በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእውነተኛው አምልኮ ደጋፊዎች—ጥንትና ዛሬ

የእውነተኛው አምልኮ ደጋፊዎች—ጥንትና ዛሬ

የእውነተኛው አምልኮ ደጋፊዎች—ጥንትና ዛሬ

ለጥንቷ ኢየሩሳሌም ያለቀሰላትን ሰው ስም ታስታውሳለህ? ‘ኢየሱስ’ ትል ይሆናል። አልተሳሳትክም፤ ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም አልቅሷል። (ሉቃስ 19:​28, 41) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ሌላ የአምላክ አገልጋይ ለኢየሩሳሌም አልቅሶላት ነበር። ስሙ ነህምያ ይባላል።​—⁠ነህምያ 1:​3, 4

ነህምያ ለኢየሩሳሌም እንዲያለቅስ ያደረገው ምን ነበር? ለከተማዋና ለነዋሪዎቿ ምን የሚጠቅም ነገር አከናውኗል? ከእርሱ ምሳሌ ምን እንማራለን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በዘመኑ የተከናወኑትን አንዳንድ ነገሮች እንመርምር።

ሩኅሩኅና ቆራጥ ሰው

ነህምያ የኢየሩሳሌም ገዥ ከመሆኑ በፊት በሱሳ በሚገኘው የፋርስ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበር። ሆኖም ተንደላቅቆ የሚኖር መሆኑ በጣም ርቃ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት አይሁዳውያን ወንድሞቹ ደህንነት እንዳያስብ አላደረገውም። እንዲያውም አንድ የአይሁዳውያን የልኡካን ቡድን ወደ ሱሳ ሲመጣ ነህምያ በመጀመሪያ ያነሳው ጥያቄ

“የዳኑትን ከምርኮ የተረፉትን የአይሁድን ነገር የኢየሩሳሌምንም ነገር” ነበር። (ነህምያ 1:​2) ልኡካኑ የኢየሩሳሌም ሰዎች “በታላቅ መከራ . . . አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል” ብለው ሲነግሩት ነህምያ ‘ቁጭ ብሎ አለቀሰ፣ አያሌ ቀንም አዘነ።’ ከዚያ በኋላ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ። (ነህምያ 1:​3-11) ነህምያ እንዲህ ያዘነው ለምን ነበር? ምክንያቱም በምድር ላይ የይሖዋ አምልኮ ማዕከል የነበረችው ኢየሩሳሌም ችላ ተብላ ስለነበር ነው። (1 ነገሥት 11:​36) ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋ መፈራረስ ነዋሪዎቿ ያሉበትን አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ያመለክት ነበር።​—⁠ነህምያ 1:​6, 7

ነህምያ ለኢየሩሳሌም የነበረው ተቆርቋሪነትና ለነዋሪዎቿ የተሰማው ጥልቅ ሐዘን ራሱን በፈቃደኝነት እንዲያቀርብ አነሳስቶታል። ከፋርሱ ንጉሥ የሥራ ፈቃድ እንዳገኘ ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርገው ረጅም ጉዞ ዕቅድ ማውጣት ጀመረ። (ነህምያ 2:​5, 6) ጉልበቱን፣ ጊዜውንና ችሎታውን ቅጥሩን በማደሱ ሥራ ላይ ለማዋል ፈለገ። ኢየሩሳሌም ከደረሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ የከተማዋን ቅጥር ሙሉ በሙሉ ለማደስ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀቀ።​—⁠ነህምያ 2:​11-18

ነህምያ ቅጥሩን የማደሱን ከባድ ሥራ ጎን ለጎን ሆነው ለሚሠሩ በርካታ ቤተሰቦች አከፋፈለው። a እያንዳንዳቸው አንድ “ክፍል” የሚያድሱ ከ40 የሚበልጡ ቡድኖች ነበሩ። ውጤቱስ? ወላጆችንና ልጆ​ችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በመስጠታቸው ከባድ መስሎ የታየው ሥራ ሊገፋ ቻለ። (ነህምያ 3:​11, 12, 19, 20) ሁለት ወራት ከፈጀ ከባድ ሥራ በኋላ ቅጥሩን የማደሱ ሥራ ተጠናቀቀ! ነህምያ ሥራውን የተቃወሙት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ‘ሥራው በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ’ ለመገንዘብ መገደዳቸውን ጽፏል።​—⁠ነህምያ 6:​15, 16

