‘የአምላክን መንጋ ጠብቁ’
“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”
‘የአምላክን መንጋ ጠብቁ’
“ዘወትር እኛን ለማዳመጥና መንፈሳችንን የሚያነቃቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመለገስ ዝግጁ ናችሁ።”—ፓሜላ
“እኛን ለመርዳት ለምታደርጉት ጥረት ከልብ እናመሰግናችኋለን። የእናንተ እርዳታ በእርግጥ ያስፈልገናል።”—ሮበርት
ፓሜላ እና ሮበርት ከላይ ያሉትን የአድናቆት ቃላት የጻፉት በየጉባኤያቸው ለሚገኙት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም ‘የአምላክን መንጋ የሚጠብቁት’ ሽማግሌዎች ለሚያደርጉላቸው ያልተቋረጠ ድጋፍና እንክብካቤ አመስጋኞች ናቸው። (1 ጴጥሮስ 5:2) በእርግጥም የይሖዋ ሕዝቦች ሽማግሌዎች የሚያደርጉላቸውን በርካታ ነገሮችና ይህንንም የሚያከናውኑበትን መንገድ ያደንቃሉ።
‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’
ክርስቲያን ሽማግሌዎች በርካታ ኃላፊነቶች አሏቸው። (ሉቃስ 12:48) ለጉባኤ ስብሰባዎች ንግግሮችን ይዘጋጃሉ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመመሥከሩ ሥራ ይካፈላሉ። ኃላፊነታቸው ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እረኝነት ማድረግንም ይጨምራል። ሽማግሌዎች የራሳቸውን ቤተሰብ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍላጎቶች ችላ ሳይሉ በዕድሜ የገፉትንና ሌሎች ለየት ያለ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውንም ይጠይቃሉ። (ኢዮብ 29:12-15፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5፤ 5:8) አንዳንድ ሽማግሌዎች በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ድጋፍ ይሰጣሉ። ሌሎች ደግሞ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ወይም በሕሙማን ጎብኚ ቡድኖች ውስጥ ይሠራሉ። እንዲሁም አብዛኞቹ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በፈቃደኝነት ያገለግላሉ። አዎን፣ ሽማግሌዎች ‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:58) የመንጋው አባላት ለእነዚህ ብዙ የሚደክሙ ሽማግሌዎች አድናቆታቸውን መግለጻቸው ምንም አያስገርምም!—1 ተሰሎንቄ 5:12, 13
ቤታቸው በመሄድም ይሁን በሌሎች ቦታዎች አዘውትረው በመጎብኘት የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መንፈሳዊነት ለመገንባት የሚጥሩ ሽማግሌዎች የብርታት ምንጭ ናቸው። አባት በሌለበት ቤት ውስጥ ያደገው ቶማስ “ሽማግሌዎች በፍቅር እገዛ ባያደርጉልኝና ባያበረታቱኝ ኖሮ ዛሬ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል መቻሌን እጠራጠራለሁ” ብሏል። በነጠላ ወላጅ ያደጉ ብዙ ወጣቶች የሽማግሌዎች የቅርብ ክትትል ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ለማዳበር እንደረዳቸው ይናገራሉ።
በጉባኤ ውስጥ ያሉ አረጋውያንም የሚደረግላቸውን እረኝነት ከልብ ያደንቃሉ። በ80ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ሁለት ሽማግሌዎች ከጎበኟቸው በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ላደረጋችሁልን አስደሳች ጉብኝት አድናቆታችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
ያነበባችሁልንን ጥቅሶች እናንተ ከሄዳችሁ በኋላ እንደገና አነበብናቸው። የሰጣችሁንን ማበረታቻ ፈጽሞ አንረሳውም።” አንዲት የ70 ዓመት መበለት ለሽማግሌዎች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይሖዋ እንዲረዳኝ እየጸለይኩ ነበር፤ እሱም እናንተን ሁለታችሁን ላከልኝ። ያደረጋችሁልኝ ጉብኝት ከይሖዋ የመጣ በረከት ነው!” በጉባኤህ የሚገኙ ሽማግሌዎች በቅርቡ ጎብኝተውሃል? መንጋውን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያደርጉትን ጥረት ሁላችንም ከልብ እንደምናደንቅ ጥርጥር የለውም!የአምላክንና የክርስቶስን ምሳሌ የሚከተሉ እረኞች
ይሖዋ አፍቃሪ እረኛ ነው። (መዝሙር 23:1-4፤ ኤርምያስ 31:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:25) ኢየሱስ ክርስቶስም ድንቅ መንፈሳዊ እረኛ ነው። እንዲያውም “መልካም እረኛ፣” “ትልቅ እረኛ” እና “የእረኞች አለቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 10:11፤ ዕብራውያን 13:20፤ 1 ጴጥሮስ 5:4) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሊሆኑ የሚፈልጉ ሰዎችን የተቀበላቸው እንዴት ነበር? “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” የሚለውን ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።—ማቴዎስ 11:28
