በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገ ተጋድሎ

መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገ ተጋድሎ

መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገ ተጋድሎ

ነፃ አስተሳሰብ የማራመድ ባሕል የፈለቀባት ምድር እንደሆነች በሚነገርላት በግሪክ መጽሐፍ ቅዱስን አብዛኛው ሕዝብ ወደሚግባባበት ግሪክኛ ለመተርጎም ረዥምና ከባድ ትግል ማድረግ አስፈልጎ እንደነበር ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ማንኛውም ሰው በቀላሉ በሚረዳው ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገውን ጥረት የተቃወመው ማን ነበር? ለምንስ?

አንድ ሰው በርከት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያ በግሪክኛ ስለተጻፈ ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች የታደሉ ናቸው ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘመናዊው ግሪክኛ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሴፕቱጀንት ትርጉምም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከተዘጋጁበት ግሪክኛ በእጅጉ የተለየ ነው። እንዲያውም ላለፉት ስድስት መቶ ዓመታት ግሪክኛ ተናጋሪ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ግሪክኛ ከባዕድ ቋንቋ ለይተው አያዩትም ነበር። ጥንት ይሠራባቸው የነበሩ ቃላት በአዳዲስ የተተኩ ሲሆን የሰዋሰው አገባቡና የዓረፍተ ነገር አሰካኩ ከጥንቱ የተለየ ነው።

ከ3ኛው እስከ 16ኛው መቶ ዘመን ከተዘጋጁ አንዳንድ የግሪክኛ ቅጂዎች መረዳት እንደሚቻለው ሴፕቱጀንት በመባል የሚታወቀውን ትርጉም ይበልጥ ዘመናዊ ወደሆነ ግሪክኛ ለመተርጎም ጥረት ተደርጎ ነበር። በሦስተኛው መቶ ዘመን፣ የአዲሷ ቂሳርያ ጳጳስ የነበረው ግሪጎሪ (ከ213 እዘአ ገደማ-270 እዘአ ገደማ) ከሴፕቱጀንት ላይ የመክብብን መጽሐፍ ቀለል ባለ ግሪክኛ ተርጉሞ ነበር። በመቄዶንያ ይኖር የነበረ ጦቢያስ ቤን ኤሊኤዘር የተባለ አንድ አይሁዳዊ በ11ኛው መቶ ዘመን ከሴፕቱጀንት ትርጉም ላይ የኦሪት መጽሐፎችን በከፊል ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊረዳው በሚችል ግሪክኛ ተርጉሟል። እንዲያውም ይህ ሰው ከግሪክኛ በስተቀር ሌላ ቋንቋ መናገር የማይችሉ ሆኖም የዕብራይስጥ ፊደላትን ማንበብ የሚችሉ የመቄዶንያ አይሁዳውያንን ለመጥቀም ሲል በዕብራይስጥ ፊደላት ተጠቅሟል። አምስቱም የኦሪት መጽሐፎች በ1547 ቁስጥንጥንያ ውስጥ በዚህ መልክ ታትመዋል።

በጨለማ ውስጥ ጭላንጭል ታየ

በባይዛንታይን ግዛት ግሪክኛ ተናጋሪ የነበሩ አካባቢዎች በ15ኛው መቶ ዘመን በኦቶማን ቱርክ ቁጥጥር ሥር ከወደቁ በኋላ በዚያ የሚኖረው አብዛኛው ሕዝብ ትምህርት ተጠምቶ ነበር። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኦቶማን አገዛዝ ውስጥ ተደማጭነት የነበራት ቢሆንም ጭሰኛው ምዕመን ከድህነትና ከመሃይምነት እንዲላቀቅ የወሰደችው እርምጃ አልነበረም። ቶማስ ስፔሊዮስ የተባሉ ግሪካዊ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ትኩረትና የሥርዓተ ትምህርቷ ዋነኛ ዓላማ ምዕመናኖቿን እስልምናና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሚያሰራጩት ፕሮፓጋንዳ መጠበቅ ነበር። በዚህም ምክንያት የግሪክ ትምህርት ባለበት የቆመ ያህል ሆኖ ነበር።” በወቅቱ እንዲህ ያለ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ቢሰፍንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ያላቸው ሰዎች ለሕዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ መጽናኛ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ከ1543 እስከ 1835 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከመዝሙር መጽሐፍ ሕዝቡ በሚጠቀምበት ግሪክኛ 18 ጊዜ ተተርጉሟል።

