መሰብሰባችሁን አትተዉ
መሰብሰባችሁን አትተዉ
መጽሐፍ ቅዱስ “በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 10:25) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ አምላኪዎች ‘ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ ለመነቃቃት’ በአንድ የአምልኮ ቦታ እንዲሰበሰቡ ታዝዘዋል።—ዕብራውያን 10:24
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ከላይ ያለውን ሲጽፍ በኢየሩሳሌም የሚገኘው አስደናቂ ቤተ መቅደስ ለአይሁዳውያኑ የአምልኮ ቦታ ሆኖ ያገለግል ነበር። በወቅቱ ምኩራቦችም ነበሩ። ኢየሱስ “አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በመቅደስ” አስተምሯል።—ዮሐንስ 18:20
ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እርስ በርስ ለመበረታታት አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ሲመክራቸው በአእምሮው ይዞት የነበረው የመሰብሰቢያ ቦታ ምን ዓይነት ነው? የሕዝበ ክርስትና ግዙፍ ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች ኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ ጋር ምን ዝምድና አላቸው? ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሕንጻዎችን መሥራት የጀመሩት መቼ ነው?
‘ለአምላክ ስም የሚሆን ቤት’
የአምልኮ ቦታን በሚመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው መመሪያ የሚገኘው በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ ነው። ይሖዋ አምላክ የተመረጠ ሕዝቡን እስራኤልን ‘የማደሪያ ድንኳን’ ዘጸአት ምዕራፍ 25-27፤ 40:33-38) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ድንኳን ‘የእግዚአብሔር መቅደስ’ እና ‘የእግዚአብሔር ቤት’ በማለትም ይጠራዋል።—1 ሳሙኤል 1:9, 24
ወይም “የመገናኛ ድንኳን” እንዲሠራለት አዘዘው። የቃል ኪዳኑ ታቦትና ሌሎች በርካታ ንዋየ ቅዱሳት እዚያ መቀመጥ ነበረባቸው። ድንኳኑ በ1512 ከዘአበ ተሠርቶ ሲያልቅ ‘የእግዚአብሔር ክብር ማደሪያውን’ ሞላው። ይህ ተንቀሳቃሽ ድንኳን ከ4 መቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ሆኖ ቆይቷል። (ከጊዜ በኋላ ዳዊት በኢየሩሳሌም ሲነግሥ ለይሖዋ ክብር ቋሚ የሆነ ቤት የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ። ይሁን እንጂ ዳዊት የጦር ሰው ስለነበር ይሖዋ “ለስሜ ቤት አትሠራም” አለው። በሱ ፈንታ ልጁ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን እንዲሠራ ተመረጠ። (1 ዜና መዋዕል 22:6-10) ሰሎሞን 7 ዓመት ተኩል ከፈጀ የግንባታ ሥራ በኋላ በ1026 ከዘአበ ቤተ መቅደሱን አስመረቀ። ይሖዋም “ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ” በማለት ሕንጻውን እንደተቀበለው ገለጸ። (1 ነገሥት 9:3) ይሖዋ ሞገሱን በቤቱ ላይ የሚያደርገው እስራኤላውያን ታማኝ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ ብቻ ነው። ትክክል የሆነውን ማድረጋቸውን ካቆሙ ግን ሞገሱን ከቤቱ ላይ ያነሳል። ቤቱም “ባድማ ይሆናል።”—1 ነገሥት 9:4-9፤ 2 ዜና መዋዕል 7:16, 19, 20
ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ከእውነተኛው አምልኮ ዘወር አሉ። (2 ነገሥት 21:1-5) “ስለዚህም [ይሖዋ] የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እነርሱም . . . የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፣ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፣ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፣ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ። ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ።” በቅዱስ ጽሑፉ ዘገባ መሠረት ይህ የሆነው በ607 ከዘአበ ነው።—2 ዜና መዋዕል 36:15-21፤ ኤርምያስ 52:12-14
በነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት አይሁዳውያኑን ከባቢሎን ነጻ ለማውጣት አምላክ የፋርሱን ንጉሥ ቂሮስን አስነሳ። (ኢሳይያስ 45:1) የ70 ዓመቱ ግዞት እንዳበቃ ማለትም በ537 ከዘአበ አይሁዳውያኑ ቤተ መቅደሱን መልሰው ለመገንባት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። (ዕዝራ 1:1-6፤ 2:1, 2፤ ኤርምያስ 29:10) ሥራው ለጥቂት ጊዜ ተጓትቶ የነበረ ቢሆንም በ515 ከዘአበ ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ በመጠናቀቁ የአምላክ ንጹህ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ። ቤተ መቅደሱ ሰሎሞን እንደሠራው ዓይነት ክብራማ ባይሆንም ወደ 600 ለሚጠጉ ዓመታት አገልግሏል። ሆኖም እስራኤላውያን የይሖዋን አምልኮ ቸል በማለታቸው ይኸኛውም ቤተ መቅደስ ቢሆን ለረጅም ጊዜ እድሳት ሳይደረግለት ቆይቶ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ቤተ መቅደሱ በንጉሥ ሄሮድስ ከፍተኛ እድሳት እየተደረገለት ነበር። የዚህኛው ቤተ መቅደስ ዕጣስ ምን ይሆን?
“ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም”
ኢየሱስ ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:1, 2) የአይሁዳውያኑን ዓመፅ ለማስቆም የመጣው የሮም ሠራዊት ለብዙ ዘመናት የአምላክ አምልኮ ማዕከል በመሆን ያገለገለውን ይህን ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ እንዳልነበረ ባደረገው ጊዜ እነዚህ ቃላት ፍጻሜአቸውን አግኝተዋል። a ይህ ቤተ መቅደስ ዳግም አልተገነባም። በ7ኛው መቶ ዘመን ዶም ኦቭ ዘ ሮክ በመባል የሚታወቀው የሙስሊሞች ቤተ መቅደስ በቦታው ላይ የተሠራ ሲሆን ይህ ቤተ መቅደስ ዛሬም በቀድሞው የአይሁዳውያን የአምልኮ ቦታ ላይ ቆሞ ይገኛል።
የአምልኮ ቦታን በተመለከተ ለኢየሱስ ተከታዮች ምን ዓይነት ዝግጅት ተደርጎላቸው ይሆን? የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች መጥፊያው በተቃረበው ቤተ መቅደስ ውስጥ ማምለካቸውን ይቀጥሉ ይሆን? አይሁዳውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖችስ አምላክን የት ሆነው ያመልኩት ይሆን? የዛሬዎቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች ለጠፋው ቤተ መቅደስ ምትክ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉን? ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ያደረገው ውይይት ስለዚህ ነጥብ ተጨማሪ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል።
ለብዙ መቶ ዓመታት ሳምራውያን አምላክን ሰማሪያ በሚገኝ ተራራ ላይ በተሠራ ትልቅ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያመልኩት ቆይተዋል። ሳምራዊቷ ኢየሱስን “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም:- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው።” ኢየሱስም “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፣ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” በማለት መለሰላት። ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” በማለት ለይሖዋ አምልኮ በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ የማያስፈልግበት ጊዜ እንደሚመጣ ገልጿል። (ዮሐንስ 4:20, 21, 24) ሐዋርያው ጳውሎስ ቆየት ብሎ “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም” በማለት ለአቴና ሰዎች ነግሯቸዋል።—ሥራ 17:24
ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች በቅድመ ክርስትና ዘመን ከነበረው የቤተ መቅደስ ዝግጅት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የላቸውም። እንዲሁም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንደነዚህ ዓይነቶቹን ሕንጻዎች የሚሠሩበት አንዳችም ምክንያት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ አስቀድሞ የተነገረው ክህደት ብቅ አለ። (ሥራ 20:29, 30) ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በ313 እዘአ ወደ ክርስትና ከመለወጡ ብዙ ዘመናት አስቀድሞ ክርስቲያን ነን ባዮች ኢየሱስ ካስተማረው ትምህርት ማፈንገጥ ጀምረው ነበር።
ቆስጠንጢኖስ “ክርስትናን” ከአረማዊው የሮማውያን ሃይማኖት ጋር በመቀላቀል ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ዮሐንስ የተባሉ ሦስት ታላላቅ ቤተ ክርስቲያኖች ሮም ውስጥ እንዲሠሩ ትእዛዝ ያስተላለፈው ቆስጠንጢኖስ ራሱ ነው። . . . ቆስጠንጢኖስ በመካከለኛው መቶ ዘመን በምዕራብ አውሮፓ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመሥፈርትነት ያገለገለውን የመስቀል ቅርጽ ያለው ንድፍ ፈጥሯል።” ሮም የሚገኘውና ዳግም የተገነባው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ማዕከል ተደርጎ ይታያል።
ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “ቤተ ክርስቲያን አረማዊ አምልኮ ከነበራት ከሮም አንዳንድ ልማዶችንና አምልኮዎችን ወርሳለች” በማለት ጽፈዋል። ይህም “የቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ ንድፍ” ይጨምራል። ከ10ኛው እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የአብያተ ክርስቲያናትና የካቴድራሎች ግንባታ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን ለሕንፃው ንድፍ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ነበር። በዛሬው ጊዜ ድንቅ የታሪክ ቅርስ ተደርገው የሚታዩት በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች የተሠሩት በዚህ ጊዜ ነው።
