሳይያስ 54:​13) ለአምላክም ሆነ ለወንድሞቻቸው ፍቅር ስላላቸው በሌሎች አገሮች ውስጥ ባሉ ክርስቲያኖች ወይም በሌላ በማንኛውም ሰው ላይ ሰይፍ ማንሳትን ፈጽሞ አያስቡትም። በመካከላቸው የሰፈነው ሰላምና አንድነት በእርግጥ የአምላክ መንፈስ እንዳላቸው የሚያሳይ የአምልኳቸው ዋነኛ ክፍል ነው። (መዝሙር 133:​1፤ ሚክያስ 2:​12፤ ማቴዎስ 22:​37-39፤ ቆላስይስ 3:​14) “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን” መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ ‘ሰላምን ይሻሉ ይከተሉትማል።’​—⁠መዝሙር 34:​14, 15

ክርስቲያኖች ለዓለም ምን አመለካከት አላቸው?

12. የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ በዓለም ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ያለውን የትኛውን አመለካከት ይኮርጃሉ? እንዴትስ?

12 ይሖዋ በዚህ ዓለም ላይ የቅጣት ፍርድ የበየነበት ቢሆንም በዓለም ላይ በሚኖር በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ግን ገና ፍርድ አላስተላለፈም። ይህን የሚያደርገው በልጁ በኢየሱስ በኩል እርሱ ራሱ በወሰነው ጊዜ ይሆናል። (መዝሙር 67:​3, 4፤ ማቴዎስ 25:​31-46፤ 2 ጴጥሮስ 3:​10) እስከዚያው ድረስ ግን ለመላው የሰው ዘር ፍቅር ማሳየቱን ይቀጥላል። እያንዳንዱ ሰው የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን አጋጣሚ ለመክፈት ሲል አንድያ ልጁን እስከመስጠት ደርሷል። (ዮሐንስ 3:​16) ምንም እንኳን ጥረታችን ብዙውን ጊዜ ተቀባይነት ባያገኝም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አምላክ የሰውን ዘር ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ለሌሎች በመንገር የእርሱን ፍቅር እንኮርጃለን።

13. ስለ ዓለማዊ ገዥዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን መሆን ይኖርበታል?

13 በዓለም ውስጥ ላሉ ገዥዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? ጳውሎስ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው [“ባለ ሥልጣኖች አንጻራዊ የሆነ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው፣” NW ]” ብሎ በጻፈ ጊዜ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (ሮሜ 13:​1, 2) ሰዎች ያላቸው ሥልጣን “አንጻራዊ” ነው። የአንዱ ሰው ሥልጣን ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ሥልጣን እንዲይዙ የፈቀደላቸው ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ በመሆኑ እሱ ካለው ቦታ አንጻር ሲታይ ሁሉም የበታች ናቸው። አንድ ክርስቲያን ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገዛው ይሖዋን እንደሚታዘዝ የሚያሳይበት አንደኛው መንገድ በመሆኑ ነው። ታዲያ አምላክ ከእኛ በሚጠብቀውና ሰብዓዊ መንግሥታት በሚጠብቁብን ግዴታ መካከል ግጭት ቢፈጠር ምን እናደርጋለን?

የአምላክ እና የቄሣር ሕግ

14, 15. (ሀ) ዳንኤል ታዛዥነትን በሚመለከት ጉዳይ ግጭት ውስጥ ከመግባት መራቅ የቻለው እንዴት ነበር? (ለ) ሦስቱ ዕብራውያን ሊሸሹት የማይችሉት የታዛዥነት ፈተና ባጋጠማቸው ጊዜ ምን እርምጃ ወሰዱ?