የካሊፖሊስ መነኩሴ የሆነው ማክሲመስ ካሊፖሊቲስ የተባለ ግሪካዊ በ1630 የመጀመሪያውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም አዘጋጀ። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የለውጥ አራማጅ እንደሆነ በሚነገርለት በሲረል ሉካረስ አመራርና ድጋፍ ነበር። ይሁን እንጂ ሉካረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተቃዋሚዎች የነበሩት ሲሆን እነዚህ ሰዎች ምንም ዓይነት የተሃድሶ ለውጥ እንዲደረግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ተራው ሰው በሚግባባበት ግሪክኛ እንዲተረጎም አይፈልጉም ነበር። a ከሃዲ ነው ብለው አንቀው ገደሉት። የሆነ ሆኖ በ1638 የማክሲመስ ትርጉም በ1, 500 ገደማ ቅጂዎች ታተመ። ከ34 ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌም የሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖድ መጽሐፍ ቅዱስን “ማንበብ የሚገባቸው አስፈላጊውን ምርምር አድርገው ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን ማስተዋል የሚችሉ ሰዎች እንጂ ማንም ተራ ሰው ማንበብ አይገባውም” የሚል ድንጋጌ በማውጣት ለዚህ የትርጉም ሥራ ያለውን ተቃውሞ ገለጸ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለባቸው የተማሩ ቀሳውስት ብቻ ናቸው ከማለት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

ከሌዝቮስ ደሴት የመጣ ሴራፊም የተባለ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ መነኩሴ በ1703 ለንደን ውስጥ የማክሲመስን ትርጉም አሻሽሎ ለማሳተም ሙከራ አድርጎ ነበር። ከእንግሊዝ መንግሥት ቃል የተገባለትን የገንዘብ እርዳታ ማግኘት ስላልቻለ አሻሽሎ ያዘጋጀውን ትርጉም በራሱ ወጪ አሳተመ። ሴራፊም ኃይለኛ መልእክት ባዘለው መቅድሙ ላይ “ማንኛውም ለአምላክ ያደረ ክርስቲያን” መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደሚኖርበት ጠበቅ አድርጎ ከመግለጹም በላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የያዙት ቀሳውስት “ሕዝቡን በድንቁርና በማሰር ክፉ ምግባራቸው እንዳይታወቅባቸው ጥረት እንደሚያደርጉ” አጋልጧል። እንደተጠበቀው ሁሉ ተቃዋሚዎቹ ሩሲያ ውስጥ ካስያዙት በኋላ በ1735 እስከሞተበት ዕለት ድረስ ሳይቤርያ ውስጥ በግዞት እንዲኖር አድርገውታል።

አንድ የግሪክ ቄስ ከጊዜ በኋላ ተሻሽሎ የወጣውን የማክሲመስ ትርጉም አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ላይ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆነው ሕዝብ በወቅቱ የደረሰበትን መንፈሳዊ ጠኔ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ግሪካውያንም ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ተቀብለው ያነበቡት በከፍተኛ ጉጉትና ስሜት ነበር። በዚህም ምክንያት ከውስጥ ይሰማቸው የነበረው ሥቃይ ጋብ ሲልና በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት . . . ሲጠናከር ተሰማቸው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ መሪዎቻቸው ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብብ ከሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነው የቀሳውስቱ ትምህርትና ድርጊት ይጋለጣል የሚል ፍርሐት ያዛቸው። ስለሆነም የቁስጥንጥንያው የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት በመጀመሪያ በ1823 ከዚያም በ1836 እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተሰብስበው እንዲቃጠሉ ደነገገ።