ሰዎች ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ማነቃቂያና ማበረታቻ ያገኛሉ? በብራዚል የሚኖረው ፍራንሲስኮ “ለእኔ ቤተ ክርስቲያን ማለት አሰልቺና አድካሚ ቦታ ነው” በማለት ተናግሯል። “የቅዳሴ ሥርዓት መንፈሳዊ ፍላጎቴን የማያረካ፣ ትርጉም የለሽና ተደጋጋሚ ክንውን ነው። ሥነ ሥርዓቱ ሲያልቅ እንደተገላገልኩ ሆኖ ይሰማኛል።” የሆነ ሆኖ እውነተኛ አምላኪዎች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ታዝዘዋል። ታዲያ የሚሰበሰቡት የት ነው?
“በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን”
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የት ይሰበሰቡ እንደነበር በመመርመር በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ክርስቲያኖች የት መሰብሰብ እንዳለባቸው ማወቅ ይቻላል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት አብዛኛውን ጊዜ በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ . . . በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።” (ሮሜ 16:3, 5፤ ቆላስይስ 4:15፤ ፊልሞና 2) እዚህ ላይ “ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ የተተረጎመው ኤክሊሲያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ሲሆን ቃሉ የሚያመለክተው ለአንድ አላማ የተሰበሰቡ ሰዎችን እንጂ አንድን የተወሰነ ሕንጻ አይደለም። (ሥራ 8:1፤ 13:1) እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምልኮ የተንቆጠቆጡ ሃይማኖታዊ ሕንጻዎችን መጠቀም አያስፈልጋቸውም።
የጥንት ክርስቲያኖች ስብሰባዎቻቸውን የሚያካሂዱት እንዴት ነበር? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የክርስቲያኖችን ስብሰባ ለማመልከት ጉባኤ ተብሎ የተተረጎመውን ሲናጎገን [ምኩራብ] የሚል ግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። (ያዕቆብ 2:2 አ.መ.ት (ትልቁ) የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) ይህ ግሪክኛ ቃል “መሰብሰብ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ኤክሊሲያ (ጉባኤ) ከሚለው ቃል ጋር በተወራራሽነት ይሠራበታል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ምኩራብ የሚለው ቃል ስብሰባ የሚካሄድበትን ቦታ ወይም ሕንጻ ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። በምኩራብ የሚካሄደው ነገር ለመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንግዳ አልነበረም። b
አይሁዳውያን ዓመታዊውን በዓላቸውን ለማክበር ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚሰበሰቡ ሲሆን ምኩራቦች ደግሞ ሕዝቡን እዚያው በያለበት ስለ ይሖዋና ስለ ሕጉ ለማስተማር ያገለግሉ ነበር። ምኩራብ ውስጥ ይከናወኑ ከነበሩት ነገሮች መካከል ጸሎት፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ንባብና ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ይገኙበታል። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎችን መሠረት ያደረጉ ምክሮችና ማሳሰቢያዎች ይሰጡ ነበር። ጳውሎስና ሌሎች ወንድሞች አንጾኪያ ወደሚገኘው ምኩራብ በሄዱ ጊዜ “የምኩራቡ አለቆች:- ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው።” (ሥራ 13:15) የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ የነበረ ሲሆን ስብሰባዎቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ የሚገኝባቸውና በመንፈሳዊ የሚያንጹ እንዲሆኑ ለማድረግ ተመሳሳይ መንገድ እንደተከተሉ ምንም አያጠራጥርም።
ለመበረታታት የሚያገለግሉ ጉባኤዎች
እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማርና እርስ በእርስ ለመተናነጽ የሚሰበሰቡባቸው የአምልኮ ቦታዎች የተንቆጠቆጡ አይደሉም። ለብዙ ዓመታት በግል ቤቶች ውስጥ ስብሰባዎቻቸውን ያከናወኑ ሲሆን አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች እንዲሁ ይደረጋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የጉባኤዎች ቁጥር አድጎ ከ90, 000 በላይ የደረሰ ሲሆን ዋነኛው የመሰብሰቢያ ቦታቸው የመንግሥት አዳራሽ በመባል ይታወቃል። እነዚህ ሕንጻዎች በጌጥ የተንቆጠቆጡ ወይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ዓይነት አሠራር ያላቸው አይደሉም። በየሳምንቱ የአምላክን ቃል ለማዳመጥና ለመማር የሚመጡትን ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች ሊይዙ የሚችሉና ልከኛ በሆነ መንገድ የተሠሩ ናቸው።
አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በሳምንት ሦስት ጊዜ ይሰበሰባሉ። አንደኛው ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የሕዝብ ንግግር ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ በአንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጭብጥ ወይም ትንቢት ላይ ያተኮረ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ይጠናል። ሌላው ስብሰባ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሌሎች ለማስተማር የሚያስችል ሥልጠና የሚገኝበት ትምህርት ቤት ነው። ከዚህ ቀጥሎ በተለይ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚሆኑ ተግባራዊ ሐሳቦች የሚቀርቡበት ስብሰባ ይከተላል። በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ በትንንሽ ቡድኖች ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰባሉ። ሁሉም ስብሰባዎች ለሕዝብ ክፍት ናቸው። ምንም ዓይነት ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም።
አስቀድሞ የተጠቀሰው ፍራንሲስኮ በመንግሥት አዳራሽ የሚደረጉት ስብሰባዎች በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ ይሰማዋል። እንዲህ ይላል:- “ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁበት የመሰብሰቢያ ቦታ በመሃል ከተማ የሚገኝ ምቹ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን ከአዳራሹ የወጣሁት ተደስቼ ነበር። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ወዳጃዊ ስሜት ያሳያሉ። በመካከላቸው ፍቅር መኖሩን ተገንዝቤአለሁ። ተመልሼ እስከምሄድ ድረስ በጣም ቸኩዬ ነበር። እንዲያውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድም ስብሰባ አምልጦኝ አያውቅም። እነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መንፈስን የሚያነቃቁ ናቸው። መንፈሳዊ ፍላጎቴንም አርክተውልኛል። በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሣ ባዝንና ብተክዝም እንኳ ተበረታትቼ እንደምመለስ ስለማውቅ ወደ መንግሥት አዳራሽ እሄዳለሁ።”
የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከተገኘህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የማግኘት፣ የሚያንጽ ወዳጅነት የመመሥረትና አምላክን የማወደስ አጋጣሚም አለህ። ለቤትህ ቅርብ ወደሆነው የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ በዚያ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። እንዲህ በማድረግህ አትጸጸትም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቤተ መቅደሱ በሮማውያን አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል። ብዙ አይሁዳውያን ለመጸለይ ሲሉ ከሩቅ ቦታ የሚመጡበት ዌይሊንግ ዎል የተባለው ግንብ የዚያ ቤተ መቅደስ ክፍል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የቤተ መቅደሱ አደባባይ የታጠረበት ግምብ ነው።
b በምኩራቦች መሰብሰብ የተጀመረው ቤተ መቅደስ ባልነበረበት በ70 ዓመቱ የባቢሎን ግዞት ወቅት ወይም ከግዞት መልስ ቤተ መቅደሱ እንደገና በመገንባት ላይ በነበረበት ወቅት ይመስላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እያንዳንዱ የጳለስጢና ከተማ የራሱ የሆነ ምኩራብ የነበረው ሲሆን ትልልቆቹ ከተሞች ደግሞ ከአንድ በላይ ምኩራቦች ነበሯቸው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀደም ሲል የመገናኛው ድንኳን ከዚያም ቤተ መቅደሱ ይሖዋ የሚመለክበት ማዕከል ሆነው አገልግለዋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮም የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች በግል ቤቶችና በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