በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሚስዮናዊነት የተመደብንበትን ቦታ የትውልድ አገራችን አድርገነዋል

በሚስዮናዊነት የተመደብንበትን ቦታ የትውልድ አገራችን አድርገነዋል

የሕይወት ታሪክ

በሚስዮናዊነት የተመደብንበትን ቦታ የትውልድ አገራችን አድርገነዋል

ዲክ ዋልድሮን እንደተናገረው

ዕለቱ መስከረም 1953 እሁድ ከሰዓት በኋላ ሲሆን ቀድሞ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (አሁን ናሚቢያ) ወደተባለችው አገር ከመጣን ብዙም አልቆየንም። እዚህ ከገባን ገና ሳምንት ያልሞላን ቢሆንም በዋና ከተማዋ በዊንድሆክ የሕዝብ ስብሰባ ለማድረግ ሽር ጉድ በማለት ላይ ነን። ለመሆኑ ከአውስትራሊያ ተነስተን ወደዚህች አፍሪካዊት ምድር የመጣነው ለምንድን ነው? ባለቤቴና እኔ እንዲሁም ሌሎች ሦስት ወጣት እህቶች ወደዚህች አገር የመጣነው የአምላክን መንግሥት ምሥራች የምንሰብክ ሚስዮናውያን ሆነን ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

 ራቅ ብሎ በሚገኘው አገር ማለትም በአውስትራሊያ በታሪክ ጉልህ ስፍራ በሚሰጠው ዓመት በ1914 ተወለድኩ። በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ሳለሁ ዓለም በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት በመመታቷ ቤተሰቤን በኢኮኖሚ ለመደገፍ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ ነበረብኝ። በወቅቱ ሥራ ማግኘት ስላልቻልኩ በአውስትራሊያ በብዛት የሚገኙትን የዱር ጥንቸሎች እያደንኩ በማምጣት ለቤተሰባችን የሚሆን ምግብ አቀርብ ነበር።

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ በሜልቦርን ከተማ የኤሌክትሪክ ባቡሮችና አውቶቡሶች ላይ መሥራት ጀመርኩ። በአውቶቡሶቹ ላይ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች በፈረቃ የሚሠሩ ሲሆን በእያንዳንዱ ፈረቃ ከተለያዩ ሾፌሮች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበረኝ። አብዛኛውን ጊዜም “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ብዬ በመጠየቅ ስለ እምነታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡኝ አደርግ ነበር። አርኪ መልስ ሊሰጠኝ የቻለው አንድ የይሖዋ ምሥክር ብቻ ነበር። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ነገረኝ።​—⁠መዝሙር 37:​29

በዚሁ ወቅት እናቴም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝታ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ አመሻሹ ላይ ከሥራ ስመለስ ከእራቴ ጋር መጽናኛ የተባለው መጽሔት (አሁን ንቁ! ይባላል) ይቆየኝ ነበር። ያነበብኩት ነገር አስደሰተኝ። ብዙም ሳይቆይ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ ተረዳሁ። በመሆኑም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩና ግንቦት 1940 ተጠመቅሁ።

በሜልቦርን 25 የሚያክሉ አቅኚዎች የሚኖሩበት አንድ ቤት የነበረ ሲሆን እኔም አብሬያቸው መኖር ጀመርኩ። በየዕለቱ በስብከቱ ሥራ ያጋጠሟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ሲናገሩ እሰማ ስለነበር እንደነርሱ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። በመጨረሻም የአቅኚነት ማመልከቻ አስገባሁ። ማመልከቻዬ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ አውስትራሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ገብቼ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። በዚህ ሁኔታ የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆንኩ።

