በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

በአነስተኛ ገንዘብ ቁማር መጫወት ስህተት ነው?

የአምላክ ቃል ቁማርን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም ቁማር መጫወት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደሚጋጭ የሚያሳዩ ሐሳቦችን ይዟል። a ለምሳሌ ያህል ቁማር ስግብግብ እንደሚያደርግ በስፋት ይታወቃል። ክርስቲያኖች ከቁማር እንዲርቁ ይህ ብቻውን በቂ ምክንያት ይሆናቸዋል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ስግብግቦች” የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ የሚናገር ሲሆን መጐምጀትንም ከጣዖት አምልኮ ጎን ይፈርጀዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ቆላስይስ 3:5

በተጨማሪም ቁማር ራስ ወዳድነትንና ጤናማ ያልሆነ የውድድር መንፈስን ማለትም ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ፍላጎትን ያነሳሳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” በማለት ከእነዚህ ጎጂ ባሕርያት እንድንርቅ አስጠንቅቆናል። (ገላትያ 5:26) ከዚህም በላይ ቁማር አንዳንዶች በዕድል ላይ አጉል እምነት እንዲያሳድሩ ያደርጋቸዋል። ቁማርተኞች እድል ቀንቷቸው እንዲያሸንፉ በአጉል እምነት ውስጥ ይጠላለፋሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ‘መልካም ገድ ለተባለ ጣዖት ማዕድ ያዘጋጁትን፣ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን የቀዱትን’ ከዳተኞቹን እስራኤላውያንን ያስታውሱናል።​—⁠ኢሳይያስ 65:11

አንዳንዶች ለመዝናናት ሲባል ጥቂት ገንዘብ አስይዞ ከዘመዶችና ከቅርብ ጓደኞች ጋር ቼዥ ወይም ዳማ ወይም ካርታ መጫወት ምንም ጉዳት የለውም ሊሉ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አነስተኛ ገንዘብ አስይዞ የሚጫወት አንድ ሰው ራሱን እንደ ስግብግብ፣ ራስ ወዳድ፣ የፉክክር መንፈስ እንደያዘው ወይም በአጉል እምነት እንደሚያምን አድርጎ ላይቆጥር ይችላል። ሆኖም አብረውት በሚጫወቱት ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? አብዛኞቹ የቁማር ሱሰኞች ወደዚህ ደረጃ የደረሱት ‘ለመዝናናት’ ብለው ትንሽ ገንዘብ እያስያዙ በጀመሩት የቁማር ጨዋታ ነው። (ሉቃስ 16:10) መጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት እንደሌለው የጊዜ ማሳለፊያ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው ጨዋታ የኋላ ኋላ የከፋ መዘዝ ይዞ ይመጣል።

በተለይ ልጆችን በሚመለከት ይህ እውነት ሆኖ ተገኝቷል። ብዙ ልጆች ትናንሽ በሚባሉ የቁማር ጨዋታዎች ማሸነፍ የሚያስገኘው ደስታ ብዙ ገንዘብ አስይዘው ቁማር እንዲጫወቱ ገፋፍቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) በዩናይትድ ስቴትስ የአሪዞና የቁማር ሱሰኝነት ካውንስል ለረጅም ጊዜ ጥናት አካሂዶ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ የቁማር ሱሰኞች ቁማር መጫወት የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸው “በስፖርታዊ ውድድሮች ወቅት ወይም ከጓደኞቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር በሚያደርጉት የካርታ ጨዋታ በአነስተኛ ገንዘብ በመወራረድ ነው።” ሌላ ሪፖርት ደግሞ “ልጆች ቁማር መጫወት የሚጀምሩት በቤታቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ካርታ በመጫወት ነው” በማለት ይናገራል። ሪፖርቱ አክሎም “ቁማር ከሚጫወቱት ልጆች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ቁማር መጫወት የጀመሩት ገና አሥራ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ነው” ብሏል። ሰዎች ይህን ያህል ቁማርተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?​—⁠ልማደኛና ሱሰኛ ቁማርተኞች በሚል ጭብጥ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ ቁማርተኞች ለቁማር የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማግኘት ወንጀልና የጾታ ብልግና ይፈጽማሉ። መጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስለው ነገር የኋላ ኋላ የሚያስከትለው መዘዝ ምንኛ አሳዛኝ ነው!

የምንኖረው ወጥመድና ፈተና በተሞላበት ዓለም ውስጥ ሆኖ ሳለ ራሳችንን ለተጨማሪ ፈተና ለምን እናጋልጣለን? (ምሳሌ 27:12) ልጆች ባሉበትም ሆነ በሌሉበት፣ በትንሽም ሆነ በብዙ ገንዘብ ቁማር መጫወት መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ፈጽሞ ሊወገድ ይገባዋል። ለመዝናናት ብለው እንደ ቼዝ ወይም ዳማ ወይም ካርታ የመሰሉ ጨዋታዎችን መጫወት የሚወዱ ክርስቲያኖች የጨዋታውን ውጤት በወረቀት ላይ እየጻፉ ወይም እንዲሁ ውጤት ሳይመዘግቡ ቢጫወቱ የተሻለ ይሆናል። የራሳቸውም ሆነ የጓደኞቻቸው ወይም የቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊነት የሚያሳስባቸው አስተዋይ ክርስቲያኖች ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ አስይዞ ቁማር የመጫወት ልማድን ያስወግዳሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ ቁማርን “በአንድ ጨዋታ ወይም ክንውን ውጤት ወይም አንድ ነገር ለመፈጸም ባለው አጋጣሚ ላይ መወራረድ” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። አክሎም “ቁማርተኞች . . . አብዛኛውን ጊዜ እንደ ሎተሪ፣ ካርታና ዳይ በመሳሰሉ ጨዋታዎች ላይ ገንዘብ በማስያዝ ቁማር ይጫወታሉ” ይላል።