ሊታወስ የሚገባው ምሳሌ

ነህምያ ለሥራው ያበረከተው ጊዜውንና የማደራጀት ችሎታውን ብቻ አልነበረም። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ቁሳዊ ሃብቱንም ተጠቅሟል። ለባርነት የተሸጡ አይሁዳውያን ወንድሞቹን በራሱ ገንዘብ ተቤዥቷቸዋል። ገንዘቡን ያለ ወለድ አበድሯል። ለአለቃ የሚገባውን አበል እንዲሰጡት በመጠየቅ በአይሁዳውያን ላይ ሸክም ‘አላከበደባቸውም።’ ከዚህ ይልቅ ‘በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ ወደ እነርሱ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች’ ለመመገብ ቤቱን ክፍት አድርጓል። “ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች” ለእንግዶቹ ያቀርብ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በየአሥር ቀኑ በራሱ ወጪ “ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ” ያቀርብላቸው ነበር።​—⁠ነህምያ 5:​8, 10, 14-18

ነህምያ ልግስናን በተመለከተ ለጥንቶቹም ሆነ ለዛሬዎቹ የአምላክ አገልጋዮች ምንኛ ግሩም ምሳሌ ትቷል! ይህ ደፋር የአምላክ አገልጋይ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የሚደክሙትን ሠራተኞች ለመደገፍ ቁሳዊ ንብረቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷል። ስለዚህም ይሖዋን “አምላኬ ሆይ፣ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ” ብሎ መጠየቁ የተገባ ነበር። (ነህምያ 5:​19) ይሖዋ ያደረገውን ለበጎ እንደሚያስብለት የታወቀ ነው።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

ዛሬም ብዙዎች የነህምያን ምሳሌ ኮርጀዋል

ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛውን አምልኮ ከልብ ሲደግፉ፣ ለሥራ በፈቃደኝነት ሲነሳሱና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ሲያሳዩ መመልከት ያስደስታል። ክርስቲያን ወንድሞቻችን መከራ እንደደረሰባቸው ስንሰማ ደህንነታቸው በጥልቅ ያሳስበናል። (ሮሜ 12:​15) ልክ እንደ ነህምያ እኛም ችግር የደረሰባቸውን ወንድሞች በማስመልከት “ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ” በማለት ወደ ይሖዋ እንጸልያለን።​—⁠ነህምያ 1:​11፤ ቆላስይስ 4:​2

ይሁን እንጂ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን መንፈሳ​ዊና አካላዊ ደህንነት እንዲሁም ለእውነተኛው አምልኮ መስፋፋት ያለን አሳቢነት በጸሎት ብቻ ተወስኖ ይቀራል ማለት አይደለም። ለተግባርም ያንቀሳቅሰናል። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ልክ እንደ ነህምያ በአገራቸው ያለውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ለመዛወር በፍቅር ተገፋፍተዋል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያለው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ ኋላ እንዲያደርጋቸው ባለመፍቀድ ለእውነተኛው አምልኮ መስፋፋት ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሠራሉ። የሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በእርግጥም የሚያስመሰግን ነው።

በምንኖርበት አካባቢ የየራሳችንን ድርሻ መወጣት

አብዛኞቻችን ወደ ሌላ ቦታ መዛወር እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም ባለንበት ሆነን እውነተኛውን አምልኮ እንደግፋለን። ይህም ቢሆን በነህምያ መጽሐፍ ውስጥ ተንጸባርቋል። ነህምያ ቅጥሩን በማደሱ ሥራ ስለተካፈሉት አንዳንድ ታማኝ ቤተሰቦች ያከለውን ሐሳብ ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። . . . ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።” (ነህምያ 3:10, 23, 28-30፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው በቤታቸው አቅራቢያ በእደሳው ሥራ ላይ የየራሳቸውን ድርሻ በመወጣት ለእውነተኛው አምልኮ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ዛሬ ብዙዎቻችን በምንኖርበት አካባቢ እውነተኛውን አምልኮ በተለያዩ መንገዶች እንደግፋለን። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን በመርዳቱ ሥራና ከሁሉም በላይ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንካፈላለን። ከዚህም በተጨማሪ በግላችን በግንባታ ወይም በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን በመርዳቱ ሥራ መካፈል ቻልንም አልቻልን ነህምያ በዘመኑ እንዳደረገው ሁሉ እውነተኛውን አምልኮ በቁሳዊ ንብረቶቻችን የመደገፍ ልባዊ ፍላጎት አለን።​—⁠“በፈቃደኝነት መንፈስ መስጠት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

እያደገ የመጣውን የሕትመት፣ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን የመርዳትና በዓለም ዙሪያ የሚከናወኑትን የሌሎች በርካታ እንቅስቃሴዎች ወጪ ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት አንዳንድ ጊዜ ከአቅም በላይ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም በነህምያ ዘመን ረጅሙን ቅጥር የማደሱም ሥራ የማይቻል መስሎ ይታይ እንደነበር አስታውስ። (ነህምያ 4:​10) ይሁን እንጂ ሥራውን ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ ቤተሰቦች ተከፋፍለውት ስለነበር እደሳውን ማጠናቀቅ ተችሏል። ዛሬም በተመሳሳይ እያንዳንዱ ሰው ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ከቀጠለ ሥራውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ይቻላል።

“አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች” የሚለው ሳጥን የመንግሥቱን ሥራ በቁሳዊ መንገድ መደገፍ የሚቻልባቸውን በርካታ መንገዶች ይዘረዝራል። ባለፈው ዓመት በርካታ የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ያለውን ድጋፍ ሰጥተዋል። በዚህ አጋጣሚ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል በፈቃደኝነት መዋጮ ለማድረግ ልባቸው ላነሳሳቸው ሁሉ ልባዊ አመስጋኝነቱን ለመግለጽ ይወድዳል። ከሁሉም በላይ ይሖዋ ሕዝቦቹ እውነተኛውን አምልኮ በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ልባዊ ጥረት አብዝቶ በመባረኩ እናመሰግነዋለን። አዎን፣ ባለፉት ዓመታት ይሖዋ የሰጠንን አመራር ስናስብ ነህምያ በአመስጋኝነት ስሜት “የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም . . . ሆነች” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ለማስተጋባት እንገፋፋለን።​—⁠ነህምያ 2:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ነህምያ 3:​5 አንዳንድ አይሁዳውያን ‘መኳንንቶች’ (አ.መ.ት ) በዚህ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ይገልጻል። ሆኖም ይህንን ያደረጉት እነርሱ ብቻ ነበሩ። ካህናትን፣ ወርቅ አንጥረኞችን፣ ሽቱ ቀማሚዎችን፣ አለቆችንና ነጋዴዎችን ጨምሮ የተለያየ ቦታና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሥራው ተካፍለዋል።​—⁠ቁጥር 1, 8, 9, 32

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች

ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:​14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።

ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአገራቸው ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ። በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎች በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም ለማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት

አንድ ሰው የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበትን ልዩ ዝግጅት በማድረግ መስጠት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ውድ ዕቃዎችን በስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ:-

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን እንዳለ በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት:- ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በስጦታ መስጠት ወይም ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።

የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ማኅበሩ ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ለቀረቡለት ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው። በተጨማሪም ብሮሹሩ ከማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ከገንዘብና ከታክስ ጋር በተያያዘ እቅድ ማውጣትን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ነው። ከዚህም ሌላ ብሮሹሩ ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን መንገዶች ይጠቁማል። የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ ለሚከታተለው ቢሮ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል።

ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ ከሚከታተለው ቢሮ ጋር በመማከር ብዙዎች ማኅበሩን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ እንዲህ ማድረጋቸው ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለው ቢሮ ከእነዚህ ዝግጅቶች ጋር ግንኙነት ስላላቸው የስጦታ ሰነዶች ሊነገረውና የሰነዶቹ ቅጂ ሊላክለት ይገባል። ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች በአንዱ መዋጮ ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመህ ወይም ወደ ማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል ማሳወቅ አለብህ።

Charitable Planning Office

Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania

100 Watchtower Drive,

Patterson, New York 12563-9204

ስልክ:- (845) 306-0707

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በፈቃደኝነት መንፈስ መስጠት

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በፈቃደኝነት መንፈስ መስጠት ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ሲጠቁም ሦስት ጉልህ ነጥቦችን ጠቅሷል። (1) ጳውሎስ ገንዘብ ስለማዋጣት ሲጽፍ “ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 16:2) ስለዚህ ለመስጠት አስቀድሞ ማሰብ እንዲሁም እቅድና ፕሮግራም ማውጣት ያስፈልጋል። (2) ጳውሎስ እያንዳንዱ “እንደ ገቢው መጠን” መስጠት እንዳለበትም ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 16:​2 አ.መ.ት ) በሌላ አባባል በፈቃደኝነት መዋጮ ማድረግ የሚፈልግ ሰው እንደ አቅሙ መስጠት ይችላል ማለት ነው። አንድ ክርስቲያን ገቢው በጣም አነስተኛ በመሆኑ የሚያደርገው መዋጮ ትንሽ ቢሆንም እንኳ በይሖዋ ፊት ከፍተኛ ዋጋ አለው። (ሉቃስ 21:​1-4) (3) በተጨማሪም ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) እውነተኛ ክርስቲያኖች ከልባቸው ማለትም በደስታ ይሰጣሉ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነህምያ ሩኅሩኅና ቆራጥ ሰው ነበር

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፈቃደኝነት የሚሰጡ መዋጮዎች በዓለም ዙሪያ ለሕትመት ሥራ፣ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን ለመርዳት፣ ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታና ለሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይውላሉ