መልካም ምግባርን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች
መልካም ምግባርን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች
በ2001 መገባደጃ ላይ የሞዛምቢክ ራዲዮ ብሔራዊ ስርጭትን ሲያዳምጡ የነበሩ ሰዎች የሚከተለው መግለጫ ሲነገር ሰምተው ነበር:-
“የሪፑብሊኳ ርዕሰ ብሔር በማፑቶ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጎበኙ። ይህ ሃይማኖታዊ ጉባኤ በቤተሰብ ውስጥ መልካም ምግባርን ለማስፈንና ጎልማሶችን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልበት አበረታተዋል። እስካሁን 10, 000 የሚያህሉ ሰዎች ከዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል። እንደ ርዕሰ ብሔር ሺሳኑ አባባል እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞች በዚች አገር ላይ የተደቀኑትን የትምህርት ችግሮች በመፍታት ረገድ ለማኅበረሰቡ የላቀ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክቱ ሊበረታቱ ይገባል።”
መግለጫው የሚከተለውን የርዕሰ ብሔሩን ንግግር በቀጥታ አሰምቷል:- “ብዙ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው መመልከቱ የሚያበረታታ ነው። መሃይምነትን በእጅጉ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ተራው ኅብረተሰብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ማንበብና መጻፍ የማስተማር ፕሮግራማቸውን በማንኛውም ቋንቋ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማበረታታት እፈልጋለሁ። ሰዎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉና በቀላሉ እንዲግባቡ እንዲሁም ወደፊት በትምህርት ዘርፍ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መርዳት መቻል በጣም ትልቅ ነገር ነው።”
በሞዛምቢክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች የአምላክን ቃል ራሳቸው ማንበብ ይችሉ ዘንድ በመላው አገሪቱ ውስጥ በ850 ቦታዎች ማንበብና መጻፍ ያስተምራሉ። በተጨማሪም በየሳምንቱ 50, 000 ለሚያህሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ያስተምራሉ። ይህ ሁሉ በአሁኑ ወቅት በ235 አገሮች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር መርሐ ግብር ክፍል ነው። (ማቴዎስ 24:14) እርስዎም ከዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለጉ በአቅራቢያዎ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ይችላሉ።