ይቅርታ መጠየቅ ይህን ያህል ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?
ይቅርታ መጠየቅ ይህን ያህል ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?
ሐምሌ 2000 በዩናይትድ ስቴትስ የካሊፎርኒያ ግዛት ሕግ አውጪ ክፍል ሰዎች ድንገተኛ አደጋ አድርሰው ይቅርታ መጠየቃቸው በሕግ ተጠያቂ የማያደርጋቸው መሆኑን የሚገልጽ ሕግ አውጥቷል። እንዲህ ያለ ሕግ ማውጣት ለምን አስፈለገ? ብዙ ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ሳቢያ ለደረሰ ጉዳት ይቅርታ መጠየቅ ጥፋትን እንደማመን ተቆጥሮ በሕግ ያስቀጣል በሚል ፍራቻ ይቅርታ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደሚሉ በመስተዋሉ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ ይቅርታ መባል ይገባኝ ነበር ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይቅርታ ባለመጠየቃቸው የተነሳ በጣም ሊበሳጩና ትንሹ ነገር ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያመራ ስለሚችል ነው።
እርግጥ ነው፣ ላላደረስከው አደጋ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልግህም። ሆኖም ስለምትናገረው ነገር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። አንድ ጥንታዊ ምሳሌ “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 10:19፤ 27:12) ያም ሆኖ አክብሮት ማሳየትና ሌሎችን መርዳት ትችላለህ።
ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በሕግ ፊት የሚያስጠይቃቸው ባይሆንም እንኳ ይቅርታ መጠየቅ ማቆማቸው እውነት አይደለም? አንዲት ሚስት ‘ባሌ
ፈጽሞ ይቅርታ አይጠይቅም’ በማለት ታማርር ይሆናል። አንድ አለቃ ‘ሠራተኞቼ ፈጽሞ ስህተታቸውን አያምኑም። አንድም ቀን ይቅርታ ጠይቀው አያውቁም’ በማለት በምሬት ሲናገር ይደመጥ ይሆናል። አንድ መምህር ‘ልጆች ይቅርታ የመጠየቅ ልማድ እንዲያዳብሩ አልሠለጠኑም’ በማለት ሪፖርት ያደርግ ይሆናል።አንድ ሰው ይቅርታ እንዳይጠይቅ የሚያደርገው አንደኛው ምክንያት ተቀባይነት አጣለሁ የሚለው ፍራቻ ሊሆን ይችላል። ሰዎች ያኮርፉኛል ብሎ በመፍራት ትክክለኛ ስሜቱን ላይገልጽ ይችላል። እንዲያውም ተበዳዩ ግለሰብ ከበዳዩ ሙሉ በሙሉ ሊርቅና እርቅ የመፍጠሩን አጋጣሚ ሊያጠብበው ይችላል።
አንዳንዶች ይቅርታ እንዳይጠይቁ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ለሌሎች ስሜት ግድየለሽ መሆናቸው ነው። ‘ይቅርታ ጠየቅሁ አልጠየቅሁ ምን ለውጥ ያመጣል’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ይቅርታ ከመጠየቅ ወደ ኋላ ይላሉ። ‘ተጠያቂ ብሆንስ? ካሳ እንድከፍል ብጠየቅስ?’ ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይቅርታ መጠየቅን ከሁሉም በላይ ከባድ የሚያደርገው ኩራት ነው። “ይቅርታ” የምትለዋን ቃል ከአፉ ማውጣት በጣም የሚከብደው ሰው ‘ስህተቴን በማመን ክብሬን ማጣት አልፈልግም። ይቅርታ ከጠየቅሁ ክብሬ ይቀንሳል’ ብሎ ያስባል።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ብዙዎች ይቅርታ የሚለውን ቃል ከአፋቸው ማውጣት ይከብዳቸዋል። ታዲያ ይቅርታ መጠየቅ የግድ አስፈላጊ ነው? ይቅርታ መጠየቅ ምን ጥቅሞች አሉት?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ልጆች ይቅርታ የመጠየቅ ልማድ እንዲያዳብሩ አልሠለጠኑም”
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሠራተኞቼ ፈጽሞ ስህተታቸውን አያምኑም”
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ባሌ ፈጽሞ ይቅርታ አይጠይቅም”