14 ዳንኤልና ሦስቱ ባልንጀሮቹ ለሰብዓዊ መንግሥታትና ለአምላክ ሥልጣን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዴት መገዛት እንደሚቻል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። እነዚህ አራት ዕብራውያን ወጣቶች በምርኮ ተወስደው በባቢሎን ሲኖሩ ለአገሩ ሕግ ይታዘዙ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ለአንድ ልዩ ሥልጠና ተመረጡ። ዳንኤል ሥልጠናው ከይሖዋ ሕግ ጋር ሊያጋጫቸው እንደሚችል ስለተገነዘበ ጉዳዩን ከሚመለከተው ባለሥልጣናት ጋር ተወያየ። በዚህም ምክንያት የአራቱን ዕብራውያን ሕሊና ለማክበር ሲባል አንድ ልዩ ዝግጅት ተደረገ። (ዳንኤል 1:​8-17) የይሖዋ ምሥክሮች አመለካከታቸውን ለባለሥልጣናት ጥበብ በታከለበት መንገድ በሚያስረዱበት ጊዜ አላስፈላጊ ችግር እንዳይፈጠር የዳንኤልን ምሳሌ ይኮርጃሉ።

15 ይሁን እንጂ በሌላ ወቅት ላይ ተገዥነትን በሚመለከት ጉዳይ መሸሽ የማይቻል ፈተና መጣ። የባቢሎን ንጉሥ በዱራ ሜዳ ላይ አንድ ግዙፍ ጣዖት አስገንብቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የአውራጃ ገዥዎችን ጨምሮ ትላልቅ ባለሥልጣናት እንዲገኙ ትእዛዝ አስተላለፈ። ይህ በሆነበት ወቅት ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች የባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች ሆነው ተሹመው ስለነበር የተላለፈው ትእዛዝ እነርሱንም ይመለከታቸዋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በሙሉ አንድ ምልክት ሲሰጣቸው በምስሉ ፊት እንዲሰግዱ ይጠበቅባቸው ነበር። ዕብራውያኑ ግን እንዲህ ማድረጉ ከአምላክ ሕግ ጋር እንደሚጋጭ ያውቃሉ። (ዘዳግም 5:​8-10) ስለሆነም እዚያ የተገኙ ሰዎች በሙሉ ሲሰግዱ እነርሱ ከቆሙበት ንቅንቅ ሳይሉ ቀሩ። ንጉሡ ያስተላለፈውን ትእዛዝ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ ተፈረደባቸው። ከሞት የተረፉት በተዓምር ነበር። ሆኖም ይሖዋን ሳይታዘዙ ከመቅረት ሞትን መርጠዋል።​—⁠ዳንኤል 2:​49–3:​29

16, 17. ሐዋርያት ስብከታቸውን እንዲያቆሙ በታዘዙ ጊዜ ምን ምላሽ ሰጡ? ለምንስ?

16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኢየሩሳሌም ውስጥ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ፊት እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ በኢየሱስ ስም መስበካቸውን እንዲያቆሙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። ምን መልስ ሰጡ? ኢየሱስ በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎችን ጨምሮ አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልዕኮ ሰጥቷቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌምና በተቀረው ዓለም በሙሉ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሥራ 1:​8) ሐዋርያት፣ የኢየሱስ ትእዛዛት አምላክ እነርሱ እንዲያከናውኑት የሚፈልገው ሥራ ማለት እንደሆነ ተገንዝበዋል። (ዮሐንስ 5:​30፤ 8:​28) ስለሆነም “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል መልስ ሰጥተዋል።​—⁠ሥራ 4:19, 20፤ 5:29

17 ሐዋርያት ይህን በማለታቸው እንደ ዓመፅ ሊቆጠርባቸው አይችልም። (ምሳሌ 24:​21) ሰብዓዊ ገዥዎች የአምላክን ፈቃድ እንዳያደርጉ ሲከለክሏቸው ‘ከሰው ይልቅ አምላክን መታዘዝ ይገባናል’ ከማለት ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ 12:17) የሰውን ቃል ሰምተን መለኮታዊውን ትእዛዝ ብንጥስ ለአምላክ የሚገባውን ለሰው እንደ መስጠት ይሆንብናል። ከዚህ ይልቅ የቄሣር የሆነውን ሁሉ ለቄሣር እንሰጣለን፤ ሆኖም ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ሥልጣን ያለው መሆኑን እንቀበላለን። እርሱ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ፣ ፈጣሪ እንዲሁም የሥልጣን ምንጭ ነው።​—⁠ራእይ 4:​11

ጸንተን እንቆማለን

18, 19. ብዙ ወንድሞቻችን በምሳሌነት የሚጠቀስ ምን አቋም ወስደዋል? ምሳሌያቸውን መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

18 በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉትን የገለልተኝነት አቋም ያከብራሉ፤ ለዚህም አመስጋኞች ነን። በአንዳንድ አገሮች ግን የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “መልካሙን የእምነት ገድል” ተጋድለዋል። ይህ መንፈሳዊ ውጊያ አሁንም እንደቀጠለ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​12

19 ታዲያ እንደ እነርሱ ጸንተን መቆም የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ተቃውሞ ሊያጋጥመን እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል። ተቃውሞ ቢያጋጥመን መደንገጥ ወይም መደነቅ አይገባንም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል አስጠንቅቆታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12፤ 1 ጴጥሮስ 4:​12) የሰይጣን ተጽእኖ በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ ከተቃውሞ እንዴት ነጻ ልንሆን እንችላለን? (ራእይ 12:​17) ታማኝነታችንን ጠብቀን እስከኖርን ድረስ ‘እየተሳደቡ የሚደነቁ’ ሰዎች አይጠፉም።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​4

20. የትኞቹን እውነታዎች ማስታወሳችን ሊያበረታታን ይችላል?

20 በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋና መላእክቱ እንደሚደግፉን እናምናለን። በጥንት ዘመን የኖረው ኤልሳዕ እንደተናገረው “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉ።” (2 ነገሥት 6:​16፤ መዝሙር 34:7) ይሖዋ ለበጎ ዓላማው ሲል ተቃዋሚዎች የሚያደርሱብን ተጽእኖ ለጊዜውም ቢሆን እንዲቀጥል ሊፈቅድ ይችላል። የሆነ ሆኖ በፈተናው ለመጽናት የሚያስችለንን ብርታት መስጠቱን አያቋርጥም። (ኢሳይያስ 41:​9, 10) አንዳንዶች ሕይወታቸውን መክፈል ጠይቆባቸዋል፤ ሆኖም ይህ ወደኋላ እንድንል አያደርገንም። ኢየሱስ “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:16-23, 28) በዚህ ሥርዓት ውስጥ “መጻተኞች” መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም። ይህን ጊዜያችንን ‘እውነተኛውን ሕይወት ለመያዝ’ ይኸውም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ልንጠቀምበት እንፈልጋለን። (1 ጴጥሮስ 2:​11፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​18, 19) ለአምላክ ታማኝ ሆነን እስከኖርን ድረስ ማንም ሰው ቢሆን ይህንን ሽልማት ሊያሳጣን አይችልም።

21. ልንዘነጋው የማይገባ ጉዳይ ምንድን ነው?

21 ስለሆነም ከይሖዋ አምላክ ጋር ውድ ዝምድና መመሥረታችንን እናስታውስ። የክርስቶስ ተከታዮችና የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆናችን ላስገኘልን ጥቅም ምንጊዜም አመስጋኞች እንሁን። ወንድሞቻችንን ከልብ እንውደድ እንዲሁም እነርሱ በሚያሳዩን ፍቅር ዘወትር እንደሰት። ከሁሉም በላይ ደግሞ “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት እንታዘዝ። (መዝሙር 27:14፤ ኢሳይያስ 54:17) እንዲህ ካደረግን ከእኛ በፊት እንደነበሩት እልቆ መሳፍርት የሌላቸው ክርስቲያኖች ሁሉ የዓለም ክፍል ሳንሆን ገለልተኝነታችንን ጠብቀን ተስፋችንን እስክናገኝ ድረስ ጸንተን መቆም እንችላለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ከዓለም የተለየን እንድንሆን የሚያደርገን እንዴት ነው?

• የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንደመሆናችን መጠን ከዓለም ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

• ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ገለልተኞችና ከዓለም የተለየን የሚያደርገን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆናችን ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት የሚነካው እንዴት ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሁቱ እና ቱትሲ በደስታ አብረው ሲሠሩ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይሁድና አረብ ክርስቲያን ወንድሞች በአንድነት

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰርብ፣ የቦስንያ እና የክሮኣት ጎሣ አባላት በሆኑ ክርስቲያኖች መካከል የጠበቀ ወዳጅነት አለ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገዥዎች የአምላክን ሕግ እንድንጥስ በሚያዝዙን ጊዜ ልንወስደው የሚገባው ትክክለኛ እርምጃ ምንድን ነው?