በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

ለአምላክ የተሳልነውን ስእለት ሁሉ የግድ መፈጸም ይኖርብናልን?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ስእለት አንድ ተግባር ለማከናወን፣ አንድ ነገር ለመስጠት፣ በአንድ ዓይነት አገልግሎት ለመካፈል ወይም በአንድ ሁኔታ ተወስኖ ለማገልገል አሊያም ደግሞ በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም እንኳ ከአንዳንድ ነገሮች ለመታቀብ በመወሰን ለአምላክ ቃል መግባትን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የጠየቁትን ከፈጸመላቸው እነሱም በአጸፋው አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ስለገቡ ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና “አቤቱ፣ የሠራዊት ጌታ ሆይ፣ . . . እኔንም ባትረሳ፣ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፣ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፣ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች።” (1 ሳሙኤል 1:11) መጽሐፍ ቅዱስ ስእለት በፈቃደኝነት የሚደረግ እንደሆነም ይናገራል። ለአምላክ የተሳልነውን ስእለት ምን ያህል አክብደን ልንመለከተው ይገባል?

የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ” ብሏል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል።” (መክብብ 5:4, 5) በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል:- “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፣ ኃጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘገይ።” (ዘዳግም 23:21) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ለአምላክ ስእለት መሳል በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ነገር ነው። ስእለት በጥሩ የልብ ግፊት ሊደረግ የሚገባ ሲሆን የተሳለው ግለሰብም የገባውን ቃል መፈጸም እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ባይሳል ይሻላል። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ከተሳልን፣ ቃል የገባነውን ሁሉ መፈጸም አለብን ማለት ነው?

አንድ ሰው ከተሳለ በኋላ ስእለቱ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ቢገነዘብስ? እንበልና ስእለቱ ከጾታ ብልግና ጋር የተያያዘ ቢሆንስ? (ዘዳግም 23:18) ግለሰቡ እንደዚህ ዓይነቱን ስእለት መፈጸም እንደማይኖርበት ግልጽ ነው። እንዲሁም በሙሴ ሕግ ሥር አንዲት ሴት የተሳለችውን ስእለት ባልዋ ወይም አባትዋ ሊሽሩት ይችሉ ነበር።​—⁠ዘኁልቊ 30:3-15

ነጠላ ሆኖ ለመኖር ለአምላክ የተሳለና አሁን ግን ልቡ የተከፈለን ሰው ሁኔታም እንመልከት። ስእለቱን መፈጸም ሥነ ምግባርን በተመለከተ የወጡ መለኮታዊ ሕግጋትን ወደ ማፍረስ እንደሚመራው ተሰምቶታል። ያም ሆኖ ስእለቱን ለመፈጸም መታገል ይኖርበታልን? ስእለቱን አፍርሶ በማግባት ራሱን ከሥነ ምግባር ብልግና መጠበቅና አምላክ ይቅር እንዲለው መጠየቅ የተሻለ አይሆንምን? በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማድረግ የሚችለው ራሱ ግለሰቡ ብቻ ነው። ማንም ሰው ይህንን ውሳኔ ሊያደርግለት አይችልም።

አንድ ሰው ቆየት ብሎ ሲያስበው በችኮላ የተደረገ እንደሆነ የተሰማውን ስእለት ቢሳልስ? በዚህም ጊዜ ቢሆን ስእለቱን ለመፈጸም መጣር ይኖርበታልን? ዮፍታሔ ለአምላክ የተሳለውን ስእለት መፈጸም ቀላል ባይሆንለትም ስእለቱን ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። (መሳፍንት 11:30-40) አንድ ሰው ስእለቱን ሳይፈጽም መቅረቱ አምላክ ‘እንዲቆጣ’ እና ሰውዬው ያከናወነውን ሁሉ ከንቱ እንዲያደርግበት ሊያነሳሳው ይችላል። (መክብብ 5:6) የተሳሉትን ስእለት የመፈጸም ግዴታን አቅልሎ መመልከት የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣ ይችላል።

ኢየሱስ ክርስቶስ “ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:37) አንድ ክርስቲያን ለአምላክ የተሳለውን ስእለት መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን በአምላክም ሆነ በሰዎች ፊት ቃሉን የሚጠብቅ ሰው የመሆኑም ጉዳይ ሊያሳስበው ይገባል። መጀመሪያ ላይ መልካም መስሎት ከሌላ ግለሰብ ጋር የተስማማበትን ነገር በኋላ ላይ በደንብ ሲመለከተው ትክክለኛ ውሳኔ እንዳልሆነ ቢሰማውስ? እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን አቅልሎ ሊመለከታቸው አይገባም። ሆኖም ጉዳዩን በቁም ነገር ከተወያዩበት በኋላ ምናልባት ሌላኛው ግለሰብ ከግዴታው ነጻ ሊያደርገው ይስማማ ይሆናል።​—⁠መዝሙር 15:4፤ ምሳሌ 6:2, 3

ስእለትንና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን በተመለከተ በዋነኛነት ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ምንጊዜም ቢሆን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን ለመቀጠል እንጣር።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐና ስእለቷን ለመፈጸም አላመነታችም

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮፍታሔ ስእለቱን መፈጸም ቀላል ባይሆንለትም ስእለቱን ከመፈጸም ወደኋላ አላለም