ደፋር ተርጓሚ

እንዲህ ዓይነት ከባድ ተቃውሞም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት ልባዊ ፍላጎት በታየበት በዚያ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ዘመናዊ ግሪክኛ በመተርጎም ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወት አንድ ታላቅ ሰው ብቅ አለ። ይህ ደፋር ሰው ኒዮፊጦስ ቫምቫስ ነው። ቫምቫስ በቋንቋ ችሎታው የተካነ፣ ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁርና “አገሪቱ አሉኝ ከምትላቸው አስተማሪዎች” መካከል አንዱ ነበር።

ቫምቫስ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ድንቁርና ተወቃሽዋ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ያምን ነበር። ሕዝቡን ከመንፈሳዊ እንቅልፍ ለማንቃት መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ ይነገር ወደ ነበረው ግሪክኛ መተርጎም አለበት የሚል ጠንካራ እምነት ነበረው። ቫምቫስ በ1831 በሌሎች ምሁራን እርዳታ በዘመኑ የነበረውን የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን በግሪክኛ መተርጎም ጀመረ። የትርጉም ሥራው ተጠናቅቆ በ1850 ታተመ። ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ድጋፍ ማግኘት ስላልቻለ የትርጉም ሥራውን ማሳተምና ማሰራጨት የሚችልበትን ሁኔታ በተመለከተ ከብሪታንያና ከባሕር ማዶ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር ተባብሮ ሠርቷል። ቤተ ክርስቲያኒቱ “ተቃዋሚ” የሚል ስም ያወጣችለት ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ሕብረተሰቡ አገለለው።

የቫምቫስ ትርጉም የኪንግ ጄምስ ትርጉምን በጥብቅ የተከተለ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስና የቋንቋ እውቀት ውስንነት ምክንያት በኪንግ ጄምስ ትርጉም ላይ የታየው ስህተት በዚህም ትርጉም ላይ ተንጸባርቋል። ሆኖም ሕዝቡ ለብዙ ዓመታት የተጠቀመበት ይበልጥ ዘመናዊ የሆነው የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ነበር። በጣም ደስ የሚለው የአምላክ የግል ስም አራት ቦታዎች ላይ “ኢኦቫ” ተብሎ ተቀምጧል።​—⁠ዘፍጥረት 22:​14፤ ዘጸአት 6:​3፤ 17:​15፤ መሳፍንት 6:​24

ሕዝቡ ለዚህና በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችል መንገድ ለተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያደረበት ስሜት ምን ነበር? በአጭሩ ሕዝቡ በጣም ተደስቶ ነበር! ከአንዲት የግሪክ ደሴት ተነስቶ በጀልባ ጉዞ የጀመረ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሻጭ “[መጽሐፍ ቅዱስ] ፍለጋ የመጡ ብዙ ሕፃናትን የጫኑ በርካታ ጀልባዎች ወደ እነርሱ ሲመጡ ተመለከተ።” ሻጩ የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቦታ ላይ እንዳይጨርስ ስለፈራ “ጀልባዋን እንዳያቆም ካፒቴኑን ለማዘዝ ተገድዶ ነበር።” ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም።