እስርና እገዳ

በቤቴል የተሰጠኝ አንዱ ሥራ በእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን መሥራት ነበር። እንጨት በመቁረጥ ለነዳጅ የሚሆን ከሰል እናከስል ነበር። በጦርነቱ ምክንያት የቤንዚን እጥረት በመከሰቱ ከሰሉ በቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙትን መኪናዎች ለማንቀሳቀስ ያገለግል ነበር። በእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኑ እንሠራ የነበርነው አሥራ ሁለታችንም ለውትድርና እድሜ የደረስን ስለነበርን ብዙም ሳይቆይ በገለልተኛ አቋማችን ምክንያት የ6 ወር እስር ተፈረደብን። (ኢሳይያስ 2:​4) ከዚያም የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ራቅ ወዳለ ካምፕ ተላክን። እዚያ የተሰጠን ሥራ ምን ነበር? የሚያስገርመው በቤቴል ሥልጠና ያገኘንበትን እንጨት የመሰንጠቅ ሥራ ነበር!

ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዳይሰጡን ጥብቅ ትእዛዝ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም ሥራውን ጥሩ አድርገን በመሥራታችን የእስር ቤቱ ኃላፊ እነዚህን ጽሑፎች እንድናገኝ ፈቀደልን። በማኅበራዊ ኑሮ ረገድ ጠቃሚ ትምህርት ያገኘሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ቤቴል ሳለሁ ከአንድ ወንድም ጋር ፈጽሞ አንስማማም ነበር። ይህ የሆነው የተለያየ አመለካከት ስለነበረን ብቻ ነው። ታዲያ አንድ ክፍል ውስጥ የታሰርኩት ከማን ጋር ይመስላችኋል? ከዚሁ ወንድም ጋር ነበር። አሁን እርስ በርስ ይበልጥ ለመተዋወቅ የሚያስችል ጊዜ ያገኘን ሲሆን ይህም የጠበቀና ዘላቂነት ያለው ወዳጅነት ለመመሥረት አስችሎናል።

ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በአውስትራሊያ ታገደ። ያለው ገንዘብና ንብረት በሙሉ በመወረሱ የቤቴል ወንድሞች ምንም ገንዘብ አልነበራቸውም። አንድ ጊዜ አንድ ወንድም “ዲክ፣ ከተማ ሄጄ መመስከር እፈልግ ነበር። ግን እንደምታየው ከዚህ ካደረኩት የሥራ ጫማ በስተቀር ሌላ የለኝም” አለኝ። እኔም በደስታ ጫማዬን ሰጠሁትና አድርጎት ወደ ከተማ ሄደ።

ከዚያም ይህ ወንድም ሲሰብክ እንደተያዘና እንደታሰረ ሰማን። “በደረሰብህ ሁኔታ በጣም አዝኛለሁ። ሆኖም ያቺን ያዋስኩህን ጫማዬን አድርጌ አለመገኘቴ እንደበጀኝ ሳልጠቁምህ አላልፍም” በማለት ቀልድ አዘል ማስታወሻ ጻፍኩለት። ይሁን እንጂ ወዲያው እኔም በገለልተኛ አቋሜ ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ ታሰርኩ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በቤቴል ቤተሰብ የእርሻ ቦታ ላይ እንድሠራ ተመደብኩ። በወቅቱ በፍርድ ቤት ተሟግተን ስለረታን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳም ተነስቶ ነበር።

በቅንዓት የምታገለግል ወንጌላዊ አገባሁ

በእርሻ ቦታው በመሥራት ላይ ሳለሁ ስለ ትዳር በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያም ኮረሊ ክሎገን ከተባለች አንዲት ወጣት አቅኚ ጋር ተዋወቅሁ። ከኮረሊ ቤተሰብ በመጀመሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያሳዩት ሴት አያቷ ነበሩ። ሊሞቱ በማጣጣር ላይ ሳሉ ለኮረሊ እናት ለቬረ “ልጆችሽ አምላክን እንዲወዱና እንዲያገለግሉ አድርገሽ አሳድጊያቸው። አንድ ቀን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንገናኛለን” በማለት ነግረዋት ነበር። ከጊዜ በኋላ አንዲት አቅኚ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ቬረን አገኘቻትና ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም በተባለው ቡክሌት አማካኝነት አነጋገረቻት። በዚህ ጊዜ ቬረ እናቷ የነገሯት ነገር ይበልጥ ግልጽ ሆነላት። ቡክሌቱ የሰው ልጆች ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ እንደሆነ አሳመናት። (ራእይ 21:​4) በ1930ዎቹ መግቢያ ላይ የተጠመቀች ሲሆን በእናቷ ማበረታቻ መሠረት ሉሲ፣ ጄንና ኮረሊ የተባሉትን ሦስት ልጆቿን አምላክን እንዲወድዱ አድርጋ አሳደገቻቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በቤተሰብ ውስጥ ሊከሰት ይችላል በማለት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት የኮረሊ አባት የቤተሰቡን ሃይማኖት አጥብቆ ይቃወም ነበር።​—⁠ማቴዎስ 10:​34-36

የክሎገን ቤተሰቦች በጠቅላላ የሙዚቃ ተሰጥዎ ያላቸው ሲሆኑ እያንዳንዱ ልጅ አንድ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ይችላል። ኮረሊ ቫዮሊን የምትጫወት ሲሆን በ1939 ማለትም በ15 ዓመቷ በሙዚቃ ዲፕሎማ አግኝታለች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ኮረሊ ስለ ወደፊት ሕይወቷ በቁምነገር ማሰብ ጀመረች። ምን ባደርግ ይሻላል የሚለውን ነገር በተመለከተ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረባት። በአንድ በኩል የሙዚቃ ተሰጥኦዋን ማሳደግ የምትችልበት አጋጣሚ ተከፍቶላታል። በሜልቦርን ሲምፖኒ ኦርኬስትራ ውስጥ እንድትጫወት ግብዣ ቀርቦላታል። በሌላው በኩል ደግሞ የአምላክን መንግሥት በመስበኩ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠመድ ትችላለች። በጉዳዩ ላይ በጥሞና ካሰበችበት በኋላ በ1940 እርሷና ሁለት እህቶቿ ተጠመቁ። ከዚያም በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አደረጉ።

ኮረሊ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል በወሰነችበት ወቅት በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ በከፍተኛ ኃላፊነት ይሠራ የነበረውንና በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነውን ወንድም ሎይድ ባሪን አገኘችው። ሜልቦርን መጥቶ ገና ንግግር ሰጥቶ መጨረሱ ነበር። ወዲያው ኮረሊን “ወደ ቤቴል መመለሴ ነው። ለምን ከእኔ ጋር በባቡር አትሄጂም?” በማለት ጠየቃት። እርሷም ግብዣውን ተቀበለች።

ኮረሊ እና ሌሎች የቤቴል እህቶች በጦርነቱና በእገዳው ዓመታት አውስትራሊያ ለሚገኙት ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በወንድም ማልኮልም ቬል የበላይ ተመልካችነት አብዛኛውን የህትመት ሥራ የሚሠሩት እነርሱ ነበሩ። አዲሱ ዓለም እና ልጆች የተባሉት መጻሕፍት ከመታተማቸውና ከመጠረዛቸውም በተጨማሪ ከሁለት ዓመት በላይ በቆየው የእገዳ ወቅት አንድም የመጠበቂያ ግንብ እትም አምልጦን አያውቅም።

ማተሚያ ማሽኑን ፖሊሶቹ እንዳያገኙት ለመደበቅ ስንል 15 ጊዜ ያህል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር ተገደናል። በአንድ ወቅት ከውጭ ሲታይ የተለመደ ዓይነት የሕትመት ሥራ የምናከናውን በማስመሰል ምድር ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን  እናትም ነበር። አስጊ ሁኔታ ከተፈጠረ እህቶች  መጽሔቶቹን እንዲደብቁ እንግዳ መቀበያ ክፍል ያለችው እህት ምድር ቤት ላሉት እህቶች ደወል በመደወል ምልክት ትሰጣቸው ነበር።

አንድ ቀን ፖሊሶች ለፍተሻ መጥተው ሳለ እህቶች አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም ጠረጴዛው ላይ ፊት ለፊት መቀመጡን ሲመለከቱ ደንግጠው የሚያደርጉት ጠፋቸው። ፖሊሱ ወዲያው እንደገባ ቦርሳውን መጠበቂያ ግንቡ ላይ አስቀምጦ ፍተሻውን ጀመረ። ፈትሾ ምንም ስላላገኘ ቦርሳውን አንስቶ ከክፍሉ ወጣ!

እገዳው ከተነሳና የቅርንጫፍ ቢሮው ንብረት ለወንድሞች ከተመለሰ በኋላ ብዙዎቹ ቤቴላውያን ልዩ አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ አጋጣሚ ተሰጣቸው። ኮረሊ ወደ ግሌኒኒስ ለመሄድ ፈቃደኝነቷን የገለጸችው በዚህ ጊዜ ነበር። ከዚያም ጥር 1, 1948 ተጋባንና አብረን ማገልገል ጀመርን። ምድቡን ለቅቀን ስንሄድ በጥሩ ሁኔታ እያደገ ያለ አንድ ጉባኤ ነበር።

የሚቀጥለው ምድባችን ሮክሃምተን ነበር። ይሁን እንጂ ለማረፊያ የሚሆን ቦታ ባለማግኘታችን ፍላጎት ባሳየ አንድ ግለሰብ እርሻ ቦታ ላይ ድንኳን ተከልን። በዚህ ድንኳን ውስጥ 9 ወር ተቀመጥን። ከዚህ የበለጠ ጊዜም እንቀመጥ ነበር። ግን ምን ያደርጋል የክረምቱ ዝናብና ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ድንኳኑን ከጥቅም ውጪ አደረገው። a

የውጪ አገር ምድብ መቀበል

በሮክሐምተን ሳለን በ19ኛው የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ግብዣ ቀረበልን። በ1952 ከዚህ ትምህርት ቤት ከተመረቅን በኋላ በወቅቱ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ተብላ ወደምትጠራው አገር የተላክነው በዚህ መልኩ ነበር።

የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሚስዮናዊነት ሥራችንን በተመለከተ ተቃውሞ መግለጽ የጀመሩት እዚያ እንደደረስን ነበር። ቤታችሁ ሲመጡ እንዳትቀበሏቸው እንዲሁም ግራ ሊያጋቧችሁ ስለሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ እናንብብላችሁ ቢሏችሁ እሺ እንዳትሏቸው በማለት ለስድስት ተከታታይ ሳምንታት እሁድ እሁድ እኛን በተመለከተ ለምዕመናኖቻቸው ከመድረክ ማስጠንቀቂያ ይሰጡ ነበር። በአንድ አካባቢ ከቤት ወደ ቤት እየሄድን በርካታ ጽሑፎች ብናበረክትም ቄሱ ከኋላ ከኋላችን እየተከተለ ያበረከትናቸውን ጽሑፎች በሙሉ አንድ በአንድ ሰብስቦ ወስዶ ነበር። በአንድ ወቅት ከቄሱ ጋር ስንወያይ በርካታ ጽሑፎቻችን እንዳሉት ተገነዘብን።

ብዙም ሳይቆይ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሥራችንን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት የጀመሩ ሲሆን ከኮምኒስቶች ጋር ግንኙነት እንዳለን አስበው ነበር። እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ያደረጉት ቀሳውስቱ እንደነበሩ የታወቀ ነው። እንዲያውም የጣት አሻራችን የተወሰደ ሲሆን ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሰዎችም ተጠርተው ተጠይቀዋል። ይህ ሁሉ ተቃውሞ ቢኖርም የተሰብሳቢዎች ቁጥር ያለማቋረጥ ይጨምር ነበር።

እዚህ አገር ከገባንበት ጊዜ አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የአገሬው ተወላጆች ለሆኑት ለኦቫምቦ፣ ለሄሬሮ እና ለናማ ጎሳዎች የማዳረስ ከፍተኛ ፍላጎት አደረብን። ይሁን እንጂ ይህን ማድረጉ ቀላል አልነበረም። በወቅቱ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካን በሚያስተዳድረው የአፓርታይድ መንግሥት ሥር ነበረች። ነጮች እንደመሆናችን መጠን ያለ መንግሥት ፈቃድ ጥቁሮች በሚኖሩበት አካባቢ እንድንመሰክር አይፈቀድልንም ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ ማመልከቻ ብናስገባም ፈቃድ ለማግኘት አልቻልንም።

በውጪ አገር ምድባችን ለሁለት ዓመታት ከቆየን በኋላ አንድ አዲስ ነገር ተከሰተ። ኮረሊ አረገዘች። ጥቅምት 1955 ሻርሎት የተባለችው ልጃችን ተወለደች። ሚስዮናውያን ሆነን መቀጠል ባንችልም እኔ የትርፍ ጊዜ ሥራ መሥራትና ለጥቂት ጊዜ አቅኚ ሆኜ መቀጠል ችዬ ነበር።

የጸሎታችን መልስ

በ1960 ደግሞ ሌላ ፈተና አጋጠመን። ኮረሊ እናትዋ በጠና በመታመሟ መጥታ ካላየቻት ሌላ ጊዜ ላታያት እንደምትችል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሳት። ስለዚህም ደቡብ ምዕራብ አፍሪካን ለቅቀን ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ እቅድ አወጣን። ይሁን እንጂ በምንሄድበት ሳምንት አንድ ነገር ተከሰተ። ካቱቱራ ወደተባለው የጥቁሮች መንደር እንድንገባ የሚፈቅድ ደብዳቤ ደረሰን። አሁን ምን ማድረግ ይሻለናል? ፈቃዱን ለማግኘት ለሰባት ዓመታት ከታገልን በኋላ አሁን ስናገኘው አንፈልግም እንበል? ምን ችግር አለ ሌሎች ይህን ሥራ ሊሠሩት ይችላሉ ብሎ ማሰቡ ቀላል ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከይሖዋ የተገኘ በረከትና የጸሎታችን መልስ አይደለምን?

ወዲያው ውሳኔ ላይ ደረስኩ። ሁላችንም ወደ አውስትራሊያ ከሄድን ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ያደረግነው ትግል መና ይቀራል ብዬ ስላሰብኩ እነርሱን ለመላክና እኔ እዚሁ ለመቆየት ወሰንኩ። በሚቀጥለው ቀን የመርከብ ጉዞዬን ሰረዝኩና ኮረሊንና ሻርሎትን ለረዥም እረፍት ወደ አውስትራሊያ ላክኋቸው።

እነርሱን ከላክሁ በኋላ ጥቁሮች መንደር ገብቼ መመስከር ጀመርኩ። የሰዎቹ ፍላጎት የሚያስገርም ነበር። ኮረሊና ሻርሎት ሲመለሱ ከጥቁሮች መንደር የመጡ አንዳንድ ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀምረው ነበር።

በዚህ ወቅት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ወደ ስብሰባዎች የማመላልስበት አንድ አሮጌ መኪና ነበረኝ። ስብሰባ ባለ ቁጥር በእያንዳንዱ ጉዞ ሰባት፤ ስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዎች እጭንና አራት ወይም አምስት ጊዜ እመላለስ ነበር። የመጨረሻው ሰው ከመኪና ሲወርድ ኮረሊ “ወንበሩ ስር ስንት ቀሩህ?” እያለች ትቀልድብኝ ነበር።

በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን በአካባቢው ሰዎች ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች ያስፈልጉናል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት (እንግሊዝኛ) የተባለው ትራክት ሄሬሮ፣ ናማና ንዶንጋ ወደተባሉት የአገሪቱ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ዝግጅት የማድረግ መብት አግኝቻለሁ። ተርጓሚዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን እናስጠናቸው የነበሩ የተማሩ ሰዎች ሲሆኑ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በትክክል መተርጎሙን ለማየት አብሬያቸው መሥራት ነበረብኝ። ናማ ውስን ቃላት ያሉት ቋንቋ ነው። ለምሳሌ ያህል “በመጀመሪያ አዳም ፍጹም ሰው ነበር” የሚለውን ሐሳብ ለማብራራት እየሞከርኩ ሳለሁ ተርጓሚው ጭንቅላቱን አከክ አከክ አደረገና በናማ ቋንቋ “ፍጹም” ለሚለው ቃል ተመሳሳይ ቃል ማግኘት እንዳልቻለ ገለጸልኝ። በመጨረሻ ግን “አሁን ገባኝ” ካለ በኋላ “በመጀመሪያ አዳም ልክ እንደበሰለ ኮክ ነበር” በማለት ተናገረ።

ሚስዮናዊ ሆነን በተመደብንበት ቦታ ደስተኞች ነበርን

አሁን ናሚቢያ ተብላ ወደምትጠራው አገር ከገባን ወደ 49 የሚያክሉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከአሁን በኋላ ወደ ጥቁሮች መንደር ለመግባት ፈቃድ አያስፈልግም። ናሚቢያ የዘር መድሎ በማያደርግ አዲስ መንግሥት ሥር በመተዳደር ላይ ትገኛለች። ዛሬ በዊንድሆክ ምቹ በሆኑ የመንግሥት አዳራሾች የሚሰበሰቡ አራት ትላልቅ ጉባኤዎች ይገኛሉ።

አብዛኛውን ጊዜ በጊልያድ የሰማናቸውን “ሚስዮናዊ ሆናችሁ የተመደባችሁበትን ቦታ እንደ ትውልድ አገራችሁ አድርጋችሁ ተመልከቱት” የሚሉ ቃላት እናስታውሳለን። ይሖዋ ነገሮችን መልክ ስላስያዘበት መንገድ ስናስብ ይህን ምድባችንን ልክ እንደ ትውልድ አገራችን አድርገን እንድንመለከተው የረዳን እርሱ ራሱ እንደሆነ እንገነዘባለን። የተለያየ ባሕል ያላቸውን ወንድሞቻችንን መውደድ ችለናል። የደስታቸውም ሆነ የሃዘናቸው ተካፋዮች ሆነናል። በመኪናችን ወደ ስብሰባዎች እናመላልሳቸው ከነበሩት አዳዲሶች መካከል አንዳንዶቹ ዛሬ በጉባኤዎቻቸው ውስጥ እንደ አምድ ሆነው ያገለግላሉ። በ1953 እዚህ ሰፊ ክልል ስንደርስ የአስፋፊዎቹ ቁጥር ከ10 የሚያንስ ነበር። ከዚህ አነስተኛ ጅምር ተነስቶ አሁን ቁጥራችን ከ1, 200 በላይ ሆኗል። እኛም ሆንን ሌሎች ‘የተከልነውንና ያጠጣነውን’ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት አሳድጎታል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​6

ኮረሊና እኔ በመጀመሪያ በአውስትራሊያ ቀጥሎ ደግሞ በናሚቢያ ያሳለፍናቸውን በርካታ የአገልግሎት ዓመታት መለስ ብለን ስናስብ ጥልቅ እርካታ ይሰማናል። ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል መስጠቱን እንዲቀጥል እንመኛለን እንዲሁም እንጸልያለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዋልድሮንና ቤተሰቡ (ስማቸው አልተጠቀሰም) በዚህ ከባድ ምድብ እንዴት ሊጸኑ እንደቻሉ የሚገልጽ አስደናቂ ታሪክ በታኅሣሥ 1, 1952 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 707-8 ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮክሐምተን አውስትራሊያ ወደሚገኘው ምድባችን ስንሄድ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ጊልያድ ስንጓዝ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በናሚቢያ መስበክ በጣም ያስደስተናል