ዛሬ ያሉት ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ለመንጋው የእረፍት ምንጭና ከለላ ለመሆን ይጥራሉ። “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ናቸው። (ኢሳይያስ 32:2) እንደነዚህ ያሉት ደግ እረኞች የእረፍት ምንጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የመንጋውን አክብሮት ያተርፋሉ እንዲሁም የአምላክን ሞገስ ያገኛሉ።—ፊልጵስዩስ 2:29፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:17
ሚስቶቻቸው የሚያደርጉላቸው ከፍተኛ ድጋፍ
የአምላክ ሕዝቦች ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለሚያደርጉላቸው እርዳታና እነዚህ ወንዶች ከሚስቶቻቸው ለሚያገኙት ፍቅራዊ ድጋፍ አመስጋኞች ናቸው። እነዚህ ሴቶች ለባሎቻቸው ድጋፍ ለመሆን በአብዛኛው መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቅባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ባሎቻቸው የጉባኤ ሥራዎችን ሲሠሩ ወይም እረኝነት ሲያደርጉ እነሱ ቤት ቁጭ ብለው ለመጠበቅ ይገደዳሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በጉባኤ ውስጥ አንድ አጣዳፊ ጉዳይ በመፈጠሩ ምክንያት ቀደም ብለው ያወጡትን የግል ፕሮግራማቸውን ማፍረስ ይኖርባቸዋል። ሚሼል “እንደዚያም ሆኖ ባለቤቴ ለስብሰባዎች በመዘጋጀት ወይም እረኝነት በማድረግ በሥራ ተወጥሮ ስመለከት የሚሠራው የይሖዋን ሥራ መሆኑን አስብና በተቻለኝ አቅም ለመደገፍ እጥራለሁ” ብላለች።
የጉባኤ ሽማግሌ ሚስት የሆነችው ሼረልም እንዲህ ትላለች:- “በጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ሽማግሌዎችን ማነጋገር እንደሚፈልጉ ስለማውቅ ባለቤቴን በፈለጉ ጊዜ ሁሉ ሊያገኙት እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ማድረግ እፈልጋለሁ።” እንደ ሚሼልና ሼረል ያሉ ደጋፊ የሆኑ ሴቶች ባሎቻቸው የአምላክን መንጋ እንዲንከባከቡ ሲሉ በፈቃደኝነት መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። የሽማግሌዎች ሚስቶች ለባሎቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ የሚደነቅ ነው።
ያም ሆኖ ግን አንድ ሥራ የሚበዛበት ሽማግሌ የሚስቱንና የልጆቹን መንፈሳዊም ሆነ ሌሎች ፍላጎቶች ቸል ማለት የለበትም። ባለትዳር የሆነ ሽማግሌ “ነቀፋ የሌለበት፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልጆቹም አማኞችና በመዳራት ወይም ባለመታዘዝ ስማቸው የማይነሣ” ሊሆን ይገባዋል። (ቲቶ 1:6 አ.መ.ት ) አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሊያሟላው ከሚገባው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት አንዱ ቤተሰቡን አምላካዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር ነው።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-7
አንድ ሥራ የሚበዛበት ሽማግሌ የምትደግፈው ሚስት ማግኘቱ ትልቅ ስጦታ ነው! አድናቂ የሆነ ባለትዳር ሽማግሌ ስለ ሚስቱ እንደዚህ እንደሚሰማው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ” ይላል። (ምሳሌ 18:22) እንደዚህ ዓይነት ሽማግሌዎች በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው ሚስቶቻቸውን ከልብ እንደሚያደንቁ ያሳያሉ። አንድ ላይ ሆነው ከልብ ከመጸለይና ከማጥናት በተጨማሪ እነዚህ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች አብረው የሚንሸራሸሩበትና የሚዝናኑበትም ጊዜ አላቸው። አዎን፣ ሽማግሌዎች ለሚስቶቻቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ በማድረግ ይደሰታሉ።—1 ጴጥሮስ 3:7
ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ የአምላክን መንጋ የሚንከባከቡ ሽማግሌዎች ለይሖዋ ሕዝቦች የእረፍት ምንጭ ናቸው። በእርግጥም እነዚህ ወንድሞች ለጉባኤው በረከት የሆኑ ‘ስጦታዎች’ [NW ] ናቸው!—ኤፌሶን 4:8, 11-13