የኦርቶዶክስ ቀሳውስት ሕዝቡ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዳይገዛ ከማስጠንቀቅ ወደኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል አቴንስ ከተማ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይወረስ ነበር። በ1833 በቀርጤስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በአንድ ገዳም ውስጥ “የአዲስ ኪዳን” መጽሐፍ ቅዱሶችን አግኝቶ አቃጥሏቸዋል። አንድ ቄስ አንድ የአዲስ ኪዳን ቅጂ የደበቀ ሲሆን በአቅራቢያው ባሉ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ጳጳሱ ደሴቲቱን ለቅቆ እስኪሄድ ድረስ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ለመደበቅ ተገድደዋል።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኮርፉ በተባለች ደሴት ላይ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖድ በቫምቫስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ እገዳ ጣለ። ይህ ትርጉም እንዳይሸጥ ከመከልከሉም በላይ ታትመው የነበሩ ቅጂዎችም እንዲቃጠሉ ተደርጓል። በቺዮስ፣ በሲሮስና በሚይኮኖስ ደሴቶች ላይ ቀሳውስት ከተቃውሟቸው የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን እስከማቃጠል ደርሰዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ በዚህ አላበቃም።

አንዲት ንግሥት መጽሐፍ ቅዱስን ለማሳተም ያደረገችው ጥረት

በ1870ዎቹ ኦልጋ የምትባል አንዲት የግሪክ ንግሥት ሕዝቡ በአጠቃላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው እውቀት ውስን እንደሆነ ተገነዘበች። ሕዝቡ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ቢኖረው መጽናናትና እርካታ እንደሚያገኝ በማመን ከቫምቫስ ትርጉም ይበልጥ ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲዘጋጅ ጥረት ማድረግ ጀመረች።

የአቴንስ ሊቀ ጳጳሳትና የቅዱስ ሲኖዶሱ መሪ የነበሩት ፕሮኮፒዮስ በግል ቀርበው ንግሥቲቱን ስለ ጥረትዋ በማመስገን አበረታቷት። ቅዱስ ሲኖዶሱ ፈቃድ እንዲሰጣት በጠየቀች ጊዜ ግን እንዳሰበችው ሊሆንላት አልቻለም። የሆነ ሆኖ ተስፋ ሳትቆርጥ በ1899 አዲስ ማመልከቻ አስገባች። በዚህ ጊዜም ምላሹ ያው ነበር። ፈቃድ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በመተው መጠነኛ ብዛት ያላቸውን ቅጂዎች በራስዋ ወጪ ለማሳተም ወሰነች። ይህ የሆነው በ1900 ነበር።

በቀላሉ እጅ የማይሰጡ ተቃዋሚዎች

በ1901፣ አሌክሳንደር ፓሊስ የሚባል አንድ ተርጓሚ እንግሊዝ ሊቨርፑል ውስጥ በዘመናዊ ግሪክኛ የተረጎመው የማቴዎስ ወንጌል ዚ አክሮፖሊስ በተባለ አንድ ታዋቂ የአቴንስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጣ። ፓሊስ እና ባልደረቦቹ ይህን ያደረጉት ‘ግሪካውያንን ለማስተማር’ እና “አገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ” ነበር።

የኦርቶዶክስ ቲኦሎጂ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው “የአገሪቱን ንዋየ ቅዱሳት እንደ ማቃለል” እና መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማራከስ ይቆጠራል በማለት ለትርጉም ሥራው ያላቸውን ስሜት ገልጸዋል። የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ ሳልሳዊ ኢዮአኪም ደግሞ ይህን ትርጉም በመቃወም አንድ ጽሑፍ አውጥተዋል። ውዝግቡ ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መጥቶ እርስ በርስ የሚናቆሩ የተለያዩ የፖለቲካ አንጃዎች ዓላማቸውን ለማሳካት ያለ አግባብ ተጠቀሙበት።

