በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢያሱ ካሳለፈው ተሞክሮ ያገኘው ጥቅም

ኢያሱ ካሳለፈው ተሞክሮ ያገኘው ጥቅም

ኢያሱ ካሳለፈው ተሞክሮ ያገኘው ጥቅም

ይሖዋ “ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስን ተሻገሩ” አለ። (ኢያሱ 1:2) ኢያሱ ምንኛ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል! ለ40 ዓመታት ያህል የሙሴ ሎሌ ሆኖ አገልግሏል። አሁን ግን የጌታውን ቦታ እንዲይዝና በአመዛኙ አስቸጋሪ የሆኑትን እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ እንዲያስገባ ተነገረው።

ኢያሱ ከፊቱ ምን ሥራ እንደሚጠብቀው በሚያስብበት ወቅት ከዚህ በፊት ያጋጠሙትንና የተወጣቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች አንድ በአንድ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ኢያሱ ያሳለፈው ተሞክሮ በወቅቱ በጣም ጠቅሞት እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ነው።

ከባሪያነት ወደ አዛዥነት

ኢያሱ በባርነት ቀንበር ሥር ያሳለፋቸው በርካታ ዓመታት ከአእምሮው የሚጠፉ አልነበሩም። (ዘጸአት 1:​13, 14፤ 2:​23) ኢያሱ በዚያ ወቅት ያሳለፈውን ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ስለማይነግረን ሕይወቱ ምን ይመስል እንደነበር ከመገመት በቀር በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ኢያሱ በግብፅ ያከናውን የነበረው ሥራ ጥሩ የማደራጀት ችሎታ እንዲያዳብር ረድቶት መሆን አለበት። እስራኤላውያንና “ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ግብፅን ለቅቀው በሚወጡበት ጊዜ ጉዟቸውን በማደራጀት ረገድ እገዛ አድርጎም ሊሆን ይችላል።​—⁠ዘጸአት 12:​38

ኢያሱ ወገኑ ከኤፍሬም ነገድ ነበር። አያቱ ኤሊሳማ የኤፍሬም ነገድ አለቃ ከመሆኑም በላይ 108, 100 ሠራዊት ያቀፈውን በሦስት በሦስት ነገዶች ከተከፈለው የእስራኤል ብሔር አንዱን ይመራ እንደነበር መረዳት ይቻላል። (ዘኍልቍ 1:4, 10, 16፤ 2:18-24፤ 1 ዜና መዋዕል 7:20, 26, 27) ይሁንና እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ አማሌቃውያን ውጊያ በከፈቱባቸው ጊዜ ሙሴ ጥቃቱን የሚከላከል ኃይል እንዲያደራጅ ለኢያሱ ነገረው። (ዘጸአት 17:​8, 9ሀ) ለዚህ ኃላፊነት አያቱ ወይም አባቱ ሳይሆኑ ኢያሱ የተመረጠው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት:- “[ኢያሱ] የትልቁ የኤፍሬም ነገድ አለቃ ከመሆኑም በላይ የማደራጀት ችሎታው የተመሰከረለትና በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታ ያተረፈ በመሆኑ ሙሴ ተዋጊዎቹን ለመመልመልና ለማዘጋጀት ከእርሱ የተሻለ ብቃት ያለው መሪ ማግኘት ስላልቻለ ይሆናል።”

ኢያሱ እንዲመረጥ ያበቃው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ሙሴ ያዘዘውን በትክክል ፈጽሟል። እስራኤላውያን ምንም ዓይነት የውጊያ ልምድ ያልነበራቸው ቢሆኑም እንኳ ኢያሱ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ነበር። በመሆኑም ሙሴ “ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ” ባለው ጊዜ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያገኝ ተማምኗል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ይሖዋ በዘመኑ የነበረውን ከፍተኛ የጦር ኃይል መደምሰሱን ኢያሱ ሳያስታውስ አልቀረም። በነጋታው ሙሴ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እጁን ወደ ላይ ዘርግቶ በቆመበት ወቅት የትኛውም ጠላት ቢሆን እስራኤልን መቋቋም አልቻለም፤ አማሌቃውያንም በውጊያው ድል ተነሡ። ከዚያም ይሖዋ “የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁ” የሚለውን መለኮታዊ ፍርድ በመጽሐፍ እንዲጽፍና ‘በኢያሱ ጆሮ እንዲናገር’ ሙሴን አዘዘው። (ዘጸአት 17:​9ለ-14) አዎን፣ ይሖዋ ይህን የቅጣት እርምጃ መውሰዱ አይቀርም።

የሙሴ ሎሌ

ከአማሌቅ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ይህ ሁኔታ ኢያሱንና ሙሴን ይበልጥ አቀራርቧቸው መሆን አለበት። ኢያሱ “ከልጅነቱ ጀምሮ” ሙሴ እስከሞተበት ዕለት ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል የሙሴ ሎሌ ወይም “አገልጋይ” የመሆን መብት አግኝቷል።​—⁠ዘኍልቍ 11:28

ይህ ሥራ መብት ከመሆኑም በላይ ኃላፊነትም አለው። ለምሳሌ ያህል ሙሴ፣ አሮን፣ የአሮን ወንዶች ልጆችና 70 የእስራኤል ሽማግሌዎች ሲና ተራራ ላይ ወጥተው የይሖዋን ክብር በራእይ በተመለከቱ ጊዜ ኢያሱም አብሯቸው ሳይኖር አይቀርም። ኢያሱ ሎሌ ሳለ ከሙሴ ጋር ወደ ተራራው የወጣ ሲሆን ሙሴ የይሖዋን መገኘት የሚያመለክተው ደመና ውስጥ ሲገባ እርሱ በርቀት ቆሞ ይጠብቀው ነበር። የሚያስገርመው ነገር ኢያሱ ተራራው ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት የቆየ መሆኑ ነው። ሙሴ የምስክሩን ጽላት ይዞ ከተራራው ሲወርድ ኢያሱን እዚያው ያገኘው መሆኑ ኢያሱ የጌታውን መመለስ በትዕግሥት ይጠባበቅ እንደነበረ ያሳያል።​—⁠ዘጸአት 24:​1, 2, 9-18፤ 32:​15-17

እስራኤላውያን ለወርቁ ጥጃ በመስገድ ጣዖት አምልኮ ከፈጸሙ በኋላ ኢያሱ ከሠፈሩ ውጪ በተተከለው የመገናኛ ድንኳን ሙሴን ማገልገሉን ቀጥሏል። እዚያም ይሖዋ ሙሴን ፊት ለፊት አነጋገረው። ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበትም ጊዜ ኢያሱ “ከድንኳኑ አይለይም ነበር።” ከአካባቢው የማይለየው እስራኤላውያን ረክሰው እያሉ ወደ ድንኳኑ እንዳይገቡ ለመከልከል ሊሆን ይችላል። ኢያሱ የተሰጠውን ኃላፊነት ምንኛ አክብዶ ተመልክቶት ነበር!​—⁠ዘጸአት 33:​7, 11

ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንዳለው ከሆነ ሙሴ ኢያሱን በ35 ዓመት ይበልጠው ነበር። ኢያሱ በዕድሜ ከሚበልጠው ከሙሴ ጋር መቀራረቡ እምነቱን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሮለት መሆን አለበት። በሁለቱ መካከል የነበረው ዝምድና “በጎልማሳና በወጣት፣ በአስተማሪና በተማሪው መካከል ያለ ግንኙነት” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ይህም ኢያሱ “ቆራጥና እምነት የሚጣልበት ሰው” እንዲሆን አስችሎታል። በዛሬው ጊዜ በመካከላችን እንደ ሙሴ ያሉ ነቢያት የሉም። ሆኖም በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ ካካበቱት ተሞክሮና መንፈሳዊነት የተነሳ የድጋፍና የብርታት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ክርስቲያኖች አሉ። እነዚህን ክርስቲያኖች በአድናቆት ትመለከቷቸዋላችሁ? እንዲሁም ከእነሱ ጋር በመቀራረብ እየተጠቀማችሁ ነው?

ከነዓንን እንዲሰልል ተላከ

እስራኤል ሕጉን ከተቀበለ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢያሱ በሕይወቱ ውስጥ አንድ ከባድ ሁኔታ አጋጠመው። የራሱን ነገድ ወክሎ ተስፋይቱን ምድር ከሚሰልሉት ጋር እንዲሄድ ተመረጠ። ታሪኩ በሰፊው የሚታወቅ ነው። ምድሪቱ ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ‘ወተትና ማር የምታፈስስ’ እንደሆነች 12ቱም ሰላዮች አምነዋል። ይሁን እንጂ አሥሩ እምነት በማጣት እስራኤላውያን ነዋሪዎቹን ከምድሪቱ ማባረር አይችሉም የሚል ፍርሃት አደረባቸው። ይሖዋ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን በመተማመን ሕዝቡ ከፍርሃት የተነሳ ማመፅ እንደሌለባቸው የተናገሩት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ከመቃወማቸውም በላይ ሁለቱን በድንጋይ ለመውገር ተማከሩ። ይሖዋ ክብሩን በመግለጥ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ በድንጋይ ከመውገር አይመለሱም ነበር። እምነት በማጣታቸው ምክንያት አምላክ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር አይገቡም ሲል ፍርድ አስተላለፈ። ከእነዚህ መካከል ተስፋይቱ ምድር የገቡት ኢያሱ፣ ካሌብና ሌዋውያን ብቻ ነበሩ።​—⁠ዘኍልቍ 13:1-16, 25-29፤ 14:6-10, 26-30

ሕዝቡ ሁሉ ይሖዋ ግብፅ ውስጥ ያከናወናቸውን ተአምራት ተመልክተው አልነበረም? ታዲያ አብዛኞቹ ጥርጣሬ ሲያድርባቸው ኢያሱ አምላክ እንደሚረዳቸው እንዲያምን ያስቻለው ምንድን ነው? ኢያሱ ይሖዋ ቃል የገባቸውንና የፈጸማቸውን ተስፋዎች መለስ ብሎ ያስብባቸውና ያሰላስልባቸው ስለነበር መሆን አለበት። ከብዙ ዓመታት በኋላ ‘ይሖዋ ስለ እስራኤል ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል’ ብሎ ለመናገር ችሏል። (ኢያሱ 23:​14) በመሆኑም ኢያሱ ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ በእርግጥ እንደሚፈጸሙም እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:​6) ይህ ጉዳይ አንድ ሰው እንደሚከተለው እያለ ራሱን እንዲጠይቅ ሊያነሳሳው ይገባል:- ‘የእኔስ ሁኔታ እንዴት ነው? ይሖዋ ቃል የገባቸውን ተስፋዎች ለመመርመርና በእነርሱ ላይ ለማሰላሰል የማደርገው ጥረት ተስፋዎቹ በእርግጥ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ጽኑ እምነት እንዲያድርብኝ አስችሎኛልን? አምላክ ከመጪው ታላቅ መከራ ከሕዝቦቹ ጋር እኔንም ሊያድነኝ እንደሚችል አምናለሁ?’

ኢያሱ እምነት የነበረው ከመሆኑም በላይ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ድፍረት አሳይቷል። ከይሖዋ ጎን የቆሙት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ፤ ማኅበሩ ሁሉ ግን እነሱን በድንጋይ ለመውገር ተማከሩ። አንተ ብትሆን ምን ይሰማህ ነበር? በፍርሃት ትርድ ነበር? ኢያሱ ቅንጣት ታክል ፍርሃት አልተሰማውም፤ እሱና ካሌብ ያመኑበትን ነገር በግልጽ ተናግረዋል። እኛም ለይሖዋ ያለን ታማኝነት አንድ ቀን ተመሳሳይ አቋም እንድንወስድ ያስገድደን ይሆናል።

በተጨማሪም ስለ ሰላዮቹ የሚናገረው ታሪክ የኢያሱ ስም መለወጡን ይጠቁመናል። ሙሴ “መዳን” የሚል ትርጉም ባለው አውሴ በሚለው የመጀመሪያ ስሙ ላይ መለኮታዊውን ስም የሚያመለክት ፊደል በማስገባት ኢያሱ ብሎ ጠራው። ትርጉሙም “ይሖዋ ያድናል” ማለት ነው። ሴፕቱጀንት ስሙን “ኢየሱስ” ብሎ ተርጉሞታል። (ዘኍልቍ 13:8, 16 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ስሙ ከያዘው ከፍተኛ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኢያሱ ይሖዋ አዳኝ መሆኑን በድፍረት አስታውቋል። የኢያሱ ስም የተለወጠው እንዲያው በአጋጣሚ ሊሆን አይችልም። ሙሴ ለኢያሱ ባሕርይ ያለውን አድናቆት እንዲሁም ኢያሱ አዲሱን ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ በማስገባት ረገድ የሚጫወተውን ትልቅ ሚና የሚገልጽ ነበር።

እስራኤላውያን አባቶቻቸው ሞተው እስኪያልቁ ድረስ አሰልቺ የሆኑ 40 ዓመታትን በበረሃ በመቅበዝበዝ አሳልፈዋል። በዚህ ወቅት ኢያሱ ስላሳለፈው ሕይወት ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ብዙ ትምህርት አግኝቶበት መሆን አለበት። አምላክ ዓመፀኛ በሆኑት በቆሬ፣ በዳታን፣ በአቤሮን እና በተከታዮቻቸው እንዲሁም በፌጎር በሚካሄደው አስነዋሪ የበኣል አምልኮ በተካፈሉት ሰዎች ላይ የወሰደውን የቅጣት እርምጃ ሳይመለከት አልቀረም። ሙሴ ከመሪባ ውኃ ጋር በተያያዘ ይሖዋን ሳይቀድስ በመቅረቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ መከልከሉን ኢያሱ ባወቀ ጊዜ ጥልቅ ሐዘን እንደሚሰማው ጥያቄ የለውም።​—⁠ዘኍልቍ 16:1-50፤ 20:9-13፤ 25:1-9

የሙሴ ተተኪ ሆኖ ተሾመ

ሙሴ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ እስራኤል “እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን” እሱን የሚተካ ሰው እንዲሾም አምላክን ጠየቀ። ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? “መንፈስ ያለበት ሰው” ኢያሱ በሕዝቡ ሁሉ ላይ እንዲሾም ተመረጠ። በመሆኑም እርሱን እንዲታዘዙት ይጠበቅባቸዋል። ምንኛ ትልቅ ሹመት ነው! ይሖዋ ኢያሱ እምነትና ችሎታ እንዳለው ተመልክቷል። የእስራኤል መሪ መሆን የሚችል ከእሱ የተሻለ ብቃት ያለው ሰው አልነበረም። (ዘኍልቍ 27:15-20) ይሁንና ኢያሱ ከባድ ፈተናዎች እንደሚጠብቁት ሙሴ ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ከተተኪው ከኢያሱ ጋር እንደሚሆን በመተማመን ሙሴ “ጽና፣ አይዞህ” በማለት አበረታቶታል።​—⁠ዘዳግም 31:​7, 8

አምላክ ለኢያሱ ተመሳሳይ ማበረታቻ የሰጠው ሲሆን አክሎም እንዲህ ብሎታል:- “ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፣ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፣ አይዞህ፤ አትፍራ፣ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”​—⁠ኢያሱ 1:7-9

ኢያሱ በሕይወት ዘመኑ ካካበተው ተሞክሮ በተጨማሪ ከይሖዋ ያገኘው ይህ የማበረታቻ ቃል ሙሉ ትምክህት እንዲያድርበት እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም። ምድሪቱን ድል አድርገው እንደሚይዙ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። እንዲያውም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የሚፈስሰውን የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር የመጀመሪያው ከባድ ፈተና ነበር። ሆኖም ይሖዋ ራሱ “ተነሥታችሁ . . . ይህን ዮርዳኖስን ተሻገሩ” የሚል ትእዛዝ ሰጠው። ታዲያ ሊወጣው የማይችለው ምን ችግር ሊኖር ይችላል?​—⁠ኢያሱ 1:​2

በኢያሱ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙት ክንውኖች ማለትም የኢያሪኮ መያዝ፣ የጠላቶቻቸው ድል መደረግ እንዲሁም ምድሪቱን ተከፋፍለው መያዛቸው አምላክ ቃል የገባላቸውን ተስፋዎች ሁልጊዜ እንዲያስብ አድርገውት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ኢያሱ በሕይወቱ ዘመን ማብቂያ ላይ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው ባሳረፋቸው ጊዜ ሕዝቡን ሰብስቦ አምላክ ምን እንዳደረገላቸው በማስታወስ እሱን በሙሉ ልባቸው እንዲያገለግሉ አሳሰባቸው። ከዚህም የተነሳ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የገቡትን ቃል እንደገና ያደሱ ከመሆኑም በላይ መሪያቸው የተወውን ምሳሌ በመከተል “ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ . . . እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ።”​—⁠ኢያሱ 24:​16, 31

ኢያሱ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በርካታ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። በይሖዋ ዘንድ ያገኘነውን ሞገስ እንዳናጣና የገባቸውን ተስፋዎች መውረስ እንድንችል እነዚህን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መወጣት ያስፈልገናል። ኢያሱን ለስኬት ያበቃው ጠንካራ እምነት የነበረው መሆኑ ነው። እንደ ኢያሱ የይሖዋን አስደናቂ ሥራዎች የማየት አጋጣሚ እንዳላገኘን የታወቀ ነው። ሆኖም ማንም ሰው ጥርጣሬ ቢያድርበት ይሖዋ የተናገራቸው ነገሮች በእርግጥ ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ ለመገንዘብ የዓይን ምሥክር የጻፈውን የኢያሱን መጽሐፍ ማንበብ ይችላል። እኛም እንደ ኢያሱ የአምላክን ቃል በየዕለቱ የምናነብና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ጥበብና ስኬት እንደምናገኝ ዋስትና ተሰጥቶናል።

ክርስቲያን ባልንጀሮችህ በሚያሳዩት ጠባይ የተጎዳህበት ጊዜ አለ? እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜ ኢያሱ እምነት የለሽ በሆኑት ወገኖቹ ጦስ ያለ ጥፋቱ በበረሃ ለመንከራተት በተገደደባቸው 40 ዓመታት ውስጥ ያሳየውን ጽናት መለስ ብለህ አስብ። አንተስ ላመንክበት ነገር ጥብቅና መቆም ይከብድሃል? ኢያሱና ካሌብ ያደረጉትን አስታውስ። እምነታቸውና ታዛዥነታቸው አስደናቂ ወሮታ አስገኝቶላቸዋል። አዎን፣ ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጽም ኢያሱ ልባዊ እምነት ነበረው። እኛም የእሱ ዓይነት እምነት ይኑረን።​—⁠ኢያሱ 23:​14

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢያሱ ከሙሴ ጋር የነበረው ቅርርብ እምነቱን አጠናክሮለታል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ ኃይል ላይ ትምክህት ነበራቸው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢያሱ አመራር ሕዝቡ ይሖዋን የሙጥኝ ብለው እንዲከተሉ አነሳስቷቸዋል