የአምልኮ ቦታዎች ያስፈልጉናልን?
የአምልኮ ቦታዎች ያስፈልጉናልን?
‘ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡና በቀለማት ያሸበረቁ ልብሶች የለበሱ ህንዳውያን ተሳላሚዎች የከበሮውን ምት ተከትለው ጥንታዊውን ዳንስ ሲያሳዩ ቀናኢዎቹ ደግሞ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል እየተጋፉና በጉልበታቸው እየዳሁ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይና በዙሪያው ወዳሉት ጎዳናዎች ይጎርፋሉ።’
ኢል ኢኮኖሚስታ የተባለው ጋዜጣ ታኅሣሥ 2001 ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ ለአምልኮ የወጣውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የገለጸው በዚህ መልኩ ነበር። በዚያን ወቅት ወደ 3 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በጉዋዳሉፕዋ ድንግል ላይ ያላቸውን እምነት ለመግለጽ ሜክሲኮ ሲቲ ወደሚገኘው ግዙፍ ቤተ ክርስቲያን ጎርፈዋል። ሮም የሚገኘውን የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊ ሕንጻዎችም እጅግ ብዙ ተሳላሚዎች አሏቸው።
ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች አምላክን ለማምለክ በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ይሰጣቸዋል። በብራዚል የምትኖረው ማሪያ እንዲህ በማለት የሚሰማትን ገልጻለች:- “ቤተ ክርስቲያን ወደ አምላክ የምቀርብበት ቅዱስ ቦታ እንደሆነና ወደዚያ መሄድ ከኃጢአት ያነጻል ብዬ አምን ነበር። እሁድ እሁድ በቅዳሴና በኑዛዜ ሥነ ሥርዓት ላይ አለመገኘት ኃጢአት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።” በሜክሲኮ የምትኖረው ኮንሱዌሎ ደግሞ “ቤተ ክርስቲያን ስሄድ አንዳች ልዩ ስሜት ይሰማኛል። ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ግምት አለኝ። እዚያ ስሆን ሰማይ ቤት የገባሁ ይመስለኛል” በማለት ተናግራለች።
አንዳንዶች ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ግምት ያላቸው ቢሆንም ሌሎች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮ አስፈላጊ ቦታ ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ። ፒተር ሲበርት የተባሉ አንድ እንግሊዛዊ የካቶሊክ ቄስ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር መቀነሱን አስመልክተው ሲናገሩ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሰዎች ሃይማኖታቸውን የሚመርጡት ደስ እንዳላቸው ነው። አብዛኞቹ በእድሜ የገፉ ሰዎች ካቶሊኮች ሲሆኑ ከእምነታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ይመላለሳሉ። በወጣቶቹ ዘንድ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ወጣቶቹ ግዴታ እንዳለባቸው ሆኖ አይሰማቸውም።” በለንደን የሚታተመው ዴይሊ ቴሌግራፍ በኅዳር 20, 1998 እትሙ ላይ እንደገለጸው “ከ1979 ጀምሮ እንግሊዝ ውስጥ 495 የሚያክሉ
አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናት ሲገነቡና 150 ቤተ ክርስቲያናት እድሳት ሲደረግላቸው በአንጻሩ ግን 1, 500 የሚያክሉ ቤተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል።”ዙዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ሙኒክ ጋዜጣ በ1997 የሚከተለውን ዘግቦ ነበር:- “አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሲኒማ አዳራሽነትና ወደ መኖሪያ ቤትነት እየተለወጡ ነው። አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ከማቆማቸውም በላይ የአምልኮ ቦታዎች ለሌሎች ተግባራት ውለዋል። . . . በኔዘርላንድስና በእንግሊዝ የተለመደው ነገር በጀርመንም እየታየ ነው።” አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ጀርመን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ30 እስከ 40 የሚያክሉ አቢያተ ክርስቲያናት ተሸጠዋል።”
አምላክን ለማምለክ ሃይማኖታዊ ሕንጻዎች የግድ ያስፈልጋሉ? ግዙፍና የተንቆጠቆጡ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አላቸው? እውነተኛና ሕያው ከሆነው አምላክ አምልኮ ጋር ተያይዘው የተገለጹት ምን ዓይነት ሕንጻዎች ናቸው? የአምልኮ ቦታዎችን አስፈላጊነትና እዚያ መከናወን ያለበትን ነገር በተመለከተስ ከእነዚህ ሕንጻዎች ምን እንማራለን?