በአቴንስ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ተደማጭነት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች የፓሊስን ትርጉም የሚደግፉ ሰዎችን “አምላክ የለሾች፣” “ከሐዲዎች” እና በግሪክ ማኅበረሰብ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር ቆርጠው የተነሱ “ባንዳዎች” ብለው በመጥራት ትርጉሙን ማጣጣል ጀመሩ። በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ አንዳንድ አክራሪ ቡድኖች ቆስቋሽነት ተማሪዎች ከኅዳር 5 እስከ 8, 1901 አቴንስ ከተማ ውስጥ ረብሻ አነሱ። ተማሪዎቹ ዚ አክሮፖሊስ በተባለው ጋዜጣ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸውም በላይ ወደ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ ቁጣቸውን ገለጹ። በተጨማሪም የአቴንስን ዩኒቨርሲቲ በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅቅ ጠየቁ። ረብሸኞቹ ከጦር ሠራዊቱ ጋር በፈጠሩት ግጭት ስምንት ሰዎች ተገደሉ። በማግሥቱም ንጉሡ ሊቀ ጳጳስ ፕሮኮፒዮስ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን ከሁለት ቀናት በኋላ መላው ካቢኔ ተበተነ።

ተማሪዎቹ ከአንድ ወር በኋላ እንደገና የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የፓሊስን ትርጉም አንድ ቅጂ በአደባባይ አቃጠሉ። ትርጉሙ እንዳይሰራጭና ይህን ሲያደርግ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከባድ ቅጣት እንዲወሰንበት የሚጠይቅ የአቋም መግለጫ አወጡ። መንግሥት ይህን እንደ ምክንያት አድርጎ በማቅረብ ማንም ሰው በዘመናዊ ግሪክኛ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳያነብ የሚከለክል ደንብ አወጣ። በእርግጥም ጨለማ የዋጠው ዘመን ነበር!

‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም ይኖራል’

በዘመናዊ ግሪክኛ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያግደው ውሳኔ የተሻረው በ1924 ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቡ እጅ እንዳይገባ ጥረት ብታደርግም ሙሉ በሙሉ ሽንፈት ተከናንባለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች ብዙ አገሮች ውስጥ እንደሚያደርጉት በግሪክም መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ረገድ ግምባር ቀደም ሆነዋል። ከ1905 ጀምሮ በቫምቫስ ትርጉም ተጠቅመው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ግሪክኛ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲያገኙ ረድተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ምሁራንና ፕሮፌሰሮች መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የሚያስመሰግን ጥረት አድርገዋል። ዛሬ ማንኛውም ግሪካዊ በቀላሉ የሚረዳቸው 30 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ16 ሚልዮን በላይ ግሪክኛ ተናጋሪዎችን ለመጥቀም በ1997 ታትሞ የወጣው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ነው። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ ትርጉም የአምላክን ቃል ለማንበብ ቀላል በሆነና ለመረዳት በማያስቸግር መንገድ ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ የጥንቱን ቅጂ በጥብቅ ይከተላል።

መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገው ይህ ትግል አንድ ሐቅ ያስገነዝበናል። ሰው በጥላቻ ተነሳስቶ ቃሉን ለማጥፋት ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግም ‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም እንደሚኖር’ በግልጽ ያሳያል።​—⁠1 ጴጥሮስ 1:​25

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ ሲረል ሉካረስ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የካቲት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-9⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሲረል ሉካረስ በ1630 ሙሉው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግሪክኛ እንዲተረጎም አድርጓል

[ምንጭ]

Bib. Publ. Univ. de Genève

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወቅቱ ይነገር በነበረው ግሪክኛ የተዘጋጁ አንዳንድ ትርጉሞች:- መዝሙረ ዳዊት (1) በ1828 የታተመው የኢላሪየን ትርጉም፣ (2)  በ1832 የታተመው የቫምቫስ ትርጉም፣ (3) በ1643 የታተመው የጁሊያኑስ ትርጉም። “ብሉይ ኪዳን” (4) በ1840 የታተመው የቫምቫስ ትርጉም

ንግሥት ኦልጋ

[ምንጭ]

መጽሐፍ ቅዱሶች:- National Library of Greece; ንግሥት ኦልጋ:- Culver Pictures

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፓፒረስ:- Reproduced by kind permission of The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፓፒረስ:- Reproduced by kind permission of The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin