በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወታችንን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

ሕይወታችንን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

ሕይወታችንን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

“በትናንትናው ዕለት ጀንበር ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ እያንዳንዳቸው እንደ አልማዝ ውድ የሆኑ ስድሳ ደቂቃዎች ያሏቸው ሁለት ወርቃማ ሰዓታት በከንቱ ባክነውብኛል። እስከ ወዲያኛው ስለጠፉ ላገኘልኝ ሰው እከፍላለሁ የምለው ወሮታ የለም!”​—⁠አሜሪካዊቷ ደራሲ ሊዲያ ኤች ሲጎርኔ (1791-1865)

የሕይወት ዘመናችን አጭርና እንደ ጥላ በቅጽበት የሚያልፍ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት በሕይወት አጭርነት ላይ ካሰላሰለ በኋላ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣ የዘመኔንም ቁጥር አስታውቀኝ፤ አላፊ ጠፊ መሆ[ኔ]ንም ልረዳ። እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤ ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው” ብሎ ለመጸለይ ተገፋፍቷል። ዳዊትን የሚያሳስበው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አምላክን የሚያስደስት አኗኗር መከተሉ ነበር። እምነቱን የጣለው በአምላክ ላይ እንደሆነ ሲናገር “ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው” ብሏል። (መዝሙር 39:4, 5, 7 አ.መ.ት ) ይሖዋም ሰምቶታል። በእርግጥም ደግሞ ይሖዋ ዳዊትን የሚያደርጋቸውን ነገሮች አንድ በአንድ በመመዘን ባርኮታል።

እያንዳንዷን ደቂቃ በሥራ ተጠምዶ ማሳለፍና በጥድፊያ የተሞላ ሕይወት መምራት ይቻላል። ብዙ ማከናወን ያለብን ነገር እንዳለና ጊዜ እንደሚያጥረን ተሰምቶን ልንጨነቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ የሚያሳስበን ልክ እንደ ዳዊት ሕይወታችንን የአምላክን ሞገስ እንድናገኝ በሚያስችለን መንገድ መምራት ነው? ይሖዋ እያንዳንዳችንን እንደሚመለከተንና ሁኔታችንን በጥንቃቄ እንደሚመረምር የተረጋገጠ ነው። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ ከዛሬ 3, 600 ዓመት በፊት ይሖዋ አካሄዱን እንደሚመለከትና እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን እንደሚመረምር ተገንዝቦ ነበር። ኢዮብ “ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?” በማለት ጠይቋል። (ኢዮብ 31:4-6, 14 አ.መ.ት ) ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት፣ የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅና ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ሕይወታችንን በአምላክ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ መምራት እንችላለን። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምራቸው።

ለመንፈሳዊ ነገሮች ቀዳሚውን ቦታ እንስጥ

በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ፈትናችሁ ውደዱ’ በማለት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ ያሳስበናል። ይበልጥ አስፈላጊ የተባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? ‘ትክክለኛ እውቀትና ማስተዋል’ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ስለ ይሖዋ ዓላማ ማወቅ እንድንችል ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም ይኖርብናል። ቢሆንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቀዳሚውን ቦታ መስጠታችን እርካታ ያለው ሕይወት ያስገኝልናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ሁልጊዜ ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እንድንመረምር’ ያሳስበናል። ይህም ዝንባሌያችንንና የልባችንን ፍላጎቶች ማጤንን የሚጨምር መሆን አለበት። ሐዋርያው በመቀጠልም “የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 5:​9, 10, 17) ታዲያ ይሖዋን ደስ የሚያሰኘው ምንድን ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ከፍ ከፍ አድርጋት፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች” በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። (ምሳሌ 4:7, 8) ይሖዋ አምላካዊ ጥበብ ባለውና ያንንም በሚጠቀምበት ሰው ይደሰታል። (ምሳሌ 23:15) የእንዲህ ዓይነቱ ጥበብ ልዩ ባሕርይ አንዴ ካገኘነው ሊወሰድብን ወይም ሊጠፋ አለመቻሉ ነው። እንዲያውም “ከክፉ መንገድ . . . ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች” ጥበቃና ከለላ ሊሆንልን ይችላል።​—⁠ምሳሌ 2:10-15

እንግዲያው ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ግድየለሽ የመሆን ዝንባሌን መዋጋታችን ምንኛ ጥበብ ነው! ለይሖዋ ቃል አመስጋኝ መሆንና ለእርሱ ጤናማ ፍርሃት ማዳበር ያስፈልገናል። (ምሳሌ 23:​17, 18) ምንም እንኳን እንደዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ በየትኛውም እድሜ ላይ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ገና በወጣትነታችን ይህንን ትክክለኛ ጎዳና መከተላችንና ባሕርያችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መቅረጻችን የተሻለ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” በማለት ተናግሯል።​—⁠መክብብ 12:​1

ለይሖዋ የአድናቆት ስሜት ማዳበር የምንችልበት ወሳኝ የሆነው መንገድ በየዕለቱ ወደ እርሱ በግል መጸለይ ነው። ዳዊት “አቤቱ፣ ጸሎቴን ስማ፣ ጩኸቴንም አድምጥ፣ ልቅሶዬንም ቸል አትበ[ለ]ኝ” ብሎ ካቀረበው ልመና ለመረዳት እንደምንችለው በይሖዋ መታመን ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ነበር። (መዝሙር 39:12) ከይሖዋ ጋር ካለን የጠበቀ ዝምድና የተነሳ ስሜታችን ተነክቶ የምናነባበት ጊዜ አለ? ደግሞም የልባችንን ምስጢር ገልጸን የምናዋየውና በቃሉ ላይ የምናሰላስል ከሆነ እርሱም ይበልጥ ወደ እኛ ይቀርባል።​—⁠ያዕቆብ 4:8

መታዘዝን ተማሩ

በአምላክ ላይ መታመን እንደሚያስፈልገው አምኖ የተቀበለው ሌላው ሰው ደግሞ ሙሴ ነበር። ሙሴም ልክ እንደ ዳዊት ሕይወት በመከራ የተሞላ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ‘ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረው ዘንድ ዕድሜውን መቁጠር እንዲያስተምረው’ አምላክን ተማጽኗል። (መዝሙር 90:10-12 አ.መ.ት ) ጥበበኛ ልብ ማግኘት የሚቻለው የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመማርና ሥራ ላይ በማዋል ብቻ ነው። ሙሴ ይህን ያውቅ ስለነበር እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው በፊት የአምላክን ሕግጋትና መመሪያዎች እየደጋገመ በማስተማር ይህን መሠረታዊ እውነት በውስጣቸው ለመቅረጽ ጥረት አድርጓል። ከጊዜ በኋላ እስራኤልን እንዲያስተዳድር በይሖዋ የሚመረጠው ማንኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ የሕጉን ቅጂ ለራሱ መገልበጥና በሕይወት ዘመኑ በሙሉ በየዕለቱ ማንበብ ነበረበት። ለምን? አምላክን መፍራት እንዲማር ነው። ይህ የአንድን ንጉሥ ታዛዥ መሆን አለመሆን የሚፈትን ነበር። በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ የሚጠብቀው ከመሆኑም በላይ የንግሥና ዘመኑንም ያራዝምለታል። (ዘዳግም 17:18-20) ይሖዋ ለዳዊት ልጅ ለሰሎሞን “አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፣ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፣ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ” በማለት ተመሳሳይ ቃል ገብቶለት ነበር።​—⁠1 ነገሥት 3:10-14

ታዛዥነት በአምላክ ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር ነው። አንዳንዶቹን የይሖዋን ትእዛዛት እንደማያስፈልጉ ነገሮች አቅልለን የምንመለከታቸው ከሆነ ይህንን ዝንባሌያችንን መመልከቱ አይቀርም። (ምሳሌ 15:3) ይህን መገንዘባችን መለኮታዊ መመሪያዎቹን ጠብቆ መመላለስ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳን ሁሉንም መመሪያዎች ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይገባል። ሰይጣን የአምላክን ሕግጋትና መመሪያዎች ለመከተል ስንጥር ‘ከመንገዳችን ለማሰናከል’ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:18 NW 

በተለይ ለአምልኮና እርስ በርስ ለመተናነጽ አንድ ላይ እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዘዳግም 31:12, 13፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ስለዚህ ራሳችንን ‘በእርግጥ ጠቃሚ የሆነ ነገር ለማድረግ የሚያስፈልገው ቁርጠኝነትና ጽናት አለኝ?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። የተደላደለ ኑሮ ለማግኘት ብለን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናገኘውን ትምህርትና አስደሳች ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ችላ ብንል ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይዳከማል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ [ይሖዋ] ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:5) ይሖዋን በፈቃደኝነት መታዘዛችን እርሱ እንደማይተወን ያለንን ሙሉ እምነት ያሳያል።

ኢየሱስ መታዘዝን ተምሯል፤ ደግሞም በመማሩ ተጠቅሟል። እኛም ልንጠቀም እንችላለን። (ዕብራውያን 5:​8) ታዛዥነትን ይበልጥ ባዳበርን መጠን በትናንሽ ነገሮችም መታዘዝ ቀላል እየሆነልን ይሄዳል። በታማኝነታችን ምክንያት ከሌሎች የሚደርስብንን መከራና መጉላላት ተቋቁመን መኖር ያስፈልገን ይሆናል። ይህ በተለይ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ሊያጋጥመን ይችላል። ቢሆንም እስራኤላውያን ‘ይሖዋን ቢወድዱት፣ አጥብቀው ቢከተሉትና ቃሉን ቢያዳምጡ እርሱ ሕይወታቸውና የዘመናቸው ርዝመት እንደሚሆን’ የተሰጣቸውን ማረጋገጫ በማስታወስ መጽናናት እንችላለን። (ዘዳግም 30:20) ይኸው ተስፋ ለእኛም ይሠራል።

ጊዜን በጥበብ መጠቀም

የሕይወት ዘመናችንን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ መምራት የምንችልበት ሌላው መንገድ ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ነው። ጊዜን እንደ ገንዘብ ለሌላ ጊዜ ቆጥበን ልናስቀምጠው አንችልም። ጥቅም ላይ ካልዋለ በከንቱ ባክኖ ያልፋል። እያንዳንዱ ሰዓት አንዴ ካለፈ ለዘላለም አይመለስም። ልንሠራው የምንፈልገው ነገር ካለን ጊዜ አንጻር በጣም ብዙ ስለሚሆን ጊዜያችንን የምንጠቀምበት ከሕይወታችን ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው? የሁሉም ክርስቲያኖች ዋነኛ ግብ በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ቋሚ ተሳትፎ ማድረግ መሆን አለበት።​—⁠ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

ጊዜያችንን በጥበብ የምንጠቀምበት ዋጋማነቱን በሚገባ ስንገነዘብ ብቻ ነው። ኤፌሶን 5:16 ‘ዘመኑን እንድንዋጅ’ የሚሰጠው ማሳሰቢያ ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑትን ነገሮች ወደ ጎን በመተው ጊዜን “መግዛትን” ያመለክታል። በሌላ አባባል ጊዜ የሚያባክኑ ነገሮችን መቀነስ ማለት ነው። ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም ኢንተርኔት ከፍቶ ይህንንም ያንንም በማሰስ፣ እርባና የሌላቸውን ዓለማዊ ጽሑፎች በማንበብ ወይም በመዝናኛና በጨዋታ ብዙ ጊዜ ማጥፋት ሰውነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። በተጨማሪም ቁሳዊ ነገሮችን ማካበትም ጥበበኛ ልብ ለማግኘት የሚያስፈልገንን ጊዜ ሊያባክንብን ይችላል።

በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቃ መሆንን የሚያበረታቱ ሰዎች “ግልጽና ተጨባጭ የሆነ ግብ ሳያወጡ ጊዜን በአግባቡ ልጠቀም ማለት ዘበት ነው” በማለት ይናገራሉ። ግብ ለማውጣት የሚያስፈልጉትን አምስት ነገሮች ይዘረዝራሉ። አንድ ግብ ቁርጥ ያለ፣ ምዕራፍ በምዕራፍ የሚከናወን፣ ሊደረስበት የሚችል፣ ከእውነታው ያልራቀና የጊዜ ገደብ ያለው ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ።

አስፈላጊ ከሆኑት ግቦች መካከል አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ልማዳችንን ማሻሻል ነው። የመጀመሪያው እርምጃ ግባችን ቁርጥ ያለ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ ነው። ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ ግባችን ምዕራፍ በምዕራፍ የሚከናወን እንዲሆን ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ያደረግነውን መሻሻል መከታተል እንችላለን። የምናወጣቸው ግቦች ተጨማሪ ጥረት እንድናደርግና እንድንሻሻል የሚረዱን ሊሆኑ ይገባል። እንዲሁም ሊደረስባቸው የሚችሉና ከእውነታው ያልራቁ መሆን አለባቸው። የግል ችሎታችንን፣ ሙያችንንና ጊዜያችንን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። አንዳንዶች ግባቸውን ለማሳካት ከሌሎች ይበልጥ ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋቸው ይሆናል። በመጨረሻም ግባችን የጊዜ ገደብ ሊበጅለት ያስፈልጋል። አንድን ሥራ የምናጠናቅቅበትን የጊዜ ገደብ ማውጣታችን ሥራውን ለማከናወን ልባዊ ጥረት እንድናደርግ ሊያበረታታን ይችላል።

በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉት የዓለም አቀፋዊው ቤቴል ቤተሰብ አባላት በቤቴል የመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበው የመጨረስ ግብ አላቸው። ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልማድ ለመንፈሳዊ እድገታቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ራሳቸውን እንዲጠቅሙ ከሚያስተምራቸው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት እንደሚረዳቸው ይገነዘባሉ። (ኢሳይያስ 48:17) እኛም በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ግብ ማውጣት እንችል ይሆን?

የሕይወት ዘመናችንን ትርጉም ባለው መንገድ መጠቀም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

ለመንፈሳዊ ነገሮች ቀዳሚውን ቦታ መስጠት ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶች ያስገኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ስኬታማ ከመሆን የሚመነጨውን እርካታ እንድናገኝና ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር እንድንችል ይረዳናል። ልባዊ የሆነ ጸሎት በማቅረብ ከይሖዋ ጋር አዘውትረን መነጋገራችን ወደ እርሱ የበለጠ እንድንቀርብ ያደርገናል። ወደ እርሱ መጸለያችን በእርሱ እንደምንታመን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ” እያዘጋጀ የሚያቀርብልንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በየዕለቱ ማንበባችን አምላክ የሚነግረንን ለማዳመጥ ፈቃደኞች መሆናችንን ያሳያል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህም በሕይወታችን ውስጥ ትክክለኛ ውሳኔዎችንና ምርጫዎችን ለማድረግ የሚያስችለንን ጥበበኛ ልብ እንድናገኝ ይረዳናል።​—⁠መዝሙር 1:1-3

የይሖዋን ትእዛዛት መጠበቅ ሸክም ስላልሆነ እንዲህ በማድረጋችን በጣም ደስ ይለናል። (1 ዮሐንስ 5:3) እያንዳንዱን ቀን በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ለመጠቀም ስንጥር ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። እንዲሁም ለክርስቲያን ወንድሞቻችን እውነተኛ መንፈሳዊ ድጋፍ እንሆናቸዋለን። ይህም ይሖዋ አምላክን ደስ ያሰኘዋል። (ምሳሌ 27:11) አሁንም ሆነ ለዘላለም የይሖዋን ሞገስ ከማግኘት የሚበልጥ በረከት ደግሞ የለም!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ግምት ይሰጣሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊዜህን በጥበብ እየተጠቀምክበት ነውን?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እያንዳንዱን ዕለት በይሖዋ ፊት ትርጉም ባለው መንገድ ስንጠቀምበት ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል